በአዝማቹ ክፍሌ
የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢህአዴግ አገሪቱን እንደተቆጣጠረ በተለያዩ አካባቢዎች አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ግድያና ማፈናቀል ተከስቶ ነበር። በወቅቱ የሽግግር መንግሥት ምስረታ ላይ ባለመስማማት ጥሎ የወጣው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (በኦነግ) ድርጊቱ ተፈፅሟል ተብሎ ተደመደመ።
በጉራፈርዳና በሌሎች አካባቢዎች ይፋዊ ተጠያቂ ሳይኖር የንፁሃን ደም ፈሶ በከንቱ ቀረ። የኢህአዴግ አስተዳደር በለውጥ ፈላጊ ኃይል 2010 ዓ.ም ላይ ሲተካ የማፈናቀልና አንድ ብሔር መርጦ የማጥቃት ዘመቻው ተጧጡፎ እስካሁን እንደቀጠለ ይገኛል።
ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን በአገሪቱ ከምዕራብ ወለጋ እስከ ጉጂ፣ ከምሥራቅ ሐረርጌ እስከ ምዕራብ ሐረርጌና ምሥራቅ አርሲ፣ ከአፋር እስከ ሶማሌ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከማሽና መተከል ዞኖች እስከ ደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ድረስ የንፁሃን ዜጎች ሕይወት ሲቀጠፍ መስማት የተለመደ ክስተት ሆኗል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሳምንታት ልዩነት በተፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ቁጥራቸው በግልጽ የማይታወቁ ዜጎች ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ ከእነዚህ ጥቃቶች ብዛት ያላቸው ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል። በእነዚህ ጥቃቶች ሳቢያ ሲፈስ የቆየው እንባ ሳይታበስ፣ በመተከል ዞን በድጋሚ የንፁሃን ዜጎች ሕይወት እየጠፋ ይገኛል።
አገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘው መንግሥት አንዴ ህወሓት አንዴ ደግሞ ኦነግ ሽኔ እያለ መግለጫና የኀዘን እንጉርጉሮ ከማሰማት በዘለለ ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታ አልቻለም። የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመተከል ዞን በመገኘት ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት አድርገው በተመለሱ በማግስቱ ጥቃቶች ተፈፅመዋል። ይህ የሚያሳየው ለመንግሥት የሚገዛ አስተዳደር እንደሌለና በተጠናና በተደራጀ መልኩ ጥቃቶች እየተፈፀሙ መሆኑን ነው።
ኦነግ ሸኔ ላለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል የሰላም መደፍረስ ተጠያቂ ሲደረግ የክልሉ መንግሥት ቡድኑን ለሕግ ለማቅረብና ለመደምሰስ ምን ሰራ ሲባል መልሱ ምንም ይሆናል። ምክንያቱም የክልሉ መንግሥት የሚያሰለጥናቸውን ልዩ ኃይል አባላት አሰማርቶ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር ይልቅ ዝምታን መምረጡን ስለተመለከትን ነው።
በቅርቡም የህወሓት አጥፊ ቡድን ለማስወገድ ከተደረገው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጎን ለጎን የኦነግ ሸኔን ቡድን ለመደምሰስ ሙከራዎች ተደርገዋል። ይህ ማለት ግን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ገና ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ ሳይረሳ ነው።
ከዚሁ ከኦሮሚያ ክልል ሳንወጣ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎችና ማፈናቀሎች በተከሰቱበት ወቅት የኦነግ ሰራዊት ከነመሣሪያው ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የተለያዩ አካላት በጭብጨባና በእጀባ መቀበላቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል። መንግሥት በሚመራው ክልል ውስጥ መሣሪያ የታጠቀ ኃይል የራሱን አስተዳደር መስርቶ ያሻውን ሲያደርግ መመልከት የተለመደ ተግባር ሆኗል። ቡድኑም አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ግድያ ሲፈፅም የቆየ ሲሆን አሁንም በተግባሩ ቀጥሎበታል።
