በትግራይ ክልል በተካሄደ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጁንታው እንዳይጠገን ሆኖ ቢደቅም፣ አንዳንድ ወገኖች እርማቸውን ሳያወጡ ቆይተዋል።እርም እንዳይበሉ ብለው ነው መሰል ይመለሳል ብለው እየጠበቁ ናቸው ይባላል።
መንግስት በቅርቡ ደግሞ ጁንታው ድል ሲመታ የሸሹ የጁንታውን ቀንደኛ አመራሮች ሲያድን ቆይቶ እጅ አልሰጥ ያሉትን ከነአጃቢዎቻቸው ደምስሷል። የትህነግ መስራቹንና በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ትእዛዝ ካስተላለፉት መካከል አንዱ የሆኑትን አቦይ ስብሃትን ጨምሮ በርካታዎቹን ቱባ ቱባ ወንጀለኞች ደግሞ በቁጥጥር ስር አውሏል።
ጁንታው ይመለሳል ብለው ሲጠብቁ የቆዩት አንዳንድ የዋሆች ብቻ ላይሆኑ ይችላሉ። ሴረኞችም ቅጥረኞችም ሊኖሩ ይችላሉ። የሕግ ማስከበር ስራው እዚያው አጠገባቸው እየተፈጸመም ማመን አልቻሉም፤ መሪዎቹ ላይ እርምጃ መወሰዱ እየተገለጸላቸውም ሊያምኑ አልቻሉም።
በቁጥጥር ስር የዋሉት ኦቦይ ስብሃት ‹‹የሞትነው ኢህአዴግ የፈረሰ ጊዜ ነው፤እናንተ እያረጋችሁ ያላችሁት የቀብር ሥነሥርዓት መፈጸም ነው›› ሲሉ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት መናገራቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። አሁንም ማመን ሊከብዳቸው ይችላል። ቢያምኑ መልካም ነበር፤ማመኑ ትግራይን መልሶ ለማቋቋምና ሰብዓዊ ድጋፍ በሚገባ ለማድረግ ፋይዳ የጎላ ይሆን ነበር፡ካላመኑም፤በሂደት ያምናሉ።
እነሱ አመኑም አላመኑ ጁንታው በመላ ኢትዮጵያ በተላላኪዎቹ የፈጸመው ግፍ አንሶት በቀን ጎዶሎ በሰራው ግዙፍ ስህተት ሰሜን እዝን ነክቶ የእድሜ ገመዱን አሳጥሯል።በሰሜን እዝ ላይ ድል ተቀዳጀሁ እያለ አለም ዘጠኝ ሲጨፍር በድርጊቱ የተቆጣው መከላከያ ሰራዊት ከደረሰበት ጉዳት በአስቸኳይ አገግሞ በወሰደበት ጥቃት እንዳይጠገን አርጎ ሰባብሮ ጥሎታል፤አድቅቆታል። እስቲ አስቡ የደቀቀ መስታወት መልሶ መስታወት ሲሆን?
ጦርነት ከእኔ በላይ ላሳር ሲል የነበረው ጁንታው በመከላከያ ሰራዊት የ15 ቀናት ፈጣን እርምጃ ስብርብሩ ወጥቶ ያስጥለኛል ወደአለው እና በሱር ኮንስትራክሽን ባስገነባውና ሲፈጠር ይጠቀምበት ወደ ነበረው ዋሻ የገባው።መከላከያ የገባበት እየገባ መቆሚያ መቀመጫ አሳጥቶ ትግራይ የመከላከያ መቀበሪያ ትሆናለች ሲል ራሱ በማሰው ጉድጓድ ራሱ ተቀበረበት።ለጠላቴ ብለህ አርቀህ አትቆፍር ራስህም ልትገባበት ትችላለህና አስተውል ነው የተባለው።ራሱ ተቀበረበት።
የቀረው ስራ ወንጀለኞችን ማደን ነበር።እሱም ቢሆን በድል እየተጠናቀቀ ይገኛል።አንዳንዶቹ የጁንታው አውራዎች ተደምስሰዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ይህም ጁንታው ተመልሶ ይመጣል ብለው ሲጠብቁ ለቆዩ ሀይሎች መራር መርዶ ነው።
