(ክፍል ሁለት )
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
ባለፈው ሐሙስ በዚሁ ጋዜጣ ባስነበብሁት የመጀመሪያ ክፍል ስለ ስብሀት ማንነትና ስረወ _ መንግሥቱን ስላቆመባቸው ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አዕማዶች አንስቼ ነበር። በዛሬው መጣጥፌ ደግሞ በትህነግ/ኢህአዴግም ሆነ ለ30 ዓመት አገዛዝ ላይ በነበረው ቡድን የስብሀት የገዘፈ ሰብዕና ምን እንደሚመስል አነሳሳለሁ።
የባንዳው የፊታውራሪ ነጋ ዘር አይደለም በትህነግ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መልከዓ በጋራ፣ በሸንተሩ ፣ በዱር በገደሉ ፤ በሸለቆው ፣ በኮረብታው ፣ በሳር በቅጠሉ ይገኛል። የወልደስላሴ በትግል ስሙ የስብሃት አባት ፊታውራሪ ነጋ ከተለያዩ ሚስቶች 18 ልጆች ወልደዋል። ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ የአለፉ ሲሆን የተቀሩት በሕይወት አሉ።
ምንም እንኳ ቅሌታሙ ሽማግሌ ሰሞኑን ሲያዝ ፤ «ከሞትን እኮ ቆየን ፣» ቢሉም ። ፊታውራሪ ነጋ እነዚህን ልጆች ከተለያዩ ሚስቶች መውለዳቸው ዘራቸውን እንደ ዋርካ ያሰፋዋል። እሳቸውም ሆኑ ልጆቻቸው ከእነዚህ ሚስቶች ወገን ተዛምደዋል። ተጋምደዋል። 16ቱ ልጆቻቸው ሲጋቡና ሲዋለዱ ደግሞ የሚፈጠረውን ዝምድና እና ትስስር ማሰብ ነው።
ፊታውራሪ ነጋ በትግራይ አድዋ አውራጃ የአዲያቡ ገዢ ነበሩ። በትግራይ አካባቢ ባንዳነት ትልቅ ሥራ ነበር እና እሳቸውም ትልቅ ባንዳ ነበሩ። የስብሃት አጎት የእናት ወንድም ተክሉ መሸሻም ታዋቂ ባንዳ ነበሩ። ባንዳነት ከሀዲነት ከቤቱ ነው ይሏል እንዲህ ነው።
ከፊታውራሪ ነጋ ልጆች ፤ በላይ ነጋ ፣ ስብሃት ነጋ ፣ ገብረእግዛቤር ነጋ፣ ዮሴፍ ነጋ ፣ ወልደሩፋኤል ነጋ፣ አቤሴሎም ነጋ፣ እስጢፋኖስ ነጋ ፣ ቅዱሳን ነጋ ፣ እቴነሽ ነጋ ፣ አበራሽ ነጋ ፣ ሃይሌአባይ ነጋ ይገኙበታል። ሁሉም የስብሀት ስረወ መንግሥት አካል ነበሩ። ትህነግም ሆነ የኢኮኖሚ ኢምፓየሩ በእነሱ ዙሪያ ስለተገደገደና ስለተማገረ ስልጣኑም ሀብቱም በእነሱ ደጅና እጅ ተመላልሷል። ተገላብጧል።
የስብሀት ስረወ መንግሥት የኢኮኖሚ ኢምፓየር ከኢትዮጵያ አልፎ በጁባና በካርቱም አሳብሮ በዱባይና በዶሀ አድርጎ ኳላላምፑርና ጃካርታ ላይ አለፍ ገደም ብሎ ቻይና መለስ ቀለስ ብሎ በአውሮፓና በአሜሪካ ዘና ፈታ ብሎ በአቤሶሎም ነጋ አውስትራሊያ ይምነሸነሻል።
የስብሀት ታናሽ እህት ቅዱሳን ነጋ የፀጋየ በርሄ ባለቤት ናት። አይተ ፀጋየ ደግሞ የቀድሞ የትግራይ ገዢ ነበር። በኋላ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የመከላከያ እና ደህንነት ጉዳዮች አማካሪና አዛዥ ናዛዥ ነበር ። “ በትርፍ ጊዜው ደግሞ !? “ የአፋርን ጨው ጨምሮ የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብትና ኢኮኖሚ ከስረወ መንግስቱ ኔት ወርክና የጥቅም ትስስር አለመውጣቱን በቅርብ ይከታተል ነበር።
