ከመምህር አሠምሬ ሣህሉ
ሰው በህይወት ዘመኑ ሁሉ ነገሮች ምቹና አልጋ በአልጋ ሆነውለት አይኖርም።ይወጣል፤ ይወርዳል፤ እንደወረደ ደግሞ አይቀርም ይወጣል፤ ወርዶ ለመቅረት ካልወሰነ በስተቀር።ስለዚህ፣ ለጊዜው በጊዜው ምክንያትና ሁኔታ ዝቅታ ሲገጥመው በውስጡ ባለው የመለወጥ የብርቱነት መንፈስ ለመለወጥ መዘጋጀት ይገባዋል።ለዚህም ነው፤ ሰው ካለው ብቃት ከአምስት አንድ እጁን ያህል እንኳን በአግባቡ መጠቀም ከቻለ አሁን ካለበት ሁኔታ በተሻለ መንገድ መኖር ፣ መሥራት ፣ መግባትና መውጣት ይሆንለታል፤ ሲሉ ጠበብት የሚናገሩት።አዎ፣ በውስን ዕድሜው ውስጥ፣ የሰው ልጅ ብቃት ወሰን-አልባ ነው፡፡
“አላግባብ የሆነ ብዙ ጉድለት ቢያውቅም ፣
ሰው እርጥብ ነውና መቼም ነድዶ አያልቅም፡፡”
(ገጣሚና ጸሐፊ አበበ አያሌው)
የሰው ልጅ፣ ባናደደው ነገር ነድዶ ፣ በገጠመው ፈተና ተሸንፎ የሚቀር ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናያት ዓለም አትለወጥም፤ ተለውጣም ለውጧን መገንዘብ አንችልም፤ አንጠቀምም ነበር።በሰው ልጅ ብቃት ውስጥ፣ ዓለምን የመለወጥ ድንቅ ብቃት አለና።ይህንን ብቃት የተገነዘቡ ጥቂት ሰዎችም አሁን የምናየውን ዓለም፣ የአኗኗር ስልት በማምጣት አስደናቂ ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል።ለዚህም ነው፤ የሰው ልጅ ከሚገምተው በላይ ለለውጥና ለተሻሻለ አኗኗር ምክንያት የሚሆን ከግምት በላይ የሆነ ብቃት በውስጡ እንዳለ መገንዘብ ያለበት።አዎ፣ አለው፡፡
የሰው ልጅ ይህንን ለማድረግም በቅድሚያ፣ የአስተሳሰብ አድማሱን መለወጥና እና ምርጫውን ማወቅ አለበት። ምርጫን ማወቅ አማራጮችን ለማየትና ዙሪያ ገባውን በማጤን ምንን መለወጥ እችላለሁ ብሎ እንዲያስብ ያስችለዋል።ብዙ አዳጋች የሚመስሉ ግን በቀላሉ ከሚለወጡ ነገሮች ለውጥን መጀመር ይቻላል። ይኼኛው እንኳን አይቻልም ፤ የማለት “የእጥረት መንፈስ” ውስጥህን ከወረሰው አትችልም። ለዚህም ነው፤ ይቻላል ከአይቻልም ጋር፣ ከቶም በጋራ ዕቁብ መጠጣት የማይችሉት፡፡
