ለምለም መንግሥቱ
የብራናው ልስላሴና ንጣት ነጭ ወረቀት እንጂ የእንስሳት ቆዳ ተፍቆና ለስልሶ የተዘጋጀ ብራና ነው ብሎ ለመቀበል እንደኔ ላለው ከተሜ እንግዳ ነው። በነጩ ብራና ላይ በቀይና በጥቁር ቀለማት ጎልቶ የሰፈረው የግዕዝ ጽሁፍም እንዲሁ ቀልብን ይስባል። የጽሁፍ ቀለማቱም በአካባቢ በሚገኝ ግብአት የተዘጋጀ መሆኑ ደግሞ በፋብሪካ ሂደት ውስጥ አልፎ ከሚዘጋጅ የመጻፊያ የቀለም አይነቶች መላቁ ሌላው አግራሞት የጫረብኝ ጉዳይ ነው። የብራና ጽሁፍ እየደመቀ እንጂ እየደበዘዘ የሚሄድ እንዳልሆነም ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣ የግዕዝ ጽሁፍ በመጻፍና ታሪኩንም በማቆየት ተጠቃሽ ናት። በጽሁፌ መግቢያ ላይ ያነሳሁትን ለየት ያደረገው በልጅነት የቀሰሙትን ዕውቀት ኑሮአቸውን ከተማ ውስጥ አድርገው እንኳን ከራሳቸው አልፈው ለተተኪ ትውልድም በማስተላለፍ ላይ የሚገኙ አባት ማግኘቴ ነው። ተማሪዎችን እያፈሩ፣ ለገበያም በማቅረብ እየተጠቀሙ፣ ጥንታዊውን የብራና ላይ ጽሁፍ ቅርስ በማቆየት ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ያሉት እኝህ አባት ሊቀጠበብት መምህር ሲሳይ ሽፈራው ይባላሉ።
ብራናውን ለማዘጋጀት ማንኛውም የእንስሳት ቆዳ መጠቀም ቢቻልም እርሳቸው ግን በቅርብ ከሚያገኙት የበግና የፍየል ቆዳ ነው የሚያዘጋጁት። መምህሩ በፈለገዮርዳኖስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስና ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ ‹‹ወንበር አስፍቼ። ጉባኤ ዘርግቼ የአብነት መምህር ሆኜ ኃይማኖታዊ ትምህርት እያስተማርኩ። ቤተክርስትያንም እያገለገልኩ እገኛለሁ›› ሲሉ ስለአገልግሎታቸው በመግለጽ ነው እራሳቸውን ያስተዋወቁት። የመምህሩን የብራና ላይ ጽሁፍ ለማየት ዕድሉን ያገኘሁት ስለዛሬው የከተራና የነገውን የጥምቀት በዓል አስመልክተው እንዲያጫውቱኝ ወደ እርሳቸው በሄድኩበት ወቅት እግረመንገዳቸውንም ሥራቸውን አሳይተውኝ ነው። መምህሩ ስለበዐሉ የገጠሩንም የከተማውንም ተሞክሮአቸውን አካፍለውኛል።
በቅድሚያም ከሊቀጠበብት መምህር ሲሳይ ጋር የተገናኘነው በጥምቀት ዋዜማ መዳረሻ ላይ ስለነበር እርሳቸው በዐሉን ለመታደም ከአልባሳት ጀምሮ ያላቸውን ዝግጁነት ነበር የጠየኳቸው። በዐሉን በጉጉት እንደሚጠብቁት በፊታቸው ላይ ከሚነበበው ደስታ ነበር የተገነዘብኩት። የሀገር ባህል ልብስና በላዩ ላይ የሚደርቡትን ነጭ ካባ አዘጋጅተዋል።
ለበዐሉ በአዘቦቱ ጥቁር የሚለብሱት ጳጳሳትና ቀሳውስት ሳይቀሩ በነጭ አልባሳት አምረውና ደምቀው መታየት አለባቸው። የእምነቱ ተከታይ አዳም ከፍዳ የዳነበትና የታደሰበት ቀን ነው ብለው የሚያከብሩት የደስታ በዐል በመሆኑ ሁሉም ነጭ ነው የሚለብሰው። ታቦታቱም እንዲሁ በተለየ ሁኔታ እንዲደምቁ በማድረግ በዐሉ ከፍ ብሎ ይከበራል። ስለካባ አለባበሱም እንዳጫወቱኝ በገጠሩና በከተማ ይለያያል።
በገጠር ልክ በዓለማዊው ትምህርት ያልተማረ ሰው የመመረቂያ ልብስ እንደማይለብሰው ሁሉ በገጠሩ በቤተክርስቲያን የሚያገለግሉ የኃይማኖት አባቶች የበቁና ከበሬታ የሌላቸው እርሳቸው እንደሚሏቸው የአብነት መምህራን ካልሆኑ ሌሎቹ ካባ አይደርቡም። በቀድሞ ጊዜ ግራዝማች፣ ቀኛአዝማችና ብላታ በሚል ማዕረግ የሚጠሩ የአካባቢ አስተዳዳሪ ሹመኞች እንኳን ከቤተክርስቲያን ደብር አስተዳዳሪ ፍቃድ ሳያገኙ ካባ ደርበው በበዐሉ አይታደሙም። ፍቃድ ካገኙ ለየት ያለ ካባ ነው የሚደርቡት። በከተማው ግን ልዩነት አለማስተዋላቸውን ይናገራሉ።
የበዐል አከባበሩ በገጠርና በከተማ ይለያይ እንደሆነም መምህሩ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ ከምላሻቸው የተረዳሁት የከተማውን ባይነቅፉትም ተወልደው የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉበት የገጠሩ ይበልጥ ይስባቸዋል። የበዓሉ አከባበር ይለይባቸዋል። ለየት ብሎ ይከብርባቸዋል። የገጠር የልጅነት ጊዜያቸውን እንዲህ ያስታውሳሉ።
