አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የጀመረቻቸውን ስራዎች መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዓለም ባንክ አስታወቀ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመራሮች በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር በሆኑት ዶክተር ኦስማን ዲዮን ከተመራ የልኡካን ቡድን ጋር ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ተወያይተዋል።
በወቅቱም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሐም በላይ (ፒ ኤች ዲ) ዓለም ባንክ በተለያዩ ዘርፎች በኢትዮጵያ በተለይም የዲጂታል ፋውንዴሽን ስራና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚከናወኑ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ያሳየውን ፍላጎትና ድጋፍ አድንቀዋል። ሚኒስትሩ የቴሌኮም ዘርፉን ፕራይቬታይዝ የማድረግ ስራ ላይ ከፖሊሲ አንጻር የነበሩ ስራዎች ከዓለም ባንክ ጋር በቅርበት መስራታቸውን አስታውሰዋል።
በውይይቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) በዲጂታል 2025 ፕሮግራም ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የዲጂታል አሰራርን ለመዘርጋት የሄደችውን ርቀት ለልዑካን ቡድኑ አብራርተዋል።
ዶክተር አሕመዲን ፕሮግራሙ ወደ ትግበራ ለመግባት ከልዩ ልዩ አካላት ጋር ድጋፍና ትብብር በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተቀናጅቶ ለመስራት የልየታ ስራ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ተወካዩ ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው በተለያዩ ሀገራት ካገኟቸው ተሞክሮዎች አንጻር የዲጂታል አጀንዳን ትግበራ ለማረጋገጥ የተሻለ ጅምር እንዳለ ተናግረዋል።
በተለይም ቬትናም የዓለም ባንክ ፕሮግራም በሚመሩበት ወቅት ካላቸው ልምድ አንጻር በኢትዮጵያ ያለው ጅምር ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል።
ዓለም ባንክ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ከተማና ትራንስፖርት እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች በቴክኖሎጂና ዲጂታይዜሽን ለማዘመን በኢትዮጵያ የሚደረገውን ጥረት ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚደግፍ ቃል ገብተዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የጀመራቸውን የተለያዩ ፕሮግራሞች ውጤታማ ለማድረግ የዓለም ባንክ የቴክኖሎጂ አማካሪዎች ቡድን ለመመደብ ዝግጁ ነን ብለዋል።
ከየኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ዶክተር ኦስማን ዲዮን በበርካታ ሀገራት የአለም ባንክ ፕሮግራሞችን መርተዋል። በአሁኑ ወቅት መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ላይ አድርገው የሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ፕሮግራሞችን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 11/2013