አዲሱ ገረመው
በቅርብም፣ በሩቅም (እነ ዲያስፖራ) ያላችሁ ወዳጆቼ እንዴት ሰነበታችሁ? ሠላም ነው! ሰበር ዜናው፣ ማለቴ ቅዝቃዜው እንዴት ይዟችኋል? የሚመች ነገር ቢኖርም ባይኖርም ይመቻችሁ! ስሙኝማ ይልቅ የሙያ ቅጥር የሚባለው ገበያው ሲቀዘቅዝ ለአቅመ ሹመት የደረሱት ገበያውን እየተቆጣጠሩት ነው አሉ። እውነት ይሆን እንዴ?
ለነገሩ በዘመነ ኢህአዴግ ገበያው ይሄው ሆኖ ነው የቆየው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተማረ ሰው እየተረሳ ነው፤ የሚሾመው ሌላ ሌላው ነው ሲባሉ ምን ብለው ነበር የመለሱት።
የኢህአዴግን አላማ/አብዮታዊ ዴሞክራሲን ማለታቸው መሰለኝ/ እስከ አሳካ ድረስ የፈለገንን እንሾማለን ምን ትሆኑ አይነት ነገር ተናግረው ነበር።
በዚህ አያያዝ እድገታችን ወደ ሦስት አሀዝ/ዲጂት/ ሊያሻቅብ ይችላል የሚል መላ ምት (መላ ለምን ይመታል ግን) ብናስቀምጥስ? “ወይ ጣሊያን!” አለች ምዕራብ ጀርመን! እንዲህ እንዲህ እያልን እንተንፍስ እንጂ።
አንዱ ወዳጄ የሰሞኑን የአሜሪካውን አመጽና ሰልፍ አይቶ፣ እኛና አሜሪካ አንድ ነን፤ ሁለታችንም ዴሞክራት፤ ሁለታችንም ጋር የኑሮ ውድነት አለ፤ ሁለታችንም ጥጋብ አንወድም፤ ልዩነቱ እነሱ ተቸገርን ብለው በበላ አፋቸው በአደባባይ ሲጮሁ እኛ በአደባባይ ቀርቶ በባዶ ሆዳችን ተቸገርን ብለን ማሰብ አንችልም፤ አለኝ።
እኔ ግን ተቃውሞዬን ገለጽኩለት። እኛ አገር አሁን ላይ እንኳን ጮሆ መናገር፣ ጮክ ብሎ መፃፍም ይቻላል አልኩታ። ለዚህ አይደል ታዲያ እኔስ ዳርዳር ማለቴ። እናላችሁ አገራችን በሹመት እምርታ አሳይታለች።
ለዚህም በሹመት ቦታ መሙላት ምክንያት የባለሙያው መድረሻ ማጣትና እንግልት ምስክር ነው።
ወዳጄ በቅርቡ ሥራ ስቀጠር በመጀመሪያው ወር ደመወዜ ማኪያቶ እጋብዛሃለሁ ያልከኝን አስታወስክ? ለካ እያሽሟጠጥክ ኖሯል? ግድ የለም ሹም ስትሆን ጋብዘኝ። ቅጥሩማ በየት በኩል።
የስላቅ ሰፈሩ ወዳጄ የተጠበብክባት የማኪያቶ ግብዣ ስላቅ ግን ታስገርመኛለች እኮ። ሥራ ልትቀጠር ሄደህ ሹመት በሩን ዘጋብህ አይደል? እንግዲህ እኔ አልፈርድልህ፤ እርሱ አንድዬ ይመልከትህ እንጂ።
ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው አንድ የመንግስት ተቋም ሰሞኑን ሽርጉድ በዝቶበታል። ሹመት የሚያገኙ አዳዲስ ሰዎች መኖራቸውን ተከትሎ ራሳቸውን ከአመራር ተርታ የሚመድቡት ሲዶልቱ ነው የሚውሉት። ወሬው ሁሉ “እከሌ የት ቦታ ሊመደብ ይችላል?፤ እነ እከሌ እንኳን እነ እከሌ እያሉላቸው ምንም አይሆኑም” የሚል ሆኗል። ለዛሬው ይህችን አጭር መጣጥፍ ለመጻፍ መነሻ የሆነኝም ይኸው ነው።
