አዲስ አበባ፡- መንግሥት በአገሪቱ የሚታዩትን የሰላምና የፀጥታ ችግሮች ለመፍታት እየወሰደ ያለው እርምጃ በቂ አለመሆኑን ምሁራን ተናገሩ፡፡ የክልሎች ስልጣን ከፌደራል እየበለጠ መምጣት ሰላምና መረጋጋቱ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ኑሩ መሀመድ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ብዙ ጊዜ መንግሥት ብጥብጦች ጉዳት ካደረሱ በኋላ ነው እርምጃ የሚወሰደው፡፡ ይህ ደግሞ በኅብረተሰቡ ላይ የሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራን ያስከትላል፡፡ ለዚህም በኦሮሚያ ክልል የነበረውን ሁኔታ ማየት ይቻላል፡፡ በአካባቢው በነበረው ግጭት አገሪቱ ብዙ ዋጋ እንድትከፍል አድርጓታል፡፡
እንደአቶ ኑሩ ገለፃ በኦሮሚያ ክልል ሰላም ለማምጣት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ወደ ተግባር መግባቱ አስፈላጊ ቢሆንም የዘገየ እርምጃ በመሆኑ ቀላል የማይባል ኪሳራን አስከትሏል፡፡ ከዚያም አልፎ በዘገየው እርምጃም የተፈለገውን መረጋጋት በሚጠበቀው ልክ ማምጣት አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ወደፊት እርምጃ ሲወሰድ ነገሮች መቀጨት ባለባቸው ወቅት እንዲቀጩ ካልተደረገ የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት መውደም ያስከትላሉ፡፡
በየክልሉ ያሉ አመራሮችን በመሰብሰብ ችግሩ ሲፈጠር እርምጃ ለመውሰድ ከአመራሮቹ ጋር መግባባት ላይ መደረስ አለበት የሚሉት አቶ ኑሩ በክልሎች መካከል ያለው መግባባትና መተማመን ካላደገ ችግሮች ሲፈጠሩ ብቻ እየሄዱ ለማረጋጋት መሞከሩ ጥቅም የለውም ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ኑሩ ገለፃ፤ የፌዴራል መንግሥት ከተወሰኑ ክልሎች ውጭ እንደፈለገው እርምጃ መውሰድ የሚችልበት ሁኔታ አይታይም፡፡ ትክክለኛ እርምጃ መወሰድ አለበት ከተባለ የፌዴራል መንግሥት የመስራት አቅሙ ማደግ አለበት፡፡ የክልል መንግሥታት የፌዴራል ትዕዛዝ መቀበል አለባቸው፡፡ አንዱ ክልል ከሌላው ክልል ጋር ተስማምቶ የመስራት አቅሙም ሊዳብር ይገባል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት የበላይ የሆኑበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በዚህ የተነሳ በአሁን ወቅት የፌዴራል መንግሥት ሙሉውን አገሪቱን እያስተዳደረ ነው ለማለት በማያስደፍር ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ህገ መንግሥቱ የፌዴራል መንግሥት የበላይነትን አስከብሮ ክልሎችም በህገ መንግሥቱ የሚተዳደሩበትን መመሪያ ማውጣት ከእርምጃዎች ሁሉ ቀዳሚ መሆን አለበት፡፡
አሁን በአገሪቱ ያለው ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ በማነትና ወሰን ኮሚሽን አካባቢ ያለው ቅራኔ ይሰፋል የሚሉት አቶ ነሩ፤ ክልሎች የነዋሪዎቻቸው ማንነት ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው ከሌላው ተገንጥሎ እንዲኖር የሚያደርጉት ግፊት ከበዛ አገራዊ አንድነት እንደሚጠፋ አመልክተዋል፡፡ አሁን ከሚቋቋሙ ፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኛው የማንነት አቀንቃኝ እንጂ አገራዊ አንድነት ላይ የሚሰራ ተቋም እየጠፋ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ህዝቡ ቅርቡ ያለውን መሪ የሚከተል በመሆኑ በአገራዊ አንድነት ላይ ከፍተኛ ስጋት ስለሚፈጥር ወደ ርስበርስ ግጭት የማምራት አዝማሚያዎች እንደሚታዩም አመልክተዋል፡፡
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ሻሎም አሊ በበኩላቸው በአገሪቱ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስታርቁት አካላት ችግሩን ከምንጩ አድርቀዋል የሚለው መታየት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሽማግሌዎች ተሰሚነት አላቸው ሌላ ቦታ ደግሞ ግጭቱን የሚፈቱት ሰዎች እንደ ፖለቲከኛ የሚቆጠሩበትና ሽማግሌዎች ተዓማኒነት የሌላቸውና እንደ ፖለቲከኛ የሚቆጠሩበት ሁኔታ መብዛቱን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአስተዳደር ችግሮችና ድንበር ጥያቄዎች ላይ የተጣላው ከማስታረቅ በዘለለ ዘላቂ የሆነ መሬት ላይ የወረደ ነገር እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ ሻሎም አሁን ያለው የሆነ ቦታ ግጭት ሲነሳ ያንን ሄዶ ማረጋጋት እና ተመልሶ መውጣት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የግጭቶቹን ምንጭ መለየትና ከስሩ ለመፍታት የሚያስችል ተቋማዊ አሰራር እንደሚያስፈልግ ተናረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 27/2011
በመርድ ክፍሉ