አስመረት ብሰራት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅርንጫፍ የሆነው የተባበሩት መንግስታት የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና የሴቶች ማጎልበት (ዩኤን ውሜን) የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ሰባት ሴት ተመራማሪዎች መካከል ኢትዮጵያዊት ተመራማሪ መምረጡን በአንድ ድረ ገፅ ላይ ተመለከትኩ። ስለእኚህ የድንቅ ብቃት ባለቤት መረጃዎችን ሳገላበጥ ቢቢሲ የፃፈውን መረጃ አገኘሁ። ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደሚሆን አድርገን አቅርበነዋል መልካም ንባብ።
የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰባት ስመጥር ተመራማሪዎች መካከል ኢትዮጵያዊቷ ዶክተር ሰገነት ቀለሙ ይገኙበታል። ዶክተር ሰገነት ተቀማጭነቱ ናይሮቢ ኬንያ የሆነው የነፍሣት አካላት እና አካባቢ ጥናት ዓለም አቀፍ ማዕከል (ኢሲፔ) ዋና ዳይሬክተር ናቸው። ከክብር ዶክተሬት ጀምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኙት እኚህ ሰው ህይወት ባጭሩ እንመልከት።
ዶክተር ሰገነት ቀለሙ ተወልደው ያደጉት የጎጃሟ ፍኖተ ሰላም ከተማ ነው። ፍኖተ ሰላም ያኔ በጣም ትንሽ የገጠር መንደር ነበረች። መብራት፣ የቧንቧ ውሃ እንዲሁም ምንም አይነት መሰረተ ልማት አልነበረም። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱባት መንደር የመማር እድል ቢያገኙም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአካባቢው ስላልነበረ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመከታተል ደብረ ማርቆስ ሄደው እንደተማሩ መረጃው ይጠቁማል።
በወቅቱ ከቤተሰብ ማንም አብሯቸው ያልነበረ ቢሆንም አላማው ትምህርት ነውና ብቸኝነትን ተጋፍጦ መማር የግድ ሆኗል። ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ወላጆቼ በእኔ ላይ እምነት ነበራቸው። የትም ብሄድ ራሴን ተንከባክቤ እንደማስተዳደር ያውቃሉ›› የሚሉት ዶክተሯ ቤተሰቦቻቸው በእርሳቸው ላይ ያላቸውን መተማመን በኩራት ያስታውሳሉ።
ዶክተሯ የልጅነት ጊዜያቸውን እንጨት ለቅመው፣ እህል በእጃቸው እየፈጩ፣ ብቅል እያበቀሉ፣ ደረቆት ለጠላ አዘጋጅተው ቤተሰቦቻቸውን እያገዙ ይማሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ‹‹ያኔ የፊደል ዘር አያለሁ ብሎ የትምህርት ቤት ደጃፍ የረገጠ ፈተና የሚሆንበት ደብተር፣ እስክሪብቶ፣ እርሳስ ማሟላት ነው።
ትምህርት ቤቱም ቢሆን በቁሰቁስ እና በመጻህፍት የተሟላ አይደለም›› የሚሉት ዶክተር ሰገነት ማጣት ልምድ ሆኗቸው ዛሬም በቢሮዋቸው እርሳስና እስክርቢቶ እንዲሰበሰቡ አድርጓቸዋል። በልጅነታቸው አስቸጋሪ እንደነበሩ የሚናገሩት ዶክተር ሰገነት፤ ዛፍ ላይ መውጣት፣ አህያ መጋለብ፣ ሴት አትሰራውም የተባለውን በሙሉ ለመስራት ይሞክሩ እንደነበር ይናገራሉ።
