አዲሱ ገረመው
ነገርን ከማንዛዛት በመቆጠብ ብዙም ቦታ ከመርገጥ በኪነ ጥበብ አክናፍ እየበረርን፣ ጉዳዩ የሚመለከተው ግለሰብ ላይ እያረፍን፣ የተገኘውን እንቃርም ዘንድ ወደድኩ። የወሬ ውላችን ደግሞ ወጣቱ አርቲስት ታምራት እሸቱ ነው ።የውልደቱንና አስተዳደጉን ጉዳይ እንዲሁም ጠቅላላ ነጽሮቶቹን መዘርዝር እናልፋለን።እርሱን (ዝነኛውን) ይዘን ኪናዊ ልዕልና በተስተዋለበት የውሎውና ተያያዥ የስንክሳሩ ጉዳዮች ተሰንጥረን እንገባለን ።ዞሮ ዞሮ ከቤት እንዲሉ በመጨረሻም በጨዋታችን መደምደሚያም አንዳች ቁም ነገር እንጨብጣለን ።ኑማ ተከተሉኝ፡፡
የኪነ ጥበቡን ያጠረ ቀሚስ ጨምድዶ ይዞ፤ እንደ ብሶተኛ ሳያለቃቅስ ተከተላት ።(መቻያውን ይስጠው) የጥበብን ፈለግ ተከትሎ እንዴት በእሱ አቅም ቻለው? የኢትዮጵያውያንን ባህሎች እንዴት መረመራቸው? ከጥበብ ጋር የተያየባትን መንደር ስሟን ከፍ ማድረግ እንዴት ተቻለው? የባህል ውዝዋዜ ዝነኞችን እግር አሻራ በልቡ አጭቆ የያዘው ወጣቱ አርቲስ ታምራት እሸቱ ። የባህል ግዑዛን መድረኮች አንደበት ቢሰጣቸው ለዚህ ሁሉ ምስክርነት በሰጡ ነበር ።
የኪነ ጥበብ ቀሚስ በየዘመኑ ሲያጥርና ሲረዝም ኖሯል። ቀሚሱ ዘርፋፋ ሆኖ ሞገሱ ሲጨምር አለሁልሽ የሚል ከያኒ ይበዛል ።ቀሚሱ ሲያጥር ግን ያጥፋሽ ይበትንሽ የሚላት ይበዛል። ወጣቱ አርቲስት ግን «እንዴት በጥበብ ተስፋ መቁረጥ ይቻለኛል» በማለት የጥበብ ቀሚስ ባጠረ ጊዜ ወደ ኋላ ሳይል ዛሬ ላይ በስኬት ማማ ላይ ተቀምጦ ሌሎችን ማስተማር ይዟል ።
ወጣቱ አርቲስት ታምራት እሸቱ ይባላል ።መሀል ግንፍሌ ሺ ሰማኒያ የምትባለዋ ደግሞ የተወለደባት፣ ያደገባት፣ ኪነ ጥበብን የጀመረባትና ያስተማርባት አድባር ነች ።በኢትዮጵያ የባህል ውዝዋዜ ታሪክ አሻራውን ማኖር የጀመረው ገና ከልጅነቱ አንስቶ ነው ።
ከአገር ፍቅር እስከ ብሔራዊ ቴአትር የውዝዋዜን መድረክ ነግሶበታል ።ከጀማሪ ሙዚቀኞች እስከ አንጋፋዎቹ የክሊፕ ሥራዎች ላይ ተሳትፏል ።በቀለም ትምህርቱ የቢዝነስ ማኔጅመንት ተመራቂ ተማሪና የሲኒማቶግራፊ ምሩቅ ሲሆን፤ የተለያዩ የአገሪቷ ባህሎች ላይ ጥናት በማድረግም ይታወቃል ።የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህልና ትውፊታቸው ተጠብቆ ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ኪናዊነታቸውን ከቀለም ጋር አዋህዶ ለዘመን የዋጀ ከያኒ ነው ።
ሙያውን የተቀላቀለው በአጋጣሚ ቢሆንም ከኪነ ጥበብ ዓለም ጋር ከተቆራኘበት ጊዜ ጀምሮ የነፍስ ጥሪው ኪነ ጥበብ እስኪመስል ድረስ ለሙያው ያለው ፍቅር ማለዳ አዲስ እየሆነ መምጣቱን በአንደበቱ ያስረዳል ።ዛሬ ላይ ዝነኛ የሆነበትን የባህላዊ ውዝዋዜ ወደ ገሀድ እንዲወጣ ያደረገው ደግሞ «ኢትዮጵያዊነት የባህል ቡድን» ነው፡፡
«ኢትዮጵያዊነት» የባህል ቡድን ከተጸነሰበት ጊዜ ጀምሮ በዓላማና በጽናት ለማስጓዝ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል ።የቡድኑ መስራች በመሆኑ ዛሬ ላይ ልበ ሙሉነት ይሰማዋል። አርቲስቱ እንደሚለው ኢትዮጵያዊነት የባህል ቡድን በአገር አቀፍ ደረጃ ያልሰራቸው የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃዊ ክዋኔዎች የሉም ማለት ይቻላል ።በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን በአሜሪካዊው አቀንቃኝ ጄሰን ድሩሎ ክሊፕ ላይ በመሳተፍ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ያደርጋቸዋል ። ከዓመታት በፊት የባላገሩ ምርጥ የተሰጥኦ ውድድር በባህላዊ ውዝዋዜ ዘርፍ አንደኛ በመውጣት የኪነ ጥበቡን ቤተሰብ አስደምሟል ። ታምራት የቡድኑ አጋር በመሆኑ የዚህ ትሩፋቱ ባለቤት ለመሆን በቅቷል ።
