(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
ከርዕሰ ጉዳዩ በፊት . . .
“ፈተና” ስሙም ሆነ ግብሩ ያስፈራል፣ ያስደነግጣል፣ ያባትታል። ግድ ካልሆነ በስተቀር መፈተንን ማንም አይመርጥም። “ፈተና” እየተሳቀ የሚጋፈጡት እየተፍለቀለቁ የሚያስተናግዱት ክስተት አይደለም።
የባህር ማዶ ብሂለኞች በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ መልከ ብዙ የፈተና ዓይነቶችን ጠቅልለው የሰየሙት “Necessary evils” በማለት ነው። “አይቀሬ ተግዳሮት” በማለት በግርድፉ ብንተረጉመው ተቀራራቢ ፍቺ ሊሆን ይችላል።
ተማሪና ፈተና የተቆራኙ መሆናቸው ይታወቃል። ከክፍል ወደ ክፍል ለመሸጋገር በፈተና ውስጥ ነጥሮ መውጣት የግድ ይላል። ተምሮ ያልተፈተነና ማወቁን በፈተና ያላስመሰከረ ተማሪ ከቶውንም ተማሪ ሊሰኝ አይችልም።
የክፍል ፈተና፣ የአካባቢ/የክልል ፈተና፣ ብሔራዊ ፈተና፣ ዓለም አቀፍ ፈተና ወዘተ. በመባል የሚታወቁት የዕውቀት መፈተኛ ወንጠፍቶች ዓይነታቸውም ሆነ ባህሪያቸው ብዙና ዝንጉርጉር ነው። ተማሪ በተማረው፣ ወታደር በግዳጅ ውሎው፣ ነጋዴ በትርፍና ኪሳራው፣ ሃይማኖተኛው “እምነቱን በሚጻረሩ መንፈሳዊ ኃይላት፣ ሀገርም በልጅ ቀበኛ፣ በባዕድ ምቀኛ መፈተናቸው ያለና የሚኖር አንዱ የሕይወት “መራር ክፍል” ነው።
ፈተናን በአሸናፊነት ድል መንሳት ብቻም ሳይሆን ተሸንፎና ተረትቶ “ገበርኩ” ማለት ተመራጭ ባይሆንም የፈተና አንዱ “ውጤት” መሆኑ ግን እውነት ነው።
ሳይፈተን ያሸነፈ፣ ከስኬት በፊት ያልተደነቃቀፈ ሰብዓዊ ፍጡር ካለ እርሱ ኑሮው “አልጫ” መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሃሞቱ የቀጠነ፣ ጉልበቱ የተልፈሰፈሰ ምስኪን የሚባል ዓይነት ሰው ነው።
ይህን መሰሉን ሰው “የታደለ” ብሎ ማሞካሸት ምፀት እንጂ ሙገሳ አይሆንም። ማንም ሰው በደረጃው፣ የትኛውም ግለሰብ በአቅሙና በልኩ መጠን በመሽቶ በነጋ ሳይፈተን ውሎ አያድርም።
የአይሁድ እምነት አባት የሚባለው አብርሃም፣ የክርስትና እምነት መሥራቹ ክርስቶስ፣ የእስልምናው እምነት ነብዩ መሐመድ፣ የቡድሂዝም ሃይማኖት “አባት” የሚባለው ቡድሃ (የዓለም ሃይማኖቶችን በሙሉ መዘርዘር ተራራ የመውጣት ያህል ይፈትናል) የሁሉም የፈተና ዓይነት ይለያይ እንጂ ፈጣሪ በፈቀደላቸው ወንጠፍቶች ነጥረው በመውጣት በአስተምህሮታቸው ሚሊዮኖችን በመማረክ ከኋላቸው ያስከተሉ የእምነት ብቻ ሳይሆን የጽናት ምሳሌዎችም ናቸው።