ባለቤቱ ቅዱሳን ነጋም የቀድሞ የመቐሌ ከንቲባ እና በህወሓት የሴቶች ጠርናፊ ነበረች። የስብሀት ወንድም ልጅ ፈትለወርቅ ገ/እግዛቤር ደግሞ የአባይ ፀሐዬ ባለቤት ነበረች። በፓርቲውና በመንግስት ስልጣንም ከፍ ያለ ተጽዕኖና ተሰሚነት ነበራት።
የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፤ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ስረወ መንግስቱን አገልግላለች። የስብሃት ነጋ ቤተሰብ መረብን ተሻግሮ ኤርትራም ይደርሳል። ሌላው የኢሳያስ አፈወርቅ ፀሐፊ አበራሽ ነጋ (አሁንም በዚሁ ኃላፊነት ስለመኖሯ መረጃ የለኝም፤) እንዲሁም የኤርትራው ጀነራል ስብሃት ኤፍሬም ባለቤትም ነች። የኤርትራው ጀነራል ፍፁም (ወዲ መቐለ)ም የስብሃት ሚስት ወንድም ነው።
ይህ ቤተዘመድ ከልጓም ዘር ይስባል ካላልን በስተቀር ከስብሀት ስረወ መንግስቱ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል ብሎ መገመት ይከብዳል። የአርከበ ሚስት የብርሀነ ገብረክርስቶስ እህት ስትሆን የአርከበ እህት ደግሞ የአዲስአለም ባሌማ ሚስት ናት። የከሀዲው ትህነግ ላዕላይ መዋቅር በስብሀት ስረወ መንግስትና በጋብቻ የተጠላለፈ ነው። የስረወ መንግስቱ ቤተኛ የማይመስለው ጌታቸው አሰፋ እንኳ ከስብሀት ሚስት ጋር የአቋጥሩኝ ዝምድና እንዳለው ይነገራል። መግቢያዬ ላይ የባንዳው ፊትአውራሪ ቤተሰብ እንደ ዋርካ የሰፋ ነው ያልሁትን ያስታውሷል።
ስብሀት ነጋ ዘንድ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ፤ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትም ሆነ ፤ “ ድርጅቴ ህወሓት/ ኢህአዴግ በመደበችኝ በማንኛውም ቦታ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ። “ የሚሏት አስመሳይ ጨዋታ አትሰራም። የትህነግ ሊቀ መንበር መሆን ሲፈልግ በአረጋዊ በርሄ እግር ተተክቶ ወይም ጥርሱን በነቀለበት ሴራ ጠልፎ ሊቀ መንበር ሆነ። በወቅቱ የድርጅቱ ጊዜያዊ ሊቀመንበር የነበረው አረጋዊ በርሄ ሲሆኑ፤ በ1971 ዓ.ም የድርጅቱ የመጀመሪያ ጉባኤ ከተካሄደ በኋላ ስብሐት የመጀመሪያው ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጠ።
የስረወ _ መንግስቱን ፖለቲካዊ መዋቅር በማይናወጥ መሰረት ላይ ማቆሙን እርግጠኛ ሲሆን ከአስር አመት በኋላ በ1981 ዓ.ም መሰሪውንና ዘረኛውን መለስ ዜናውን ተክቶ እሱ የበላይ ጠባቂ ሆነ። የኤፈርት የዘረፋ ኢምፓየር የትህነግ መመኪያና መመጻደቂያን የነበረውን ግዙፍ ድርጅት ያለ አፍጣጭና ገልማጭ እስኪበቃው አገላብጦታል።
ሲሰለቸው ደግሞ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ጥናት ተቋምን ጡረታ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ በዋና ዳይሬክተርነት ገዝቷል። ስብሀት ከዚህ በላይ ተጽዕኖ ፈጣሪና ግዙፍ ነበር። በተመሳሳይ ጊዜ የትህነግ አባት፣ የጡት አባትና ጠባቂም ነበር።
