ለገሀር አካባቢ ነው – ጠዋት፡፡ የቀረበው በእግሩ የሩጫን ያህል እየፈጠነ የራቀው ደግሞ ባገኘው ትራንስፖርት በየአቅጣጫው ለሥራና ለጉዳዩ ይቻኮላል፤ ይራወጣል፡፡ ወደ ስታዲየም አቅጣጫ ከሚያቀኑ ታክሲዎች አንደኛው በመብራት ምክንያት ተሳፋሪዎቹን እንደጫነ ቆሟል፡፡ አንድ ዕድሜው 15 አካባቢ የሚሆን ልጅ ወደ ታክሲው ተጠግቶ እጁን ለምጽዋት ዘርግቷል፡፡ የለበሰው ሹራብ የቀድሞ ቀለሙን አጥቷል፡፡ ከገረጣው የልጁ ፊት አሳዛኝ ገጽታ በጉልህ ይነበባል፡፡
በእጁ መዳፍ አንድ ነገር ይዟል፡፡ እጁን በተደጋጋሚ ወደ አፉና አፍንጫው እያስጠጋ ይመልሳል፤ ቤንዚን እየሳበ በረሀብና በብርድ የተኮማተረውን ሰውነቱን ይበልጥ የሚያደነዝዝ ባዕድ ነገር ደጋግሞ ይምጋል፡፡ ተሳፋሪው ልብ ብሎ ያየውም አይመስልም፡፡ መኪናው ተፈቅዶለት ሲንቀሳቀስ ልጁ ወደ አንደኛው ጥግ ተኮራምተው ወደተኙት ጓደኞቹ ተጠግቶ ከጎናቸው አረፍ አለ፡፡
በላይ አዱኛ ይባላል ጎዳና ኑሮውን ካደረገ ሦስት ዓመቱ ነው፡፡ የቤተሰብ ችግር ከቤት እንዳስወጣውና ተገዶ የገባበት የጎዳና ህይወት እጅግ ፈታኝ እንደሆነበት ይናገራል፡፡ በላይ ከዚህ በፊት የተለያዩ ተቋማት ትቋቋማለችሁ በሚል በተደጋጋሚ የመዘገቡት ቢሆንም የተወሰነ ድጋፍ ማድረግ ጀምረው መልሰው እንደሚተውት ይናገራል፡፡ ‹‹ዕድል ባገኝ ጎዳናን መላቀቅ ህልሜ ነው፡፡›› የሚለው በላይ ከጎዳና ህይወቱ መላቀቂያ ገጠመኝ በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡
ለተለያየ ማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለማቋቋምና በዘላቂነት ለመርዳት ከዚህ በፊት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ችግሩ መባባሱ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች አስረጂ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን በተለይም የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማቋቋም ከዚህ በፊት ከሁለት ጊዜ ያላነሰ ጥረቶች ማድረጓን የከተማዋ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ይገልጻል፡፡
አቶ እንዳሻው አበራ በአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ችግር ተጎጂዎች መልሶ ማቋቋም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የማቋቋም ሥራው በብዙ ምክንያቶች ስኬታማ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው መጨመር፣ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያዘው በጀት አነስተኛ መሆን፣ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመቋቋም አገልግሎት አለመሰጠቱ፣ ስለ ችግሩና መፍትሄው በቂ ጥናት አለመደረጉ ዋንኛ ምክንያቶች እንደነበሩ ያሳታውሳሉ፡፡
ከ50ሺ ያላነሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚኖሩባት አዲስ አበባ በቅርቡ አዲስ መላን ዘየድኩ፣ በቋሚነትም ላቋቁማቸው አሰብኩ ማለቷ ተነግሯል፡፡ እቅዱ የእኛና የእነዚህ ቁጥራቸው የበዛ ጎዳና ተዳዳሪ ወገኖች መኖሪያና የአፍሪካ መዲና ለሆነችው አዲስ አበባ ለልጆቿ ህይወት መቃናት እንዲሁም ለገጽታዋም መስተካከል ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በተግባራዊነቱ ላይ ክትትል ይደረጋል የተባለለት ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ከዚህ በፊት ከነበሩ ጥረቶች ከፍ ባለ መልኩ ለችግሩ እልባት ያስገኛል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዘላቂነት መርዳት የሚያስችል ማህበራዊ ትረስት ፈንዱ መቋቋም ይፋ ማድረጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን በተለይም በችግር ጎዳና የወጡ ወገኖችን መርዳትና መደገፍ የሁሉም ህብረተሰብ ወሳኝ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመስረት ልጆቿን ሁሉ ይዘን ነው፡፡›› በማለት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ማቋቋምና በሀገር ግንባታ ተሳታፊ ማድረግ ወሳኝነት እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለማቋቋም የሁሉም ህብረተሰብ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ መንግሥትም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡
ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ በተለይም የጎዳና ተዳዳሪ ወገኖች ችግር በቋሚነት ለመቅረፍ ታምኖበት ይፋ የተደረገው የማህበራዊ ዋስትና ፈንድ በከተማዋ አስተዳደር አንድ መቶ ሚሊዮን ብር መነሻ ተይዞለት ወደ ሥራ መግባቱን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገልፀዋል፡፡ ይህም ሥራውን በተቀናጀ ሁኔታ ለማስጀምር እና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ እንደሚረዳም አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባስጠናው ጥናት መሰረት 92 በመቶ የሚሆኑት የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚመጡት ከክልል መሆኑም ታውቋል፡፡ የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ችግሩን ከስር ለማድረቅ ከክልል ጋር በጋራ ለመሥራት መታቀዱን ይገልጻሉ፡፡ ክልሎችም በከተሞቻቸው ላይ የሚገኙ ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ወገኖችና የጎዳና ተዳዳሪዎች የማቋቋም ሥራ እንዲሠሩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡
ልጆች ወደ ጎዳና ከመውጣታቸው በፊት ቤተሰብ ጋር እያሉ የሚረዱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከወላጆች፣ ከትምህርት ቤቶችና እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመሥራት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ በተቋቋመው ትረስት ፈንድ ወደ ማዕከል የሚገቡ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሥልጠና በመስጠት ዘላቂ የሆነና ህይወታቸውን የሚቀይር ሥራ ለማስጀመር በትኩረት እንደሚሠራም የቢሮ ኃላፊዋ አመልክተዋል፡፡
የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማቋቋም ወደተዘጋጁ ማዕከላት የማስገባቱ ሥራ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንደሚሆንም ከንቲባው ገልፀዋል፡፡ ‹‹የጎዳና ተዳዳሪዎችና ሌሎች ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ህልም አላቸውና ከህልማቸው ለማገናኘነት መጣር ያለብን እኛ ነን›› በማለት ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ወገኖች ችግር መቅረፍ የማህበረሰቡ ድርሻ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ይናገራሉ፡፡
ማህበራዊ ትረስት ፈንዱን ለመደገፍ የእምነት ተቋማት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና አርቲስቶች ቃል መግባታቸውን ኢንጅነር ታከለ ገልጸዋል፡፡ ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመው ትረስት ፈንዱ ተቋማዊ አደረጃጀት እንደሚኖረውና በቋሚነት የድጋፍ ሥራ እንደሚሠራ ኢንጅነር ታከለ ገልጸዋል፡፡
ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተውጣጥተው ማህበራዊ ትረስት ፈንዱ የሚመሩ 15 የቦርድ አባላት የተመረጡ ሲሆን፣ ዶክተር ደበበ ኢሮ በሰብሳቢነት፣ ኡዝታዝ አቡበክር አህመድ በምክትል ሰብሳቢነትና ዶክተር ሜሎን በቀለ በጸሀፊነት የሚመሩት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለማኅበራዊ ትረስት ፈንዱ ድጋፍ ማድረጊያ ‹‹6400››የመልእክት መላኪያ ስልክ መስመርና የባንክ ቁጥር የተዋወቀ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም ድጋፉን በማበርከት የበኩሉን እንዲወጣ ተጠይቋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጎዳና ተዳዳሪዎቹን ለማቋቋም ስድስት ማዕከላት ተዘጋጅተዋል፡፡ ከትናንት ጀምሮ ወደ ተቋማቱ እየተወሰዱ ሲሆን፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በማጓጓዝ ሥራው ተጀምሯል፡፡ አሰራሩ እየተገመገመ እና ልምድ እየተወሰደበት የሌሎቹ ክፍለ ከተሞችም ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን ጥር26/2011
ተገኝ ብሩ
假期带小孩岀行,要提前的行程和車票都儘量安排好,發現这里订票很方便,服務也不錯。HOPEGOO這個訂票的系統很贊!期待下次。