“ለአዳር የመጣን እንግዳ ፊትህን ሳታጠቁር አቅፈህ ሳመው” እንዲሉ ፈተና ይምጣ ብሎ የግድ ባይጎተትም ሊወጡት የሚገባ አይቀሬ የሕይወት ተራራ መሆኑን በመረዳት ሃሞትን ሳያፈሱ መጋፈጥ እንጂ ሸሽቶ ለማምለጥ ወይንም እጅ ለመስጠት መሞከሩ አዋጭም አትራፊም አይሆንም።
ሀገርም እንደ ሰው ይፈተናል!? አዎን አሳምሮ ይፈተናል። ፈተናን ተጋፍጦ ያላለፈ አንድ ሀገር መጥራት ከተቻለ ጠሪው ራሱ ሀገር ሊሸለም ይገባዋል። ኢትዮጵያም እንዲሁ ትፈተናለች።
ፈተና የምድር “መቅሰፍት” ብቻ ሳይሆን በገነት ውስጥም ቢሆን አዳምና ሔዋን (አደምና ሐዋ) በወደረኛ ጠላታቸው እንደተፈተኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል። የሀገራችን ታሪክ በዋነኛነት የተሸመነው በቀለመ ደማቅ የፈተና ዓይነቶች ስለመሆኑ በትምህርትም ሆነ በአበው ጨዋታ ሲተረክና ሲወራ መኖሩን አንክድም።
የእኩይ የውጭ ወራሪዎችን ታሪክ፣ የውስጥ ባላንጣዎቿን ተግዳሮቶች አንድ በአንድ እንዘርዝር ብንል በቀላሉ አንወጣውም። ደግነቱ ሀገራችን የተፈተነችባቸው ጋሬጣዎች በሙሉ ከጉዞዋ አደናቅፈው ሊያስቀሯት ብርታት አልነበራቸውም። መከራዋ ቢበዛም በአሸናፊነት መወጣት ልማዷ ብቻም ሳይሆን ከፈጣሪ የታደለችው ፀጋዋም ጭምር ነው። ዕድሜ ለጀግኖች አርበኞቿ፣ አክብሮት ለአትንኩን ባይ ዜጎቿ፣ ምስጋና ለኢትዮጵያ ጉልበትና ብርታት ለሆነው ፈጣሪ እንደየድርሻቸው ባርኮታችን ይድረሳቸው።
ሃሳባችንን በአዘቦት ገለጻ እንግለጸው ካልን የኢትዮጵያ ታሪክ የተሸመነው በብዙ መከራና ፈተና “ድንርና ማግ” ተሸምኖ ነው ማለት ግዙፉን ሃሳብ ይጠቀልል ይመስለኛል።
የሀገራችን ፈተና ዛሬም ቢሆን አበቃለት የሚባል አይደለም። እንዲያውም የዛሬው የፈተና ዓይነት መልኩም ሆነ ባህርይው ካሁን ቀደም ተጋፍጣ ድል ከነሳቻቸው ውሎዎቿ እጅግ የተወሳሰበ ይመስላል።
የውስጥ ችግራችንን መክረንና ዘክረን ገና አላገባደድነውም። በማህፀኗ ውስጥ የበቀሉ ልጆቿ ሳይቀሩ ነክስው ካቆሰሏት ህመም ገና ሙሉ ለሙሉ አላገገመችም። ለቅጣት የሰነዘረችባቸው ሰይፍም ገና ወደ ሰገባው አልተመለሰም። “የእናት ጡት ነካሽ” እና “ጁንታው” የሚሉ ቅጽል ስሞች የተሰጣቸው የትውልድና የታሪክ ማፈሪያዎች ከወቅታዊ ፈተናዎቿ መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ አንዱ የታሪኳ ገጽ ነው። ሁለተኛው የፈተናዋ ገጽ የጎረቤቶቿ የትንኮሳ ድርጊት ነው።
