ሙሉቀን ታደገ
በኢትዮጵያ ከአያት ከቅድመ አያቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የቆየ የመረዳዳትና መደጋገፍ ባህል ያላት ሀገር ናት፡፡ ይህ ባህል እያደገና እየሰፋ የኢትዮጵያውያን ዋነኛ መለያ ወይም መገለጫ ባህሪ ሆኗል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ ከኢትዮጵያ ውጭ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በተለያየ ጊዜ ለወገኖቻቸው ድጋፍ በማድረግ ከሀገራቸው ጎን በመቆም ያላቸውን እውቀት፣ በገንዘብም እንዲሁም በሃሳብ በመርዳት ለሀገራቸው አንድነት፣ ብሎም ሉአላዊነት መከበር ይበል የሚያስኝ እና የማይተካ ሚና ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
አሁንም ለሀገር አስፈላጊውን ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህን በጎ ሃሳብ ወደ ፊትም በተጠናከረ መልኩ አጠናክረው ለማስቀጠል የሚያስችል ሥራዎችን እየሰሩ መሆኑን በተለያየ ጊዜያት ለሀገራቸውና ለወገኖቻቸው ከሚሰጡት ድጋፍ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሁን አሁን በሀገሪቱ ላይ የሚስተዋሉ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ለማስቆም መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅነታቸውን ከማሳየት ባለፈ የዲፕሎማሲ ስራቸውን በማጠናከር የሀገራቸውን ገፅታ ግንባታ ላይ አተ ኩረው እየሰሩ እንዳለ የሚታወቅ ነው ፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ በውጭ በተለያ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖቻቸውን ለመደገፍና ለማቋቋም የሚሆን የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰባቸው የሚያስመሰግን ተግባር እየሰሩ እንደሆነ በተለያየ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኤምባሲዎች አስተባባሪነት በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው እና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ወገኖቻቸውን ለመደገፍና ለማቋቋም የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰባቸው የሚያስመሰግን ብቻ ሳይሆን የተቀደሰም ተግባር እንደሆነ ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል፡፡
ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት በቅርቡ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ ሰላማዊ ዜጎችን ለመደገፍ በዩናይትድ ኪንግደም ለሦስት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየው የበይነ መረብ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ላይ ነው፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም፤ መንግስት ላለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሂደት ውስጥ መግባቱን አስታውሰው፤ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ እያካሄደ ያለው ሪፎርም ባልተዋጠላቸው የውስጥና የውጭ አካላት ቅንብር በተገመደ ሴራ ህዝባችን ለችግርና ለጥፋት ሲዳረግ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡
በቅርቡም በህወሓት ጁንታ የሰሜኑን የአገራችንን ክፍል ሉኣላዊነት በማስከበር ላይ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በውድቅት ሌሊት የተፈፀመው ኢሰብኣዊ ድርጊት መላውን ህዝባችንን ያስቆጣ እኩይ ተግባር መሆኑን አስታውሰው፣ መንግስት ይህን ዘግናኝ ድርጊት በፈፀሙ የክህደት ሃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ ማስከበርና ሀገርን የመታደግ ተግባር አከናውኗል ብለዋል፡፡
በተደረገው ሁለገብ ርብርብም ጁንታው ፈጽሞ በማያዳግም መልኩ ግብአተ መሬቱ መጠናቀቁና ርዝራዦቹም በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ህግ የማስከበር ሂደት በሰሜኑ የአገራችን ክፍልና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖች በፀረ ሰላም ሃይሉ በተነዛው ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳና ሆን ተብሎ በዚህ ሃይል በተፈጠሩ ግጭቶች ወገኖቻችን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንና ለስደት መዳረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመልዕክታቸው ፤ ከዚህ ቀደም ለመከላከያ ሰራዊታችን ካበረከቱት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ተፈናቃይ ዜጎቻችንን ለማቋቋም እያደረጉ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ መንግስት የጀመራቸውን ሪፎርሞች ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ ዲያስፖራው ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ወደሀገር ውስጥ በመላክ የጥቁር ገበያው የገንዘብ ዝውውርን ለማምከን በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ብርቱካን አያኖ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት በዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል ሀገራቸውን ለመደገፍ የገንዘብ ፣ የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ አሁንም የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ለመርዳት ለሚያደርጉት የገንዘብ ማሰባሰብ ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊትም በበኩላቸው የዲያስፖራውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ እንዲቻል መንግስት የዲያስፖራ ኤጀንሲን ማቋቋሙን ጠቅሰው፣ ኤጀንሲውም ከሴክተር ተቋማት ጋር በመቀናጀት የዲያስፖራውን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በትኩረት በማከናወን ላይ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ቅንጅታዊ አሰራሩም ዲያስፖራው የሀገሩን እድገትና ብልፅግና ለማፋጠን የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስገንዝበዋል፡፡
ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፤ ዲያስፖራው ልዩ ልዩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ እያሳየ ስላለው የተጠናከረ ተሳትፎ አመስግነው፣ ይህንኑ መልካም ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ያመለክታሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም የኢፌዴሪ አምባሳደር ክቡር ተፈሪ መለሰ በበኩላቸው ዲያስፖራው ሪፎርሙን በመደገፍ ከኤምባሲው ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለሀገራችን ብሄራዊ ጥቅሞች መከበርና ለወቅታዊ ጥሪዎች ምላሽ ለመስጠት በዲያስፖራው የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በማጠቃለያ የኢትዮጵያውያን ግብረ ሃይል በዩናይትድ ኪንግደም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዘላለም ተሰማም ዲያስፖራው የተጀመረውን ሪፎርም ለመደገፍ አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸውን ከእንግሊዝ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 05/2013