ይሄን እሱም “አቦይ” ስለሚለው ቅጽል በቢቢሲ አማርኛ ሲጠየቅ ፤ “ አቦይ” የሚል አጠራር በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው አገላለጽ ነው። ቃሉ ዕድሜን ብቻ አመላካች ሳይሆን ‘ዋናው’ የሚል ትርጓሜም ሊሰጠው ይችላል። “ በማለት የትህነግ ዋና ፣ ቁንጮና አራጊ ፈጣሪ መሆኑን በዘወርዋራ ይነግረናል። የከሀዲው ትህነግም ተንቀሳቃሽ አውደ ርዕይና ቤተ መጽሐፍት ነው።
ምን አደከማችሁ ስብሀት የሚታይና የሚዳሰስ ተቋም ነው። ስብሀት የትህነግ የአደጋ ጊዜ ተጠሪ፤ አምቡላንስና እሳት አደጋ ነው። ትህነግን ከፈተና፣ ከጥላ ወጊ ( ስትሮክ ) ከእሳት ቃጠሎ ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ታድጎታል። በ1968 ዓ.ም በትህነግ አመራር ተፈጥሮ የነበረውን ሕንፍሽፍሽ (መከፋፈል) እና በድህረ ኢትዮ_ኤርትራ በ1993 ዓ.ም በእነ ገብሩና በመለስ አንጃ ተፈጥሮ የነበረው መሰንጠቅ በመለስ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።
በሌላ በኩል በ1968 ዓ.ም በድርጅቱ ውስጥ የተከሰተው ‘ሕንፍሽፍሽ’ በሚል የሚታወቀው መከፋፈልም ሆነ በ1977 ዓ.ም እነ አቶ አረጋዊ በርሄ እና አቶ ግደይ ዘርአጽዮን ከድርጅቱ የተገለሉት በስብሀት የእጅ ስራ በሴራ እንደሆነ ይነገራል። በመጨረሻ ትህነግ ለዚህ ሊበቃ የቻለው የስብሀትን ስጋት ስጋቱ ባለማድረጉ ፣ የጠረጠረውን ባለመጠርጠሩ ፣ ቀልቡ ያልወደደውን ባለመውደዱ እና ትህነግ ሽማግሌውን ንቆ በራሱ በመታበዩ ነው። ስብሀት ዐቢይ በተመረጠ ማግስት ለትህነግ አመራሮች በመቐሌ በትግረኛ የሰጠው ኑዛዜ አዘል ሙሾ ጓዶቹ እንደ በፊቱ እሱን በጀ ብለው ባለማድመጣቸው ድርጅቱን ለውድቀት እንደዳረገው ይናገራል።
ስብሀት ዐቢይ አሕመድ (ፒኤችዲ) ወደ ኢህአዴግ ሊቀ መንበርነት የመጣበት ምርጫ ዛሬ ድረስ የእግር እሳት ሆኖ ይለበልበዋል። ለዚህ ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ የተጫወተው የዚያን ጊዜው የብአዴን ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንን መሆኑን በቁጭት ይናገራል። ” ደመቀ የሸወደንን ያክል መሰሪው ሻእቢያ እንኳን አልሸወደንም ! ” ይላል እንደ እባብ ካብ ለካብ የሚተያየውን የመጠባበቅና የመነዳደፍ የፖለቲካ ስልቱን እያስታወሰ ።” ደመቀ ለትህነግ ታማኝና ታዛዥ ነበር። ፈፅም! የተባለውን ነገር ለመፈፀም ‘ለምን? ‘ ብሎ እንኳን አያውቅም ።
አንድ ቀን ግን የሱዳን ግዛት የሆነውን አዋሳኝ መሬት ለመስጠት ፈርም ሲባል “አይሆንም አልፈርምም!” ብሎ አሻፈረኝ ሲል ያኔ ይህ ሰው አንድ ቀን እንደሚሸውደን እርግጠኛ ሆኜ ለጓዶቼ ነግሬያቸው ነበር። “ እዚህ ላይ ስብሀት እራሱ ደመቀ ፈጽም የተባለውን ሁሉ የማይፈጽም መሆኑን በማረጋገጥ ከራሱ ሀሳብ ጋር ሲቃረን እንታዘባለን ። “ ሁሉም የእኔን እይታ (እርስ በርሱ ስለሚቃረነው ስለደመቀ ያለው እይታ መሆኑ ነው፤ ) ሳያቅማሙ ሲቀበሉኝ ጌታቸው አሰፋ ግን ‘ አታስብ እሱ መዳፋችን ውስጥ ነው። የትም አይደርስም ! ‘ብሎ በንቀት ሲመልስልኝ የሰሙ ጓዶች በጌታቸው ላይ ከፍተኛ እምነት ስለነበራቸው እነሱም ስጋቴን ወደጎን ተውት። እኔ ግን’ ጀግናን የሚገድለው ተራ ወይም የተናቀ ሰው ነው።