“ቡና አጣጫያቺን” የመሃዲስቶችና የደርቡሾች ሀገሯ ሱዳን የውስጥ ፈተናችንን እንደ መልካም ዕድል በመቁጠር “የድንበር ውጋት” ሆና ልትቀስፈን እየሞከረች ነው። የቅድመ አያቶቻቸውን ውርደት የዘነጉ የዛሬዎቹ ደርቡሾች የሚነቀንቁት ነገር ራሳቸውን መልሶ እንደሚወጋቸው ከታሪክ መማር ባለመቻላቸው ሊታዘንላቸው ይገባል። እነርሱ ሰይፋቸውን ሲስሉ ሀገሬ በትእግስት እያስተማረቻቸው መሆኑንም የተረዱ አይመስልም።
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ከመግባት “እንቅልፍ አሸልቧት” የማያውቀው የፈሪዖኗ ምስርም በሱዳንና በሌሎች ኃይሎች ጀርባ ተጠልላ ቤንዚንና እሳት በማቀበል እየተጋች ነው። “ወይ አለመተዋወቅ!” አለ ይባላል ሌቦ ሣህሉ! የውርደት ታሪካቸውን ዞር ብለው ቢያመሳክሩ ኖሮ ድፍረታቸው ያሸማቅቃቸው ነበር። የባዕድ ምድርን የእንጀራቸው ማዕድ ያደረጉ የራሳችን “ጉግ ማንጎጎችም” ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር አብረው የፈተናዋን ትኩሳት “በፈጠራና በበሬ ወለደ ፕሮፓጋንዳ” ለማጋጋል ሲሞክሩ መመልከት ያሳፍራል።
እነዚህ የእንግዴ ልጆች የፍጻሜያቸው ታሪክ ለልጅ ልጆቻቸው ተላልፎ ሲያሳፍራቸው እንደሚኖር ያለመረዳታቸው የልባቸውን ድንዳኔ የሚያሳይ ብቻም ሳይሆን የትምክህታቸውን ጥግ የሚያመለክት ዕብሪት ጭምር ነው።
አንገታቸውን ደፍተውና ዳናቸውን አጥፍተው ሰላማዊ በመምሰል ሴራ የሚያውጠነጥኑ የቤት ልጆችም እንዲሁ የፈተናዋ ሌላ ገጾች ናቸው። በአጭሩ የዛሬይቱ ኢትዮጵያን ቀስፈው ሊይዙ የተዘረጉት የፈተና እጆች ብዛታቸው ብቻም ሳይሆን ረቂቅ ባህርያቸውም ከእስከ ዛሬው ተግዳሮቶቿ በእጅጉ የተለዩ ናቸው።
ከግራና ከቀኝ፣ ከፊትና ከኋላ የተሰለፉት ፈታኝ ታሪካዊ ጠላቶቿ ከፊሉ በረቺነት ስካር ናውዞ ከበሮ ሲደልቅ ከፊሉ የሽብር አዚም እየነዛ ለማስበርገግ ሲሞክር፣ አንዳንዱም የሀሰት ዐውሎ ነፋስ እያስነሳ ለማወክ ሲጥር እያየንም እየሰማንም ነው።
የውስጦቹም ሆኑ የውጭ ጠላቶቿ ያልገባቸው ረቂቅ ምሥጢር ኢትዮጵያ “እፍ ብለው የሚያጠፏት ሻማ፣ እንዳሰቡት ሰንዝረው የሚጥሏት ግዳይ” ያለመሆኗ ነው።
ፈተና ለኢትዮጵያ እንግዳ ክስተት እንዳይደለ ቀደም ሲል በዝርዝር ተገልጧል። ውቂያኖስ ቀዝፈው፣ በአየር ከንፈው የወረሯትን ባዕዳን ጠላቶች እንደ ጉም በትና ከትቢያ ጋር እንደደባለቀቻቸው ብዙ አብነቶችን ማስታወስ ይቻላል።