እነዚህ ኃይሎች በሁለት መልኩ ነው ጁንታው ሞተ ተቀብሮ እያለ ይመጣል ብለው እንዲያስቡ የተገደዱት።አንዱ በአንድም ይሁን በሌላ ለጁንታው ካላቸው እምነትና ፍቅር በመነጨ ሊሆን ይችላል።ሌላው ደግሞ በአስገዳጅ ሁኔታ አብረው እየኖሩ በመላመዳቸው የተነሳ ሊሆን ይችላል።ቅጥረኛም ሊኖር ይችላል፤ቡድኑ በባህሪው ይታወቃልና።
እምነት እና ፍቅሩ በራሱ በአንድም ይሁን በሌላ ሊከሰት ይችላል።አንዲት ልጃገረድ ተጠልፋ ሳትወሰድ በግድ ለትዳር ብትዳረግ ጠላፊዋን እየጠላችው የምትወድበት ሁኔታ ውስጥ ትገባለች።አብራ በቆየች ቁጥር ጉዳቱን ዋጥ አርጋ ወይም ለምዳው ብዙ እድሏ ተሰብሯል ብላ በማሰብ ችላ ልትኖር ትችላለች። ልጆች ወልዳም ስለልጆቿ ስትል አብራ ትኖራለች።
ጁንታው ይመለሳል እያሉ የሚጠብቁ ኃይሎችም ፈርተው ቢመለስ ምን ይውጠናል ብለው ወይም እምነቱና ፍቅሩ ስላላቸው በመናፈቅ አለያም ቅጥረኛ ሆነው ሊሆን ይችላል ወደዚህ እርምጃ የገቡት።
የእነኚህን ሰዎች አመለካከት መቀየር ጊዜ ቢወስድም ጁንታው ሲደመሰስ ማየታቸው እና መደምሰሱንና በቁጥጥር ስር መዋሉን ማወቃቸው ትልቅ ትርጉም አለው። መረጃው በፎቶም ጭምር በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው።ይህ ሁሉ አመለካከታቸውን እየቀየሩ እንዲመጡ ሊያደርጋቸው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
የጁንታው አመለካከት በእነዚህ ወገኖች ላይ የተጫነው በውድም በግድም ነው፤ይህ ደግሞ የሆነው ከአርባ አመታት በላይ ለሆነ ጊዜ ነው።በጊዜ ብዛት አመለካከቱ ተጠቅጥቆባቸዋል።ይህን እያወጡ ማሽቀንጠር በቀላሉ የሚቻል አይደለም።
አንድ ጆንያ ብዙ እንዲይዝ በሚል ልንጠቀጥቀው እንችላለን። ጠቅጥቀን ያስገባነውን ፈጥነን እናወጣለን ብለን የምናስብ ከሆነ ስህተት ነው።ለመጠቅጠቅ የወሰደውን ጊዜ ያህል ቢሆን መውጣቱ ጊዜ ሊወሰድ እንደሚችል በመረዳት የተወሰነ ጊዜ ሰጥቶ ማውጣት ያስፈልጋል።
በአዲስ አበባ በከተማ አውቶብስ ላይ እንደሚስተዋለው ተጠጋጉ እየተባለ ሲጫን በር መዝጋት እስከሚያስቸግር ድረስ አውቶብሱ ሊሞላ ይችላል። አውቶብሱ ይህን ያህል ሰው ሲጭን ብዙ ጊዜ ሊወስድም ይችላል።
የአውቶብሱ አሽከርካሪ በዚህ አይነት መልኩ ጠቅጥቆ መጫኑን ዘንግቶ በየፊርማታው ለምን ቶሎ ቶሎ አልወረዳችሁም ቢል አያስኬድም፤አጫጫኑን ማሰብ አለበት።ቅርብ እወርዳለሁ ያለውን ሁሉ እየገፋ ወደ ውስጥ እንዳስገባው ሁሉ ለማውረድም መጠበቅ ይኖርበታል።
የጁንታው አመለካከት በግድም በውድም የተጠቀ ጠቀባቸው ወገኖችንም እንደዚያው ማየት ሊያስፈልግ ይችላል። ከአመለካከቱ በቀላሉ ይላቀቃሉ ተብሎ አይጠበቅም።መጠበቅም የዋሃነት ነው።
በአይናቸው በብረቱ ያዩትን በገዛ ጆሯቸው የሰሙትን ማመን እየተቸገሩ ያሉበት ሁኔታ አንድም ይህን ያመለክታል።የሚነገራቸውን ለማመን ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል።
በሆነ መልኩ ከተጠናወታቸው አመለካከት ለመላቀቅ የጁንታው ተሰባብሮ መውደቅ አመራሮቹም መደምሰስና በቁጥጥር ስር መዋላቸው ትልቅ ትርጉም እንዳለው መገንዘብ አያዳግትም።አመለካከት መለወጥ ላይ አጥብቆ መስራት ግን ቀጣይ ትልቅ ስራ ሊሆን ይገባል።
