ታምራት ተስፋዬ
አገሮች እዚህ ደረጃ የደረሱት ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸውን ዜጎች በባትሪ ፈልገው በማደንና የመጠቀም ስትራቴጂ ስለተከተሉ እንደሆነ ይታመናል። ኢትዮጵያ በአንጻሩ ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆች ሀብታም ብትሆንም ስጦታዎቿን መጠቀም ሳትችል ዓመታትን አስቆጥራለች። ፀጋ የታደሉ ልጆቿን ስትገድላቸው እንጂ እያደነች በባትሪ ስትፈልግና ስትጠቀምባቸው አልታየችም።
የመንግሥት ትኩረትም አጠቃላይ የትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ እንጂ ተሰጥኦ ያላቸውን ሕፃናት ፈልጎ የማደንና በተፈጥሮ ያገኙትን ፀጋ ለአገር ጥቅም እንዲያውሉ በማድረግ ላይ የተጠመደ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ሀገሪቷ የበርካታ ልጆቿን ፀጋ ወደ ጥቅም መመንዘር ሳትችል በመቅረቷ ስታባክናቸው ቆይታለች።
ይሁንና ከሦስት ዓመት በፊት ድንገት ከእንቅልፍ ነቅታለች። በተፈጥሮ ልዩ ተሰጥኦ የታደሉ ሕፃናት ከልጅነታቸው ጀምሮ ልዩ ክትትል ተደርጎባቸው ወደ ተቋም በመግባት የሚመጥናቸውን ትምህርትና ሥልጠና እንዲያገኙ ወስናለች። ለዚህም ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው በኦሮሚያ ክልል ቡራዩ ከተማ ግዙፍ «የኢትዮጵያ የልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ትምህርት ማዕከል» የሚል ስያሜ የተሰጠውን ማእከል እያስገነባች ትገኛለች።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ ‹‹ተሰጥኦ›› የሚለው ቃል የሰው ልጅ በተፈጥሮ የታደለውን የላቀና ልዩ ችሎታውን የሚገልጽ ነው። ‹‹ተውህቦ›› ማለት ደግሞ በአንድ የትምህርት ዓይነት ወይም ተግባር ለአብነት ያህል በሒሳብ ትምህርት ወይም በሙዚቃ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ፣ ይህንንም የላቀ ችሎታ በትምህርት ማምጣትና ማሳደግ የሚችሉ ግለሰቦችን የሚመለከት ነው።
ባሳለፍነው ዓመት የካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከHP Computing and Printing Middle East የቴክኖሎጂ ተቋም ጋር ትምህርት ቤትን በዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመማር ማስተማር ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።
አምስት ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በተያዘ የመንግሥት በጀት የተጀመረና በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙት ልዩ ተሰጥኦና ተውህቦ ያላቸው ተማሪዎች ገብተው የሚማሩበትና የሚሰለጥኑበት ይህ ማእከል በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እየተገነባ ይገኛል።
ፕሮጀከቱም በተለያዩ ጊዜያት በከፍተኛ አመራሮች ተጎብኝቷል። በነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም በተጎበኘበት ወቅትም፣ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራር ፕሮጀክቱ ባለፉት ዓመታት በነበሩ ሀገራዊ ምክንያቶች መዘግየት አጋጥሞት እንደነበር አስታውሰው፣ ያጋጠሙ መዘግየቶችን በማካካስና በተጠናከረ አመራርና ድጋፍ በ2013 ዓ.ም ሁለተኛ ሩብ ዓመት መጀመሪያ ወራት ሥራ ለማስጀመር እንደሚሰራ ገልፀው ነበር።
ከዚህ በኋላም ፕሮጀክቱ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ተጠናቆ ሥራ እንዲጀምር መሟላት የሚገባቸው ግብዓቶችን ከማቅረብ አንስቶ መጠነ ሰፊ ርብርብ ተደርጓል። በውጤቱም የግንባታ አፈፃፀሙ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል።
