ውቤ ከልደታ
በአንድ ወቅት አንድ ሀብታም ገበሬ ቤት የሚኖሩ እንስሳት ነበሩ። ከነዚህም መካከል አህያና ውሻ ይገኙበታል። እነዚህ እንስሳት ታዲያ በሚሠሩት ሥራ ደስተኛ አልነበሩም። አህያው ቀኑን ሙሉ እህል ሲሸከም፤ ውሃ ሲቀዳ እና ሌሎች ሥራዎችን ሲሰራ ይውላል። ከዚህም ይባስ ብሎ በዱላ ይደበደባል። በዚህም ብስጭት ነበረበት።
በተመሳሳይ ውሻም ሌሊቱን ሙሉ የጌታውን ግቢ ብርድ ላይ ሆኖ ሲጠብቅ ያድራል። ከባለቤቱ ግን ተገቢው ክብር አይሰጠውም። ከዚያ ይልቅ ማታ ቁራሽ እየተወረወረልኝ አንተውሻ ውጣ ከዚህ እየተባልኩ መኖር ሰልችቶኛል። ድመት ግን ምንም ሳትሰራ ከባለቤቶቹ ጋር ተንደላቃ ትቀመጣለች። እኔ ምን አጥፍቼ ነው እያለ ይማረራል። በዚህም አህያና ውሻ በባለቤታቸው ላይ አምፀው ለምን አንጠፋም ተባባሉ። እና አንድ ምሽት ተያይዘው ጠፉ።
ከዚያ ሲሄዱ አንድ ጫካ አገኙ። እዚያም ለምለም ሣርና ውሃ አለ። እና እዚህ ለምን አናርፍም ሲሉ ተነጋገሩ። በዚህ ተስማምተውም ቁጭ እንዳሉ አህያው ከእርጥቡ ሣር ነጨት ነጨት ማድረግ ቀጠለ። ከዚያ ሣሩን ከጋጠ በኋላ ውሃውን ሲጠጣ ሆዱ ሞላ። በዚህ ጊዜ ከዚህ ቀደም በአሳዳሪው ሲወረወርለት የነበረውን ጥቂት ሣር አስታውሶ እንዴት ተጎድቼ ኖሬያለሁ ብሎ አሰበ። በዚህም አላበቃም ባለፈው ህይወቱ ተቆጨ።
አሁን ጥጋብ ጥጋብ ስላለው ተመልሶ ሲመጣ ውሻው ምንም ስላልበላ ደክሞት እና ርቦት እጥፍጥፍ ብሎ ተኝቶ አገኘው። የጠገበ የረሃብን ስቃይ አይገነዘብምና ውሻው እንደዚያ ሆኖ ሲመለከተው ምን ሆነህ ነው የተኛኸው ብሎ ጠየቀው። ውሻውም ደከመኝ፣ በዚያ ላይ ርቦኛል፣ ስለዚህ ትንሽ ልተኛ፤ አንተም አረፍ በል አለው። ከዚያ አህያው እኔ ለምን እተኛለሁ፤ በሽተኛ አይደለሁም፤ ይልቁንም ሆዴ ስለተነፋ ትንሽ ባናፋ ይለቀኛል ሲል ለውሻው ነገረው። ውሻው ግን ተው አይሆንም፤ ድምጽህ ከተሰማ አውሬ ይመጣብናል አለው።
ጥጋብ ማገናዘብን ያጠፋልና አህያው ግን የውሻውን ምክር አልሰማም። እና አንድ ጊዜ ጩኸቱን ለቀቀው። በዚህ ጊዜ ከሩቅ የነበሩ ጅቦች በዚህ ሰዓት የአህያ ድምጽ በመስማታቸው ከየት እንደሆነ ለማጣራት ጆሮአቸውን ቀና አድርገው ማዳመጥ ጀመሩ። ነገር ግን ጩኸቱ ከየት እንደሆነ ለማወቅ አልቻሉም። እናም ተመልሰው የሚበሉትን ለማግኘት መዟዟር ቀጠሉ።
ከዚያ አህያው ዳግመኛ ሣሩን ከበላና ውሃውን ከተጎነጨ በኋላ ወደውሻው መጥቶ አንተ ውሻ አሁንም ተኝተሃል። እኔስ ይህ ሣር ሆዴን ስለነፋኝ ካላናፋሁ አይሻለኝም፤ እና አሁንም ላናፋ ነው አለው። ውሻው ግን አሁንም ማስጠንቀቂያውን ደገመለት። አህያው ግን አሁንም ሊሰማ አልቻለም። እና ለሁለተኛ ጊዜ ድምፁን ከፍ አድርጎ አናፋ። በዚህ ጊዜ ጅቦቹ አሁን የአህያው ድምጽ ከየት አካባቢ እንደሚጮህ አወቁ። እናም ፍለጋ ጀመሩ። ከሁሉም አቅጣጫ ጅቦቹ የአህያውን ድምጽ ወደሰሙበት መትመም ጀመሩ።
