በአገራችን የፊልም ጥበብ ዘለግ ያለ ታሪክ ቢኖረውም ለመነገር የሚበቃው ግን ብዙም አይደለም። በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የነበረው ጅማሮ፤ ከዛ ሲሻገር በፊልም ሙያ እውቅናም ብቃትም ባላቸው በፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ የተሠሩ ቀዳሚ ሥራዎች፤ አለፍ ሲል በኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ ያለው የሆሊውድ ተጽዕኖዎች ናቸው ዐብይ ጉዳይ ሆነው ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሱት። የዚህ ነገር ምክንያት በቋሚነት ተሠርቶ የሚቀጠልና ባለሙያዎች እርስ በእስር የሚቀባበሉበት ስርዓት ባለመኖሩ ነው።
ነገራችን አሠራሩንና የፊልም ባለሙያውን ለመኮነን ሳይሆን ያሉትን ጠቃቅሰን ችግሩ እንዴት ይስተካከላል? ወደፊትስ እንዴት ማስቀጠል ይቻላል? የሚለው ጥያቄ ላይ ነው። ለዚህም ደግሞ ለዛሬ ዓመታዊ የፊልም ፌስቲቫሎችን እናነሳለን። በአገራችን የፊልም ፌስቲቫል እድሜ ከ15 ዓመታት የዘለለ አይደለምና መለስ ብለን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ልምድ፤ ከተለያዩ ጥናታዊ ወረቀቶችና ድረገጽ ያገኘነውን ጠቅሰን እንመለሳለን።
የፊልም ፌስቲቫል መቼ ተጀመረ?
የፊልም ፌስቲቫል በርከት ያሉ የተለያዩ ፊልሞች ለተከታታይ ቀናት በተቀናጀ መርሃ ግብርና በተለያዩ ቦታዎች ለእይታ የሚቀርብበት የክዋኔ ዓይነት ነው። እነዚህ ፌስቲቫሎች እንደየዓላማቸው የሚያቀርቧቸው ፊልሞችም ይለያያሉ። ለምሳሌ የዘጋቢ ፊልም፣ የመደበኛ ፊልም፣ የአጫጭር ፊልሞች ወዘተ እያለ በዘውግ እየተከፋፈሉ ፌስቲቫሎቹ ይካሄዳሉ።
በዓለማችን የመጀመሪያው ፊልም ፌስቲቫል የተካሄደው በጣሊያኗ ቬነስ ከተማ፤ በጣሊያን ፋሽስት ዘመን፤ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1932 ነበር። አሁንም በዓለማችን ያለ በእድሜ ትልቁ ፊልም ፌስቲቫል ይህ ነው። ፌስቲቫሉ በዓለማችን የመጀመሪያው ፊልም ለእይታ ከቀረበ አርባ ዓመታት በኋላ የተካሄደ ሲሆን፤ በዚህም ላይ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ በርካታ ፊልሞች ለእይታ ቀርበዋል።
ይህ ፌስቲቫል የመጀመሪያ እንደመሆኑ ከወቀሳ አልዳነም ነበር። እንዳልነው ከተለያዩ አገራት ፊልሞች የተውጣጡ ቢሆንም የጣሊያንና የጀርመን ፊልሞች የበለጠውን ቦታ ይዘዋል የሚሉ ቅሬታዎች ተነስተውበታል። ከዛም ውጪ በፌስቲቫሉ ማብቂያ ላይ ሽልማት ሊያገኝ የሚገባው ፊልም ባለማግኘቱም ብዙ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ከዚህ በኋላ ነው ሌሎች የፊልም ፌስቲቫሎችም በተለያዩ አገራት የተጀመሩት።
ዝነኞቹ ፊልም ፌስቲቫሎች