ፈተናውን አጥንቼ መድረስ አልችልም፤ በመኪና ተጉዤ አልዘልቀውም ፣ የእግረኛ መንገዱ ጠባብ ነው፤ መንገዱ በአዳላጭ ጭቃዎች የተሞላ ነው፤ ኮረብታማዎቹን መንገዶች መውጣት ዘበት ነው፤ ከሴትየዋ ጋር ግቢውን ስለማሳመር ማውራት አይቻልም፤ የአያቴ ማስታወሻ ስለሆነ አልነካውም ወዘተ….የሚሉ ሰበባ ሰበብ በመፍጠር ራስን ፈተናውን ከመውሰድ መከልከል፣ “የሰማይ ሰረገላ” ካልቀረበልኝ አልሄድም ብሎ ከሚሄዱበት ቦታ መቅረት፣ እግረኛው ስለሚጋፋኝ አያፈጥነኝም፤ ብሎ ከአጭር ርቀት ጉዞ መቅረት፣ ኮረብታዎቹን ባለመውጣት የመሬት አቀማመጡን ልኬት ለማወቅ አለመቻል ፣ ከሴትየዋ ጋር ተነጋግሮ ከመወሰን በፊት ለማውራት አይቻልም ብሎ የመግባቢያ በሩን ቀድሞ መዝጋት እና በአያት ማስታወሻነት ጦስ የክፍሉን አቀማመጥ ለሃያ ዓመት አለመንካት ለመለወጥና ጨርሶ ራስን ለለውጥ ለማዘጋጀት ካልወሰነ ማንነት የሚመነጭ የአስተሳሰብ ድሁርነት ነው፡፡
“እጥረት” ምንም መንገድ የለም ብሎ ሲልህ፣ “ብቃት” ደግሞ፣ አማራጮች አሉልህ፤ ዓይንህን ክፈት፤ ይልሃል።“እጥረት”፣ የያዝከው ይበቃሃል ብሎ ሲል ፤ ብቃት ደግሞ ምድር እጅግ ሰፊ እና ገና ያልተደረሰበት ማዕድ አላት፤ ይልሃል።“እጥረት” ከዚህ ሰዉ አይተባበርህም ሲልህ፣ ብቃት ደግሞ ማግባባት በር ከፋች ነውና አነጋግራቸው፤ ይልሃል።“እጥረት” የያዝካትን ይዘህ ወደቤትህ ግባ ነገን አትመነው፤ ወንድሜ ሲልህ፤ ብቃት ዛሬና መጪዎቹ ጊዜያት በውስጣቸው የያዙት በረከት ያንተ ናቸውና ነገ ሌላ ቀን መሆኑን አትርሳ፤ ይልሃል።በምርጫ ውሳኔ ወደ ተግባር መግባት ያንተና የአስተሳሰብህ ውጤት ነው።
እጥረትና አይሆንም ፣ አይሳካም ባይነት በአንደ ኛው የህይወት ጠርዝ ላይ ሆነው አትችለውም፣ አታስበው፣ አትመኘው፣ ብለው ሲያስፈራሩህ ወይም ሲያባብሉህ ፣ ብቃት ግን ይቻላል ፣ አዎ ፣ ታከናውነዋለህ አያቅትህም ፤ በህይወት ለውጥ ላይ የአንተ ድርሻ የዚህ ጸጋ ባለቤትነት እንዳይነጠቅ ተጠንቅቀህ መሥራት ነው፤ ይልሃል።
የያኔው ወጣት ሴናተር ፣ የአሁኑ ተመራጭ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ. ባይደን ለሴናተርነት በተመረጠ (29 ዓመቱ ነበረ፤ ያኔ) በአንድ ወር ውስጥ ባለቤቱንና ሴት ልጁን በመኪና አደጋ፣ በሞት ሲያጣና ሁለት ልጆቹ ደግሞ በአደጋው በሞትና በህይወት መካከል ሆነው ሲተርፉ ፣ ከድንጋጤው ብዛት ራሱን ለማጥፋት ወስኖ ነበረ። ይሁንናም መጪዎቹን ጊዜያት አጨልሞ እንዳያይ፣ በእርሱ መሰል አደጋ ውስጥ ያለፉ መካሮች ልምዳቸውን አካፍለውት ነው፤ ወደቀልቡ የተመለሰውና ለዛሬው ፕሬዚዳንትነት የበቃው። ዓለም ካለፈው የተሻለ አማራጭ ከፊትህ እንዳላት ከቶም አትርሣ እንጂ፤ በተመታህበት ስፍራ ተቸክለህ አትቅር፤ ትችላለህ፡፡