ቀደም ባሉት ዓመታትም ሆነ ትናንትና ተፈጥሮ ፊቷን አጥቁራና ፀጋዋን ነፍጋ በድርቅ፣ በልዩ ልዩ በሽታዎችና በርሃብ ስትፈተን ብትኖርም መከራዋን ተቋቁማ በአሸናፊነት ተወጥታለች እንጂ ተሸንፋ ሸብረክ አላለችም። ሰሞኑንም በክህደት ያደሟትንና በጓዳዋ የዶለቱባትን “የራሷን ምንትሶች” በቁንጥጫ አድብና ፉከራቸውን ተረት አድርጋዋለች።
የሉዓላዊነቷን ክብር በጀግንነት፣ ዓለማቀፍ ፍጥጫዎችን በዲፕሎማሲ ስክነት፣ የሀገር ውስጥ የጓዳ ችግሮቿን በጥበብና በማስተዋል እያረቀች በአሸናፊነት ስትወጣ ኖራለች። ዛሬም እያደረገች ያለችው ይህንኑ ነው።
ቀደም ባሉት ዘመናት የተፈተነችው ኢትዮጵያ ራሷ ነበረች። የዛሬውን ፈተናዋን ልዩ የሚያደርገው ግን ተፈታኟ እርሷ ብቻ ሳትሆን ኢትዮጵያዊነትም በአደጋ ላይ እንዲወድቅ የረቀቀ ሴራ መውጠንጠኑ ነው።
ፈተናዎቿ በሙሉ በድል መደምደማቸው አይቀሬ መሆኑ ቢታመንም የፈተናው አካል የሆኑት መንግሥትና ዜጎች “ለዘብ ወር ተራ ሲቆሙ” ሊያስተውሉት የሚገባቸውን አንዳንድ የተቆርቋሪ ዜጋ ቅን ሃሳቦች አስታውሶ ማለፉ አግባብ ይመስለኛል።
በፈተና ውስጥ ብንሆንም አንዳንድ የመንግሥት አካሄዶችን ደፍረንና ጫን ብለን መተቸቱ ለፈተናው የድል ፍጥነት ማገዝ ብቻም ሳይሆን ለፈውስም ጭምር ሊያግዝ ስለሚችል መንግሥት ጆሮውን ከፍቶ ቢያደምጥ ሊጠቅመው ይችላል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመንግሥት በኩል እየተስተዋሉ ያሉ አንዳንድ ድርጊቶች ሥር ሳይሰዱ መታረም ቢችሉ ትድግናው ለሕዝብም ለመንግሥትም የሚጠቅም ይሆናል። አንድ ሰው አንድ እንጂ ምን ዕውቀትና ብርታት ቢኖረው የብዙዎችን ሚና ይወጣል ተብሎ አይታመንም።
አንድ ሰው ውጤታማ እንዲሆን ካስፈለገ የተሰጠውን ውሱን ኃላፊነና ተግባር “አድምቶ እንዲፈጽም” ማድረግ እንጂ ሀገር የጥቂቶች ርሰተ ጉልት የሆነች ይመስል የተወሰኑ “አለን ባይ ግለሰቦችን” ብቻ ሃያና ሠላሳ ቦታ እየመደቡ “ተንቀሳቃሽ ሮቦት” ማድረግ ለሀገር ህልውናና ግንባታ እርባና የለውም።
በዜጎች መካከል የፖለቲካ ወገንተኝነት ብቻ ለተዓማኒነት መስፈርት ከሆነ ወይንም “በእከከኝ ልከክህ” ያረጀ ፈሊጥ፣ አለያም በመተዋወቅና በጓደኝነት ጥቂቶችን ብቻ ከአደባባይ ማዋልና በሀገር ጉዳይ ዘካሪና መካሪ እንዲሆኑ የምሉዕ በኩለሄ ሥልጣን ማጎናጸፍ ወዳጅ ነን እያሉ ደጅ ለሚጠኑቱ ግለሰቦች ወሮታ መክፈል ካልሆነ በስተቀር ለሀገር ፈተና አሸናፊነት የሚበጅ አይሆንም።
