በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
ገና ወይም በዓለ ልደት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየአመቱ ታህሳስ 29 ፣ በየአራት አመቱ ደግሞ ታህሳስ 28 ቀን የሚከበር ሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓል ነው ። ገና እየሱስ ክርስቶስ የአዳምን ዘር ሁሉ ለማዳን ከሰማይ ሰማያት ወርዶ በመንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማሪያም በበጎች ግርግም የተወለደበት ልደት የሚዘከርበት ዕለት ነው ። ለዚህ ነው የበዓላት ሁሉ በዓል ተደርጎ የሚወሰደው ። የገና ስረወ_ ቃል ( መነሻ )የበዓሉ ሁሉ ንጉስ ፣ ታላቅና ገናናነት ከሚገልጸው “ ገናና “ ከሚለው ቃል የሚመዘዝ ነው። እየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ ቤተልሔም ሲወለደ ከነገስታቱና ከመሳፍንቱ ከእነ ሔሮድሰ ተሰውሮ ለእረኞች ተገልጧል ።
እረኞችም ከመልዓክት ጋር “ ስብሀት ለእግዚአብሔር በሰማያት …” ሲሉ ለክብሩ ዘምረዋል ። አዋቂዎቹ ሰብዓ ሰገሎች የከበረ ስጦታ ይዘው በቤተመንግስት ሲፈልጉት በበጎች ግርግም ነበር የተገኘው ። እነዚህ ተምሳሌቶች እየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ በእግዚአብሔርና በሰው ልጅ መካከል ቆሞ የነበረውን የጥል ግድግዳ ለማፍረስ ፤ እርቅን ሰላምን ለማውረድ መምጣቱን ያበስራል ። ገናን ለ2013 አመታት ጊዜ ስናከብረው ፍቅሩንና ሰላሙን ልብ አላልነውም ። አልኖርነውም ። ገናን ከቅርጫው ከዳቦው ፣ ከድግሱና ሸቀጥ ከመሰጣጣት ባሻገር የልደቱን አብይ አላማ አልኖርነውም ። በተለይ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በሀገራችን የተከሰተው ቀውስ ፣ ጭፍጨፋና የመረረ ጥላቻ ይሄን የሚያረጋግጥ ነው ። እስኪ በልደት መስኮት ሌሎችን ባህላዊ ወረቶቻችንና አኳኋናችንን፤ አከራረማችንን እንቃኝ ።
በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚከበሩ መንፈሳዊና ባህላዊ ሁነቶች የተሸከሙትን ግዙፍ መልዕክቶችና አንድምታዎች አለፍ አለፍ ብለን እየተመልከትን ሒሳብ እናወራርድ ።ፍቼ ጨምበለላ ፣ ቡሔ ፣ ሻደይ ፣ አሸንዳ፣ ሶለል አይነ ዋሬ ፣ እንቁጣጣሽ ፣ መስቀል ፣ መስቀላዮ ፣ አጋመ ፣ ጊፋታ ፣ ኢ ሬቻን ፣ ጋሮ ፣ ቺሜሪ ፣ ትንሳኤ፣ ወዘተ . በአንድም በሌላ በኩል በተለያዩ የሀገራችን ማህበረሰቦች የሚከበሩ ሀይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ክዋኔዎች ናቸው ።
ሁሉም ማለት ይቻላል ተስፋን ፣ ፍቅርን ፣ ነፃነትን ፣ አብሮነትን ፣ አንድነትን ፣ ምስጋናን ፣ እርቅን ፣ ይቅርታን ፣ እኩልነትን ፣ ወዘተረፈ . የሚያውጁ፣ የሚለፍፉና የሚሰብኩ ናቸው ።ግን በነቂስ ወጥተን ለዘመናት በየአመቱ በአደባባይ የምናከብራቸው የምንዘክራቸውን ያህል በዕለት ተዕለት ኑሮአችን አንኖራቸውም ። አንለማመዳቸውም ፡፡