በልጅነታቸው ቤታቸው እህቶቻቸውን ለማጨት ሽማግሌ ሲላክ ለእሳቸው የመጣ አንድም ጠያቂ አለመኖሩን በትዝታ ወደኋላ ተመልሰው የሚናገሩት ዶክተሯ፤ ምክንያቱ ደግሞ ማህበረሰቡ ሴት ልጅ መሆን አለባት ከሚለው ስነምግባር ውጭ በማሳየታቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ይህ ጥሩ እድልም እንደሌሎቹ በልጅነታቸው ሳይዳሩ በትምህርታቸው ገፈተው ከቤተሰቦቻቸውም ባሻገር የሀገር መኩሪያ ሊሆኑ ችለዋል። የዶክተር ሰገነት ቤተሰቦች ማንበብ እና መፃፍ ባይችሉም በትምህርት ያምኑ ነበር። ስለዚህ ልጆቻቸውን ባጠቃላይ አስተምረዋል።
‹‹እህት እና ወንድሞቼ በአጠቃላይ ሰባታችንም ትምህርት ቤት ሄደናል።” የሚሉት ዶክተሯ እህቶቻቸው ቀደም ብለው ያገቡ ቢሆንም ከፊደል የለያቸው አንዳችም ሀይል እንዳልነበረ ይናገራሉ።
ዶክተር ሰገነት ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ውጤት የመጣላቸው ጊዜ ቤታቸው በደስታ ገላጮች ተሞልቶ እንደነበር ያስታውሳሉ። ጎረቤቶቻቸው ጠላ፣ አረቄ፣ ምግብ እየያዙ መጥተው ቤተሰቦቻቸውን ‹እንኳን ደስ አላችሁ› እያሉ ቀኑን ሙሉ እንዳሳለፉ ይናገራሉ። በደስታ የተሸኙት ዶክተር ሰገነት ከአንዲት ገጠር መንደር ወጥተው ሰፊ ወደ ሆነችው አዲስ አበባ ሲመጡ ድንግርግር ብሏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
‹‹መፀዳጃ ቤት ሜዳ ላይ ነው የለመድነው እዛ ደግሞ ቤት ውስጥ ነው፤ እንዴት ውሃ እንደሚለቀቅ አላውቅም። ሻወር ቤት ውስጥ ነው የምንታጠበው፤ …ፍኖተ ሰላም ሆነን ወንዝ ውስጥ ሄደን ነው ገላችንን እንታጠብ የነበረው። ትልቅ ልዩነት ነው›› የሚሉት ዶክተር ሰገነት፤ ቴሌቪዥን እና ስልክ አጠቃቀምም ሌላ እንግዳ ነገር ሆኖባቸው እንደነበር በትዝታ ወደኋላ ተመልሰው ይናገራሉ።
ዶክተር ሰገነት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለሁለተኛ ዲግሪ አሜሪካ ሄዱ። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከመጨረሳቸው በፊት ለሶስተኛ ዲግሪ የነፃ ትምህርት እድል አገኙ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ለማግኘት ከወላጆቻቸው በግድ የተነጠሉት ዶክተር ሰገነት ዲግሪ በዲግሪ ላይ መጥቶ የምሁራን ቁንጮ እንደሚሆኑ ማን ልብ ይል ነበር? ብቻ ባጠቃላይ ሁለተኛው ዲግሪ ሳይጠናቀቅ ነበር ብዙ ቦታ የስራ በር የተከፈተላቸው። ያም ያም እኔጋ እኔጋ ቢላቸውም ቅሉ ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ ቀዳሚ ምርጫቸው ሆነና ወደዛ አቀኑ።
ቤተሰቦቻቸው በተለይም ወላጅ አባታቸው የህክምና ዶክተር እንድሆን ይፈልጉ እንደነበር የሚያስታወሱት ዶክተር ሰገነት፤ ‹‹ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ እርሻ ልማር እንደሆነ የሰሙ ጊዜ አንቺ በቃ ይሄ ውንብድናሽ አሁንም አለቀቀሽ ‹ገበሬ ለመሆን ዲግሪ ያስፈልግሻል?››› ብለዋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በኋላ ግን ስለስራው እና ስኬታቸው እየተረዱ ሲመጡ የኩራታቸው ምንጭ የአይን ማረፊያ ልጅ ሆኑላቸው።
ፈተና የሕይወት አንዱ ክፍል ነው ብለው የሚያምኑት ዶክተር ሰገነት፤ ፈተናዎችን እንዴት እወጣቸዋለሁ ብሎ ማሰብ እንጂ ተስፋ መቁረጥን አስበው አለማወቃቸውን ይናገራሉ። ደቡብ አሜሪካ ኮሎምቢያ ከፍተኛ ተመራማሪ በመሆን ለአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት የምርምር ስራ ለመስራት በዓለም ላይ ካሉ ተመራማሪዎች ጋር ተወዳድረው አለፉ።
