ፍሬህይወት አወቀ
ኦሮሚያ ክልል ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰፋፊ መሠረተ ልማቶችም የሚጠይቅ እንደሆነ ይታመናል። ክልሉ በዘንድሮ ዓመት የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን እያስፋፋ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
ካለፈው ጊዜ በተሻለ በዘንድሮው ዓመት የተለያዩ የብልጽግና ዕቅዶችን አቅደው በማከናወን ላይ እንደሚገኙና ውጤታማ እየሆኑ የመጡ መሆናቸውም ጭምር የኦሮሚያ ክልል ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል ከድር አስረድተዋል።
አቶ ጀማል የቤት ልማትን በተመለከተም በክልሉ የተከናወኑትን እና በመከናወን ላይ ያሉትን ተግባራት እንደሚከተለው ገልጸዋል።
የቤት ልማት አቅርቦትና ፍላጎቱ እንደ ሀገር መጣጣም ያልቻለ ችግር ነው። ችግሩ በተለይም በሁሉም የክልል ከተሞች ላይ የሚታይ ከመሆኑም በላይ የችግሩ ስፋትና ጥልቀት እንደየክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ይለያያል።
ይሁንና እንደ ኦሮሚያ ክልል ችግሩ ሰፊ ነው። ይህን ችግር ለመፍታት ባለፉት ሁለት ዓመታት ታቅደው የተሰሩ ሥራዎች ቢኖሩም ቀሪ ሥራዎችም አሉ።
የከተማ ነዋሪም ሆነ የመንግሥት ሠራተኛው በማህበር ተደራጅተው መሬት ወስደው ቤት መገንባት እንዲችሉ የማድረግ ሥራ በዋነኛነት እንደ መፍትሔ ተወስዶ ሲሰራበት ነበር። በዚህም 251 ሺህ 463 አባላት ያሉበት 13 ሺህ 183 ማህበራት ተደራጅተው ነበር። ከእነዚህ አባላት መካከል 151 ሺህ 320 ማለትም 67 በመቶ ያህሉ መሬት ተሰጥቷቸዋል።
መሬት ካገኙት መካከልም 20 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሥራ ገብተው ግንባታ የጀመሩ ናቸው። በተጨማሪም 20 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት አጠናቀው ወደ ቤታቸው ገብተዋል። ጥያቄውና አቅርቦቱ ሲነጻጸር መሬት ያገኙት 67 በመቶ ብቻ ቢሆንም ኅብረተሰቡ ከመሬት አቅርቦት ጋር ሲያነሳ የነበረው ጥያቄ በከፊል የተፈታለት ሆኖ ተገኝቷል።
ይሁን እንጂ በመሬት አቅርቦት ካለው ችግር ባለፈ ወደ ሥራ ለመግባት ኅብረተሰቡ ከፍተኛ የሆነ የአቅም ውስንነት አለበት።
ቀሪዎቹ በማህበራት ተደራጅተው መሬት ያላገኙ አባላት በርካቶች ሲሆኑ ይህን የመሬት ተደራሽነት ተግባራዊ ለማድረግም ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ነገር ግን በክልሉ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፈታት መሬት መስጠት ብቻውን መፍትሔ አይሆንም።
ምክንያቱም ኅብረተሰቡ መሬቱ በተሰጠው መሠረት ቤቱን ገንብቶ ካለበት የመኖሪያ ቤት ችግር ሲላቀቅ አይታይም። ይህም ሰፊ የሆነ የአቅም ውስንነት ለመኖሩ አመላካች ነው።
እንደ አሰራር አንድ ማህበር መሬት የሚያገኘው ከተመዘገበ ከአምስት ዓመት በኋላ ነው። በሕጉ ላይ እንደተቀመጠውም ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ቤት መገንባት የሚያስችለውን ገንዘብ ይቆጥባል።
በመሆኑም ቤት ሊሰራ የሚያስችለውን መነሻ ካፒታል ከቆጠበ በኋላ የመሬት ጥያቄያቸው ይስተናገዳል። ይሁንና አሁን ያለው አሰራር ትክክለኛውን መንገድ የተከተለ አይደለም።
