(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ) gechoseni@gmail.com
መራር የዜጎች ትዝብት፤
የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ቢሆን ርዕዩ፣ ህልሙ፣ ግቡም ሆነ ምኞቱ ሥልጣን መጨበጥ ነው። “ሕዝብን ማገልገል” የሚለው መሸንገያ ደማቅ ሽፋን እንጂ እጅግም ትኩረት የሚሰጠው ዋና ጉዳይ መስሎ አይታይም። ከሆነም የሚገለጸው በደብዛዛው ነው። የፖለቲካ ፍላጎት ከመጠን አልፎ በውስጡ እየተንተከተከ የሚፍለቀለቅ ማንኛውም የፓርቲ አባል ግለሰብ ለይስሙላ ያህል “የሕዝብን መዳፍ” በመሃላ እየተመተመ ያሳመነ ይምሰለው እንጂ ፍላጎቱና ቅዠቱ መገልገል እንጂ ማገልገል እንዳልሆነ ማረጋገጡ ብዙም አይከብድም።
ሕዝብን ለማገልገል የቆረጠ ሰው የግድ ከፖለቲካ ቀንበር በታች መደራጀት አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። “ራሱን በመሰዊያ ላይ” ለማኖርና ለሕዝብ መስዋዕት ለመሆን መንገድና ብልሃት ያጣል ተብሎም አይገመትም። የምር ከጨከነ ሙያው፣ ሃብቱ፣ ዕውቀቱና ተሞክሮው መንገድ ሆነውት ሕዝብን በመጥቀም ልቡ የፈቀደውን መልካምነትና የዜግነት ግዴታውን ሊፈጽም ይችላል።
የፖለቲካ ሰምና ወርቅ ሁሌም በተቃርኖ የተሞላ ነው። የላይ ላይ መሸፈኛ ሰሙ “ሕዝብ” የሚባለው የብዙ ግፉዓን ውክልና ሲሆን ወርቁ ደግሞ በሰሙ ውስጥ የተሸሸገው የሥልጣን ወንበር ቅዠት ነው። ከተግባር የመከነ የሥልጣን ወንበር ጥማት ያሰክራል፣ ያቀውሳል፣ ከሰብዓዊነት ክብርም አዛንፎ ዝቅ ያደርጋል። አንድ የሚዲያ ሃያሲ አንዳሉት “ሥልጣን አናት ላይ ሲወጣ እንደሚያሳብድ ዓለም የተማረው ከትራምፕ እብሪት ነው።”
የፖለቲካ ፓርቲ ከለላና የአባልነት “አብሾ” ከተቀላቀለበትማ ሥልጣንን የሙጥኝ የማለቱ አባዜ የኅሊናን ጨርቅ አስጥሎ ጭርሱኑ ያሳብዳል። ለዚህ ትኩስ ማስረጃ ሊሆን የሚችለው ሥልጣኔን ተነጠቅሁ ብሎ የክፍለ ዘመኑን ክህደት የፈጸመው ትህነግ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲ ምርኮኞች በሙሉ በአንድ ሚዘን ይመዘኑ፣ በአንድ ጎታ ይታጎሩ ማለትም ትክክል አይደለም። ተፈጥሮ እንኳን ከጥሬ መካከል ብስል እንደማይታጣ ታስተምረናለች። ኅሊናቸው ከደረቀ ቡዙኃን “ፖለቲከኞች” መካከል ለምለም አስተውሎት ያላቸው እንደማይታጡ እሙን ነው።
