ከደብረማርቆስ ከተማ እምብርት የተነሱት የሰባተኛው ዓመታዊ የባህልና ቱሪዝም ሚዲያ ፎረም ተሳታፊ ጋዜጠኞች ጉብኝታቸውን ወደ ጮቄ ተራራ አድርገዋል። ቦታው ቅዝቃዜ ስላለው ‹‹ልብስ ደራርቡ›› የሚለውን የአስተባባሪዎች ምክር የተቀበሉ ሁለትም ሦስትም ልብስ ደራርበዋል፤ ያለውም ጃኬቱን ቆልፎ እረፋዱ ላይ ጉዞ ተጀመረ። በቀድሞ ስሟ መንቆረር የምትታወቀው የደብረማርቆስ ከተማን አስፓልት መንገድ ያጠናቀቁ ተሽከርካሪዎች የፒስታውን መንገድ ተያይዘውታል። የሮብ ገበያን አግድም እያየን የሦስት ሰዓት የጠጠር መንገድ ጉዟችንን አገባደን የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ ስፍራዎች ደረስን። ከመጠነኛ ቅዝቃዜ ውጪ የተለየ ብርድ አላጋጠመንምና ጮቄን ከስምና ዝናው ባሻገር ለምን እንዳልቀዘቀዘ መጠየቄን ቀጠልኩ።
የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ በዋናነት ምሥራቅ ጎጃም አስተዳደር ዞን የስናን ወረዳ ውስጥ ይገኛል። እንደ ስናን ወረዳ ሰፋ ያለ ቦታ ባይኖረውም ጮቄ በደባይ ጥላት ግን፣ ሁለት እጁ እነሴ፣ ቢቡኝ እና ማቻከል ወዳረዎች ላይም ግዛቱን አስፋፍቷል። አካባቢው ከፍታው ከመሬት ወለል በላይ አራት ሺ አንድ መቶ ሜትር ይደርሳል። ቱሪስት ዝር የሚልበት ቦታ ባይሆንም ነብር እና ቀበሮ እንዲሁም የተለያዩ የወፍ ዝርያዎች ይገኙበታል ተብሎ በወረዳው ባህልና ቱሪዝም እየተዋወቀ ይገኛል። የአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ከቀን ወደ ቀን በሰው ሰራሽ ችግሮች አማካኝነት ክፉኛ እየተጎዳ ነው። በዚህም ምክንያት ስነምህዳሩ ዳግም እንዲያገግም መጠበቅ እንደሚያስፈልገው የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ሲወተውቱ ብዙ ጊዜ ይደመጣሉ። እኔም ቦታው ድረስ ሄጄ እንዳረጋገጥኩት ተቆርጠው ሥራቸው ደርቆ የሚታዩ በርካታ ዛፎች በቦታው ይታያሉ። በተጨማሪ አንድም የዱር እንስሳ አይታይም፤ ቀድሞ ሲነገርለት የነበረ ቅዝቃዜው አብሮት የለም።
ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ምን ይሆን? የሚለውን እያብሰለሰልኩ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑትን ወይዘሮ ወርቂት ባየሁ ስለጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ ተፈጥሮ ሀብት መዳከም ጠየቅኳቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቦታው ጮቄ የተባለው ውሃ የሚበዛበት እና ቀድሞ መሬቱ ሲረገጥ ከጭቃው ጋር ተዳምሮ ‹‹ጮቅ ጮቅ›› የሚል ድምጽ ስለሚሰጥ ነው። ቀደም ባሉ ዓመታት እንደ አስታ እና ጥድ የመሳሰሉ በርካታ አገር በቀል ዛፎች ነበሩበት። አሁን አካባቢው ቢረገጡትም ደረቅ እና የተሰነጣጠቀ ሆኗል፤ ዛፎቹም ተመንጥረው ገላጣ ሜዳ ሆኗል።
የጮቄ ተራራ ቀደም ባለው ጊዜ በረዶ የሚሠራ አየር ንብረት ነበረው የሚሉት ወይዘሮ ወርቂት፤ ቅዝቃዜው ሰው ገደለ የተባለበትም ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ። አሁን ላይ ግን ካልተዳፈሩ በካናቴራ ብቻ ቢንቀሳቀሱ የሚያስቸግር አይደለም። ደኑም ስለተመናመነ እንደጉሬዛ እና ድኩላ የመሳሰሉ ቀድሞ ነበሩ የሚባሉ እንስሳት ጠፍተዋል። ከዚህ ቀደም የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጉዳዩን ይዞ ለመሥራት ሲመጣ ህብረተሰቡ መሬታችን ሊሸጥ ነው በሚል ሲገዳደረው ቆይቷል። አሁን ላይ ግን ጥቅሙን የተረዳው ማህበረሰብ ለዩኒቨርሲቲ ሰዎቹ ገብተው ችግሩን እንዲፈቱ ፈቃድ መስጠቱን ይናገራሉ።