ይሁንና ከገጠሙን ቀውሶች ፣ ፈተናዎች መውጣት ማገገምና ማንሰራራት የቻልነው በቀሩን ሽርፍራፌ እንጥፍጣፌ በባህላዊ ንብረቶቻችን መሆኑን ልብ ይሏል ።ባለፉት 27 አመታት ቀን ከሌት እንደ ተሰበከው ልዩነት ፣ ጥላቻና ዘርኝነት ቢሆን ኑሮ እርስ በእርስ ተበላልተናል ።ተጨራርሰናል ።ለዚህ ነው መዳኛችን ፣ ማገገሚያችንና ማንሰራሪያችን የሆነውን ባህላዊ ወረት ወደሙላቱ መመለስ ለነገ የሚባል ጉዳይ የማይሆነው ።
ባህላዊ ወረታችን ለበጎ አላማ ሲውል ሀገርን ከጥፋት ከእልቂት እሳት እንደሚታደግ በጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ተመልክተናል ።የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ለበቀል ተነስቶ የነበረውን የአርባ ምንጭና የአካባቢውን ወጣት ለምለም ሳር ይዘው ተንበርክከው በመለመን ቁጣውን አብርደው መልሰውታል ።
ይህን የሀገር ሽማግሌዎች ገድል በጥሞና ለተረዳው የአርባ ምንጩን እሳት ብቻ አይደለም ያጠፉት የአርባ ምንጩን ጥፋት ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ ሊዛመት የነበረውን የበቀል ሰደድ እሳት ጭምር እንጅ ።ቁጣ አብራጁ ይህ የጋሞ አባቶች ልመና ( ጋሞ ወጋ ) እየጠፋ ፣ ትኩረት እየተነፈገው ያለው ባህላዊ ወረታችን ተጠብቆ ለትውልድ ሲተላለፍ ሀገርን እንዴት ማዳን እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው ።
የጋሞ አባቶች ከሁለት አመት በፊት ልዩ የበጎ ሰው ተሸላሚ መሆናቸው በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ያለ አንዳንች ልዩነት ዳር እስከዳር አድናቆትን ተቀባይነትን ያተረፈው በዚህ እሳቤ ነው ።ሕግን ለማስከበር ከምናደርገው ጅምር ጥረት ባልተናነሰ በየአካባቢው እንደ ጋሞ ወጋ አይነት የሽምግልና ፣ የእርቅ ባህላዊ ካፒታሎቻችንን ላይም መስራት ይጠበቅብናል ።ከዚህ መሳ ለመሳ የአክራሪነት አዝማሚያ ፣ እኩይ አስተሳሰብ እንዲገታ ብሎም ተሸንፎ ከሰላምና ከእርቅ መንገድ ገለል ፣ ዘወር እንዲል ድልብ የሆኑ ባህላዊ ንብረቶቻችን ጥንስስ ፣ ወረት የማይተካ ሚና አላቸው ።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ባህላዊ ወረቶች ባለፀጋ ስለሆኑ የየራሳቸውን መዋጮ ማበርከትና ወደ ስራ መግባት ይጠበቅባቸዋል ። በየአካባቢያችን ፣ በየቀዬአችን የምናንፀው ፣ የምናቀነቅነው ከባቢያዊ ብሔርተኝነት ወደ አክራሪነት ፣ ፅንፈኝነት የሚያንደረድር ወደገደል አፋፍ የሚገፋ ስለሆነ እነዚህን ባህላዊ ወረቶች በመጠቀም መግታት ያስፈልጋል ።የዜጎች ማንነት እሴት እንደተከበረ ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የሚያደርሰንን ቀና መንገድ በቅንነት መቀላቀል ፣ መያያዝ ይገባል ።
ይህ ሀገራዊ ብሔርተኝነትም ከገደቡ ፣ ከውሃ ልኩ እንዳያልፍ ጥንቃቄ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ ።አይደለም ዘውጌአዊ ፣ ወንዜአዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በአግባቡ ካልተያዘ ፤ የጎረቤቱን የሚጎመጅ ፣ የሚመኝ ፣ የሚመቀኝ ሆኖ የመውጣት አደጋ ስላለው በብልሀት ፣ በማስተዋል ሊቀነቀን ይገባል ።በዛድባሬ ይመራ የነበረው “ የታላቋ ሶማሊያ “ አክራሪ ብሔርተኝነት ለዚህ ጥሩ አብነት ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ጥንታዊ መሆኗን የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ ። ከ3000 እሰከ 8000 አመት የሚደርስ ታሪክ ባለጸጋ እንደሆነች የታመናል ። ጥንታዊነቷ የዳበረ ሀገረ መንግስት ባለቤት አድርጓታል። የደለቡ ባህላዊ ወረቶች ( cultural capitals ) መናኸሪያም ናት ። ባህል ፣ ባህላዊ ንብረትስ ምንድን ነው የሚለውን ለመግባቢያ ያህል እንመለከታለን ።