በዓለማችን በቀዳሚነት ሦስት ታላቅ የሚባሉ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች አሉ። እነርሱንም «Big Three» ይሏቸዋል። እነዚህም የመጀመሪያውን የቬነስ ፊልም ፌስቲቫልን ጨምሮ ካንስ እንዲሁም በርሊን ዓለምአቀፍ የፊልም ፌስቲቫል የተባሉ ናቸው።
የካንስ ፊልም ፌስቲቫል በፈረንሳይ ካንስ ከተማ የሚካሄድና በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1946 የተጀመረ ነው። ፌስቲቫሉ በየዓመቱ መጀመሪያ ላይ ለሦስት ተከታታይ ሳምንታት እንዲካሄድ እቅድ የተያዘለት ነበር። በዚህም ፌስቲቫል ሁሉም ዓይነት ዘውጎች ሲካተቱ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሁሉንም አገራት ፊልሞች የሚያሳትፍ ነው።
በዚህ ፌስቲቫል ለመጀመሪያ ጊዜ 21 አገራት ተሳትፈዋል። በመካከል የተሳታፊ ቁጥር ሲቀንስ፤ ደግሞ ሲቋረጥ፤ በፊልም ባለሙያዎች ጥረትና ጥቅሙን በተረዱት ምክንያት ግን እስከአሁን ቀጥሎ ይገኛል። በዚህም ዓለምአቀፍ የአጫጭር ፊልሞች ውድድር የሚካሄድበትና በፊልሙ ዘርፍ የቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ በትኩረት የሚሠራበት ሆነ።
በርሊን ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ምንጩ ከጀርመን ነው። ይህም በበርሊን ከተማ የሚካሄድ ሲሆን በ1951 ተጀምሯል። በዓለማችን ካሉ ፌስቲቫሎች ሁሉ ብዙ ተሳታፊዎችን የሚቀበለው ይህ ፌስቲቫል እንደሆነ ይነገራል። በየዓመቱ እስከ አምስት መቶ ሺህ የሚደርሱ ባለሙያዎች ለተሳትፎ ጥያቄ እንደሚያቀርቡም ይገለጻል። በድምሩ አራት መቶ የሚደርሱ ፊልሞች በፌስቲቫሉ ለእይታ የሚቀርቡ ሲሆን ለውድድር እጩ የሚሆኑት ግን ሃያዎቹ ናቸው።
እነዚህ ፊልም ፌስቲቫሎች በቆይታቸው ውድድሮችና የሽልማት መርሃ ግብሩን ጨምሮ የውይይትና ምክክር መድረኮች ያዘጋጃሉ። አዳዲስ ሃሳብ የያዙ ፊልሞች እንዲሁም ልጆችና ወጣቶች ላይ ያተኮሩ ሥራዎች ለብቻና በትኩረት እንዲታዩ የሚደረጉባቸው አሠራርም አላቸው።
እነዚህ ሦስት ታላላቅ የዓለማችን የፊልም ፌስቲቫሎች ፍጹም ናቸው የሚባሉ አይደሉም። በየጊዜውም የተለያዩ ጭቅጭቆችና አለመግባባቶች ይሰማባቸዋል። ይሁንና ሁሉም የቆሙት ለአንድ ዓላማ እንደመሆኑ ፌስቲቫሎቹ እየገነኑ እንጂ ከደረጃቸው ዝቅ እያሉ አልሄዱም። የፊልም ሙያ ማኅበራትና ባለሙያዎችም ለፌስቲቫሎቹ መሳካትና ለዘርፉ ለውጥ ይተጋሉ። በእርግጥም የደረሱበት የቴክኖሎጂ እድገት ደረጃና የብዙ ዓመታት ልምድም ሳያግዛቸው አይቀርም።
ከእነዚህ ፌስቲቫሎች ቀጥሎ ስሙ የሚነሳውና በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1935 የተጀመረው የሞስኮ ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ሲሆን፤ ከ1959 ወዲህ እንደ አጀማመሩ ያልቀጠለ በመሆኑ እንጂ ከቬነሱ ቀጥሎ እድሜ ጠገብ የሚባል ፌስቲቫል ነበር።