ፕሮጀክቱ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ከቀናት በፊት ሲጎበኝም የአገር አቀፍ የልዩ ተሰጥኦ ማስተማሪያና ማበልጸጊያ ፕሮጀክቱ ፊዚካዊ አፈጻጸም ከሦስት ወር በፊት ከነበረበት የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ተችሏል። ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የግንባታ አፈጻጸም ሂደቱም በሩብ ዓመቱ ከነበረበት የ80 በመቶ ወደ 91 በመቶ እድገት አሳይቷል።
ለአፈጻጸሙ ማደግም የፕሮጀክቱ ተቋራጮች ቀንና ሌሊት መስራታቸው በምክንያትነት ተጠቅሷል። ይሁን እንጂ ከሚጠበቀው አኳያ በታቀደለት ጊዜ መጠናቀቅ አልቻለም ተብሏል። ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከሚጠብቀው አኳያ መዘግየት ታይቶበታል።
ለግንባታው መዘግየት የተለያዩ ችግሮች ቀርበዋል። የማጠናቀቂያ ሥራዎችን የሚሰሩ ባለሙያዎች በቅርበት አለመኖርና አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ የወሰን ማስከበር ሥራዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከሁሉ ጎልተው በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። ለፕሮጀክቱ ተቋራጭ የሰው ኃይል ቁጥርን በማብዛት፣ የባለሙያዎችን ምልልስ በመቀነስና ሌትና ቀን 24 ሰዓት በመስራት በሁለት ወራት ውስጥ ማጠናቀቅ እንዲቻል መመሪያ ተሰጥቶበታል።
የመንገድ ግንባታም የአገር አቀፍ የልዩ ተሰጥኦ ማስተማሪያና ማበልጸጊያ ፕሮጀክቱ አካል ነው። ፕሮጀክቱ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚገነባው ይህ የመንገድ ፕሮጀክትም የአንድ ነጥብ አምስት ኪሎሜትር ርዝማኔ አለው።
በአስፓልት ደረጃ የሚገነባው ግንባታም ወደ ማእከሉ ከማድረስ ባሻገር ሌሎች ገፀ በረከቶችንም የሚያቋድስ ነው። ከሁሉም በላይ ለከተማዋ አዲስ ትሩፋትና ለነዋሪዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያው መስተጋብር በተለይ ለኑሮ መሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል።
ማዕከሉ ከከተማዋ ራቅ ብሎ በሚገኝ አካባቢ ላይ በመሆኑ መንገዱ ሲጠናቀቅ ለቡራዩ ከተማ መስፋፋትና ማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነት የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
በጉብኝቱ ወቅትም የቡራዩ ከተማ አስተዳደርና ሕዝብ ከፕሮጀክቱ ጅማሮ እስካሁን ላሳዩት ያልተቋረጠ ድጋፍና ተጠናክሮ ለቀጠለው ትብብር ከሚኒስቴሩ ልዑካን አድናቆትና ምስጋና ተችሯቸዋል። ሕዝቡና አመራሩ እያደረገ ያለውን ድጋፍና ትብብር ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምርም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ ተጥሏል።
የከተማ አስተዳደሩ በመንገድ ግንባታ ሥራው የወሰን ማስከበር ሥራዎችን ከሕዝቡ ጋር በመነጋገር እየፈታ መቀጠሉ የተረጋገጠ ሲሆን አልፎ አልፎ የሚታዩ መጓተቶችን ለመፍታት በትኩረት ሊይዘው እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በመንገድ ግንባታው ከነዋሪው ከሚነሱ የወሰን ማስከበር ጥያቄዎች ባሻገር ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች አፋጣኝ ምላሽ እንደሚፈልጉ ታውቋል። ሚኒስቴሩም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የችግሩን አሳሳቢነትና የፕሮጀክቱን አስቸኳይነት ተመልክቶ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥበት ጥሪ አቅርቧል።
በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካና ዘላቂነት እንዲኖረው የአሰራር መመሪያዎችን፣ የትብብር ማዕቀፎችን፣ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትን፣ የተውህቦና የክህሎት መለያ መስፈርቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮች እየተካሄዱ ነው። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም በመጀመሪያ አንድ ሺ ተማሪዎችን የሚቀበል ይሆናል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2013