በዚህ አቅጣጫ መንግሥት እየተከተለ ያለውን አካሄድ ይህ ጸሐፊ አምርሮ የሚሞግተው በሀገሩ ጉዳይ ቸልታ “የእርግማን” ያህል ስለሚከብደው ነው። አስተዳደጉም ሆነ አቋሙ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ፅኑ መሠረት ላይ ስለተመሠረተ እንጂ ባለፉት ሦስት ተኩል ዐሠርት ዓመታት በዚሁ አንጋፋ ጋዜጣ ላይ በትጋት የየሥርዓቱን ህፀፆች ሲሞግት ባልኖረ ነበር።
ሀገር ያስተማረቻቸው፣ ተሞክሮ ያበቃቸው፣ ልምዳቸው ያበለጸጋቸው ብዙ ዜጎች የሀገራቸውን ክፍተት ለመሙላት በረከት መሆን እየቻሉ ጥቂት “በረኞች” ብቻ መግቢያና መተላለፊያ ኮሪደሩን መውጫና መዝጊያ እየከረቸሙ “እኛ ብቻ የሀገር ዘቦችና ምርጦች” ሲሉ መመልከት ፈተናችንን ያባብስ ካልሆነ በስተቀር ችግሮቻችንን በጋራ ለመመከት ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ አይታመንም።
በፖለቲካው ምህዳር ላይም ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡን የርዕዮተ ዓለም አምላኪዎችም ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ለወቅታዊው የሀገር ፈተና መፍትሔ እንዲሆኑ እንጂ እንቅፋት ለመሆን ራሳቸውን የመሰናክል ድንጋይ አድርገው ባያነጥፉ መልካም ይሆናል።
ሆደ ባሻዎቹ ብዙኃን የሀገሬ ምሁራንም “ዝም አይነቅዝም” ከሚል ያፈጀ መርህ ተላቀው ሀገር ላለችበት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ተግተው መውጫውን እንዲያመላክቱ ግዴታም አደራም እንደተጫናቸው ቢረዱ አይከፋም።
ፈላጊ ካገኙ ይህ ጉዳይ እንደማይጠፋቸው ጸሐፊው ጽኑ እምነት አለው። የማኅበረሰብ አንቂና ተሟጋች፣ የሚዲያና የኪነጥበባት ባለሙያዎች፣ ለበጎ ተግባር እጃችንን እየዘረጋን ነው የሚሉ የተራድኦ ተቋማትና ቤተኞች በዚህ የፈተና ወቅት ራሳቸውን ለመፍትሔ ጠቋሚነት ሊያዘጋጁ እንጂ የፈተናውን ወላፈን የሚያጋግሉ አራጋቢዎች ሊሆኑ አይገባም።
በመጨረሻም ሀገሬ ጠቀሜታው ባይጠፋትም ደፍራ ትኩረት ያልሰጠችበት ነፃ የሀሳብ አመንጪ ቡድኖች (Think Tank Groups) በብዛትና በጥራት ተቋቁመው በየሙያቸው ለፈተናዎቻችን መፍትሔ እንዲያፈልቁ ልታግዛቸውና ልታበረታታቸው ይገባል።
እንዲያም ሆነ እንዲህ፣ ያም ተባለ ይህ ዋጋ አስከፍሎንና ጊዜያችንን ቀርጥፎ ይጎዳን ካልሆነ በስተቀር የሀገሬ ፈተናዎች በሙሉ የሚደመደሙት በድል ዝማሬ ስለመሆኑ እኛም ዜጎች ሆንን የሩቅ ባዕዳን የምንመሰክረው በአንድ ቃል “እርግጥ ነው!” በማለት ነው። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ጥር 8/2013