ወርቅነሽ ደምሰው
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የዲያስፖራውን ተሳትፎ ለማጠናከር ፣ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ተሳትፎ ያለበት ሁኔታና በቀጣይ ዘላቂ ስትራቴጂ ለማዘጋጀት ሀገር አቀፍ ጥናት ማከናወን በሚያስችል ሁኔታ ላይ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየሰራ ይገኛል።
በዚህም የዲያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰሩ ያሉ ጥሩ ተሞክሮ ካላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ጅግጅጋ፣ሃዋሳና ወሎ ዩኒቨርስቲዎችን በተወሰኑ መልኩ ለመቃኘት ወደድን
በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የዲያስፖራ ተሳትፎ አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር ትዕንግርቱ ገብረጻዲቅ እንደሚናገሩት፤ የዲያስፖራ ተሳትፎ ፕሮጀክት እኤአ በ2019 የተጀመረና ሲቲ አሊያንስ በሚባል ድርጅት የሚደገፍ ነው። ዲያስፖራው ከፍተኛ የከተሞች የልማት አጋር ቢሆንም፤ ለረጅም ጊዜ የዲያስፖራውን ተሳትፎ በማሳደግ በኩል ከተሞች እጥረት እንደነበረባቸው ይናገራሉ።
በፕሮጀክቱ የጂግጅጋ ከተማ እንደ ፓይለት በመወሰድ የዲያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ ፤ የክልሉ አስተዳደር፣ የክልሉን ዲያስፖራና ኢንቨስትመንት ቢሮ አቅማቸውን እንዲያጎለበት ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል ። በዚህ ፕሮጀክት ወደ አስራ ሁለት የሚጠጉ ተግባራት ያሉ ሲሆን ፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያ የዲያስፖራ ፖሊሲ ነው።
ፖሊሲው ከወጣ በኋላ ወደመሬት ወርዶ ለማስፈጸም የሚያስችል አሠራር ያልተዘረጋለት በመሆኑ በጂግጅጋ ከተማ ላይ ስትራቴጂ በመንደፍ በተለይ ክልሉ የዲያስፖራ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚረዱ የተለያዩ ሁኔታዎች ላይ እገዛ በማድረግ እየሰራ ይገኛል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ትዕንግርቱ ገለጻ፤ የከተማዋን ዲያስፖራ አቅም ማጎልበት የሚያስችሉ ሥራዎች መስራትና ሀገር አቀፍ የሱማሌ ዲያስፖራ ንቅናቄ በመፍጠር ዲያስፖራው ክልሉን በልማት እንዲያግዝ የማድረጉ፤ በተለይ በክልሉ ያሉ ከተሞችን ልምድ እንዲወስዱ በማድረግ ብዙ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በሱማሌ ክልል የዲያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ጋር በመሆን ይህንን ስትራቴጂ ወደ ሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ ታልሞ እየተሰራ ነው ።
ከዚህ በፊት የዲያስፖራ ስትራቴጂ ከላይ ወደ ታች የሚወርድበት አካሄድ ሲከተል እንደነበር የጠቆሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ ፤ አሁን ግን በክልል ላይ ተሞክረው ውጤታማ የሆኑ ስትራቴጂዎች በማሳደግ ወደ ሀገር አቀፍ ደረጃ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው ፖሊሲ ላይ ያሉ ክፍተቶች በመለየት መከለስና አሁን ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች አዳዲስ ለውጦች ያካተተ ፖሊሲ ሀገሪቷ እንዲኖራት ማስቻል ላይ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የዲያስፖራ ኢንቨስትመንትና ተሳትፎ ሁኔታ በመለየት ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች የዲያስፖራን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ የሚያደርጉ የድጋፍ ሥራዎች የሚሰሩበት ሁኔታዎች መኖራቸውን ያብራራሉ።
በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ ከዲያስፖራ ጋር ተያይዞ በሀገር አቀፍ ደረጃ መስፋት የሚችል ጥሩ ተሞክሮ ያለው ነው፤ ሌሎች ክልሎችም ከሱማሌ ክልል አስተዳደር ጋር ልምዶችንና አሠራሮችን መውሰድ የሚችሉበት እድል አለ።
ዩኒቨርሲቲው በዲያስፖራ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ብዙ ባለሙያዎች ስላሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚሰሩ ሥራዎች ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤ ዩኒቨርሲቲዎች አቅሙ ላላቸው የከተማ መስተዳድሮችና ክልሎች ደግሞ ያንን አቅም በደንብ አውጥተው መጠቀም እንዲችሉ ድጋፍ ያደርጋል።
በሱማሌ ክልል የዲያስፖራ ተሳትፎ እኤአ ከ2016 ጀምሮ በጣም ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴዎች አሉት የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የዲያስፖራ ኢንቨስትመንት መኖሩን ይጠቁማሉ።
