ለጥምቀት በዓል አምረውና ደምቀው በደሥታ ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል ያሉትንም አነጋግረናል።የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ካሰች ቱሉ ሁሌም እንደሚያደርጉት እርሳቸውም፣ ልጆቻቸውና ባለቤታቸው በሀገር ባህል ልብሥ ደምቀው በዐሉን ለመታደም ተዘጋጅተዋል።በበዐሉ በየአመቱ እየታደሙ ግን ሁሌም እንደ አዲስ በጉጉት ነው የሚጠብቁት።እርሳቸው እንዳሉት ታቦት ሲሸኙም ሆነ በማግሥቱ ታቦታቱን ወደ ቤተመቅደሳቸው ሲመልሱ ከጠዋት እስከ ምሽት ከቤታቸው ውጭ ከብዙ ሰዎች ጋር ሆነው ማክበራቸው ደስታን ይሰጣቸዋል።ከመንፈሳዊው የበዓል አከባበርና ከዛ ከሚያገኙት ደስታ በተጨማሪ ከሚያውቋቸውም ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር ለመገናኘትና ለመጫወት ዕድል ስለሚሰጣቸው የተለየ ስሜት ይፈጥርባቸዋል።ሁሉም ደምቆ በበዐሉ መታደሙ ለሀገርም አምባሳደር ሆኖ የሚወከል መስሎ ይሰማቸዋል።
እርሱና አምሥት ጓደኞቹ ተመሳሳይ የሆነ በዐሉን የሚያንፀባርቅ አልባሳት ገዝተው በበዐሉ ለመታደም መዘጋጀታቸውን ያጫወተኝ ሌላው ወጣት ምትኩ ደረሰ ይባላል።
ለበዐሉ የገዙት አልባሳት ዋጋው ውድ ነው።ግን ቀድመው ስላሰቡበት ውድ መሆኑ ብዙም አልተሰማቸውም።ከኃይማኖታዊ ሥርአቱ በተጨማሪ በዐሉን በማስተናበር ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች ለታዳሚው የሚያሳዩት ትህትና ለበዐሉ ልዩ ድምቀት የሚሰጠው መሆኑ ያስደስተዋል።በሌላው ዓለም ዘንድም ከበሬታን ያሰጠናል ብሎ ያምናል።በሥራ አጋጣሚ እንደሌሎቹ ወጣቶች ሁሉ ማስተናበር አለመቻሉ እንጂ እርሱም አንዱ ቢሆን ፍላጎቱ ነበር።
መልካምነት ዋጋ አለው ብሎ ያምናል።ወጣቱ እንዳለው የባህል አልባሳትን እያዘጋጁ ለገበያ የሚያቀርቡ ለበዐሉ አልባሳትን በማዘጋጀት ተጠምደው ነው የከረሙት።በእርግጥም ዋጋቸው የሚቀመስ እንዳልነበር ሌሎችም ገዥዎች በተመሳሳይ ሲያነሱ ነበር።ገዥ ባይኖር ነጋዴዎቹ ለገበያ አያቀርቡም ነበር የሚሉም አልጠፉም።‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› እንደሚባለው የጥምቀት በዐልን በድምቀት ለማክበር ታዳሚው በየአመቱ በአዳዲስ ነገሮች ደምቆ መታደምን ይፈልጋል።
ታዳሚው በአልባሳቶቻቸው ጭምር የሚያንፀባርቁት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት በበዐሉ ውስጥ የኢትዮጵያ ባንዲራ ጎልቶ እንዲደምቅ የሚያደርጉ በመሆናቸው በዐሉ የአንድነት ተምሳሌት ተደርጎም ይወሰዳል።
የዚህ ሁሉ ድምር ነው የጥምቀት በዐል የቱሪስት መዳረሻ ሊሆን የቻለው።ከአስር ወራት በፊት የተከሰተውና የዓለም ሥጋት ሆኖ እስካሁን በቀጠለው ኮቪድ 19 ቫይረሥ ወረርሽኝ ምክንያት ቱሪስቶች እንደቀድሞ ባይጠበቁም ጥቂቶችም ቢሆኑ እንደሚሳተፉ ተስፋ ይደረጋል።
የቱሪስቶች አለመኖር ይሄ የመጀመሪያው ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።ወረርሽኙ በኢትዮጵያም አሳሳቢ እንደሆነ በተደጋጋሚ በጤና ሚኒስቴር እየተገለጸ ነው። ነገር ግን በሽታውም መዘናጋቱም በእኩል እየጨመረ በመሆኑ የበዓሉ ታዳሚዎች ፍጹም ሊዘናጉ እንደማይገባ ከወዲሁ ማሰብ ያስፈልጋል።አስፈላጊ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግም ይገባል።
የከተራና ጥምቀት የአደባባይ በዓል በመሆኑ ከእምነቱ ተከታዮች ውጭ የሆኑትንም የሚያሳትፍ ነው። በመሆኑም በዚሁ በዓል ላይ የሚታየው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ ጭፈራ ይናፈቃል።በሌላኛው በኩል ደግሞ በአርሞኒካ የሙዚቃ መሳሪያ በዘመናዊ ዳንስ ጨዋታውን የሚያስነኩትን ወጣቶች በየዓመቱ መመልከት አይረሴ ትዝታን ያስቀራል።
ይሄን ሁሉ የበዓል ደስታና ክብር በየዓመቱ ለማድረግና ለመደሰት ታዲያ ዛሬን መኖር ይገባል። ለዚህ ደግሞ ለኮሮና ቫይረስ እንዳንጋለጥ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እንወዳለን። መልካም በዓል።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2013