ሹመት በነፃ ገበያ ቢወዳደር ቅጥር ከሚያወጣው ዋጋ ያንስ ነበር። አንዳንዴ ተሿሚዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ከባለሙያዎች ጋር ለሥራ ቢወዳደሩ ሌላኛው ችግር በደንብ ይገባቸው ነበር እላለሁ። ተሿሚ ደመወዙ ስንት እንደሆነ የሚያውቀው በዓመት አስልቶ እንጂ በወር ባንክ ቤት ተሰልፎ አይደለም።
የወንበር ከሚለው ጀምሮ የነዳጅ፣ የቤት፣ የስልክ፣ የጉዞ፣ የማትግያ ወዘተ ተብለው በተሿሚዎች ቋንቋ ብቻ የሚታወቁ ጥቅማ ጥቅሞች አስክረውት በየት በኩል ደመወዙን ይቁጠር። በዚህ ላይ በትንሽ በትልቁ ከከተማ የሚያስወጣ ስብሰባና የመሳሰለው አለ፤ አበል የሚታጨድበት። ከእርሱ እኩል ተምረው እኩል የስራ ልምድ ኖሯቸው እንደውም በልጠው የሚገኙ ሰዎች ደግሞ ይህ ሁሉ ለእነርሱ ህልም ነው።ምን ህልም ብቻ ቅዥትም ነው።
በነገራችን ላይ ሹመት የሚሰጠው፤ በዋነኛነት ለትልልቆቹ አመራሮች ባለው ቀረቤታ ላይ ተመስርቶ ነው። ትልልቆቹ አመራሮች ከወደዱህ፤ አንተ ብትማር፤ በፖለቲካ ብትበስል ባትበስል፤ ችግር የለውም።
ካንተ የሚጠበቀው ትልቁ መስፈርት የነሱ አሸርጋጅ መሆን ነው። በዚህ መልኩ፤ እጅግ ብዙ አመራር ወደ ስልጣን መጥቷል። ወደ ስልጣን የመጣ አሸርጋጅ ከብሯል። የቪላና ፎቅ ቤት ባለቤት ሆኗል። ቪ ኤይት መኪናን ሲያሻው በሾፌር አሊያም በራሱ እጅ እንደልቡ አሽከርከሯል። አሁን እንዲህ አይነት ሰዎች፤ የህዝብን አጀንዳ ወደ ጎን ትተው፤ ቀን ከሌት ስለ ራሳቸው ጉዳይ ቢጨነቁ ምኑ ይገርማል? ለዚህ እኮ ነው ሹመት ቅጥ ይኑረው የምለው።
እንደዚህ አይነት ሰዎች፤ በሆነ አጋጣሚ እንኳን ከሀላፊነት ቢነሱ፤ ምርጥ የተባለ ቦታ ተፈልጎላቸው ይመደባሉ፤ ይህ ምርጥ ቦታ ከጠፋም፤ በህግ ያልታወቀ / በመስሪያ ቤቱ መዋቅር የስራ መደብ የሌለ/ የስራ መደብ ይፈጠርላቸዋል፤ በዚህም መሰረት ተዘፍዝፈውበት ከከረሙት ስልጣን በሆነ አጋጣሚ ቢነሱ እንኳን፤ ሰናይ ኑሯቸውን እንዲገፉ ይደረጋል።
ይሄ አሰራር በተለይም ለእነዚያ 27 ዓመታት ሲተገበር የኖረ ነው። ይሄን ሁሉ የተበላሸ አካሄድ ደግሞ፤ ህዝብ አንጀቱ እያረረ በአንክሮ ሲከታተልና ሲታዘበው ከርሟል። በአሁኑ ወቅት ለህዝባችን የሚያስፈልገው የሿሚ አገልጋይ ሳይሆን በውድድር ወደ ሥልጣን የሚመጣ አገልጋይ ነው።
በሹመት ርዕዮተ ዓለም የበላይነት እሳቤ የቱንም ያህል የተማርክ ብትሆን፤ በአመራርና በፖለቲካው ብትበስል፤ እውነት ብትናገር ወዘተ. አንተ ለታላላቆቹ አመራሮች፤ እስካልተመቸሃቸው ድረስ ዋጋ ቢስ ነህ። ስለሆነም ሰበብ ተፈልጎልህ ከሥራ እንድትሰናበት ሁሉ ልትደረግ ትችላለህ።