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሻግሮ ደግሞ በርካታ የፊልም ፌስቲቫሎች በየአገራቱ ተፈጥረዋል። እነዚህም በዓለም ላይ ያሉ የፊልም አፍቃሪያን ሁሉ ሊሳተፉባቸው የሚጓጉና ቀናቸውን የሚጠብቁላቸው ናቸው። ከእነዚህ መካከል በኢንግሊዝ ሬይንዳንስ ፊልም ፌስቲቫል እና ኢደንበርግ ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫል፤ በአውስትራሊያ ሜልቦርን እንዲሁም ሲድኒ ፊልም ፌስቲቫሎች፤ በአሜሪካ የሳን ፍራንሲስኮ ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ፌስቲቫሎች አገራቱንና የፊልም ዘርፋቸውን ምን ጠቀሙ የተባለ እንደሆነ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የተለያዩ አገራት ፊልሞች እንዲመለከቱ እድል መፍጠሩ ነው። በተጨማሪ የቼክ ካርሎቪ ቫሪ፣ የስዊዘርላንድ ሎካርኖ፣ የጀርመኑ በርሊን፣ የህንድ እንዲሁም የስፔን ሳን ሰባስትያን ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎችን መጥቀስ ይቻላል።
በእኛዋ አኅጉር አፍሪካ «አፍሪካ ኢን ሞሽን» የተሰኘ ዓመታዊ የፊልም ፌስቲቫል አለ። ይህም በስኮትላንድ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከተጀመረ 13ዓመታትን አካባቢ ያስቆጠረ ነው። ይህ የፊልም ፌስቲቫል አፍሪካን በፊልሞች በኩል ለስኮትላንድ ሕዝብ እያስተዋወቀም እንደሆነ ይነገራል። ምንም እንኳ የሚካሄደው በስኮትላንድ ቀን መቁጠሪያ መሠረት ቢሆንም፤ በአፍሪካ ቀዳሚ የሚባለው ይህ የፊልም ፌስቲቫል ነው።
ፊልም ፌስቲቫል ለምን?
ከላይ በጥቂቱ የጠቃቀስናቸው ፊልም ፌስቲቫሎች እንዳሉ ሆነው፤ በዓለማችን እጅግ በርካታ የፊልም ፌስቲቫሎች አሉ። በአገራችን እንኳ ጥሩ ቢባል በቅርበት የምናውቃቸውን የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል፤ አዲስ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል እንዲሁም «ከለርስ ኦፍ ናይል» የተባለውና ለጥቂት ዓመታት የተካሄደውን ፊልም ፌስቲቫልን ልናስታውስ እንችላለን። አሁን ላይ እነዚህ ፌስቲቫሎች ያሉበት ሁኔታ ይቆየንና፤ ፌስቲቫል መኖሩ ለፊልሙ ዘርፍ ምኑ ነው ስንል እንጠይቅ።
በቀደመው ጊዜ የፊልም ፌስቲቫሎች በፊልሙ ዘርፍ ገንዘብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የፊልም አሰራጮችን ለመሳብ የሚካሄድ እንደሆነ ይታሰብ ነበር። ጀማሪዎቹ የፊልም ሰዎችም አንድም ፌስቲቫሎችን ለዚህ ዓላማ ይጠቀሟቸው ነበር። አሁን ላይ ደግሞ ፊልሞች አንዴ ከተሠሩ በኋላ በየሰው እጅ በቀላሉ የሚገኙ በመሆናቸው፤ የፊልም ፌስቲቫሎች ጥቅም ከዚህ የላቀ እንዲሆን ይጠበቃል።
