ፍሬህወት አወቀ
መንገድ ለአንድ ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከት ከሚችሉ መሰረተ ልማቶች መካከል አንዱ ነው። መንገድ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ለሚገኙ የፌዴራል፣ የክልልና የገጠር መንገዶች ጥገና ብቻ በየዓመቱ ከሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል። ይህን ወጪ ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን እና በሀገሪቱ ለሚገኙ አስሩም ክልሎች የገጠር መንገድ ኤጀንሲዎች መንገድ ፈንድ ጽ/ቤት ገቢ በማሰባሰብ ተደራሽ ያደርጋል።
መንገድ ፈንድ ጽ/ቤት ታህሳስ 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ከፌዴራልና ከክልል መንገድ ኤጀንሲዎች ጋር ባደረገው የምክክር መድረክ የበጀት እጥረት ስለመኖሩ ከክልሎች ተነስቷል። እኛም የጽ/ቤቱ የፋይናንስ ምንጭ ምን ያህል እንደሆነና በቀጣይስ ክልሎች እያነሱት ያለውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ ምን ታስቧል ስንል ላነሳነው ጥያቄ የመንገድ ፈንድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ረሺድ መሀመድ ምላሽ ሰጥተዋል።
በሀገሪቷ ውስጥ የሚገኙትን የፌዴራል፣ የክልልና የገጠር መንገዶችን የጥገና ወጪና የመንገድ ደህንነት ወጪን ለመሸፈን የመንገድ ፈንድ በአዋጅ ቁጥር 66/89 ተቋቁሞ ከ20 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ዋና የገቢ ምንጩም በነዳጅ ላይ የተጣለ ታሪፍ ሲሆን ይህም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ታሪፉ አልተሻሻለም።
ይሁንና አጠቃላይ በሀገሪቱ ያለው የመንገድ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ በገቢ መጠን ሲታይ ጽ/ቤቱ የዛሬ 20 ዓመት ሥራ ሲጀምር በዓመት ሶስት መቶ ሚሊዮን ብር ገቢ ይሰበስብ የነበረ ሲሆን በአሁን ወቅት ግን ሶስት ቢሊዮን ብር ገቢ እየሰበሰበ ይገኛል።
ጽ/ቤቱ ሲቋቋም 26 ሺ ኪሎ ሜትር መንገድ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ 128 ሺ ኪሎሜትር መንገዶች በሀገሪቷ ይገኛሉ። ይህን መንገድ ለመጠገንም በዓመት ቢያንስ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጽ/ቤቱ ባስጠናው ጥናት ማረጋገጥ ችሏል። የህም አሁን ካለው በጀት ከሃምሳ እስከ ስልሳ በመቶ ክፍተት መኖሩን ያሰያል።
ክፍተቱን ለመሙላትም በዋነኝነት የገቢ ምንጮችን ለማስፋት የተለያዩ ጥናቶች ተከናውነው ለመንግሥተ ቀርበዋል። በመሆኑም በቀጣይ የፋይናንስ ምንጩን በማስፋት ከነዳጅ ውጭ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ገቢን ማሰባሰብ የሚያስችሉ ጥናቶች እየተጠኑ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ከነዳጅ የሚመደበውን ገንዘብ በአግባቡ የመጠቀም ችግር መኖሩን ያነሱት አቶ ረሺድ፤ እንዲህ አይነት ችግሮችንም ለመቅረፍ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የመንገድ ኤጀንሲዎችን አሰራር አደረጃጀትና የሰው ሃይል ማጠናከር ያስፈልጋል።
ለዚህም ጽ/ቤቱ ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር በመመደብ የተለያዩ ማሽነሪዎችን ገዝቶ እንዲሁም ስልጠናዎችንም በማዘገጀት ችግሩን ለመፍታት እየሰራን ነው። ይህም የመንገድ ጥገናውን አቅም በከፍተኛ ደረጃ መለወጥ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የክልሎችን አቅም የሚጨምር ይሆናል።
የተመደበው ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር በየዓመቱ ከሚሰበሰቡ በጀቶች ላይ ሙሉ ለሙሉ ስራ ላይ ሳይውል የቀረና ተራፊ የሆነ በጀት ነው። ይህ ተራፊ በጀትም ለአቅም ግንባታ ቢውል የተሻለ ነው ከሚል ሀሳብ የመንገድ ፈንድ ቦርድ በወሰነው ውሳኔ መሰረት ተፈጻሚ መሆን ችሏል።
ከ90 በመቶ በላይ የሆነው ገቢ በነዳጅ ላይ ከተጣለ ታሪፍ የሚገኝ ሲሆን፤ የገቢ አሰባሰብ ሂደቱም የኢትዮጵያ ፔትሮሊየም የተባለ የነዳጅ ድርጅት ለካምፓኒዎች ነዳጅ በሚሸጥበት ጊዜ ለመንገድ ፈንድ መግባት የሚገባውን እየቀነሰ በቀጥታ በአካውንት ያስገባል። ከዚህ በተጨማሪም ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ የሚሰበሰብ ገቢን የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በመላው ሀገሪቱ ከሚገኙ ቅርንጫፎቹ እየሰበሰበ በመንገድ ፈንድ አካውንት ውስጥ ያስገባል።