በዚህ ጊዜ አሁን አህያው ዳግመኛ ሣሩን ከነጨና ውሃውን ከተጎነጨ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ውሻው ሄደ። በዚህ ጊዜ ውሻ ተኝቶ ስለነበር ቀስቅሶት አንተ ውሻ ትተኛለህ እንዴ፣ እኔ ሆዴ ተነፍቷል፤ ላናፋ ነው አለው። በዚህ ጊዜ ውሻው አንድ ምክር ለአህያው ለገሰው። የመጀመርያው ጩኸት የጥሪ ደወል ነው፤ ሁለተኛው አቅጣጫ መጠቆሚያ ነው። ሦስተኛው ግን መበያህ ነው፤ እና እባክህ አርፈህ ተኛ አለው። አይ አንተ የጥጋብን ነገር አታውቀውም ማለት ነው። እኔ ግን እንዲህ ሆዴ ተቀብትቶ መተኛት አልችልም፤ ስለዚህ ማናፋት አለብኝ ብሎ አንዴ ጩኸቱን ለቀቀው።
በዚህ ጊዜ በዙሪያው የነበሩ ጅቦች ከዚህም ከዚያም ዘለው በመምጣት አህያውን መዘነጣጠል ጀመሩ። ከዚያም በአንድ አፍታ የአህያውን ሆድ ዘርግፈው መብላት ጀመሩ። ጥቂት ከበሉ በኋላ ረሃባቸውን አስታገሱ። ከዚያ አንድ ጅብ ዞር ሲል ውሻ ተኝቶ ተመለከተ። ይህ ደግሞ እዚህ ምን ይሰራል ብሎ ጠርቶ ቀሰቀሰው። አንተ ማነህ ብሎ ጠየቀው። ውሻውም ቀና ብሎ መልስ ሰጠ። እኔ ብልት አውጭ ነኝ። አለው።
ከዚያ እንዲህ ከሆነማ ናና የዚህን አህያ ብልት በሥርዓት አውጣልን፤ ልቡን እኩል ለመካፈል ስለምንፈልግ አሉት። እሺ ብሎ ተነስቶ ሆዱ ውስጥ ገብቶ መቦጥቦጥ ያዘ። ከዚያ የሚበቃውን ያህል ከበላ በኋላ ቀና ሲል ጅቦቹ እየጠበቁ ነው። ጅቦቹም እናስ የታለ ልቡ፣ ብለው ጠየቁት። እሱም አይ ጌቶቼ ይህ አህያ ልብ የለውም፤ አላቸው።
ለምን ሲሉት ልብ ቢኖረው አይበላም ነበር፤ ብሎ መለሰላቸው ይባላል። ይህ ተረት ብዙ የሚያስተምረን ቁምነገር አለ። ከልክ ያለፈ ጥጋብ መጨረሻው ምን እንደሆነም ትልቁ መልዕክት ነው። አዎ ልብ ያለው ጥንቃቄ ያደርጋል፤ ምክርም ይሰማል። ቢያንስ ለአደጋ የሚያጋልጠውን ተግባር ከመፈፀም ይቆጠባል።
ለዚህ ተረት መነሻ የሆነኝ የህወሓት ጁንታ ድርጊት ነው። እንደው ግን ከልክ በላይ የሆነ ጥጋብ እስከህይወት ፍፃሜ ድረስ አይለቅ ይሆን የሚል ጥያቄንም እንድንጠይቅ ያደርገናል።
ህወሓት በትጥቅ ትግሉ ወቅት በደርግ ሥርዓት ከባድ ፈተና የተጋፈጠ ድርጅት ነው። የትግራይ ህዝብም በዚህ ጦርነት ከ60 ሺህ በላይ ልጆቹን ገብሯል። ነገር ግን ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ አብዛኛው የትግሉ ሰማዕትና ህዝብ ሲታገልለት የነበረው ዓላማ ወደጎን ተጥሎ ሌብነትና አልጠግብ ባይነት ቦታውን ያዘ።