ባህል ሁሉንም የሚያስማማ የሚያግባባ ወጥ የሆነ ትርጉም ብያኔ ባይኖረውም የአንድ ማህብረሰብ ወይም ሕዝብ ዕምነት ፣ ልማድ ፣ ወግ በኪነ ጥበብ እና በስነ ጥበብ ተዳውሮ ፣ ድርና ማግ ሆኖ ፣ ተሸምኖ፣ ተንሰላስሎ የመገኘት ፣ የመገለጥ ዥጉርጉር ሕብራዊ ቀለም ነው ።በደስታ ፣ በሀዘን ፣ በስራ ፣ በሀይማኖት፣ በትምህርት ፣ ወዘተ . የህይወት አንጓዎች ይገለጻል ።በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ባህልን ፦ የህብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ ፣ ወግ ፣ ልማድ ፣ እምነት ፣ … ።በማለት ሲተረጉመው ።የደስታ ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በበኩሉ ባህል ፦ ልማድ፣ ደንብ ሲል ይፈታዋል ፡፡
ባህላዊ ንብረት ( cultural capital ) የሚለው ሀረግ ፔሬ ቦርዴው በተባለ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ የተነሳ የስነ ሕብረተሰብ ተመራማሪ እንደተፈጠረ የተለያዩ የዘርፉ ድርሳናት ያትታሉ ።ባህላዊ ንብረት በማህበረሰብ ውስጥ ያለን ተቀባይነት ቦታ ከፍ ለማድረግ ዕውቀትን ፣ ፀባይና ክህሎትን የማሳደግ የማካበት ሂደት ነው ።ባህላዊ ንብረት በግለሰብ ፣ በማህበረሰብ ከፍ ሲልም በሕዝብ በሀገር ይሰላል ። የበለፀገ ባህላዊ ንብረት ያካበተ ግለሰብ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ከፍ እንደሚያደርገው ሁሉ ያደገ የለማ ባህላዊ ንብረት ያለው ማህበረሰብ ሕዝብ በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍ ያለ ተቀባይነት ይኖረዋል ።
ባህል ማለትም የህብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ ፣ ወግ ፣ ልማድ ፣ እምነት ፣ ወዘተ . በሂደት በዕውቀትና በክህሎት እየበለፀገ ፣ እየዳበረ ሲሄድ ለሀገር ሰላም ፣ አንድነት ከፍ ሲልም እድገት የላቀ አስተዋጾ ይኖረዋል ።በተቃራኒው ባህል በዕውቀት ፣ በክህሎት ካልበለፀገ አይደለም ለሀገር ሰላምና ዕድገት መዋል ይቅርና የማህበረሰቡን እሴቶች ጠብቆ ማቆየት ካለማስቻሉ ባሻገር የዕለት ተዕለት ችግሮችን እንኳ መፍታት የሚሳነው ይሆናል ።ባህላዊ ንብረት እንደ ኢኮኖሚያዊ ንብረት ማለትም ገንዘብ በአግባቡ ኢንቨስት ተደርጎ ሰላምን ፣ ፍቅርን ፣ እርቅን ፣ መነጋገርን ፣ መቀባበልን ፣ መከባበርን ፣ መተባበርን ፣ አንድነትን ፣ ወዘተ . እውን ማድረግ ካልተቻለ እንደባከነ እንደከሰረ ሊቆጠር ይችላል ።
ሀገርን ሕዝብን ከግጭት ፣ ከቀውስ ፣ ከመፈናቀል ፣ ከመጠራጠር ፣ ከጥላቻ ፣ ከበቀል ፣ ወዘተ . መታደግ አልቻለማ ።እስኪ ለአንድ አፍታ ባህሎቻችንን እምነቶቻችንን ወይም ባህላዊ ንብረቶቻችንን ከዚህ አኳይ እንመዝናቸው ።ባክነዋል ወይስ በአግባቡ ስራ ላይ ውለዋል ! ?
