አስመረት ብስራት
ስደት ክፉ እጣ መሆኑን በርካቶች ሲያማርሩ ይሰማል። ሰው በተለየዩ ምክንያቶች ቢሰደድም በተሰደደበት ሀገር ስኬታማ ሆኖ ለመውጣት የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጋል። ለአንዳንዶች ስኬት ቅርብ ሲሆንላቸው ለጥቂቶች ደግሞ አበሳ አስቆጣሪ ይሆንባቸዋል። ከሰሞኑ ከወደ ጣሊያን የተሰማው ዜናም የነገረን ከስደት ክፉ እጣዎች ስለደረሳት አንዲት ኢትዮጵያዊ ነው። በጣሊያን በስደት ትኖር የነበረችው ኢትዮጵያዊት በመኖሪያ ቤቷ ተገድላ ተገኝታለች። ስለዚህች ሴት የተለያዩ የውጭና የውስጥ መገናኛ ብዙሃን ያሰፈሩትን ለጋዜጣችን እንደሚስማማ አድርገን አቅርበነዋል።
የስደት ክፉ እጣ ገፈት ቀማሽ የሆነችው አጊቱ ጉደታ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነወ። ያደገችባትን ሀገር ለቃ ከአስር ዓመት በፊት ነበር ስኬትንም ሞትንም ወደ አስተናገደችበት ወደ ጣሊያን የሄደችው። በትምህርት አለሙም ገፍታበት ነበር። ልክ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ነበር ነጻ የትምህርት እድል አግኝታ በትሬንቲኖ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ ሳይንስ ዲግሪዋን የተቀበለችው። ከዚያም በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ለጥቂት ጊዜ ከቆየች በኋላ ወደ ጣልያን ተመልሳ ኑሮዋን በዛው አደረገች።
ጣሊያን ከገባች በኋላ ለመኖር እራሷን የምታስተዳድርበት የስራ ዘርፍ ማሰብ ጀመረች። ከዚያ ነው እንግዲህ በጣሊያን በትሬንቲኖ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ፍየሎችን ማርባትና ልዩ ልዩ የወተት ተዋጽኦችን ማምረት የጀመረችው። ስራውንም ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። ስራዋን በንቃት ከመስራቷም በላይ የተለያዩ ስደተኞችን በመርዳት የምትታወቀው አጊቱ በምትኖርበት አካባቢ በሚኖሩ ጣልያናውያን እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት በስደት ወደ ጣልያን በሄዱ ሰዎች ዘንድም ታዋቂና ተወዳጅ ነበረች።
አጊቱ በተለያዩ ጊዜያት ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገረችው እንስሳትን ማርባት በቤተሰቧ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረ ልማድ ነው። በተጨማሪም ቀደም ሲል ዋነኛ ትኩረታቸውን በአርብቶ አደሮች ላይ ባደረጉ በዘላቂ ግብርና ፕሮጀክቶች ላይ በመስራት ልምድ የነበራት በመሆኑ በእንስሳት እርባታ ሥራዋ ስኬትን እንድትላበስ በጎ አስተዋጽኦ አድርጎላታል።
በስደት የሄደችባት ሀገር አንደሁለተኛ ቤቷ አድርጋ የኖረችባት ግዛት ከፍየል ወተት አይብ ማምረት ስትጀምር ለበርካታ አፍሪካውያን የሥራ እድል ፈጥራለች። ከዚህ ባሻገርም ዘረኛነትን በመጋፈጥ እንዲሁም ለስደተኞች መብት በመቆም ትታወቃለች። ፍየሎች ላይ አተኩሮ መሥራት የሚያስደስታት ይህቺ ሴት ጣልያን ውስጥ ጥቅም ላይ ያልዋለ የእርባታ መሬት ስታገኝ አገር በቀል ፍየሎችን ለማርባት ወሰነች።
የውሳኔዋ ማስፈፀሚያ ይሆኑ ዘንድ ፔታታሞኒኪና የሚል መጠሪያ ያላቸው እና ዝርያቸው ሊጠፋ የነበሩ ፍየሎችን ማርባት ምርጫዋ ነበር። አጊቱ በመነሻዋ ላይ 15 ፍየሎች የነበሯት ሲሆን ጠንክራ በመስራቷም የኋላ ኋላ ወደ 180 የሚደርሱ ፍየሎችን ማርባት ችላለች። ከእርባታው በኋላ የፍየሎቹን ወተት በመጠቀም ታዋቂነትን ያተረፈላትን ተወዳጅ አይብ ማምረት ጀመረች። በፍየል እርባታዋና በአይብ ምርት ሥራዋ ረዳት አድርጋ ከምትቀጥራቸው ሠራተኞች መካከል አብዛኞቹ ስደተኞች ነበሩ።
