ፍሬህይወት አወቀ
መጠለያ ለሰው ልጆች ከሚያስፈልጉ መሰረታዊ ፍላጎቶች መካከል አንዱ ነው። ይሁን እንጂ በሀገሪቷ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የመጠለያ ችግር ዕለት ከዕለት እየበረታ መጥቷል። ችግሩ በተለይም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በክልል ከተሞች ሳይቀር የጸና ለመሆኑ ተየለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ የክልል ከተሞች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመዳሰስ ሞክረናል። ለዛሬው ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ ያለው የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦት ምን መልክ አለው ስንል ቅኝት አድርገናል።
ድሬዳዋ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ቀጥሎ ሰፊ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት የሚታይባት ከተማ ብትሆንም ከአዲስ አበባ እኩል ትኩረት አለማግኘቷን ጠቅሰው አጠቃላይ በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦት የከተማ አስተዳደሩ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም እንደሚከተለው አስረድተውናል።
በከተማዋ ያለው የመኖሪያ ቤት እጥረት በህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ክፍተት ፈጥሯል። ቤት ማለት ጣራና ግድግዳ ብቻ ሳይሆን ደረጃውን የጠበቀና አንድ ሰው ሊኖርበት የሚችል የባለቤትነት ወይም ተከራይቶ መቆየት የሚችልበት ነው። ይሁን እንጂ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ከሆኑ ፍላጎቶች አንዱና ዋነኛ የሆነውን መኖሪያ ቤት ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም።
በከተማዋ የሚታየውን ያልተመጣጣነ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦትን መሰረት በማድረግ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። በአሁን ወቅት በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና እጅግ አነስተኛ አቅርቦት በመኖሩ ዘርፉ ሰፊ ክፍተት እየታየበት ነው።
የጋራ መኖሪያ ቤት በመገንባት ችግሩን ለመቅረፍ በተደረገው ጥረት ከ1996 ዓ.ም እስከ 2003 ዓ.ም የተገነቡት ውስን ቤቶች ናቸው። እነዚህ ቤቶች ካለው ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር አባይን በጭልፋ እንደማለት ይሆናል።
የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታው አበረታች የነበረ ቢሆንም በነበረበት ደረጃ መዝለቅ አልቻለም።
በ2003 ዓ.ም የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ለአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ነው በሚል እንዲቋረጥ ተደርጓል። ይሁን እንጂ በወቅቱ የተጀመረው ግንባታ ፋይናንስ የሚደረገው በሁለት መንገድ ነበር።
አንደኛው በከተማ አስተዳደሩ በጀት ሲሆን ሁለተኛው ከንግድ ባንክ በሚገኝ ብድር እንደነበር ኢንጂነር ጀማል ያስታውሳሉ።
የችግሩን አሳሳቢነት የተረዳው ከተማ አስተዳደሩም ከባንክ በተገኘ ብድር የሚገነባው ግንባታ ሲቋረጥ ነገር ግን በከተማ አስተዳደሩ በጀት የተጀመረው ግንባታ እስከ 53 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበት እንዲጠናቀቅ ተደርጓል።