‘ ብዬ ጌታቸውን አስጠንቅቄው ነበር። “ እዚህ ላይ የስብሀትን እብሪትና የሴራ ጨዋታ ልብ ይሏል። “ የመጨረሻው የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ምርጫ ዋዜማ ዕለት ማታ ላይ በነበረን ስብሰባም ይህ ሰው ( ደመቀን መሆኑ ነው ፣ ) አንድ ነገር እንዳያደርግ በሚል ጥሩ ስሜት እንደማይሰማኝ ስናገር በተለይ ጌታቸው አሰፋ ፣ ጌታቸው ረዳ እና አባይ ፀሐይ ‘ አትጨነቅ ደመቀ በሚገባ አምኖበታል።
የተባለውን ባያደርግ የሚደርስበትንም ያውቃል ። በተጨማሪ ደግሞ ሁሉንም የብአዴን ፣ የኦህዴድ እና የደህዴን አባላት ቀጣይ የከፍተኛ ሚኒስትርነት ስልጣን እና ዳጐስ ያለ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው በራሳቸው ሰዎች ስለተነገራቸው በደስታ ተቀብለውታል። ‘ ብለው ሊያሳምኑኝ ሞከሩ።
በእርግጥም በተለይ የደህዴንና የብአዴን አመራሮች ለስልጣንና ለጥቅም የማይከፍሉት ዋጋ እንደሌለ በማስረጃ ሲያስቀምጡልኝ ባላምንበትም ይሁን ብዬ ተውኩት። እዚህ ላይ ዐቢይና ደመቀን ጨምሮ የለውጥ ኃይሎች ሕይወታቸውን አሲዘው የራሱን የትህነግ ቁማር እንደበሉት ያጤኑአል።
“በትጥቅ ትግል ወቅትም ሆነ በስልጣን ላይ ከሆንን በኋላ ድርጅቴ ሊደርስበት ከተጋረጠበት እስከ መፍረስ የሚያደርስ ከፍተኛ አደጋዎች በአለቀ ሰዓት እንኳን እንደታደግሁ ስለሚያውቁኝ ይቀበሉኛል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። አሁን ግን ከእኔ ውጪ የእኔን ሀሳብ የሚያስብ እና የሚደግፈኝ ሰው ሳጣ ዝም ብዬ ቁጭ አልኩና የሚሆነውን ለማየት ወሰንኩ።
በመጨረሻ ግን ለረጅም ዓመታት በነበረን የትጥቅ ትግል መሰሪው ጀበሃ(ሻእቢያ) እንኳን ሸውዶን የማያውቀውን ሽወዳ ደመቀ ሸወደን! አዋረደን ! ለዚህ ውድቀታችን ተጠያቂዎች ሁለቱ ጌታቸው የተባሉትና አባይ ፀሐይ ናቸው ። “ እያለ ይብሰከሰካል ስብሀት ፤
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ስብሀት በጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ከተያዘ በኋላ በሰጠው የመጀመሪያ ኑዛዜ እልባት ላድርግ፤” የሞትነው እኮ ስማችን የተቀየረለት ነው። ( ከኢህአዴግ ወደ ብልፅግና መሆኑ ነው ፤ )ዛሬ እያደረጋችሁ ያላችሁት የቀብር ስርዓታችንን ማስፈጸም ነው ።
“ ሦስተኛውንና የመጨረሻ ክፍሉን የእሱ ፈቃድ ከሆነ ሰሞኑን ይዤ እንደምመለስ ቃል እየገባሁ ለእነዚህ መጣጥፎቼ ፤ የገብሩ አስራትን ፣ ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ፣ 2007 ዓ .ም ፤ ቢቢሲ አማርኛን በርከት ያሉ ድረ ገጾችን መጎልጎሌን ከአክብሮት ጋር እገልጻለሁ። ምንጮቼንም በእናንተ በአንባቢዎች ስም አመሰግናለሁ ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!! አሜን፡፡አዲስ ዘመን ጥር 12/2013
አዲስ ዘመን ጥር 12/2013