ይህም የተቸገሩ ሰዎችን የመርዳት ፍላጎቷን ለማሳካት እንድትችል አድርጓት ነበር። ጣልያን ውስጥ የተማረች በመሆኗም ከመኖሪያ ፍቃድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንዴት መፈፀም እንዳለበት ባላት ግንዛቤ እርዳታ ታደርጋለች። የቀረውን በዚያው በጣሊያን ጓደኞቿም እንዲረዷት ታደርግ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ከፍየል ወተት ስለሚሠራ አይብ ለመማርና አብረዋት ለመሥራት የሚሄዱም ብዙዎች ነበሩ። እሷም የምትወደውን ሙያ ለሌሎች ከማስተማር ወደኋላ አትልም ነበር። ሙያውን ለማዳበር በፍየል አይብ ወደምትታወቀው ፈረንሳይ ሄዳ ስለ አይብ አሠራር ተምራለች። ወደ 15 የሚደርሱ የአይብ አይነቶች ለደንበኞቿ ታቀርባለች። በሥራዋ የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክተውላታል። በሚላን ኤክስፖ ላይ የምትኖርበትን ግዛት ወክሎ የቀረበውም የእሷ የአይብ ምርት ነበር።
በምትኖርበት ግዛት ከፍየል ወተት የሚሠራ አይብ ሙያ ውስጥ ማንም አልነበረም ማለት ይቻላል። አጊቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች ለሚሄዱም ለዓመታት አይብ አቅርባለች። ከፍየል ወተት የሚሠራ ተፈጥሯዊ መዋቢያ ታመርታለች። ቱሪስቶችን የፍየል መንጋም ታስጎበኛለች። ይህቺ ድንቅ ሴትም የተለያዩ ፈተናዎች ይገጥማት እንደነበረ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከፈተናዎቹም መካከል በተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃተ ይደርስባት ነበር። ጣሊያን ከጀርመን ጋር በምትዋሰንበት በተራራማዋ ትሬንቲኖ ግዛት ውስጥ ለዓመታት የኖረችው አጊቱ፣ ዘረኝነት ላይ የተመሰረቱ ጥቃቶች ያጋጥሟት እንደነበር ለፖሊስ አመልክታለች። አንዳንዶች በቆዳዋ ቀለም የተነሳ “አስቀያሚ ጥቁር እያሉ ይሰድቡኛል፤ ያለሁበትም ቦታ አገሬ እንዳልሆነ ይነግሩኛል” በማለት በግልጽ ያጋጠሟትን የዘረኝነት ጥቃቶች ስትገልጽ ነበር። ነገር ግን ‘ላ ሪፐብሊካ’ የተባለው የጣሊያን ጋዜጣ እንደዘገበው ፖሊስ ስለግድያው በሚያደርገው ምርመራ ወንጀሉ በአንድ ወጣት አፍሪካዊ ላይ ያተኩራል ብሏል።
ወጣቱ ከዚህ በፊት በአጊቱ ላይ ጥቃትና ማስፈራሪያ ከሰነዘሩት ሰዎች መካከል እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ ምናልባት በገንዘብ ጉዳይ አለመግባባት ሊኖራቸው እንደሚችል ተገምቷል። አጊቱ የሚገጥማትን የዘረኝነት ጥቃት ይፋ ባወጣችበት ጊዜ የግዛቲቱ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኡጎ ሮሲ ድርጊቱን ተቃውመው ከጎኗ ቆመው ነበር።
ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ “አጊቱ ስደተኛ ሆና የእንስሳት እርባታ ሥራዋን በግዛታችን ውስጥ ማከናወን መጀመሯ የትሬንቲኖን እንግዳ ተቀባይነትና ደጋፊነትን ያሳያል” ብለው ነበር። አጊቱ በምትኖርበት ግዛት ውስጥ ሊጠፉ ተቃርበው ነበር የተባሉ የፍየል ዝርያዎችን በማርባት ከወተታቸው የተለያዩ ተዋጽኦዎችን እያመረተች ምርቷ ተወዳጅነትን እሷም ታዋቂነትን አትርፋ ነበር።
ስራና ስራን ብቻ ቋንቋዋ ያደረገች ይህች ሴት፤ የስደት መከራ ገፈት ቀማሽ ለመሆን ብትበቃም ሁሉን ማሸነፍ የሚቻለው በስራ ነውና በምትሰራው የፍየል እርባታና የወተት ተዋጽኦ ምርት ሥራ ውስጥ ለበርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር ኑሯቸውን ቀለል አድርጋላቸው ነበር። ግድያውን መፈጸሙን ያመነው ስደተኛም ለሦስት ዓመታት እሷው ጋር ተቀጥሮ ይሰራ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።
ተጠርጣሪው ከግድያው በኋላ በነበረው ምሽት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ለሰዓታት በሰጠው ቃል ግድያውን መፈጸሙን አምኗል። የግድያው ምክንያት ምን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም በመጀመሪያ ላይ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።