በኮሎምቢያ ጥቁር ሳይንቲስት እሳቸው ብቻ ነበሩ፤ እናም በአጋጣሚ ወደ ተቋሙ የሚመጡ ጎብኚዎች ሲመለከቷቸው የፅዳት ሰራተኛ ወይም ሌላ ዝቅተኛ ስራ ላይ የተሰማሩ ይመስላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሌላው በኮሎምቢያ የሚያስታውሱት ተቀጥረው እንደሄዱ አካባቢ የተፈጠረውን አንድ አጋጣሚ ነው። በተቋሙ ስራ ሲጀምሩ 17 የቤተ ሙከራው ሰራተኞች ነጮች ነበሩ። ለቤተ ሙከራው ትልቅ ብር ተመድቦ በርካታ ቁሳቁስ ተሟልቶ ኃላፊነቱ ተሰጣቸው።
ሴት ለዚያውም ጥቁር እንዲሁም ወጣትና ቀጫጫ ከመሆናቸው የተነሳ የተሰጣቸው ኃላፊነት ያልተዋጠለት አንድ ሰራተኛ ማስቸገር ጀመረ። በዛ ላይ ስፓኒሽኛ ቋንቋ አለመቻላቸው ፈተናውን የበለጠ አከበደው። የሙከራ ጊዜ የተሰጣቸው ደግሞ ለስድስት ወር ነበር። በስድስት ወር ውስጥ መልክ መያዝ ያለበት ነገር መልክ ይዞ ውጤት ይጠበቃል።
ታዲያ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ሆነው በአንድ እለት በስራቸው የነበሩ ሰራተኞችን ሰብስባ በፀሀፊያቸው አማካኝነት እያስተረጎሙ ሲያወያዩቸውና የስራ አመራር ሲሰጡ አንድ ልግመኛ የሆነ ባለሙያ ያልተገባ ነገር ተናገራቸው። ‹ባንሰራ ምን ታደርጊናለሽ?› በማለት የሀገሪቱን የሰራተኛ ህግ እና የቀድሞ አለቃቸውን ጠቅሶ እንቢተኝነቱን አሳየ። ‹ከየት እንደመጣሽ እናውቃለን እኮ› ብሎ የኢትዮጵያን ረሃብ አነሳ። ‹‹እኔን አልፎ 80 ሚሊየን ሕዝብ ስለሰደበ ከስራ መባረሩን ነገርኩት።››
‹‹ከዛም ድርጅቱ በርካታ ገንዘብ ከፍሎ አሰናበተው። የእርሱ መሰናበት በመስሪያ ቤቱ በአጠቃለይ ተሰማ። ሌሎች ስራቸውን ሰጥ ለጥ ብለው እንዲሰሩ ምክንያት ሆነ። ያኔ ያንን ጠንካራ ውሳኔ መወሰኔ እኔንም ውጤታማ አደረገኝ›› ይላሉ። ትምህርት ከቆራጥነት ጋር ተዳምሮ ሰኬታማ ያደረጋቸው እንስት እንዲህ አይነቷን ነው።
በእንዲህ አይነት ተራ ጉዳዮች ተበሳጭተው እንደማያውቁ የሚናገሩት ዶክተር ሰገነት፤ ዋናው የረዳቸው ነገር በማንነት መኩራትን ተምረው ማደጋቸው እንደሆነ ይገልፃሉ። ‹‹በትምህርት ቤትም በቤትም ቆንጆ ነን፤ ጎበዝ ነን፤ ማንም ሰው ሊያሸንፈን አይችልም፤ ቅኝ አልተገዛንም፤ እየተባልን መማራችን በማንነቴ እንድኮራ እና በትንንሽ ነገሮች እንዳልናወጥ ጠቅሞኛል።›› የሚሉት ዶክተር ሰገነት፤ የኢትዮጵያ ረሃብ ጉዳይ በስራ ቦታ ብቻም ሳይሆን በመንገድ ላይም ገጥሟቸው እንደሚያውቅ ያስታውሳሉ።
ኢትዮጵያ የረሀብ ሀገር ናተ ለሚሉት ‹‹ኢትዮጵያ ረሃብተኛዋ አገር ሳትሆን ቡናን ለዓለም ያስተዋወቀችው ናት›› በማለት በቡናቸው የሚኮሩትን ኮሎምቢያውያን አፍ ያስይዙ እንደነበር ይናገራሉ። በሰለጠነው ዓለምም ይሁን በሀገር ላይ የትም ሃገር ሲኮን የስራን እና የቤተሰብ ሚዛንን መጠበቅ ለሴት ልጅ ከባድ እንደሆነ ዶክተር ሰገነት ይናገራሉ። ‹‹ለእኔ ጥሩነቱ ጥሩ ባል አለኝ እሱም ሳይንቲስት ነው። የቤቱን ስራ አብረን ነው የምንሰራው። እንደውም ብዙውን ይሰራ የነበረው እሱ ነው›› በማለት ስለትዳር አጋራቸው ለስኬቷ ስለሚያደርገው አስተዋፅኦ በአመስጋኝነት ስሜት ይናገራሉ።
ጥናትና ምርምር
በአሁኑ ወቅት ነፍሳት ላይ የምርምር ስራቸውን እያካሄዱ የሚገኙተ ዶክተር ሰገነት በዓለም ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የነፍሳት ዝርያ እንደሚገኙ ይናገራሉ። አብዛኞቹ ነፍሳት ሰራተኛ ናቸው የሚሉት ዶክተር ሰገነት፤ እነዚህን ነፍሳት ተጠቅሞ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ለማሻሻል የተለያዩ ጥናቶችን እየሰሩ እንደሚገኙ ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ የሐር ትልን ለማስለመድ እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን በምግብም ረገድ ነፍሳት አማራጭ እንደሚሆኑ መታሰብ እንደሚገባው ያመላክታሉ።