አቶ አስረስ ሙሉ በጮቄ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። እንደ እርሳቸው፤ የአካባቢው እንስሳት አልጠፉም፤ አሁንም በቦታው ይገኛሉ። ቀበሮ፣ ጅብ እና አነር ጮቄ ደን ውስጥ አሉ። ስለአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት መራቆት ምንም እንደማያውቁ የሚገልጹት ነዋሪው ስለጉዳዩም ያስተማረም ሆነ ያሳያቸው አካል እንደሌለ ይናገራሉ። ‹‹የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ምን መምሰል እንዳለበት ለህብረተሰቡ ያስተማረ ባለመኖሩ እንዴት አድርጎ ይንከባከበዋል?›› ሲሉም መልሰው ያጠይቃሉ። ‹‹እንደዚህ አይነቱን ጉዳይ የተማረ ብቻ ነው የሚያውቀው እኔ አላውቅም›› ሲሉም ነው በደፈናው ለችግሩ መፍትሄ ለመሆን ግንዛቤ እንደሚያስፈልጋቸው ነው የሚገልጹት።
በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የጮቄ ተፋሰስ የምርምርና የልማት ዳይሬክተር አቶ አብዮት ሞላ እንደሚገልጹት፤ በጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ የ23 ትላልቅ እና የ273 ትናንሽ የአባይ ወንዝ ገባሮች ይገኛሉ። እንዲሁም እንደ ኮሶ ጅብራ እና አሸንግድዬ የመሳሰሉ የበርካታ አገር በቀል እጽዋት መገኛ እንዲሁም በብዝሃ ህይወት የታደለ ስፍራ ነው። ይሁንና በአካባቢው አራት መቶ ሺ የሚደርሱ አርሶአደሮች በመኖራቸውና ለእለት ጉዳያቸው የተፈጥሮ ሀብቱን ያለእንክብካቤ ስለሚጠቀሙ ስነምህዳሩ ተጎድቷል። በዚህም የተራራው ውሃ አካላት ደርቀዋል፤ ደኖች እና በርካታ ብርቅዬ እንስሳት ጠፍተዋል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ስነምህዳር ወደነበረበት ለመመለስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ምርምሮች እያካሄደ ይገኛል።
እንደ አቶ አብዮት ከሆነ፤ በጥናቱ መሰረት ጮቄ በአግባቡ እንዲጠበቅ ካስፈለገ ከ10ሺ ሄክታር ይዞታው ቢያንስታው ስድስት ሺ ሃያአራት ሄክታሩ በጥብቅ ቦታ ወይም በፓርክ ደረጃ መሆን አለበት። ቦታው አሁን ላይ ጥብቅ ይባል እንጂ አርሶአደሩ እንስሳቱን ይዞ ስለሚገባ ስነምህዳሩ እየተጎዳ ነው፤ ምንጮችም ደርቀዋል። ከአምስት ዓመት በፊት መሬቱ ረግረጋማ ነበር አሁን ላይ አየር ንብረቱ በመቀየሩ አፈሩ እየደረቀ መጥቷል። በመሆኑም ለጮቄ አካባቢ አርሶ አደሮች ምን አይነት ሥራ በመፍጠር የአካባቢውን ስነምህዳር መጠበቅ ይቻላል የሚለው እየተጠና ነው። በመሆኑም አርሶአደሩ የሚተዳደርባቸውን እንስሳት ዝርያ በማሻሻል ኑሯቸው እንዲያድግ እና ወደጥብቅ አካባቢው እንዳይገቡ ለማድረግ ታቅዷል።
ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አቀፍ ሥራው ጮቄ ዋናው ጉዳይ መሆኑን አቶ አብዮት ያስረዳሉ። እንደ እርሳቸው፤ የአካባቢውን ህብረተሰብ በማወያየት ስነምህዳራዊ ጥቅሙን ለማስጠበቅ እየሠራ ይገኛል። በዋናነት ግን የአካባቢው ህብረተሰብ ስለጮቄ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ የእኔነት ስሜት እንዲያድርበት የማድረግ ሥራ ይከናወናል። ጥብቅ ሆኖ ሲቆይ እና ዕጽዋቱ እንደገና መብቀል ሲጀምሩ የዱር እንስሳቱም እየተበራከቱ ይመጣሉ። በመሆኑም በቀጣይ ጊዜያት ስጋቱን ቀንሶ የጮቄ ስነምህዳርንም በማሻሻል ለቱሪስት ምንጭነት ማዋል ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር26/2011
ጌትነት ተስፋማርያም