አንድን ኃላፊነት ልትረከብ ስትል፣ ሥራውን አትችለውም ኃላፊነቱ ከባድ ነው፤ ወንድሜ፣ ጫንቃህ እንዲወልቅ ካልፈለግህ ሥፍራውን ባትቀበል ይሻልሃል፤ ማለት ብቻ ሳይሆን አንተ ባለሙያ እንጂ፣ ለመሪነት አልተፈጠርክም ብሎ ልትወስድ የተዘጋጀኸውን ኃላፊነት አለቅጥ አክብዶ፣ ኃላፊነቱን የዳበሳ ወንበር ሊያደርግብህ የሚቃጣው ሰው ብዙ ነው።
በተለይ ልታማክረው አስበህ፣ በሦስተኛ ወገን በኩል ምክሩን ልትጠይቀው ያሰብከው ሰው፣ ደስታህንና ሞራልህን ለመስረቅ የማያመነታ ሆኖ ስታገኘው ተሸናፊው አንተ ከአሸናፊው አንተ ጋር ባልተፈለገ ጦርነት ውስጥ እንድትገቡ ያደርግሃል።ስለዚህ እየተሳሳትኩ እማራለሁ፤ እየወደቅሁ እነሳለሁ፤ እየተፍገመገምኩ እራመዳለሁ እንጂ፤ አልቆምም፣ እዘረጋለሁ፤ ማለት ካልቻልክ የአሉታዊ ሐሳብ መካሮች መቀለጃ ነው፤ የምትሆነው፤ ተጠንቀቅ፡፡
ራሳቸው እንደሚችሉት እንኳን እየተገነዘቡ፣ አንተ እንደማትችለው ሲነግሩህ አፋቸውን ያዝ አያደርጋቸውም።ስለዚህ ብቃትህን ለማውጣት የሌሎች ምከር ሳይሆን ያንተ የአስተሳሰብ ቅኝት ለውጥ ፊታውራሪውን ቦታ መያዝ ይገባዋል።ካለበለዚያ ፡-
ከፊት እንደምትቆም ክፉ ያወቀ ለታ፤
በምክር አሳብቦ ልክ እንደ ውለታ፤
አትችልም ይልሃል መቻልክን ሊመታ። (ያልታተመ)
በእጥረትና በአይሆንም መንደር ጎጆህን የቀለስክ ከሆነ አስተሳሰብህ መመጠኑ ብቻ ሳይሆን መገለጫ የሚሆኑ ባህሪያት ታሳድጋለህ፡፡
• ቁጥብና ስጉ ትሆናለህ።ይህም ማለት አዳዲስ አጋጣሚዎችን እንዳታጤን ያድርግሃል፤ በርህን ዘግተህ በመቀመጥ ትወሰናለህ።ተጠራጣሪና ምን በወጣኝ፤ ቢቀርብኝስ እንድትል ትሆናለህ፡፡
• በጣም ቀላል ኗሪ ትሆናለህ።ምክንያቱም ሌላ ተጨማሪ ነገር አትሠራም ወይም ባለህ ጠግበህ ትረካለህ ፤ ወደ የትም አቅጣጫ አታማትርምና እንደሁኔታው ነዋሪ ትሆናለህ፡፡
• ምቹና የተለመደ ኑሮ ትኖራለህ። በለመድ ከውና በምትወደው ለውጥ አልባ ሰፈር ግን በምቾት ትኖራለህ፤ ብዙ ሰዎች ያለቻቸው ጥቂት ነገር እንዳትወሰድባቸው ስለሚሰጉ ያችኑ በማስጠበቅ ለመኖር እንጂ ትንሽም ብትሆን መስዋዕትነት የሚያስከፍል ነገር ለማድረግ አይቃጡም። ወንድሜ፣ “ጎመን በጤና” ይሉሃል፤ እንጂ በኮሶ እሸት መንገድ የማር እሸትን መብላት አይፈልጉም። የተሻለ ማየት ፤ ማሰብ፣ መልበስና አልፎ ሌሎችን ማልበስ መሞከር ወይም ማደግ ለእነርሱ ዕብደት ነው። ስለዚህ ከአባቱ በወሰደው ፍራሽና ከአያቱ የተቀበለውን ጋቢ በመልበስ መኩራት ይቀልለዋል ፤ እንጂ የኔ የሚለው የተለየ መንገድ አይሠራም፡፡