የክልሎች ኢንቨስትመንት ከክልሉ ሰላምና ነባራዊ ሁኔታ ጋር በጣም የተገናኝ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ሌሎች አዳዲስ ሪፎርሞች ሲመጡ የዲያስፖራው ተሳትፎ በዚያው ልክ እየጨመረበት የሚመጣበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፤ በቅርብ ጊዜያት ከኮቪድ በኋላ በተወሰነ መልኩ በክልሉ የዲያስፖራው ተሳትፎ መቀዛቀዙን ይናገራሉ ።
ይህንን የተቀዛቀዘ ሁኔታ መልሶ ለማነቃቃት በቅርብ ሀገር አቀፍ የሆነ የሱማሌ የዲያስፖራ ፎረሞች የሚካሄድ ሲሆን፤ እነዚህ ፎረሞች በዋናነት በዲያስፖራው በኩል ያሉ ችግሮችንና በክልሉ በኩል መልካም አጋጣሚዎችን አቅሞች በማጠናከር የሚሰሩ ሥራዎች መሆናቸውን አስረድተዋል ።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ታፈሰ ማቲዮስ እንደሚናገሩት፤ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ደቡብ ክልል የነበረውን የዲያስፖራ ተሳትፎና ኢንቨስትመንት በተመለከተ ያሉበት ደረጃና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችንና በቀጣይነት ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል ጥናት ተደርጓል።
ይህ ጥናት በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የዲያስፖራ ተሳትፎ ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ነው። ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት መጠቀም ካለብን አቅም አንደኛው ዲያስፖራው ነው።
የአፍሪካ ሀገራት ይህንን አቅም በሚገባ በመጠቀም የተለያዩ ተቋማትን አደራጅተው የሚጠቀሙ ሲሆን፤ በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ኤጀንሲው እንኳን ከተቋቋመ ገና ሁለት ዓመት ነው።
ፖሊሲ ከወጣ ስምንት ዓመት ያህል ያስቆጠረ ቢሆንም ፤ ወቅቱ የሚጠይቀውን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በድጋሚ ታይተው ወደ ሥራ መግባት እንዳለበት ይገልጻሉ። ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ጥናት ባለሙያዎችን በመመደብ ጥናቱን በጥሩ ሁኔታ ለመስራት ተነሳሽነት እንዳለው ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር ታፈሰ ገለጻ፤ የዲያስፖራ ፖሊሲው ስትራቴጂዎች ስለሚያስፈልጉት ስትራቴጂዎቹ በየጊዜው መከለስ አለባቸው። ዲያስፖራው የበለጠ ውጤታማ እንዳይሆን ማነቆ የሆኑት ከመሠረተ ልማት ጋር፣ ከመንግሥት ቢሮክራሲና ከብድር ጋር የተገናኙ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በጥናቱ እንደተመላከተው ፍቃድ አውጥተው ወደ ሥራ የሚገቡት ዲያስፖራዎች የሚፈለገውን መጠን ውጤታማ እየሆኑ ባለመሆናቸው ፤ ክትትልም እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመው፤ ሰፋፊ መሬቶችን ይዘው ወደ ሥራ ያልገቡ በኢንቨስትመንት ሥም የተለያዩ ጥቅሞች ካገኙ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ከግብር ነጻ የሆኑት እንኳን በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ አለመሆናቸውን ይገልጻሉ።
ይህንን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ መከታታል የሚያስፈልግ ሲሆን፤ ለዚህ የሕግ ማዕቀፍ መኖሩ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥናቱ እነዚህና መስል ችግሮችና የመፍትሔ ሀሳቦች ያመላከተ ነው።
በወሎ ዩኒቪርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተርና የኮሙኒኬሽንና የጆርናሊዝም መምህር ተስፋዬ በዛብህ እንደሚገልጹት፤ በውሎ ዩኒቨርሲቲ የዲያስፖራ ተሳትፎን ለማሳደግ ዓለም አቀፍ የዲያስፖራ ምሁራን መማክርት ተቋቁማል። ይህ ምሁራንን የያዘ መማክርት ዩኒቨርሲቲውን በምርምር በቴክኖሎጂ ሽግግር ተማሪዎች በማማከር መምህራን እያመጡ በማስተማርና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም በአካባቢ በኢንቨስትመንት ዙሪያ አቅዶ ለመስራት የተዘጋጀ ትልቅ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ ወደፊት ከአካባቢ አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ስራዎችን ለማከናወን አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ዲያስፖራው ከኢንቨስትመንቱ አልፎ በመማር ማስተማሩ በቴክኖሎጂ ሽግግር ሆነ በሌሎች ነገሮች ኢንቨስት ከማድረግ በፊት በሀገር ዙሪያ ያለው አመለካከት ላይ የሚሰራበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል ።
በሀገር ውስጥ ብዙ ለውጦችና የፖለቲካ ውጣ ውረዶች ይኖራሉና የፖለቲካ ውጣ ውረዶች ወጥ የሆኑ ነገሮች ባለመኖራቸው ለዲያስፖራው ማነቆ ሆኖበት አልፎ ያሉት መምህር ተስፋዬ፤ አሁን ላይ ያለውን የተሻለ ለውጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ዲያስፖራ ሀገሩ ገብቶ መስራትና ማልማት እንዲችል ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2013