መንገድ ፈንድ በዚህ መንገድ ያገኘውን ወይም የሰበሰበውን ገቢ ለክልሎች ተደራሽ የሚያደርግበት የስርጭት ሂደቱ ምን ይመስላል ከክልል ክልል ያለው ልዩነትስ እንዴት ነው ብለን ላነሳነው ጥያቄ አቶ ረሺድ ሲመልሱ፤ መንገድ ፈንድ በጀት በሚመድብበት ጊዜ መንገዶቹ የተሰሩበትን ዓላማና የሚያስተናግዱት የትራፊክ መጠን ከግንዘቤ የሚገባ ይሆናል።
አጠቃላይ ጽ/ቤቱ ከሚሰበስበው ገቢ 65 በመቶ ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፤ 25 በመቶ ለአስሩም ክልሎች የገጠር መንገድ ኤጀንሲዎች ይከፋፈላል። ቀሪው አስር በመቶ ደግሞ የፈንዱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለተመረጡ ከተሞች ይከፋፈላል።
ይሁንና ለክልሎች የሚከፋፈለው 25 በመቶ ከክልሎቹ ባላቸው የመንገድ ርዝመት፣ በሚያስተናግዱት የትራፊክ መጠን እንዲሁም ከክልሎቹ ስፋት አንጻር ይለያል። ለአብነትም ኦሮሚያ ክልልን ብንመለከት ሰፊና ትልቅ እንደመሆኑ በዚህ ዓመት 245 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል።
በንጽጽር ሐረሪ ክልልን ስንመለከት ደግሞ 15 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት ማግኘት ችሏል። ከቆዳ ስፋትና ከመንገዶቻቸው ርዝመት በተጨማሪ ክልሎች የነበራቸው አፈፃፀምም በበጀት መጠን ላይ ታሳቢ ይደረጋል።
አጠቃላይ የክልሎች የስድስ ወር አፈፃፀም እንዴት ተገመገመ ለሚለው ጥያቄም አቶ ረሺድ ሲመልሱ፤ የመንገድ ኤጀንሲዎች ከ80 በመቶ በላይ ያቀዱትን የጥገና ፕሮግራሞች ማጠናቀቅ ችለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቭርሲቲ አጠቃላይ የኢትዮጵን የመንገዶች ግንኘኙነት ዘዴ ተብሎ የተጠና ጥናትም ተጠናቅቋል። ጥናቱ አጠቃላይ በሀገሪቷ ውስጥ ያሉትን መንገዶች በአንድ ቋት ውስጥ በማካተት አጠቃላይ መረጃ ማግኘት የሚያስችል ነው።
ይህ በቀጣይ በጀትን በትክክለኛና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ለመመደብ ያመቻል። ምክንያቱም በተጨባጭ ያለውን መረጃ ማሳየት ይችላል። አዳዲስ መንገዶች ሲገነቡም ወደ ቋቱ በማስገባት በኢንተርኔት መረብ ላይ ማንም ሰው በቀላሉ ማግኘት እንዲችል ይደረጋል። ሌላው አጠቃላ የመንገድ ቆጠራ ተካሂዶ ለበጀት ምደባ ውሏል። በመሆኑም ባለፉት ስድት ወራት መንገድ ፈንድ በዋናነት መስራት የሚገባውን ሥራ ሰርቷል ማለት ይቻላል።
ክልሎች በጀታቸውን በአግበቡ መጠቀም እንዲችሉም መንገድ ፈንድ የሚያደርገው ድጋፍ በተመለከተ ክልሎች የተመደበላቸውን በጀት የፊዚካልና የፋይናንስ አፈጻጸም በሪፖርት ያቀርባሉ። ሁለተኛ በሂሳብ ምርመራ ኮፕሬሽን በየዓመቱ ሁሉም የክልል መንገዶች ኦዲት ይደረግባቸዋል።
ይህን ተከትሎም ድክመት ያለባቸው ኤጀንሲዎች ካሉ የሚታወቅበትና ለእነሱም ድጋፍ የሚሰጥበት ሁኔታ አለ። እንዲህ ባለ የምክክር መድረክም የሚያነሱትን ችግሮች መነሻ በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል። ከዚህ ባለፈም አንዱ ከሌላው የሚማርበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል።
መንገድ ኢኮኖሚያው አቅምን መገንባት የሚችልና ለአንድ ሀገር ውድ ከሚባሉትና ከፍተኛ ወጪን ከሚጠይቁ መሰረተ ልማቶች መካከል አንዱ ነው። ለአብነትም በቀላሉ ኢትዮጵያን ብንወስድ በስድስት ወራት ውስጥ ከሶስት መቶ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ መንገዶች ተገንብተዋል። ነገር ግን ማህበረሰቡ ለመንገደ ሀብት ልምት ካለው የተዛባ አመለካከት የተነሳ ለመንገዶች ጥንቃቄ ሲያደርግ አይታይም። ሶስት መቶ ሚሊዮን ብር ማለት በትንሹ ሶስት የህዳሴ ግድብ አይነት ግድቦችን ሊያሰራ የሚችል መዋዕለ ነዋይ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ህብረተሰብ መንገድን የመንከባከብ ሃላፊነት ሊኖረው ይገባል።
መንግድ ከፍተኛ የሀገር ሀብት የሚወጣበት መሰረተ ልማት እንደመሆኑ የሁሉንም የህብረሰተሰብ ክፍል ተሳትፎ ይጠይቃል። በተለይም ሚዲያው በማስተዋወቅ በኩል ከፍተኛ ድረሻ ይኖረዋል። መንግሥትም መንገድ ፈንድ ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2013