• አሳሳችነቱን አይገነዝብም (አትገነዘብም)። ምክንያቱም ሌላ ለማሰብ አለመሞከርን ከጨዋነትና በልክ ከመኖር ጋር በማያያዝ ከእውነታው ጋር ይጋጫል እንጂ ወጣ ለማለት አይደፍርም። እንዲያውም በዚህ ድፍረት በተሞላበት መንገድ የሚኖሩ የአስተሳሰብ ለውጥ ያላቸውን ሰዎች ለማንኳሰስ እና ለማሳነስ ወደኋላ አይልም። “የትም ላትደርስ አትንፈራገጥ” ፤ “ይቺ እንጣጥ እንጣጥ፤ ወርዶ ለመፈጥፈጥ”ሊልህ ይችላል፡፡
• ይህ የብዙዎች መንደርም ነው።የብዙ ሰዎች አስተሳሰብ በዚህ የተቃኘ በመሆኑና “ጎመን በጤና” ባዩ ስለሚበዛ ጉርብትናና ጓደኝነቱም በርካታ ነው።ስለዚህ ወንድሜ፣ያለኝ ይበቃኛል፤ ኑሮ ምን-አለኝና እጨነቃለሁ፤ በሚል እምነት እዚሁ መከራረምን ይመርጣል ፤ የእጥረትና የአይቻልም ሰፈር ኗሪ ስትሆን ውጤቱ በመምሰልና ማስመሰል የተሞላ አህዛባዊ ነው፡፡ በሌላ በኩል የወዲያኛው የይቻላል፣ ሰፈር ነዋሪ ስትሆን ደግሞ አስተሳሰብህ የተለወጠ፣ አደራረግህ የላቀና ብቃትህን የተገነዘብክ ስለምትሆን ልዩና ብርቱ ፣ ሰው ነህ።በአንተ ሰፈር እንቅልፍ የለም፣ ቢኖርም እንቅልፍህ በሚያሳድግ ህልም የታጀበ እንጂ ቅዠትና ፍርሐት የለበትም። ስለዚህ ጥቂት መገለጫ ባህሪያቱን ላካፍላችሁ፡፡
• የድንቅ ስሜት ባለቤት ነህ።አዲስ ነገርን የማየት የመሞከርና የመሥራት ፍላጎትና እምነት ስላለህ እየሞከርክ ስትወድቅና ስትነሳ የሚሰማህ ደስታ ድንቅ ነው፡፡
• አዳጊና የሚሻሻል ነው።የይቻላል ስሜትና አስተሳሰብ ሌሎች መቻሎችንና በረከቶችን ወዳንተ ስለሚያመጣ ምንጊዜም ለመሞከርና ለመሥራት ዝግጁ ነህ። የበለጠ ውጤት ስትቀዳጅ የበለጠ ብቃትህ ይወጣልም፡፡
• ተግዳሮት አለብህ። አዳዲስ መንገዶችና መሹዋ ለኪያዎች በቀላሉ አይታለፉም ተግዳሮት አሉባቸውና። ይህንም ለመጋፈጥ በተዘጋጀህ ቁጥር ወደ አሸናፊነት ለመገስገስ አቅም ይሆኑሃል፡፡
• ሽልማትም አለህ። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የይቻላል ስሜት የመቻልን ውጤት ስለሚያመጣ ሽልማትህ የእቅድህን ግብ ማሳካት ነው፤ ይህም ስኬት ሽልማትህ ነው።በዚህም አንድን ድል የቀመሰ ሰው፣ ከድል ወደ ድል ለመጓዝ ይቀናል እንጂ ባገኘው ድል አይቆምም፡፡