ጁንታው አመለካከቱን ያሰረጸው በሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እየዋሸ ነው።ለእዚህ ደግሞ በሞቱ ዋዜማ እያጣጣረ ባለበት ወቅት ሳይቀር ገደልኩ ማረኩ እያለ ሲያወራ የነበረበትን ሁኔታ በአብነት መጥቀስ ይቻላል።ይህን ብዙዎቻችን ሰምተናል። ለእዚህ ሕያው ምስክሮች ነን ።
በሌላ በኩል ደግሞ ለአንዳንዶቹ ዳረጎት በመስጠት የጥቅም ተጋሪ በማድረግ አመለካከቱን ለማስረጽ ሞክሯል፤እነዚህ ወገኖች ደግሞ ጥቅማቸውን ሲሉ ያን አመለካከት ሲጠበቁና ሲያራምዱ ኖረዋል።
አሁንም ይህ ሁሉ መከራና መርዶ እየወረደባቸውም ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ሊሉ ይችላሉ። አንዱ ሽፍታ እንደ ፌስቡኩ ሊጫወትባቸው እንደሚችል መገመት ይገባል።የዋሆቹን ደግሞ አንድ ተራ ሽፍታ ሊጫወትባቸው ይችላል፤የፌስ ቡክ ሰራዊትም ሊጫወትባቸው ይችላል።
ይህን ታሳቢ ያደረገ የአመለካከት መለወጥ ስራ በስፋት መሰራት ይኖርበታል። ከዚህ ሁሉ ማውጣት የሚቻለው ተከታታይነት ያለው ሰፋፊ መድረኮችን በማዘጋጀት ፣መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ከጁንታው በሁዋላ እየተከናወነ ያለውን ተግባር በማሳየት ጭምር ሊሆን ይገባል።ይህ ለየዋሆቹ ይሰራል።
ከዚህ በመለስ አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም የሚባሉ አይነቶች እንዳሉም መረዳት ያስፈልጋል።እነዚህ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ መስራት ካልሆነ ደግሞ በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግም ይገባል።ሕዝብ እንዳይረጋጋ ማድረግ ወንጀል መሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስፈልጋል።
ቅጥረኞች ሊኖሩም ይችላሉ። በዚህ በኩል ጁንታው የነበረውን ልምድ በመጠቀም በግልም ይሁን በቡድን ሆነው ክልሉን እና ሀገሪቱን ለማመስ እንደ እባብ አፈር ልሰው ሊነሱ ይችላሉ።መጠርጠር መልካም ነው።
ቢልላቸው ሞኝ አውሬ ነው በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ሁለቴ የሚወጋ የሚለውን ብሂል አስበው ሰላማዊ መንገድን ለመከተል የሚያስችል መንገድን ቢመርጡ መልካም ነው ። ያ ካልሆነ ደግሞ አንደ አባቶቻቸው የመደምሰስን ወይም በቁጥጥር ስር የመዋልን ጽዋ እንዲጎነጩት ማድረግ ይገባል።
እያየ እየሰማ የማያምን ትውልድ ፈጥረውብን አልፈዋል፤ይህን ትውልድ መቀየር ቀጣይ ግዙፍ ስራ እንደሚሆን መጠራጠር አይገባም።የሕግ የበላይነትን የማስከበሩን ስራ በድል መወጣት ተችሏል፤የተጠቀጠቀውን አመለካከት የሚመጥን አመለካከትን የመተካት ዘመቻ በስፋት ማከናወን እንደሚያስፈልግ በማመን ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ይገባል ።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2013