በማህበራቱ ውስጥ ያሉት ግለሰቦች ገንዘብ ኖራቸውም አልኖራቸው የሚታወቅ ነገር የለም። የሚቆጥቡት ገንዘብም ተበድረው ወደ ባንክ የሚያስገቡበት ሁኔታ አለ። ተበድረው የሚያስገቡት ገንዘብ በራሱ ዕዳ ከመሆኑም በላይ በአሁኑ ወቅት የግንባታ ዕቃዎች እጅግ ከመወደዳቸው የተነሳ ገንዘቡ ግንባታውን መገንባት የሚያስችል አለመሆኑ በራሱ ትልቅ ችግር ነው።
መሬት እየቀረበ ያለው በጣም ዝቅተኛ በሆነ በሊዝ መነሻ ዋጋ ነው። በመሆኑም በማህበሩ የተካተተ አንድ ግለሰብ 140 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት ከስድስት እስከ ሰባት ሺህ ብር የሚደርስ ዋጋ ነው የሚከፍለው። ይህም የተለያዩ መሰረተ ልማቶች የሚገነቡበትን በመጨመር ነው ዋጋው እዚህ የደረሰው።
መንግሥት መሬቱን በዝቅተኛ ዋጋ እንዲያቀርብ ያደረገው ግንባታው የሚጠይቀውን ከፍተኛ ወጪ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለመደጎም በማሰብ ነው። ይህም ሆኖ ግን ኅብረተሰቡ ቤት የመገንባት አቅሙ በጣም ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም በቤት ልማቱ ላይ ትልቅ ማነቆ ሆኖ ቀጥሏል።
ይሁንና ችግሩ ሌሎች ችግሮችን እንዳያስከትል ይሰራል ያሉት አቶ ጀማል፤ አንደኛ ግለሰቦቹ መሬቱን በሽያጭም ይሁን በሌላ መንገድ ወደ ሌሎች እንዳያስተላልፉ የሚደረግ ይሆናል። በዚህም ማህበሩ በበጎ ፈቃድ ፋይናንስ የሚያደርጉ ተቋማት ካሉ እነሱን በማፈላለግ ማህበራቱ ከእነሱ ጋር የማስተሳሰርና አብረው የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህም ባሻገር ግንባታቸው 50 በመቶ ከደረሰ ማጠናቀቅ የሚችሉበትን ገንዘብ ከባንክ መበደር እንዲችሉ የተለያዩ ሕጎች እየተዘጋጁ ያሉና የተጀመሩትን ማጠናቀቅ ያስችላሉ ተብለው የተቀመጡ መፍትሔዎች ናቸው።
እንደሚታወቀው ማህበሩ መሬት ካገኘ በኋላ አባላቱ በሙሉ እንደ አቅሙ ይገነባል። ይህም በራሱ በከተሞች የዕድገት ደረጃ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው። አንድ ወጥ የሆነና ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ ይገንባ ማለት እንዳይቻል የሰው ሁሉ አቅም የተለያየ ስለሆነ ይህን ማድረግ አልተቻለም። አንድና ሁለት እንዲሁም ከዚያም በላይ ፎቅ የሚገነቡ አሉ። ሌላው ደግሞ እንደ አቅሙ ቪላ ብቻ መገንባት ይፈልጋል።
ከዛም ባነሰ ደረጃ ሰርቶ ሊኖር የሚገደድም ይኖራል። እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት አንድ ወጥ የሆነና በሕግ የተቀመጠ አስገዳጅ ነገር የለም። ይህ ባለመኖሩም ችግሩን መፍታት አልተቻለም። ነገር ግን አስቀድሞ ሲጀመር እንዲህ ዓይነት አስገዳጅ ሕግ ቢኖር ለከተሞች ዕድገት ጥሩ ይሆን ነበር።
ይሁንና ወደ ተግባር ሲገባ በማህበራት ውስጥ የሚሳተፈው የመንግሥት ሠራተኛውን ጨምሮ ተጨማሪና በቂ ገቢ የሌላቸው አካላት በመሆናቸው በተቻለ አቅም ኅብረተሰቡ ባገኘው መሬት ላይ መኖሪያውን እንዲገነባ እየተደረገ ነው። ይህ ሆኖም በተገኘው መሬት ልክ ቤት እየተገነባ አይደለም።
ከዚህ ውጭ እየታየ ያለው አማራጭ ቤት በራሳቸው ወጪ ገንብተው ለእነዚህ ሰዎች ለማስተላለፍ ፍላጎት ያሳዩ ድርጅቶች አሉ። ድርጅቶቹ በረጅም ጊዜ ክፍያ እና በዝቅተኛ ወለድ ግንባታውን ለማጠናቀቅና ለባለቤቶቹ ለማስተላለፍ ጥያቄ ያቀረቡ ድርጅቶች ናቸው። ነገር ግን መንግሥት እዚህ ውስጥ ጣልቃ መግባት አይፈልግም።