ይህንን ስልም አይቻልምና አይሆንም መንገዱ ጠባብ ነው፤ የምንላቸው መልሶች ሁሉ ልክ አይደሉም፤ አዎንታ ያላቸው አስተሳሰቦችና ምላሾች ሁሉ ደግሞ ተገቢ ናቸው እያልኩኝ አይደለም።“አይቻልም” የሚለው መልስ ግን ፤ ብዙ ጊዜ አማራጭ እንዳትፈልግ፣ ባለህበት እንድትቸከልና ውጤትህ እንዳያምር ፣ ጥረትህ እንዳይሰምር ያደርጋል፤ ማለቴ እንጂ፡፡
ሆኖም በ”ይቻላል” መንፈስ እና አስተሳሰብ የተቃኙ ሰዎች አዎንታዊነት ያረሰረሳቸው ስለሆኑ፣ ወደፊት መጓዝ ይቀናቸዋል።የመጀመሪያው መንገድ አልተሳካምና ሌላ መንገድ የለም ብለው አይቆሙም ፤ ይጥራሉ እንደገናም መንገድ ይፈልጋሉ፤ ይጥራሉ በአዲስ መንገድም ይነሳሉ።ታዲያ እነዚህን ብርቱና ፣ የአሸናፊነት ስሜት ያላቸው ሰዎች መምሰል ይሻላል ወይስ በነበረው ታስራችሁ፤ ባላችሁበት ቆማችሁ፤ ህይወትን አጨልማችሁ፤ ኑሮን በመፍገምገም መቀጠል ይሻላችኋል ? እንደ እኔ እንደ እኔ ሁለተኛውን መምረጥ ህይወትን መምረጥ ነው፡፡
አንድ ወዳጄ ሲነግረኝ ጡረታ ከወጣሁ በኋላ ራሴን በመጻሕፍት አጥሬ መቀመጥ ሥራዬ ሆነና ሰለቸኝ። በኋላ ላይ ድንገት አንድ ቀን ፣ የጥንት የትምህርት ቤት ጓደኛዬ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሳደግኋቸው ልምዶች አሉኝ ብሎ፤ በቴሌቪዥን መስኮት ሲናገር ሰማሁት።
እውነት ነው፤ ከ60 ዓመቱ በኋላ ጊታር መጫወት ተለማምዷል ፤ ድሮ ይሞክር የነበረውን የመሳል ስሜቱን ቀስቅሶ ሥዕል መሳል ጀምሯል፤ ያነበባቸውን መጻሕፍት ዳሰሳ በጋዜጣ ላይ ማውጣት መጀመሩንና አጫጭር ድርሰቶችን እግረ-መንገዱን መጻፍ መጀመሩን አወጋ ፤ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ አበቦችን በማሳደግ ለጎረቤትና የመንደሩ ሰዎች እየሰጠና እየሸጠም መሆኑን ሲናገር ለራሴ ቃል የገባሁት ነገር ወንድሜና አብሯደጌ ከጀመራቸው ወይም ከተናገራቸው ነገሮች ከሥዕል ሥራው በስተቀር የማልችለው ምንም ነገር እንደሌለና ሌሎች ስጦታዎቼን በማውጣት ለመጠቀም እንደምችል ለራሴ ነገርኩት ፤ በማግስቱም ወረቀትና ብእሬን አገናኘሁ ይላል።ይህ ድንቅ የይቻላል ስሜት እንደገና የማበብ ፣ እንደገና የማፍራትና እንደገና በህይወት የመኩራት ዝንባሌ አካል ነው።ስለዚህም አዎንታዊ ስሜት የአሸናፊነት በር የመክፈቻ ቁልፍ ነው፡፡