ወጣቱ አርቲስት ከመደበኛው ኪነ ጥበባዊ ሥራው በተጨማሪ ትርፍ ጊዜውን በበጎ አድራጎት ሥራ ያሳልፋል። «ሠላም አውለኝ፤ ተመስገን» የሚሉ የፈጣሪ ምስጋና ቃላት በሁሉም የአርቲስቱ የውሎ ቀናት የሚጠሩ ናቸው።ኢትዮጵያዊነት የባህል ቡድንን ጸንሶ የወለደው የአራት ኪሎ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር /ወ.ወ.ክ.ማ/ ባመቻቸው ዕድል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የባህላዊ ውዝዋዜ ተማሪዎችን አፍርቷል ።የእርሱ የኪነ ጥበብ ግርፍ የሆኑ ተማሪዎች ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪ ላይ ትልቅ አበርክቶ አላቸው ።ከአገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ ትልልቅ የሙዚቃ ክሊፖች ላይም ይሳተፋሉ ።
በየዕለቱ ስሜቱን የሚገልጽባቸው ስንኞችን ይሰድራል። እግር ኳስን እንደ ተዝናኖት ይመለከታል። የተለያዩ መጻሕፍትን ያነባል ።ለቤተሰቦቹ ጊዜ ሰጥቶ አብሯቸው ይጫወታል፣ ይዝናናል፣ ይወያያል፣ ይመካከራል ።ቤተ አምልኮ ይሄዳል ።ብዙ አዕምሯዊ እረፍት የለውም፤ ራሱን ንቁ በማድረግ በተለያዩ ሥራዎች ይጠመዳል ።ይህም ራስን በሥራ በመጥመድ መዋል አሉታዊ ጉዳዮች ወደ አዕምሮ እንዳይመጡ ያደርጋል ከሚል ግላዊ እሳቤው የመነጨ ነው ።የተለያዩ ሙዚቃዎችን መድረስ፣ ግጥሞችን ማዘጋጀት፣ አጫጭር ፊልሞችና የቴአትር ጽሑፎችን መድረስም ለአርቲስቱ የተሰጡ «መክሊቶች» ናቸው ።
ለወጣቱ አርቲስት የስኬት ጥግ ወ.ወ.ክ.ማ ትልቅ ድርሻ አለው ።አሁን ላይ የአራት ኪሎ ወ.ወ.ክ.ማን የኪነ ጥበብ ዘርፍ በጽሕፈት ቤት ደረጃ እየመራ ይገኛል ።የተለያዩ የኪነ ጥበብና ሌሎች ማህበራዊ ኃላፊነትን ለተወጡ ሰዎች የሚበረከቱ የምስክር ወረቀቶች ባላገሩ አይዶልን ጨምሮ ከተለያዩ ድርጅቶች ተበርክቶለታል ።በኪነ ጥበቡ ላይ ያለው ጉልህ አሻራ በሚያስተምራቸው ልጆች ውጤት ይገለጻል ።ለሙያው እድገት አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር ላይ ይገኛል ።ለዚህም ማሳያ በዘ-ኢትዮ አቨንት ኤንድ ፕሮዳክሽን የሚዘጋጀው ዘ- ማዕደ ጥበባት የተሰኘ የኪነ ጥበብ መርሀ ግብር ለኪነ ጥበብ አፍቃሪያን እንዲደርስ እያደረገው ያለው ጥረት ይጠቀሳል፡፡
«ዝነኛ ያደረገኝ ሥራዬና ሕዝብ ስለሆነ ሥራዬን የወደደልኝን ሕዝቤን ማገልግል አለብኝ» የሚል ጽኑ እምነት እንዳለው ወጣቱ አርቲስት ይናገራል ።የአገልግሎት ውጤቱም እየታየ ነው ።በአካባቢው የተለያዩ ማህበረሰብ አቀፍ የሆኑ እውቀት ሰጪ ስልጠናዎችን በነፃ ጭምር በመስጠት ከብዙ ፋና ወጊ ወጣት አርቲስቶች ምድብ ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል ።
ዝነኝነት በሰዎች ዘንድ እምነትና ከበሬታን ያጎናጽፋል።ታዲያ ይህን ሆኖ መገኘት የዝነኞቹ ድርሻ ነው። ከዚህ አኳያ አርቲስት ታምራት ተጠቅሞበታል፤ ለበጎ ነገርም አውሎታል ። የብዙ ሕዝብ ኃላፊነት እንዳለበት ስለሚሰማው ውሎውን ለተሻለ ነገር ይጠቀምበታል ።በተለይም ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ጨምሮ ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን የውሎው ውጤቶች ናቸው ።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2013