ምክንያቱም መንግሥት በዝቅተኛ ዋጋ መሬት ያቀረበ በመሆኑ ቀሪው ሥራ የግለሰቡ ነው ብሎ ያምናል። በመሆኑም የማህበራቱ አባላት ወጪውን ሸፍኖ ልገንባ ካሚሉ አካላት ጋር በራሳቸው ስምምነት የሚያደርጉት አሠራር ይኖራል። መንግሥት በመካከላቸው ዘልቆ እንዲገባ አልተፈለገም እንጂ ሀሳቡ እንደ አማራጭ የቀረበበት ሁኔታ አለ።
ምንም እንኳን ይህ እስካሁን መሬት በዝቅተኛ ዋጋ እየተሰጠ የቀጠለበት አሠራር ቢሆንም ብዙም ውጤታማ አልሆነም። የአብዛኛው ሰው ፍላጎትም በመሬት ዙሪያ መሆኑን እና ይህ ደግሞ ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊሰጥ እንዳልቻለ አቶ ጀማል ያነሳሉ።
ስለዚህ መንግሥት በክልል ከተሞች የቁጠባ ቤቶች እንዲገነቡና አቅመ ደካማ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጎማ በማድረግ የመኖሪያ ቤቶችን ተደራሽ ማድረግ እንዲቻል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራበት ነው።
ከተሞች በጀት መድበው የቁጠባ ቤቶችን እየገነቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ማከራየት እንዲችሉና አብዛኛውን ማህበረሰብ ተደራሽ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። ይህም እንደ ክልሉ ስፋት በክልሉ ያለውን ሰፊ የመኖሪያ ቤት ችግር መቅረፍ ያስችላል። ተግባራዊነቱን በተመለከተም በአሁኑ ወቅት የተወሰኑ ከተሞች የጀመሩ ቢሆንም ገና ወደ ሥራው ያልገቡ ከተሞችም አሉ።
ፕሮግራሙ ከተሞችን መልሶ ከማልማት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ አዋጭነቱ የጎላ ነው። በከተሞች መካከል እጅግ የተጎሳቆሉና የደቀቁ መልማት የሚገባቸው በርካታ የቀበሌ ቤቶች ይገኛሉ። ይሁንና በውስጡ የሚኖሩት ሰዎች አቅም የሌላቸው በመሆናቸው ጉስቁልናውን መለወጥ አይችሉም።
ስለዚህ የቁጠባ ቤቶቹን በሚፈለገው መጠን መገንባት ከተቻለ ቤቶቹን ለእነዚህ ሰዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማስተላለፍ ይቻላል። በዚህም እጅግ የተጎሳቆሉና የከተሞችን ገጽታ የሚያበላሹ ቤቶች ይለማሉ። ፕሮግራሙም አንደኛ በዝቅተኛ ዋጋ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው የከተሞችን ገጽታ ለመጠበቅ ታሳቢ አድርጎ የተጀመረ ነው።
ሌላው በኦሮሚያ ክልል ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ ካለው ሥራ መካከል በተለያዩ ከተሞቹ ተጀምረው በበጀት እጥረት ሳይጠናቀቁ የቀሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ማጠናቀቅ አንዱ ነው።
ይህንንም በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለማስጨረስ እየሰራ ነው። በመሆኑም በቅርቡ ተጀምረው የቀሩ 835 የጋራ መኖሪያ ሕንፃዎች በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለኅብረተሰቡ እንዲተላለፉ ውሳኔ ተላልፏል።
እነዚህ ሕንፃዎችም በአሰላ፣ በወሊሶ፣ በሆለታና በነቀምት ከተሞች የሚገኙ ሲሆን ቤቶቹ የተለያየ ደረጃ ያላቸውና ለመኖሪያና ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው።
ይሁንና አሁንም በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸውን ያነሱት አቶ ጀማል፤ በቀጣይ ቤቶቹ ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ መንግሥት በጀት አፈላልጎ ግንባታውን ማጠናቀቅ እንዳለበት በማመን እየተሰራ ይገኛል። ከዚህ ውጪም ሌሎች አማራጮችን በማፈላለግ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ጥረት ይደረጋል።
