ጌቴሴማኔ ዘ-ማርያም
የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ፋይዳው ፈርጀ ብዙ ነው። ለሀገራችን ኢኮኖሚ ዋናው መሰረት ዛሬም ግብርና ከመሆኑ አንፃር አስተዋጽኦው የላቀ ነው። የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥም ጉልህ ሚና ይጫወታል።
ሁሉም ነገር የተመሰረተው ተፈጥሮ ሀብት ላይ ነው። ተፈጥሮ ሀብት በውስጡ አፈሩን ጨምሮ ማሳውን፣ የግጦሽ መሬቱንና ሁሉንም ይይዛል። ተፈጥሮ ሀብት ኢኮ ሲስተሙን ወይም በአማርኛው አጠራር መላው ስርዓተ ምህዳርን ያካትታል። ወይም ራሱ ስርዓተ ምህዳር ነው ማለት ይቻላል።
መሬት ላይ ተወርዶ ሲታይ የሚያስገኘው ጥቅም የትኞቹም ዓይነት የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ግብዓቶች ከሚያስገኙት በእጅጉ ይልቃል። ጥቅሙን ትራክተሮችም ሆኑ ኮምባይነሮች አይተኩትም። ሌላው ቀርቶ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከአፈር ልማት ሥራው ጋር ቅርበት እንዳለው የሚነገረው ዘመናዊው ዩሪያ፣ ዳፕ እና በሰው ሠራሽ መንገድ የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንኳን አይስተካከለውም።
ምክንያቱም ተፈጥሮ ሀብት የልማት ሁሉ መሰረትና መነሻ በተለይ ለግብርናው ዘርፍ የጀርባ አጥንት ነው።ተፈጥሮ ሀብት ሲለማ ወንዞች፣ ምንጮች ይጎለብታሉ። በተደላደለ ሁኔታ መስኖ ማልማትም ይቻላል።
መንግስት ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ በዘርፉ ‹የማይታረስ መሬት አይኖርም› በሚል እንደ ሀገር በግብርናው ችግሩን ለመዋጋት ጎን ለጎንም ምርታማነትን ለመጨመር ያስተላለፈውን መመሪያ በውጤታማነት ለመፈፀም ያግዛል። ግብርናን ለማዘመንና ለማሻገር የተቀመጠውን ዓላማ ማሳካት የሚቻለውም የግብርናውን ዘርፍ በዚህ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ መደገፍ ሲቻል ነው።
በ2012/13 ምርት ዘመን የሚጠበቀውን 460 ሚሊዮን ኩንታል እህል ለማግኘትም መጀመሪያ ተፈጥሮ ሀብት ላይ በደንብ መሠራት አለበት። ቀድሞ የግድ ተፈጥሮ ሀብት ላይ የተጣለ መሰረት ያሻልና ቸል ማለት አይገባም። በመሆኑም የመጀመሪያው የትኩረት አቅጣጫ የተፈጥሮ ሀብትን ልማት ጥበቃ ሥራ ማከናወን መሆን አለበት።
የተለያዩ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎች በርብርብ መሰራት ይኖርባቸዋል። አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ብሎም የግብርናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና መላው ሕብረተሰብ በዚህ ሥራ አካባቢውን እንዲንከባከብ ማድረግ ግድ ይላል።
አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ባለቤት እንደመሆኑ በሥራው ግንባር ቀደም መሆን አለበት። በተለይ የከብቶቹን ሰውነት በማጎልበት ምርታመነታቸውን ከሚጨምረው ለምለም ግጦሽ ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማትን ተጠቃሚ የሆነው ሰፊው አርብቶ አደር በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍበት ማድረግ ያሻል።
ግብርና ሚኒስቴር ይሄን ታሳቢ አድርጎ ዘንድሮ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ እንደ ሀገር በሚያለማቸው አንድ ሺህ 500 ተፋሰሶች ለሚሳተፉ 13 ሚሊዮን አርሶና አርብቶ አደሮች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለ ድርሻ አካላት ግንዛቤ አስጨብጧል።
የልማት ሥራው በግብዓት፣ በቴክኖሎጂ፣ በአሠራርና በሌሎች ሥራውን ማቀላጠፍ በሚያስችሉ መንገዶች መደገፍ እንደሚገባው አምኖ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። እንደ ሀገር ከጥር አንድ ጀምሮ በወር ውስጥ ላሉት የስራ ቀናቶች የሚቆይ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ዘመቻ አውጆ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል።
በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በአማራ ክልሎች አሀዱ ተብሎ የአፈር ዕቀባ፣ የጎርፍ መቀልበሻ፣ ጎርፍ ማስወገጃ፣ የአፈር ለምነትን የሚጨምሩና ሌሎች ሥራዎች በስፋት እየተሰሩ ነው። ሥራው በዋናነት የሚሰራው እርሻ ማሳ ላይ ነው። በተለይ ከፍታ ላይ ባሉ ቦታዎች ላይ ባለ ማሳ ላይ ጎርፍ እርሻውን ጠራርጎ እንዳይወስደው በልዩ ትኩረት መሰራት አለበት።