ያኔ ልክ ለእነሱ አሸርጋጆች እንደሚደረገው ሁሉ፤ ላንተ ጥሩ ቦታ ተፈልጎልህ የምትመደብ እንዳይመስልህ፤ ይልቁንስ ለሲቪል ሰርቪስ ቢሮ፤ በሚመጥነው ቦታ መድቡት ተብሎ ደብዳቤ ይጻፍልሀል። ሂድ አትበለው እንዲሄድ አርገው አይነት ስራም ይፈጥርልሃል።
የሲቪል ሰርቪስ አመራርም፤ ቀድሞ ስለሚነገረው፤ ከወደደህ፤ እንደ ምንም ቦታ ፈላልጎ፤ በሚመጥንህ ይመድብሀል፤ ከደበርከው ደግሞ፤ ቦታው ስለሌለኝ፤ አንድ ደረጃ ዝቅ ብለህ ተመደብ ይልሀል፤ አንተም ደሀ ነህና እየቆዘምክ ትቀበላታለህ።
ይህ ብዙዎች የተማሩ ሰዎች የገጠማቸው እጣ ፈንታ ነው። ይሄንን ኢ-ፍትሀዊ አሰራርም እስከመቼ በትዝብት እንመልከተው?
ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲዎች ብቃትን ሳይሆን ፖለቲካዊና ዘውጋዊ ማንነትን ባማከለ መልኩ በተሾሙ የገዥው ፓርቲ እንደራሴዎች እንዲመሩ ተፈርዶባቸው ነበር። የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሾሙ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
አሁን ላይ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት በተቋሙ ተልእኮና በዓለም አቀፍ መልካም ልምድ መሰረት፣ አካዳሚያዊ ነጻነት እንዲኖረው ተደርጎ ከሹመት ተኮር ይልቅ ውድድር ተኮር ሆኖ ተሻሽሏል።
ይህ መልካም ጅማሮ በሌሎች የመንግስት ተቋማት ላይም ሊተገበር ይገባል። ይህ የዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ እየተቀመረ ወደ ሌሎች ተቋማት መውረድ ይኖርበታል።
ምህንድስናን የተማረ ሰው በውድድር ቢመራ መንገዶቻችን ባልጎረበጡን፤ ፖለቲካው በዘርፉ ትምህርት ባለው ቢመራ ኖሮ አገራችን በፖለቲካዊ ቀውስ አትናጥም ነበር።
የኢኮኖሚውን ጉዳይ የሚመራ ባለሥልጣን በዘርፉ ተምሮና ተወዳድሮ ቢመራ የእድገት ዲጂቱም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ይሆን ነበር። ሹመት የሚለው አሰራር ጎርበጥ ያደርጋል። እንደ ማህበረሰብ የሞራል ልዕልና ሰርቶ ጥሮ ግሮ በማግኘት የሚያምን ትውልድ መፍጠር ያስፈልጋል።
ፖለቲካውን ማሳለጥ ከቻለ ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል አምጥተን እንሾማለን የሚለው ኢህአዴጋዊ መርህ አላረመደምና ቀስ በቀስ ልክ እንደ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶቹ ስልጣን በውድድር የሚያዝበት ወቅት እንዲመጣ እንፈልጋለን።
አዲስ ዘመን ጥር 04/2013