አሁን ከምንገኝበት ሀገራዊ ቁመና አንጻር ባክነዋል ቢባል የሚያስኬድ ይሆናል። ታዲያ እነዚህን ባህላዊ ንብረቶቻችንን እንደ ጦር ዕቃ ለብሶ እንደ ጥሩር ደፍቶ መውጣት መግባት ፣ መመላለስ ለምን ተሳነን ! ? መልሱ ቀላል ነው ።ላይ ላዩን እንከውናቸዋለን እንጅ አንኖራቸውም ።
በቃል እናነበንባቸዋለን እንጂ በልባችን አላተምናቸውም ። ባልንጀራህን ፣ ጎረቤትህን እንደ ራሳህ ውደድ የሚሉ አብርሀማዊ እምነቶችን ማለትም ክርስትናን ፣ እስልምናንና አይሁድን እየተከተልን እንዴት በጥል ግድግዳ ተለያየን ! ? በአንድ አምላክ በዋቄ ፈና እያመንን ኢ ሬቻን በየአመቱ እያከበርን እየከወን ይቅር መባባል ለምን ተሳነን !? መልሱን ለማግኘት ሚስጥሩን ለማወቅ ሞራ ማስገለጥ ወይም ኮከብ ማስቆጠር አያሻም ።
መልሱ ቀላል ነው ።እሱም ባህላዊ ንብረቶቻችንን በሳጥን ቆልፈን እንደ ክት ልብስ በየአመቱ በዓል ለማክበር ስለምናወጣቸው ነው ። አናከብራቸዋለንን እንጂ ስራ ላይ ስላላወልናቸው ( ኢንቨስት ) ስላላደረግናቸው ነው ።ሀገራዊ ሰላምና አንድነት እውን ለማድረግ የተቆለፈባቸውን ባህላዊ ንብረቶች ከሳጥን አውጥቶ እያንዳንዱን ዜጋ በፍጥነት ማልበስን ይጠይቃል ፡፡
እንደ ገና ስጦታ
ባህላዊ ወረታችን ቱባነቱን እንደጠበቀ ማደግ ዘመንና ትውልድ መዋጀት ይጠበቅበታል ።አዎ ! የትውልዱንና የዘመኑን ህፀፅ የሚያርም ለምፅ የሚያነጻ፣ የሚዋጅ መሆን አለበት ። ዘረኝነትን ፣ ጥላቻን ፣ ቂም በቀልን ፣ ደባን ፣ መከፋፈልን ፣ ወዘተ . መቤዥ ፣ መዋጀት አለበት ።ባህላዊ ንብረታችንን ይበልጥ በማጎልበት ፣ በማልማትና በማስፋት ለመጻኢ እድላችን ፣ ለነገ ተስፋችን ፣ ለእርቅ ፣ ለሰላም ፣ ለአንድነት ፣ ለሁለንተናዊ ብልፅግና ፣ ወዘተረፈ ልናውለው ይገባል ።ስኬቶቻችንን የምናወድስበት ፣ ፈተናዎቻችንን የምንሻገርበት ነገአችንን የምንተልምበት ጭምር አድርጎ ስለመጠቀም አብክረን ማሰብ ያስፈልጋል ።የፍቅር ፣ የእርቅ ፣ የሰላም ፣ የአብሮነት ፣ የማካፈል ፣ የመተባበር ፣ የመተጋገዝ ፣ የመረዳዳት ፣ የምስጋና ፣ ወዘተረፈ . ባህሎች ፣ ልማዶች ፣ ዕምነቶች ፣ ሀይማኖቶች ከፍ ሲልም ድምር ባህላዊ ንብረቶች ባለቤት እንዲሁም የጥንታዊት ሀገር ባለቤት ሆነን አንድነትን በመከፋፈል ከሰዋን ፣ ፍቅር ከጎደለን ፣ እርቅ ከገፋን ፣ ሰላም ከራቀን ፣ አብሮነትን በቀዬአዊነት ከተካን ፣ ማካፈልን በስስት ከቀየርን ፣ መተባበርን በመለያየት ከለወጥን ፣ ምስጋናን በእርግማን ከተካን ፣ ወዘተረፈ . ምኑን ሙሉኡ ሆነው !? ባለፉት ሶስት አመታት ያለፍንባቸው ሀገራዊ ውጣ ውረዶች ፣ አሳፋሪ ድርጊቶች እውነት የእነዚህ ሁሉ መንፈሳዊና ባህላዊ ፀጋዎች ባለቤት ስለመሆናችን የሚመሰክሩ ናቸው !? ከሀዲው ትህነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ግፍና ክህደት ፤ በማይካድራ ሳምረ በተባለ የትህነግ ገዳይ የወጣት ቡድን በአማራ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ፤ በመተከል በተደጋጋሚ በዚሁ ማህበረሰብ ላይ እየፈጸመ አረመኔያዊ ግፍ ፤ ሸኔ_ኦነግ በኦሮሞና በሌሎች ማህበረሰቦች ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ፤ የአርቲስት ሀጫሉን ሞት ተከትሎ የተስተዋለው አውሬነት ፤ በመሀላችን እየጎነቆለ ያለ ጥላቻ ፣ ቂም በቀል ፣ ልዩነት ፣ ጎሰኝነት ፣ ወዘተረፈ በአብነት ስንመለከት የደለበ ባህላዊ ወረቶች ባለቤት ካለው ሕዝብና ታሪክ የሚጠበቅ አይደለም ። ስለዚህ ገናንም ከገና ባሻገር ሌሎች ባህላዊ ወረቶቻችንም በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ልንኖራቸው ልንገልጣቸው ይገባል ።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2013