የማይታረስ የወል ቦታ ላይም እንዲሁ ዘላቂነት ያለው ጥቅም የሚሰጥ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል። የተጎዳ የተፈጥሮ ሀብትን መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ግድ ይላል። የግብርናው ዘርፍ ባለሙያዎች አበክረው ሲገልፁ እንደሚሰማው አሁንም የመሬት መራቆት የሀገሪቱ ከፍተኛ ችግር መሆኑ አልቀረም።
በዚህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና በምግብ ዋስትና ዕድገት ላይ ተፅዕኖም ይፈጥሯል። እንደ መስኩ ባለሙያዎች ምክር ታድያ እነዚህን ፈርጀ ብዙ ችግሮች ለመከላከል ምርትና ምርታማነትን የሚያስቀጥሉ ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋል።ችግኝ መትከልም ዓይነተኛ መፍትሄ ነው። የተራቆተ መሬት የመከለል፣ ቦረቦር መሬቶችን በኖራና በተለያዩ ሳይንሳዊ ዘዴዎች የማከምና የማልማት ሂደትም ይመረጣል።
የድንጋይና የእንጨት ክትር የማበጀት እንዲሁም የተፋሰስና ጥምር ደን እርሻ ልማት ሥራዎች ማከናወን ወሳኝ ነው። እነዚህ ሥራዎች የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ቀድሞ በተጀመረባቸው በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በአማራ ክልሎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። እንደ ሀገር ተለይተው ለመሠራት በዕቅድ ከተያዙት 400 ሺህ ሄክታር የሚሆኑት ከመጎዳታቸው የተነሳ ከንክኪ ነፃ የሚደረጉ አካባቢዎች ናቸው።
2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ቦታዎች የስነ አካላዊ ሥራ ይሰራባቸዋል። ደለል ሞልቶ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል እርከኖችን ወደ ላይ ከፍ የማድረግ የእርከን ካብ፣ ቦዮችን የመጥረግ፣ የተለያዩ የጥገና ሥራዎች የመሥራት ዕቅዶች ተለይተው የተያዙበት አግባብ አለ። በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ሥራ አዲስ ከመሥራት ባሻገር አምና፣ካች አምናና ከዚያም በፊት የተሰሩ ሥራዎችን መልሶ የመጠገን ሥራዎችም ይከናወናሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት በዚህ መልኩ የተሰሩ ተመሳሳይ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበባቸውም ነው። በአንዳንድ ክልሎች በተከታታይ አሥር ዓመታት በተሠራው አካላዊና ሥነ ሕይወታዊ ሥራ በዋነኝነት ከ21 ሺህ ተፋሰሶች ውስጥ ሰባት ሺህ ተፋሰሶች ዘለቄታዊ ሀብት ማመንጨት ችለዋል።
በቅርቡ እንደ አማራ ክልል የዘንድሮ ተፈጥሮ ሀብት ሥራ ጥር 4 ዓ.ም የተጀመረበት ላይ አርማጮሆ ወረዳ ላይ 80 በመቶው የአካባቢው አርሶ አደር የጥምር ደን እርሻ ባለቤት መሆኑን ማየት ተችሏል።ጥምር ደን እርሻ የስነ አካላዊ ሥራ በመሆኑ መሬቱን ያጠነክራል። በሌላ በኩል የምግብ ምንጭ ነው። ገንዘብ ነው። የአረንዴ ልማት ሽፋን ነው።
በዚህ ክልል አርጎባ ወረዳ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል ሀረርጌ፣ አምቦ፣ ሜጫ በደቡብ ወላይታ፣ ሀዲያ፣ የጠረጴዛ እርከን ተሰርቶና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አርሶ አደሮች፣ ሥራ አጥ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደ ፍራፍሬ ያሉ ቋሚ ተክሎችን በመትከል ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ፣ ሕይወታቸውን መምራትና መለወጥ፣ አኗኗራቸውን ማዘመንና የምግብ ዋስትናቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ችለውበታል።
በነዚህ አካባቢዎች ልቅ ግጦሽ የሚያስቀሩ ሣርን እንደ ቅርጫ አርደው ቅርጫ አስቀምጠው ዕጣ ተጣጥለው የሚረካከቡበት ቀጣይነት ማረጋገጥ ያስቻሉ ሥራዎች ተሰርተዋል። ይሄን በመስራታቸው የአካባቢውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት የቀነሱ፣የጎርፍ መጠንን የቀነሱ፣ ደለልን የቀነሱ፣ የካርቦን ዳይኦክሳይድን ምጣኔ ያመጣጠኑና ተደማሪ ውጤት ማግኘት የተቻለባቸው አካባቢዎች በርካታ ናቸው።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2013