በዚህም መሰረት ከ1996 እስከ 2003 ዓ.ም አጠቃላይ 3ሺህ204 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል። ከእነዚህም መካካል በከተማ አስተዳደሩ በጀት 401 ቤቶች ተገንብተው 365ቱ ለመኖሪያ 36ቱ ደግሞ ለንግድ ቤት ተላልፈዋል።
ከባንክ በተገኘ ብድር እንዲሁ 2ሺህ803 ቤቶች ተሰርተዋል። ከእነዚህ መካከልም ለመኖሪያ 2ሺህ533፣ ለንግድ ሥራ 270 ቤቶች ግልጋሎት የቀረቡ ሲሆን አጠቃላይ በተጠቀሰው ጊዜ ለ15 ሺ እማወራና አባወራዎች ቤቶቹ ተደራሽ መሆን ችለዋል።
በ2008 ዓ.ም በተወሰኑ ከተሞች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲገነቡ የመኖሪያ ቤቶች ፓኬጅ በሚል የተደራጀ ስርዓት ነበር ያሉት ኢንጂነር ጀማል፤ ድሬደዋ ከተማም የኢንዱስትሪ ፓርክ ከተገነባባቸው ከተሞች አንዷ በመሆኗ በስርዓቱ ተካትታ ነበር።
የኢንዱስትሪ ፓርኩን ተከትሎ ከአጎራባች ከተሞች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የማህበረሰብ ክፍል ለስራ እንደሚመጡ ታሳቢ በማድረግ የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱ ይጨምራል።
በመሆኑም በከተማዋ 25 ሺ ቤቶችን ለመገንባት እንዲሁም እስከ 40 ሺ ተጨማሪ የስራ ዕድል ለመፍጠር በእቅድ ተይዞ ሲሰራ ነበር። ይሁንና ከ2008 እስከ 2010 በሀገሪቱ የነበረው የጸጥታ ችግር እንደ ሌሎች ዘርፎች ሁሉ በቤት ልማቱ ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሯል።
በወቅቱ በነበረው ከፍተኛ የመኖሪ ቤት ፍላጎት በመጀመሪያው ዙር ብቻ 17 ሺ የከተማዋ ነዋሪዎች የጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለመሆን ተመዝግበው እንደነበር ያስታወሱት ኢንጂነር ጀማል፤ ይህም ቀጣይነት ያልነበረው በመሆኑ ሌላ ጫና ፈጥሮ ቆይቷል። ህብረተሰቡ የነበረውን ከፍተኛ ተነሳሽነት የተረዳው ከተማ አስተዳደርም ባለው በጀትና በቻለው አቅም ቤቶችን ለመገንባት አቅዶ ተንቀሳቅሷል።
እንደሚታወቀው ድሬዳዋ ከተማ ለተወሰኑ አመታት በጀቷ ምንም እድገት ያልታየበት እና ከፌዴራል የሚሰጠው ድጎማም ለአራት ተከታታይ ዓመታት ተመሳሳይ እንደነበር ይታወሳል።
በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ ያለውን በጀት ተጠቅሞ 356 ቤቶችን ገንብቶ ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ችሏል። ባለፈው ዓመትም እንዲሁ የነበረውን አፈጻጸም በመገምገም ከ10 እስከ 20 በመቶ ቤቶችን ለመገንባት በማቀድ 524 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየተገነቡ ነው።
አፈጻጸሙም ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል። አጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ በጀትና ተነሳሽነት 880 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ጥረት ተደርጓል። ከእነዚህም መካከል ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለመተላለፍ ዝግጁ የሆኑና ግንባታቸው በጥሩ አፈጻጸም ላይ ያሉ ቤቶች ይገኙበታል።
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በፌዴራል ደረጃ የታየው ለውጥ ለድሬዳዋ ከተማም አዎንታዊ ምላሽ ነበረው ያሉት ኢንጂነር ጀማል፤ የቤት ልማት እንዲሰፋና ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ከዚህ በፊት በነበሩ አመራሮች ጭምር ሲቀርብ የነበረ ጥያቄ ነው። በመሆኑም ከ2011 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ተቋርጦ የነበረው ለቤት ልማት ትግበራ የሚውል ከባንክ የሚገኝ ብድር እንዲፈቀድ ተደርጓል።