አንደኛው አማራጭ ባለሀብቱን እና መንግሥትን አንድ ላይ በማጣመር የሚሰራ ሲሆን መንግሥት መሬት በማዘጋጀት ባለሀብቱ ደግሞ ገንዘብ ወጪ በማድረግ የሚገነባበትን ሁኔታ ምቹ ማድረግ እንዲቻል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን አንስተዋል።
ይህ ረቂቅ አዋጅም በዚህ ዓመት ፀድቆ ወደ ሥራ ይገባል ያሉ ሲሆን ፕሮግራሙም ወደ ሥራ ሲገባ በከተሞች የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ችግር የሚያቃልል እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም አርሶ አደሩ ወደ ቤት ልማቱ መግባት እንዲችል ይደረጋል የሚሉት አቶ ጀማል፤ አርሶ አደሩ በአብዛኛው መሬት የሚነጠቅ መሆኑን አንስተው፤ በቀጣይ ግን ይህን አሰራር ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ስለዚህ አርሶ አደሩ ሰፊ መሬት ካለው በቤቶች ልማት ውስጥ ታቅፎ ሌሎች ብድሮች ተመቻችተውለት እራሱ ቤት መገንባት የሚችልበትን የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት እየተሰራ ነው።
ክልሉ ለመምህራን ሰፊ መሬት በማዘጋጀት በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል። የማህበራት አደረጃጀት ሲጀመርም ለመምህራን የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት ታስቦ የተጀመረ በመሆኑ አብዛኛው መምህር ተጠቃሚ ሆኗል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት የመሬት አዋጅ ይህን አያስተናግድም መሬት የሚተላለፈው በኪራይና በሊዝ ነው ይላል።
ነገር ግን መንግሥት ያለውን ችግር በመረዳት የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖረው በማድረግ በዋነኛነት መምህራን ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል። በዚህ በተፈጠረ ዕድልም ሌሎች የክልሉ ነዋሪዎችም ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
በአሁኑ ወቅት ማህበራት ተደራጅተው መሬት የሚያገኙበት አሰራር የተቋረጠ መሆኑን የገለጹት አቶ ጀማል፤ ነገር ግን በቀጣይ ተደራጅተው መሬት ያላገኙ ማህበራትን ለማስተናገድ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል። በዚህ መሰረትም ሰበታ ከተማ ለ3900 አባላት መሬት ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ ነው። ሌሎች ከተሞችም እንዲሁ ተደራጅተው መሬት ላላገኙ ማህበራት መሬት አዘጋጅተው ለመስጠት እየሰሩ ይገኛሉ።
ይህን አጠናቅቀው ከጨረሱ በኋላ በቀጣይ ማህበራትን ከማደራጀት አስቀድሞ የመሬት ዝግጅት ማድረግ ተገቢ መሆኑን በማመን መሬት ዝግጅት ላይ እየሰሩ ይገኛሉ።
ይሁንና አጠቃላይ የቤት ፍላጎቱን ለማሟላት መሬት በመስጠት ላይ ብቻ መሰረት መደረግ የሌለበትና ሌሎች አማራጮችንም ጎን ለጎን በማስኬድ የከተሞችን ገጽታ ግንባታ ላይ የሚሰራ መሆኑንም አቶ ጀማል አንስተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2013