ጥቂት የቡድኑ አንጃዎች ሥልጣኑን ከተቆጣጠሩ በኋላ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው አገርን ወደመከፋፈልና መበታተን፤ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት ቆመው ለዘላቂ ሰላምና ዕድገት እንዳይሰሩ የቀድሞ ነጭ አክራሪ ቅኝ ገዢዎችን ሴራ እየመዘዙ ዕርስ በርሱ እንዳይተማመን አደረጉት።
ከሁሉም በላይ በ27 ዓመታት የጁንታው የበላይነት ዘመን በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀው አንድነት ትልቅ ሽንቁር የፈጠረበት ጊዜ ነበር። ይህም በተለይ አገር በሚረከበው ትውልድ ላይ ከትምህርት ሥርዓቱ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች በመዘራቱ ቀስ በቀስ ከአገራዊ ማንነትና አንድነት ይልቅ የብሔር ማንነት እየጎላ እንዲመጣ አድርገዋል።
በጣም የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ሰዎች ሰው መሆናቸውን ዘንግተው ዘላለም የሚኖሩ እስከሚመስል ድረስ ያጋብሱት የነበረው ሀብት ከልክ በላይ መሆኑና ዘረፋን የህይወታቸው አንድ አካል አድርገው በቃኝን አለማወቃቸው ነው። በዚህ ሁሉ መካከል ደግሞ ቢያንስ ብዙዎቹ እድሜአቸው ከጡረታም አልፎ በእርጅና ዘመናቸው ሌሎች ወጣቶችን ለመተካትና አዳዲስ አስተሳሰቦችን እንዲመጡ ዕድል ለመስጠት አለመቻላቸው ነው። ብዙዎቹ ከ46 ዓመት በፊት ወደበረሃ ሲሄዱ በነበረበት ወቅት ያላቸው አስተሳሰብ ላይ ቆመው የቀሩ ናቸው። በቅርቡ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ እንኳ ወደቀደመው የአኗኗር ሥርዓታቸው መመለሳቸው ለዚህ ማሳያ ነው።
በዚህ ዘመን እንኳን 46 ዓመታት ቀርቶ ሁለትና ሦስት ዓመትም በርካታ ለውጦች የሚስተዋሉበት ነው። በዚህ ዘመን ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ ለውጦችን ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነው። ለውጥ ሲመጣም በነበሩበት ደርቆ መገኘት መሰበርን ያስከትላል። የህወሓት ጁንታም ያጋጠመው ይኸው ነው፤ የመሰበር ዕጣ ፈንታ።
ይህ ግን አስተምሮን ያለፈው ትልቅ ትምህርት ነው፤ እያንዳንዱ ሰው ለውጥን መቀበል እና ሁል ጊዜ ለአዳዲስ ነገሮች መገዛት እንዳለበት ያስተምራል። አንዳንዱ በሃላፊነት ላይ ያለ አካልም ከልክ በላይ የሆነ ጥጋብም የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብና በልክ መኖርን መማር አለብት። “ከረሃብና ከጥጋብ ማን ይሻላል ሲሉት ኧረ ረሃብ በስንት ጣዕሙ” እንዳሉት አባት ጥጋብ ክፉ ነውና ሁል ጊዜ በህይወታችን ውስጥ ጥንቃቄ አይለየን።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2013