በዚህም መሰረት በቦንድ ግዢ ከባንክ ብድር ለመውሰድ ተመቻችቶ ጥሩ ምላሽ ተገኝቷል። ይህም በለውጡ ማግስት የታየ ትልቅና ተስፋ ሰጪ ጅምር መሆኑን ይናገራሉ።
ካለፈው አመት ጀምሮም የሪልስቴት ቤት አልሚዎች በከተማዋ በስፋት እየገቡ ያሉበት ሁኔታ መኖሩን ያነሱት ኢንጂነር ጀማል፤ ባለሀብቶቹ ቦታ ወስደው እያለሙ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የህብረት ስራ ማህበራት የሚሳተፉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ማህበራት እየተደራጁ መሆናቸውን እና እነሱም ሌላኛው የቤት ልማቱ አማራጭ ናቸው። ለጊዜው እንደ መነሻነትም መምህራን ዜጋን በመፍጠር ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ቅድሚያ እንዲስተናገዱ ተደርጓል።
በዚህም መሰረት ቤት የሌላቸውን 2000 መምህራን ተለይተው የቤት መስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ድጋፍና ክትተል እየተደረገላቸው ነው። በመሆኑም 12 ሄክታር መሬት የተዘጋጀላቸው ሲሆን ግማሹ ገሚሶቹ ቦታውን ተረክበዋል። ቀሪዎቹም ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ ይገኛሉ።
በተጨማሪም በሰላምና ጸጥታ ላይ ለተሰማሩ አካላትን ለማስተናገድ እየተሰራ ነው። ከዚህ ባለፈም ተሞክሮው በአንድና በሁለት ሴክተሮች ላይ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በቀጣይ ወደ ማህበረሰቡና ወደ ሌሎች ተቋማት የሚሰፋ ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ የቁጠባ ቤቶች ተብለው የተገነቡ 20 እና 30 ዓመታትን ያስቆጠሩ 120 ቤቶችን ለነዋሪዎቹ በማስተላለፍ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።
ነዋሪዎቹ በቤት ውስጥ ለረጅም ዓመታት የኖሩ መሆኑን አስተዳደሩ ካረጋገጠ በኋላ በተያዘው በጀት ዓመት የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ተደርጓል።
በአሁን ወቅት የከተማዋ የ10 ዓመት ማስተር ፕላን እየተከለሰ ያለበት ጊዜ በመሆኑ የሚለሙና ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ቦታዎች ለመለየት አመቺ ነው። ፕሮጀክቱ መሻሻል እንዳለበት በማመን በእቅድ እየሰሩ ሲሆን ህብረተሰቡም አመኔታ እንዲኖረውና በራሱ ተነሳሽነት መገንባት የሚችልበት ሁኔታ ይመቻቻል።
ይሁንና በአሁን ወቅት ወደ ትግበራ ለመግባት ዋናው የፋይናንስ ጉዳይ የያዛቸው ሲሆን ይህንንም ለመፍታት በሂደት ላይ እንደሆኑ ኢንጂነር ጀማል ተናግረዋል።
‹‹አስፍቶ የጀመረ ሰው ማጥበብ ይችላል ያጠበበ ሰው ግን ማስፋት አይችልም›› የሚል የሱማሊኛ አባባል መኖሩን ይናገራሉ ኢንጂነር ጀማል፤ በዚህ መሰረት ሰፊ እቅድ ይዘው እየሰሩ መሆኑን አልሸሸጉም።
ከዕቅዶቹ መካከልም በመንግስትና በግል አጋርነት መሳተፍ የሚፈልጉ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን አሰራሩ በሚጠይቀው አግባብ መሰረት ያሳትፋል። አዲስ አበባ ላይ የተጀመሩ ልምዶችን ቀምሮ ከፌዴራል ጋር በመናበብ የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን ለመጠቀም አቅደዋል።
98 በመቶ የሚሆነው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ህዝብ በገጠር የሚገኝ ሲሆን በከተማ ውስጥ የሚኖረው የማህበረሰብ ክፍል ከሁለትና እና ሶስት በመቶ አይበልጥም። ስለሆነም የቤት ልማቱ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ማድረግ እንዲችል እና የደሃ ደሃ ተብለው የተለዩትንም ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው።
የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ያልቻሉና የደሃውን ኑሮ ፈልገው ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሱትን እንዲሁም ድጎማ የሚያሻቸውና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማሕበረሰብ ክፍሎች በመለየት የማመጣጠን ሥራ ይሰራል።
ጎን ለጎንም በግላቸው መገንባት የሚችሉትንና አቅም ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ምን ያህል እንደሆኑ የመለየት ሥራ ይሰራል።
በዚህም መሰረት በቀጣይ አምስት ዓመት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመናበብ በመንግስት አስተባባሪነት 51 ሺ 959 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ይገነባል።
ከመንግስት አስተባባሪነት ውጭ በመንግስትና በግል አጋርነት፣ በማህበራት፣ በግል በሚገነቡ መኖሪያ ቤቶች፣ በሪልስቴቶችና በግሉ ዘርፍ በሽርክና አንድ መቶ አራት ሺ 368 ቤቶች ለመገንባት መታቀዱን ነው የተናገሩት። ለዚህም ፋይናንሱን ከገንዘብና ፋይናንስ ሚኒስቴር ዋስትና ማግኘት የቻሉ ሲሆን ከብሔራዊ ባንክ ጋርም የተለያዩ ሂደቶችን ተጀምሯል።
በጀቱን አግኝተው ወደ ሥራ ለመግባት እየተጠባበቁ ይገኛሉ። የግንባታው ዲዛይን የመሬት አጠቃቀምን መሰረት በማድረግ እስከ 11ኛ ፎቅ የሚደርስ ሳቢና ሁለገብ የሆኑ ህንጻዎች እንዲሁም በመልሶ ማልማትም የሚገነቡ ቤቶች ይኖራሉ።
ከ70 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ድሬዳዋ ከተማ የሁሉም እንደመሆኗ የቤት ልማቱን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ኢንጂነር ጀማል ይጠቅሳሉ። በቀጣዩ አምስት ዓመትም የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን በመጠቀም 155 ሺ የሚደርሱ ቤቶችን ለመገንባት እየተንቀሳቀሱ ነው።
በከተማዋ ካሉ ቀበሌዎችና ወረዳዎች መካከል ሰፋፊ መሬት ማግኘት የማይቻል በመሆኑም በድሬዳዋ ባሉ ሶስት መግቢያ በሮች በሀረር መውጫ፣ ጅቡቲ መውጫና በኢንዱስትሪ መንደር አካባቢዎች ያሉ ቦታዎች ለቤት ልማት ተለይተው ለካቢኔ ቀርበዋል። ይህም በአካባቢው የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችን በቤት ልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታሳቢ የተደረገ ነው።
2008 ዓ.ም በተጀመረው የቤት ልማት ፕሮግራም 9ሺህ900 ነዋሪዎች ቁጠባቸውን ቀጥለዋል። ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ የቆጠቡ እንዳሉ ሁሉ፤ ተስፋ ቆርጠው ቁጠባቸውን ያቋረጡ ነዋሪዎች ደግሞ ገንዘባቸውን ከባንክ አውጥተዋል።
በዚህ ወቅት ብቻ ምዝገባ ያከናወኑ 10 ሺ የሚደርሱ ዜጎች ሲኖሩ ይህ ማለት ከ10 ሺ በላይ ቤቶች የሚያስፈልጉ እንደሆነ ያሳያሉ።
ስለዚህ ቁጠባቸውን ሳያቋርጡ እየተጠባበቁ የሚገኙትን በቅድሚያ ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል።
በመሆኑም በ2010 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ በከተማው በጀት የተጀመሩ 358 ቤቶች በአሁን ወቅት ግንባታቸው እየተጠናቀቀ ያለ በመሆኑ በቀጣይ የሚተላለፉ ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ ቤቶች ካለው ፍላጎት ጋር ሊመጣጠኑ የሚችሉ አይደሉም። ስለዚህ በቀጣይ የቤት ልማቱ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ኢንጂነር ጀማል አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2013