ጥቅሉን እውነታ ስንፈትሽ ግን ከዓለማችን ታሪክም ይሁን ከሀገራችን የዋዛ ፈዛዛ የፖለቲካ ውጣ ውረዶች የተማርነውና እየተማርን ያለነው በአብዛኛው እከሌ ተከሌ ሳይባል ለፖለቲካ ርዕዮት ራሱን የሰዋ ሰው ሁሉ ምኞቱ ከፍ ያለ ወንበር፣ ቅዠቱም የቆራጭ ፈላጭነትን ብርታት በማሳየት ገንኖ መውጣትን ነው።
በበርካታ ፖለቲከኞች የተሳሳት ግምት ሚሊዮኖች ዜጎችን የታቀፈች ሀገር የምትፈረጀው “ከእኔና ከእኔ መሰሎች ውጭ ከቶውንም ሀገር ሀገር አትሆንም” በሚል ድምዳሜ ነው። የዓለምን ታሪክና የጓዳችንን ተሞክሮ በጥሞና ብንመረምር ይህ አባባል ምን ያህል እውነታነት እንዳለው ለማረጋገጥ እጅግም አይከብድም።
ሩቅ ማማተሩን ለጊዜው ትተን የሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ በራሱ ጥሩ አብነት ሊሆን ይችላል። ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሥጋቸው፣ መንፈሳቸውም ሆነ አእምሯቸው ጃጅቶ ንግሥናቸውን በክብር ማስተላለፍ አልሆን ስላላቸው በመንበራቸው ላይ እንዳንጎላጀጁ ፍጻሜያቸውን በውርደት አከሰሙ።
ዙፋኑን ተረክቦ የሀገሪቱን አስተዳደር በሶሻሊዝም ፍልስፍና ያቆረበው የደርግ መንግሥትም በእብሪትና በትዕቢት ተኮፍሶ የሥልጣኑን ወንበር ነክሶ አለቅም ብሎ በሚንገታገትበት ወቅት ከጫካ እያገሳ ቤተ መንግሥት በደረሰው ጨካኝ አውሬ ጥርሶች ተላምጦ አይሞቱ ሞት ሞቶ ተቀበረ።
በረኸኛው የኢህአዴግ ሠራዊትም ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ቀረጣጥፎ እንዳላመጣቸው፣ እንደ አሻንጉሊት እየተጫወተ እንደተሳለቀባቸውና ምድር ያፈራችውን ግፍ ሁሉ እየፈጸመ ሀብቷንና ትሩፋቷን ሙጥጥ አድርጎ የጥቂቶች መብሸንሸኛ በማድረግ ሲፏልል መክረሙንና የግፉ ዋንጫ ሞልቶ ሲገነፍልም በሕዝብ ማዕበል ተጠራርጎ በተወለደበት የበረሃ ዋሻ ውስጥ ግብዓተ መሬቱ እየተፈጸመ እንዳለ የምናየውና የምንሰማው ሐቅ ነው።
ከየትኛውም ታሪካችን በከፋ ሁኔታ የተደመደመው የዚህ እኩይ ድርጅትና የገድለኞቹ ታሪክ እንኳን ለባለጉዳዮቹ ለራሳቸው ቀርቶ ለሰሚውና ለተመልካቹም ጭምር የሚያሰቅቅና “በእነርሱ የደረሰ አይድረስባችሁ” የሚያሰኝ ነው።
የኢትዮጵያን ፖለቲካና ፖለቲከኞች ታሪክ ለትውልድ ለማሸጋገር ደፋር ኃያሲና ተንታኝ ጀግና ብቅ ብሎ ብዕሩን ያነሳ ዕለት ምን ያህል ጥራዝ፣ ምን ያህል ቅጽ መጻሕፍት ተሰንደውና ታትመው እንደሚዘረገፉልን ማሰቡ በራሱ ያጓጓል።
የሀገራችን ፖለቲካ እንቆቅልሽ፣ መልኩ ዝንጉርጉር፣ ባህርይውም ውስብስብ፣ መደምደሚያውም አሳፋሪ እንደሆነ ከትናንት እስከ ዛሬ እያስተዋልን ያለነው “የእርግማኑን” ባህርይ ለመለየት እንኳን እየተሳነን ነው።
በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ያልማለ፣ በ“አዞ እምባው” አፈሯን እየለወሰ የማስመሰል ኪዳን ያልገባ፣ “ከእኔ ወዲያ ላሳር” በማለት ራሱን እንደ ነፃ አውጭ መሲህ ቆጥሮ ሆሳዕና ያላዘመረ ፖለቲካና ፖለቲከኞችን በየዘመናቱ ማስተዋል ለእኛ ብርቃችን አይደለም። አዬ ጉድ አዬ ጉድ! ስንቱን መከራና አሳር ተጋፍጠናል! አልፎ ቢያልፍ ባልከፋ ዛሬም ከአበሳው ፍዳ አርነት መውጣት ተስኖን የዕለት ቀለባችን እንባችን ሊሆን ግድ ሆኗል።
የፓርቲ አባልነት ገመና፤
የፖለቲካ ሀራራ “በማይፈወሱት ክፉ” ደዌ የመለከፍ ያህል የከፋ ነው። ባህር ማዶኞች “Necessary evil” የሚል ገላጭ ሀረግ እንደፈጠሩለት በ”ዲሞክራሲ” ጉዳይ በተደጋጋሚ ለንባብ ባበቃሁት ጽሑፌ ውስጥ መግለጼ አይዘነጋም። በተለመደው ተዘውታሪ አባባል ሃሳቡን እናጠናክር ካልንም የሀገራችንን ፖለቲካ “ላም እሳት ወለደች፤ እንዳትለሰው ፈጃት እንዳትተወው ልጅ ሆነባት” በማለት የ“በረከተ መርገምነቱን” መንታ ባህርይ ማመላከት ይቻላል።
የሀገሬን የፓርቲ አባልነት ጉዳይና ተሳትፎ ሁሌም ባሰብኩ ቁጥር ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ አንድ “የፖለቲካ ባህል” ፈገግ እንድል ምክንያት ይሆነኛል። ይህ ባህል በቅርብ ዘመናት ሲገዙን በነበሩት ሥርዓቶች ውስጥ ሁሉ ሲወራረስ የመጣ ይመስላል። የፖለቲካ ሠፈርተኞች የሚሳተፉባቸው የመሠረታዊ ድርጅቶቻቸው የጥናት ወይንም በጥቂት ቁጥሮች የሚካሄዱ ልዩ ልዩ ስብሰባዎች ሁሌም ምሥጢር ናቸው።
የመሰብሰቢያ ሰዓታቸው እንዳይታወቅ፣ የአባላቱ ስምና መልክ ይፋ እንዳይሆን፣ በስህተትም ቢሆን የመወያያ ሰነዳቸው “ብጫቂ ወረቀት እንኳ ወድቆ እንዳይገኝ” ሁሌም እንደ ጣዖት የሚሰግዱለት ፓርቲያቸው የሚሸሽጋቸው እንደ ቅዱስ ዕቃ “ግምጃ” እያለበሰ ነው።
በጸሐፊው እውቀት በሁሉም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችም ይሁን በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የተሰባሰቡ የየትኞቹም ዘውጌም ሆነ የገዢው ፓርቲ ተራ አባላት (ከዋነኞቹ ካድሬዎችና ባለሥልጣናት በስተቀር) ምዬለታሁ ለሚሉት የርዕዮተ ዓለማቸው ኪዳን ደፍረው ለምስክርነት ሲቆሙ አይስተዋሉም።
“የቆምነው ለሕዝብ ጥቅም ነው” የሚል መሃላ እያዘነቡ ከሕዝብ መሸሸግን ምን ይሉታል? “እኔ እከሌ የሚባለው ፓርቲ አባል ነኝ። የፓርቲዬ ርዕይና ተልዕኮ ይህንንና ይህንን ይመስላል” ለማለቱስ ለምን ድፍረት ሊያጡ ቻሉ?