በጎንደር ቤተልሄም ዙራምባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቆሎ ተማሪ በነበሩበት ጊዜ አሁን የ104 የዕድሜ ባለፀጋ በሆኑት አስተማሪያቸው መምህር ጥበቡ በንቴ ተመርቀው ወደቤተሰቦቻቸው የሚሸኙት በዚህ የጥምቀት እና የትንሳኤ (ፋሲካ) በዐል ወቅት በመሆኑ በጣም ነበር የሚደሰቱት። ከቤተሰቦቻቸው፣ ከአብሮ አደግ ጓደኞቻቸውና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በዐሉን ያከብራሉ።
በቆሎ ትምህርት የአብነት መምህር ለመሆን ከዳዊት ወይንም ፊደል ከመቁጠር ጀምሮ ምዕራፍ፣ ጾመድጓ፣ ዝማሬ መዋሲት፣ ቅኔ፣ አቋቋም የተባሉት የትምህርት እርከኖች አልፎ መገኘት ይጠይቃል። የትምህርቱ ጊዜም የሚወሰነውና የሚጠናቀቀው እንደመምህሩ እና ተማሪው ጉብዝና እንደሆነ የሚናገሩት ሊቀጠበብት መምህር ሲሳይ ዛሬ እርሳቸው ለሚገኙበት ዝማሬ መዋዚት የመምህርነት ደረጃ ለመድረሳቸው መምህራቸው ደመወዝ ሳይኖራቸው በፍቅር ማስተማራቸውን በበጎ በማውሳት የተወለዱበትን የጎንደርን የጥምቀት በዐል አከባበር የበለጠ ያደንቃሉ። ጥምቀቱ ፋሲለደስ ግምብ አካባቢ መሆኑ ደግሞ ታሪካዊነቱን ያጎላዋል ይላሉ። በበዐሉ ድምቀት ለእምነቱም ሆነ ለበዐሉ ቅርበት የሌላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ሳይቀሩ በመሳባቸው በየአመቱ ይታደማሉ ሲሉ ያወሳሉ።
የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የተለያዩ ኃይማኖታዊ ክብረበዐላትን ታከብራለች። ይሁን እንጂ ከሌሎቹ ለየት ባለ የጥምቀት በዐል ሰፊ ቁጥር ያለው ታዳሚ በማሳተፍና ደመቅ ማለቱ የተለየ ምክንያት ይኖረው ይሆን? ሊቀጠበብት መምህር ሲሳይ ‹‹የጥምቀት በዐል በክረምት ቢከበር ኖሮ እንዲህ በበጋው ይደምቅ ነበር ብለን ብናስብ በፍጹም አይሆንም ነበር። ሌላው ትልቁና ዋናው መጥምቁ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስና ኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናን ያሳዩበት ስለሆነ ሚስጥሩ ዞሮ ዞሮ ከኃጢያት የነጻንበት፤ ክብር ያገኘንበት ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ።
በዐሉ ጥር 10 ቀን ከተራ፣ ጥር 11 ቀን ደግሞ ጥምቀት ተብሎ ለሁለት ቀናት በዋናነት የሚከበር ሲሆን፣ በኃይማኖታዊ ሥርአቱ ታቦታት በሚያድሩበት ጥምቀተ ባህር ለቀናት ቆይተው ወደማደሪያቸው የሚመለሱ እንዳሉ መምህሩ ይናገራሉ።
እርሳቸው እንዳሉት ከተራ የበዐሉን የዋዜማ ዝግጅት የሚያሳይ ሲሆን፣ ዙሪያውን መከተር ወይንም ማዘጋጀት ነው። ‹‹ጥር 11 ቀን የሚከበረው በዐል ሰፊ የሆነ ኃይማኖታዊ ታሪክ ሥላለው በአጭሩ መግለጹ ምሉዕ ስለማያደርገው ዝርዝሩን ትተን እየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወርዶ በመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ እጅ መጠመቁን መነሻ በማድረግ በዐሉ እንደሚከበር መግለጹ በቂ ነው። እየሱስ ክርስቶስ በ30 አመቱ የመጠመቁ ሚስጥርም አዳም ያስወሰደውን ልጅነት ለማስመለስ እንደሆነ የኃይማኖት አባቶች ሊህቃን ይናገራሉ።
በአጠቃላይ ጥምቀቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናን ያሳየበት ነው›› ሲሉ የሚያስረዱት መምህሩ ቤተክርስትያንም ሆነች የእምነቱ ተከታዮች ክርስትያኖች በዐሉን በየአመቱ የሚያከብሩት ደስታ ያገኙበት ቀን በማስታወስ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህ አማኙ እምነቱን እያጸና በበዐሉም እየተደሰተ የሚያሳልፍበት ኃይማኖታዊም ባህላዊም እሴት እንዳለው ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2013