አጊቱ በተገደለችበት ዕለት የግብርና ሥራዋን ለማስፋፋት ከቅየሳ ባለሙያዎች ጋር ቀጠሮ ነበራት። በወቅቱ በቀጠሮዋ መሰረት ባለመገኘቷ በሰዓት አክባሪነቷ የሚያውቋት ሰዎችን ቅር ያስባለ የነበረ ሲሆን ከጎረቤቶቿ አንደኛዋም “ምን ሆና ነው የጠፋችው” በሚል ወደ ቤቷ በመሄድ ወደ መኝታ ቤቷ ሲገቡ ወድቃ እንዳገኟት ጋዜጣው ዘግቧል። ከዚህ በኋላ ነበር ፖሊስ በስፍራው ደርሶ ምርመራውን የጀመረው።
ምርመራ እያደረገ እንደሆነ የገለጸው ፖሊስ እንዳለው፤ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ ጭንቅላቷ ላይ ክፉኛ ተመትታ ጉዳት ደርሶባት አስከሬኗ የተገኘው ባለፈው ማክሰኞ ነበር።
የሞተችው ጭንቅላቷ ላይ በመዶሻ ተመታ ሊሆን እንደሚችልና በግድያው ተጠርጥሮ የተያዘ ጋናዊ ስደተኛ ለፖሊስ በሰጠው ቃል ወንጀሉን መፈጸሙን ማመኑም ተገልጿል። የጣልያኑ ጋዜጣ ኮርየር ዴላ ሴራ እንደዘገበው፤ አጊቱን የገደላት ሠራተኛዋ ጋናዊው ሱሌይማን አዳምስ 32 ዓመቱ ነው። የግድያው ምክንያት ከክፍያ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ አለመግባባት ሊሆን እንደሚችል ተዘግቧል።
የትሬንቲኖ ግዛት የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ሚካኤሌ ካፑርሶ “በአጊቱ እና ሱሌይማን መካከል ጸብ መኖሩን አናውቅም። ከዚህ ቀደም ለስራ ቀጥራው አብሯት ሠርተዋል” ብለዋል። በተጨማሪም አጊቱ ከሁለት ወር በፊት በግድያው የተጠረጠረውን ሱሌይማን አብሯት እንዲሠራ እንደጠራችው ገልጸው፤ የአንድ ወር ደመወዝ አልተከፈለኝም በሚል አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር አስረድተዋል። ግድያው ተጠርጣሪ አጊቱን ቢያንስ ሦስት ጊዜ በመዶሻ እንደመታትና ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሰባት ማመኑንም ኮሎኔል ሚካኤሌ ገልጸዋል።
በሀገራችንም የአጊቱ ሞት ከተሰማ በኋላ ህብረተሰቡ ሀዘኑን በተለያየ መልክ ከመግለፁም ባሻገር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጣሊያን ሃገር በግፍ የተገደለችውን የወይዘሪት አጊቱ ጉደታ አስክሬን በትውልድ ቦታዋ በክብር ለማሳረፍ ወደ ሃገር ቤት እንዲመጣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል። ጥያቄውንም ያዳመጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወይዘሪት አጊቱ ጉደታ አስክሬን ቤተሰቦቿ እና የከተማ አስተዳደሩ ዝግጁ ነን ባሉበት ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል፡፡
ምንም ይሁን ምን የአንድም ዜጋ ደም በከንቱ መፈሰስ የለበትም። የእህታችንን የአጊቱን ደም ያፈሰሱ በህግ አግባብ መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ከዚህም በላይ በውጭ ሀገራት በስደት የሚኖሩ ብቻ ሳይሆኑ በተለያየ መልኩ በየቤታቸው ፆታዊ ጥቃት የሚደርስባቸው እህቶቻችን ጉዳይም ሁልጊዜ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። መሰልጠን ማለት ሰዎች በዘር፣ በቀለም፣ በሃይማኖትና በፆታ መካከል ያላቸውን ልዩነት ወደጎን ትተው ሁሉም ዜጋ እኩል መብት እንዳለው ሲያምኑ ነው።
ታዲያ ፆታዊ ጥቃት ማድረስ ከፀያፍ ስነምግባሮች መካከል አንዱ ሆኖ እያለ ክብር የሆነውን የሰው ደም በከንቱ ማፍሰስና ለሞት መዳረግ ከሰው ተርታ የሚያስወጣ ተግባር ነው። ታላቁ መፅሃፍም ወንድን የቤት ራስ ሲለው በኃላፊነት ሚስቱን እንዲረዳት እንጂ ጡንቻውን አፈርጥሞ ሌላውን ለማጥቃት እንዳልሆነ ልብ ያለው ልብ ይበል።
አጊቱ ጉደታ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 43 ዓመት ይሆናት ነበር። ገና ሮጣ ሳትጠግብ የተነጠቀችን እህታችንን ነፍስ ይማር በማለት ለወዳጅ ዘመዶቿም መፅናናትን ይስጥልን ብለናል።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2013