በአፍሪካ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ ሁለት ሚሊዮን ህዝብ ነፍሳት እንደሚመገብ፤ እንደ ጀርመን ያሉ ያደጉ ሀገራትም ለሕዝባቸው ይህንኑ ለማስለመድ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ኩራት እራት እንደማይሆን ለማሳየት ይጥራሉ። አሁን የሚሰሩበት መስሪያ ቤት ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል አንዱ ይህንን ማስተዋወቅ እና የምግብ ይዘቱንና ጥቅሙን መተንተን ሲሆን፤ የሚጎዱ እንዲሁም የሚጠቅሙ ነፍሳት ስላሉ ሁለቱንም አመጣጥነን መኖር እንደሚቻል በጥናትና በምርምር ለማሳየት ይሞክራሉ።
ሌላው የምርምር ስራቸው የሚያተኩረው የከብት መኖ ላይ መሆኑን ያስረዱት ዶክትር ሰገነት፤ ደቡብ አሜሪካ እያሉ ይሰሩት የነበረው እዚህ ላይ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ይህ የምርምር ስራቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ ገበሬዎችን ተጠቃሚ ማድረጉንም ይጠቁማሉ።
‹‹የበርካታ ገበሬ ሕይወት ተሻሽሏል። ከላሞቻቸው የሚያገኙት የወተት ምርት ጨምሯል፤ ይህንንም በማየቴ ደስተኛ ነኝ›› ይላሉ። ይህንን የከብት መኖ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሆኖ በዓመት ለ20 ሺህ ገበሬ ለማድረስ እቅድ እንዳላቸውም ያስረዳሉ።
ዶክተሯ ቀሪውን እድሜ ዘመናቸውን የገበሬውን ህይወት በማሻሻል ገበሬውን መርዳት ፍላጎታቸው መሆኑን አስረድተው በሚሰሩበት ቦታም ከአፍሪካ እና ከአፍሪካ ውጭ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለመስራት የሚመጡትን ተመራማሪዎች ማገዝ፣ ማሳደግ፣ ለውጤት ለማብቃት ያላቸውን እውቀት ያለስስት ማጋራት ፍላጎታቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
ዶክተር ሰገነት በግል ህይወታቸው ለዶክተር ሰገነት ከቤተሰብ የላቀ ዋጋ ያለው ነገር አይታያቸውም። ያላቸውን ጊዜ በሙሉ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማሳለፍ የደስታ ምንጫቸው እንደሆነ ያስረዳሉ። ‹‹ባለቤቴ አይሰራም አሁን ታሟል። … ደስ የሚለኝ እሱን መንከባከብ እና ልጄን ለስኬት ማብቃት ነው›› ይላሉ።
ሌላ ደስታን የሚሰጣቸው ነገር ጎበዝ የሆኑ እና ዕድል ያጡ ሰዎችን ዕድል ሰጥቶ ማብቃት ነው። የራሳቸውን ህይወት መለስ ብለው በማስታወስና የትምህርት እድል ባያገኙ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ በማጤን ግለሰቦችም ሆኑ መንግስት ትምህርት ላይ ማተኮር እንዳለበት አሳስበዋል።
በመጨረሻም ከተለያዩ አካላት ገንዘብ በማሰባሰብ የተወለዱበትን አካባቢ የገበሬዎች ማሰልጠኛ በመክፈት የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ለመስራት ምኞታቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2013