እርግጥ ነው በአንዳንድ “የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት” ዘንድ ድፍረቱ ጠፍቷል ማለት ግን አይደለም። በተለይም የገዢው ፓርቲ አባላት ነን የሚሉት ስብሰባቸውን በድብቅ፣ ውይይታቸውን በጨለማ፣ ምክክራቸውን ተሸሽገው ለማድረግ እንደሚመርጡ እንኳን ለእኛ ለባለጉዳዮቹም የገባቸው አይመስለኝም።
የተቃርኖው ዓይነት መልኩ ብዙ ነው። የደርጎቹ ኢሠፓዊያን የስብሰባና የጥናት ክበባት ባህል ይህ ነበር። የፌዴራሊስቱና የሟቹ ኢህአዴግ ልጆችም ይህንኑ ባህል አሜን ብለው ተከተለው ኖረዋል። የዛሬው የኢህአዴግ አልጋ ወራሽ የብልፅግና ልጆችም እየተከተሉት ያለው ፍልስፍና ከቀዳሚዎቹ ምንም ልዩነት የለውም። ሁሉ ድብቅ፣ ሁሉ ሽሽግ፣ ስሙ ግን “ለሕዝብ” የሚል የመሸንገያ ልባስ ነው፡
እንዲያው ሙግታችንን ግልጽ እናድርገውና ለሕዝብ ጥቅምና ለሀገር እድገት ቆሜያሁ የሚል ፓርቲና አባላቱ እንደምን ጨለማ ሊመርጡ ይችላሉ? “እስከ ሞትም ቢሆን” ዓላማዬ ብለው ለተከተሉት መርህ ከልብ ካመኑ፣ ጀርባቸው ንፁህ ከሆነ፣ የሕዝብ አክብሮትና ፍቅር ካላቸው፣ በተመደቡበት የፖለቲካ ኃላፊነትም ሆነ በሚሠማሩበት የተግባር ድርሻ በአርዓያነት የሚጠቀሱ ከሆነ አቋማቸውንና የወከሉትን ድርጅት በልበ ሙሉነት ለማስተዋወቅና ማንነታቸውን ለመግለጽ ምን ያስፈራቸዋል? ምንስ ያሳፍራቸዋል? ገዢውም ሆነ “ተገዢ ፓርቲ ተብዬዎች” በምርጫ ወቅት ብቻ ሳይሆን በአዘቦት ቀናትም “ለሕዝብ አርነት ቆመናል” እያሉ እዬዬ ከማለታቸው አስቀድሞ የሚያንገዋልሉትን አንገዋለው አባላቶቻቸውን ነፃ በማድረግ ቢፈቷቸው ደግ ሳይሆን አይቀርም።
በቅርቡ ገዢው የብልፅግና ፓርቲ “የአባሎቼ ቁጥር ከአሥር ሚሊዮን ከፍ ብሏል” በማለት መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል። ቁጥሩን ብቻም ሳይሆን የአባላቱን የማኅበራዊ ስብጥር ይዘትም ቢገልጽልን ኖሮ የምንለውን ለማለት ድፍረት እናገኝ ነበር። ሚሊዮን ቁጥር የተሰላላቸው አባላቱ የተልዕኮ ስምሪት የሚሰጣቸው ሕዝብን በቅንነት እንዲያገለግሉ ነው ወይንስ እንደ ፓርቲው ወላጅ እንደ ኢሕአዴግ በብዙኃን ጭንቅላት ላይ ፊጥ ብለው ቁልቁል በኩርኩም እንዲያሰቃዩን? የቀበሌ መታወቂያ በገንዘብ እንዲሸጡልን ወይንስ ለመብታችን ክብር እንዲሰጡ? የሕዝብ መሬትን ወርረው የተረፈውን በሥራቸው ለሚገኙት የወራሪ ሠራዊት እንዲያቀራምቱ ወይንስ በነፍሳቸውም ቢሆን ተወራርደው ከዘራፊዎች እንዲታደጉን? በብሔራቸውና በድርጅታቸው ጉያ ውስጥ ተወሽቀው እንደ ማን አለብኙ ቀዳሚ ግንባር የደሃውን መቀነት እያስፈቱና ከምስኪን ዜጎች እምባ ጋር ቀላቅለው ውስኪ እየተጎነጩ “ብልፅግና ፓርቲያችን ሆይ ሺ ዓመት ንገሥ!” እንዲሉ? የቁጥሩ መጋነን ክፉኛ አስግቶናል።
የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት እንደ ወርቅ ነጥሮ ከወጣ ፖሊሲ መቃኘቱን እያወጁልን እነርሱ ግን እንደ ትናንትናዎቹ “ጌቶቻችን” ልጆቻቸውን አውሮፓና አሜሪካ በመላክ እያቀማጠሉና እያሞላቀቁ እንዲያስተምሩ ማበረታታት? የሀገራችን የጤና ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ደረጃ ላይ ደርሷል እያሉ በመደስኮር እነርሱ ግን “ገነትን ለራሳቸው ከልለው እንደኖሩት እንደ ቀዳሚዎቹ ጉዶች” ወደ ሰለጠኑት ሀገራት በቻርተር አውሮፕላን እየተመላለሱ እንዲታከሙ? የሚሊዮኖች አባላቱ መሰባሰቢያ ባለጠጋው ገዢ ፓርቲ ልክ እንደተወለደበት ማህጸን እርሱም ብሶታችንን ለመድገም የሚጨክን ከሆነ አርፈን መቀመጡ ይበጃልና ቁርጣችንን ቢያሳውቀን አይከፋም።
እንደዚህ ጸሐፊ ጽኑ የግል እምነት ከሆነ ከፓርቲ አባላት የቁጥር ብዛት ይልቅ የብዙኃንን ልብ መማረኩ በብዙ መልኩ ውጤታማና አትራፊ የማድረግ ብቃት ያለው ይመስለኛል። ገና ለገና የምርጫ ኮሮጆን በደጋፊ ድምፅ ለመሙላት ወይንም የፓርቲውን የፋይናንስ አቅም ለማጎልበት በማሰብ አለያም “ይህን ያህል አባላት አሉኝ” እያሉ ለመፎከር እንዲያስችል “ሥራ ጠል የጎበዝ አለቆችን”፣ የሙስና ቅንቅኖችንና ሕዝብ ለሚጠይቀው ተገቢ መብት “እጅ ከምን?” እያሉ መቀነት የሚያስፈቱትን “አስለቃሾች” በአባልነት ከማፈስ ይልቅ “በተራና ገለልተኝነትን በመረጡ አስተዋይ ዜጎች” ላይ እምነት አሳድሮ በአሸናፊነት ለመውጣት መሞከሩ ድርብ ድል የሚያጎናጽፍ ስትራቴጂ ሊሆን ይችላል።
ለመሆኑ በሚሊዮን የተቆጠረው ይህ የአባላት ሠራዊት ምን ተልዕኮ፣ ምንስ የኃላፊነት ድርሻ ሊሰጠው ታቅዷል? አባል ካልሆነው ዜጋ ጋርስ በእውነቱ በሙያውና በክህሎት አቅሙ ተወዳድሮ ያሸንፋል ወይንስ የፓርቲ ንክር ለሆኑት ብቻ ቅድሚያ ይሰጥ በሚል የውስጥ ማስታወሻ ተግባራዊ ይደረጋል? ይህን መራራ ትዝብትና ስጋት በድፍረት የምንገልጠው “እባብ ያየ በልጥ በረዬ” እንዲሉ ገና ያልመሸበት የትናንቱ ፍርሃት (Phobia) ከውስጣችን ተነቅሎ ስላልወጣ ነው።