በፊልም ፌስቲቫል ሁለት ዓይነት ተጠቃሚዎች አሉ፤ እነርሱም ፊልም ተመልካች እና በዘርፉ ተሳትፎ የሚያደርጉ ባለሙያዎች ናቸው። ለፊልም ባለሙያ በፊልም ፌስቲቫል መሳተፍ አራት ጥቅሞችን እንደሚሰጥ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አንደኛው ደክመው ለሠሩት ፊልም ጥሩ ገበያ ማግኘት ነው። እንኳን በአውሮፓ ደረጃ በእኛም አገር ካየን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፌስቲቫሎች መሳተፍ የቻሉ ፊልሞች ዓለምን እየዞሩ ለእይታ ሲቀርቡ ታዝበናል።
ሌላው ውድድሩና ሽልማቱ ነው። ብቃት ባላቸውና ሙያውን ጠንቅቀው በሚያውቁ ዳኞች ፊልሞች ተወዳድረው ይሸለማሉ። ይህ ለተሸላሚዎች ትልቅ እድል ነው፤ የሚወዳደሩት ከብዙዎች ጋር በመሆኑ ቀጥሎ የሚከፈትላቸው መንገድ በቀላል አይተመንም። ከዚህ ባለፈ በፊልሞች ላይ የሌሎችን እይታና አስተያየት ማግኘት ለበለጠ ሥራ ያተጋልና፤ ችግሮችንም ቀርፎ ለመገኘት ፌስቲቫሎች ላይ የሚሳተፉ ፊልሞች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ከዚሁ በተጓዳኝ ለውይይት እንዲሁም ለመጠያየቅና ምላሾችን ለማግኘት ፌስቲቫሎች ተመራጭ ናቸው።
ብዙ ልምድና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ስለሚሳተፉ የልምድ ልውውጡም ብዙ የሚገኝበት ነው። ይህን የምንለው እንግዲህ ጠንካራና ጽኑ ስለሆኑ የፊልም ፌስቲቫሎች ስናነሳ ነው። ከአንዱ ወደ ሌላው እነዚህ ወሳኝ ጥቅሞች ይቀንሳሉ ወይም ከፍ ሊሉ ይችላሉ። ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ታድያ የፊልም ጥበብን ማድነቅና መመልከትን ማካተታቸው ነው። ከዚህ ባለፈ ለባህል ልውውጥና ለአገራት እርስ በእርስ መተዋወቅ ወሳኝ ሚና አለው።
ፌስቲቫሎች የተለያዩ አገራትን ፊልሞች ያሳትፋሉና በፊልም ባለሙያው ተከሽነው የተሠሩ የአገራት ታሪክ፣ ማንነትና እውነቶች ቁልጭ ብለው ይታያሉ። መነጋገሪያ ይሆናሉ፤ የዓለምንም ትኩረት ይስባሉ። ይህ ለአገራት የእርስ በእርስ ትስስር አንዱ መንገድ ነው። ለፊልም ባለሙያዎችም አዲስ እይታንና አዲስ መቼት ያመላክታል።
በጥቅሉ ፊልም ፌስቲቫሎች እንደተሳታፊው ሃሳብና ዓላማ በርካታ ጥቅሞች አሉት። በነገራችን ላይ ከፊልም ፌስቲቫሎች ከፊልሙ ጥበብ ጥቅም ባለፈ ገቢ ለማሰባሰብ፣ በአንድ ጉዳይ ላይ አገራዊ ድምጽ ለማሰማት ወዘተ ይከናወናሉ።
በአገራችን የፊልም ፌስቲቫሎች ሂደትና እድገት ምን ይመስላል? መቼ ተጀመረ? አሁን ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ተናፋቂ ፊልም ፌስቲቫለሎች አሉን ወይ? ለፌስቲቫሎችስ ያለው አመለካከት እንዴት ይታያል? ወዘተ የሚለው ላይ በቀጣይ ሳምንት የአዲስ ዘመን እለተ ሰንበት ጋዜጣ እትም በስፋት የምንመለስበት ይሆናል። ከእነዚህ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች የምናገኘው አንድ ትልቅ ቁምነገር ግን የፊልም ፌስቲቫል «በአንድ አፍ!» ብለው ሊይዙት የሚገባ መሆኑን ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር26/2011
ሊድያ ተስፋዬ