እዚህ ጋር ማስተዋል የሚያስፈልገው የኦነግ ታጣቂ ኃይል መሣሪያውን ሳያስረክብ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በትግራይ ክልል ሲሆን የህወሓት አጥፊ ቡድን ደማቅ አቀባበል አድርጎ ተቀብሏቸዋል። ታዲያ የኦነግ ታጣቂ ቡድን ከአጥፊው ህወሓት ጋር ምን ተመካክሮ ወደ ኦሮሚያ እንደገባ መገመት መቼም ጠንቋይ መሆን አይጠይቅም። ይህንንም ሁኔታ ለማስረዳት በቡራዩ ከተማ የተከናወነውን ዘረፋና ግድያ እንዲሁም ማፈናቀል ማስታወስ በቂ ነው።
በምዕራብ ሐረርጌና በሻሸመኔ የነበሩትን ጥቃቶች እንዲሁም በምዕራብ ወለጋ የነበረውን አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ስናስታውስ የህወሓት አጥፊ ቡድን ከኦነግ ሸኔ ጋር የሸረበው ሴራ ፍንትው ብሎ ይገለጣል።
ይህን ሁኔታ ይዘን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንመለስ። ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ብዛት ያላቸው የሌሎች ክልል ተወላጆች ይገኛሉ። በተለይ የአገው አማራ ነዋሪዎች በመተከል ዞን ውስጥ ኑሯቸውን መስርተው ሀብት አፍርተው ይገኛሉ። እነዚህን ነዋሪዎች መጤ በማለት የተደራጀ ቡድን ጥቃት እያደረሰባቸው እስከዛሬ ዘልቋል።
ክልሉን የሚያስተዳድረው መንግሥት በምናገባኝ መንፈስና ለጥቃቱ ዳር ተመልካች በመሆን ግድያውና ማፈናቀሉ ቀጥሏል። በቅርቡም ጥቃቱን በማቀነባበር በሚል የተወሰኑ አመራሮች መታሰራቸው ይታወሳል። የዚህ ጥቃት መሪና አቀናባሪ የህወሓት አጥፊ ቡድን ነው ይባል እንጂ ከጀርባው የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እጅ እንዳለበት በተደጋጋሚ የጥቃቱ ሰለባዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል።
በመተከልም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ለምን አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የበዛው ብለን መለስ ብለን ብናስብ ላለፉት 30 ዓመታት አንድ ብሔር ጨቋኝና ገዢ ተደርጎ የተሰራጨው ትምህርትና ትርክት መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። ይህ ትርክት አሁንም በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሲደጋገምም ይደመጣል።
የህወሓት ኢህአዴግ መንግሥት አገሪቱን ለብቻው ለመግዛት ሲያልም በዋነኝነት ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ መርዞንችን በካሬኩለም ደረጃ ቀርፆ በማሰራጨቱ አሁን የምናየው ክስተት እንዲፈጠር አድርጎታል። ይህ የግጭት መርዝ በአሁኑ ወቅት ክልሎችን በሚመሩ ባለሥልጣናት አዕምሮ ውስጥ የሰረፀ በመሆኑ መገደልና መፈናቀል እንዳይቆም አድርጎታል።
አንድ ብሔር ላይ ያተኮረ ጭፍጨፋ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብቻ ሳይሆን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም በትግራይ ክልልም የታየ ጉዳይ ነው። በቅርቡ በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በማይካድራ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ሁኔታ እንዲሁም በጉራ ፈርዳ የነበረውን ግድያ ማንሳት በቂ ነው። ይህ ሁሉ ሰቆቃ እየደረሰበት የሚገኘው ሕዝብ እዚያው ተወልዶ ያደገና ከአካባቢው ውጪ ምንም ቦታ የማያውቅ መሆኑ ነው።
ለእነዚህ ሁሉ መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ቢሆንም አሁን አገሪቱ ባለችበት የእኔ ልግዛ ትንቅንቅ መገደልና መፈናቀል በጊዜ መፍትሄ የሚያገኝ አይመስልም። ሁሉም የፖለቲካ መሪዎች የእኔ ሀሳብ ካልተደመጠ አገሪቱ ወደ እልቂት ታመራለች የሚሉ ማስፈራሪያዎች በግልፅ እያስደመጡ ይገኛሉ።
የሆኖ ሆኖ አሁን ከገባንበት አጣብቂኝ ለመውጣትና ተስፋ ያላትን ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማውረስ እያመሰን የሚገኘው ዘረኝነት ማስወገድ ይገባል። ህወሓት ኢህአዴግ አገሪቱን ባስተዳደረበት ዘመን የዘራቸው መጥፎ አስተሳሰቦች ሊወገዱ የሚገባው በትምህርት ካሬኩለም ውስጥ የተቀመጡት የተሳሳቱ ትምህርቶች ተነቅሰው መውጣት ሲችሉ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሶ መስራት እንደሚችል በይፋ ሲነገርና ሲከበር ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2013