ያስቸገራችሁን እና ያቃታችሁን ነገር በር ዘግታችሁበት ከመቀመጥ ይልቅ፣ እንደገና ለመሞከር መጣርና መቻል አዎንታዊነት ነው።ምድር ለሰው ልጅ የተትረፈረፈ ነገር አላት ብሎ የሚያምንና ያንን የህይወት በር ለማየት እና በመክፈት ለመካፈል የሚተጋ ሰው፣ በህይወት ከፍተኛ እምነት አለው።ስለዚህም ሰዎች ከሚገምቱት በላይ ህይወት በጓዳዋ ለእኔ ያስቀመጠችው ነገር ይበልጣል፤ ለማለት ዝግጁዎች ሁኑ፡፡
እምነት ደግሞ ባህሪን ይቀርጻል፤ ስለዚህም እኒህን መሰል ሰዎች የሚያዩ ሌሎች ሰዎች፣ የባህሪ ምስክርነት ለመስጠት አያመነቱም። ሲመሰክሩላቸውም፣ የማያመነቱ ቆራጦችና ሠርተው የማይደክማቸው ብርቱዎች ናቸው፤ አይወላውሉም ይሏቸዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ባህሪ ያላቸው ልበ-ብርቱ ሰዎች ሩቅ ዓላሚ ብቻ ሳይሆኑ ሩቃ አዳሪዎችም ናቸው። የጀመሩት መልካም ነገር፣ ማለቅ አለማለቁ ብቻ አይደለም የሚያሳስባቸው ጀምረውት ቢያልፉ እንኳን ተከታይ እንዳላቸው ራዕያቸው እንደማይ ከስም ነው፤ የሚረዱት። ስለዚህ ይጀምራሉ፤ በጽናት ይቀጥላሉ፤ ቀጥለውም እንደገና ወደግባቸው ይገስግሳሉ። ለእነርሱ ህመም የሚሆነው ወደ ህልማቸው ለመድረስ የሚያደርጉትን ጉዞ አለመጀ መራቸው ነው፡፡
ለዚህ ነው፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በ”የቴዎ ድሮስ ስንብት ከመቅደላ” ግጥማቸው ላይ፡-
“…. በውጣ ውረድ ካለፍኩባቸው ፤ ከመከራው አልፎ ትዝ የሚለኝ፤
ከሞከርኳቸው ነገሮች ይልቅ፤ ያልሞከርኳቸው ነው የሚቆጩኝ፡፡” ይላል።ልበ-ብርቱዎች እንዲህ ናቸው፤ ልበ- ብርሃኖች የሚያዩት ውስጣቸውን ነው፤ ልበ-ቀናዎች የሚመለከቱት ግለ-ድካ ማቸውንና እደርስበታለሁ፤ ወይም እደርስበት ነበር፤ የሚሉትን ራዕይ ነው፤ እንደ መይሣው ካሣ።ሳያሸንፉት የቀረውን ድካማቸውንና ፣ አዳክሞ ወደአልፈለጉት አዘቅት ውስጥ የከተታቸውን ስንፍና ያዩና ውሳኔ ይወስናሉ።ከዚህም ይነሣሉ፤ እንደ ንስርም ይበርራሉ።ዓለም ለእነርሱ በማጀቷ ፣ ምድር ለእነርሱ በጓዳ ጎድጓዳዋ ያስቀመጠችው ሰፊ ዕድል እንዳለ ስለሚያውቁ ወደጥረታቸው ይገባሉ እንጂ፤ ሰንፈው አይቀሩም።ብቃትን መገንዘብ የአሸናፊነት በር መሆኑን ጠንቅቀው ይገነዘባሉ። አበቃሁ!!
አዲስ ዘመን ጥር 10/2013