ደግሞስ ከዘጠና ሚሊዮን በላይ የሆንን ኢትዮጵያዊ ዜጎች ስጋታችንን በልባችን አምቀን ከመያዝ ይልቅ ጥርጣሬያችንን እንዲህ በአደባባይ ለመዘርገፍ ብንጀግን አሥር ሚሊዮኖቹን የፓርቲ ሰዎች መዳፈር ተደርጎ ሊቆጠርብን ይገባልን? ሌላው እንኳን ቢቀር እኛ ተራ ዜጎችም እኮ በነጻነት ሃሳባችንን ለመግለጽና አቋማችንን በግልጽነት ለማሳየት “የተኳረፍነው ሕገ መንግሥት ከለላ ሰጥቻችኋለሁ” ብሎ ማረጋገጫውን ስለሰጠን “የፓርቲ ቤትኞች” ምን ይሉን ይሆን ብለን ብንሸማቀቅ “የዲሞክራሲያችንን” ክብር ዝቅ ማድረግ ይሆናል።
አናሳዎቹን መዘከሩ ለጊዜው ይቆይና ከሁለት ክፍላተ ዘመናት በላይ ዕድሜ አላቸው የሚባልላቸውን የታላቋን አሜሪካ ሁለት ታላላቅ ፓርቲዎች ተሞክሮ ብቻ አስታውሶ ማለፉ “ውሻን ምን አገባው ከእርሻ” አሰኝቶ አያስተርትም። እኛም እኮ ሀገራችንን የወላድ መካን አድርገን ስላቆየናት እንጂ ቢሆንልን ኖሮማ ዓለም የሚማረው ከእኛ በሆነ ነበር። ባለ ዝሆን አርማው የአሜሪካው ሪፐብሊካን ፓርቲ ወይንም “ታላቁ አንጋፋ ፓርቲ” (GOP, Grand Old Party) እና በዕድሜ ርዝመት ሪፐብሊካኑን የሚቀድመውና በአገልጋዩዋ አህያ ምስል ራሱን የወከለው የዲሞክራቲክ ፓርቲ የአባሎቻቸው ቁጥር እንደ ዕድሜያቸው ርዝመት የተንዘላዘለ አይደለም።
እነዚህ የዓለማችን ሁለት ገናና ፓርቲዎች “አሉን” የሚሏቸው የአባላት ብዛት በበቂ ማስረጃና መረጃ ሊረጋገጥ አልቻለም ተብለው ስለሚወቀሱ ከድረ ገጻቸው ላይ ያስቀመጡትን ቁጥር እንደ ዋና ማመሳከሪያ መጥቀሱን አልወደድኩትም። ይልቁንስ ዲሴምቤር 17 ቀን 2020 በተደረገ አንድ የዳሰሳ ጥናት የዲሞክራቲክ ፓርቲውን እንደግፋለን የሚሉ ዜጎች ቁጥር 31 ከመቶ፣ ሪፐብሊካኑ ይሻለናል የሚሉት ደግሞ 25 ከመቶ ያህሉን እንደሚሸፍኑ ጥናቱ አረጋግጧል። በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት ብዙዎቹ የፓርቲዎቹ አባላት ያለመሆናቸውን ልብ ይሏል።
ስለዚህም በፓርቲ አባላት ላይ ብቻ ልብን ጥሎ ሚሊዮን ቁጥር ከመጥቀስ ይልቅ በፕሮግራምና በስትራቴጂ ብቃት፣ በልማትና ፍንትው ብሎ በሚታይ ውጤት ሕዝብን መማረክ ብልህነትም ጥበብም ነው። የፖለቲካ ፓርቲ አባልነትን የራስ ሥጋና ነፍስ ማጽደቂያ ምድራዊ ትሩፋት አድርጎ ከማለም ይልቅ ሕዝብን በደምና በላብ፣ በቅንነትና በፍቅር፣ በአክብሮትና በትህትና አገልግሎ በኅሊና እርካታ መሸለም በእጅጉ የከበረ ዋጋ አለው። ያለበለዚያ ግን ነገን ዛሬ ከልሎት እንደ ትናንትናዎቹ ፖለቲካን መሸቀጫ አድርጎ መዘባነን ውጤቱ ምን እንደሚሆን ለመገመት አይከብድም። “ልብ ያለው ልብ ያድርግ!” ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ጥር 13/2013