አስናቀ ፀጋዬ
የአማራ ክልል በተፈጥሮ ማዕድን ሀብት ባለፀጋ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ሀብቱን ጥቅም ላይ እንዳያውል በርካታ ችግሮች እንዳሉ ከክልሉ የመአድን ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የክልሉን የማዕድን ሀብት በሚፈለገው መጠን በጥናት አለመለየትና ተገቢ የሆነ የማዕድን ሀብት ጥበቃና ቁጥጥር ባለመኖሩ ሕገ ወጥ የማዕድን ምርትና ዝውውር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መሄድ ከችግሮቹ ውስጥ አንዱ መሆኑንም መረጃው ያሳያል፡፡
በነፃ ውድድር የሚሰራ የግብይት ሥርዓትና የገበያ ትስስር በሚፈለገው መልኩ አለመፈጠሩና ግብይቱም በሕገወጥ መንገድ ስለሚካሄድ መንግሥትም ሆነ የማዕድን አምራቾች ከዘርፉ የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ እንዳልሆነም መረጃው ያመለክታል፡፡
አቶ ፀሐዬ ካሳ የዋግኸምራ ዞን የማዕድን ሥራዎች ፍቃድ አስተዳደር ቡድን መሪ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በዞኑ በዋናነት ብረት፣ ሴራሚክ፣ እምነ በረድ፣ ወርቅ፣ ኦፓልና ኳርትዝን የመሳሰሉ ከአሥራ ሰባት በላይ የሚሆኑ በርካታ ማዕድናት ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ማዕድናት ውስጥም እስከ 53 ዓመት ድረስ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ሴራሚክ እንዳለ በጥናት ተረጋግጦ ሥራ ተጀምሯል፡፡ በተመሳሳይ 200 ዓመታት ያህል ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ብረት እንዳለም በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር መጠናቱንና በአካባቢው 23 ካራት ወርቅ እንዳለም ተረጋግጧል፡፡
ከሴራሚክ፣ ብረትና ወርቅ ውጪ ያሉት ማዕድናት ክምችታቸውና መጠናቸው እስካሁን ድረስ በጥናት አመረጋገጡንና የማስተዋወቅ ሥራም በስፋት አለመሰራቱን ይናገራሉ፡፡ ሦስቱ ምርቶች በጥናት የተረጋገጡ ቢሆንም በተለይ ሴራሚክና የብረት ማዕድን ሀብቶች ገና ወደ ማምረት አልተገባም፡፡ በባህላዊ መንገድ ግን የተደራጁ ወጣቶች ወርቅ እየተመረተ ይገኛል፡፡
እንደ ቡድን መሪው ገለፃ በጥናት የተረጋገጡ የማዕድን ሀብቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ዞኑ የሚመለከታቸውን አካላት በተለይም ክልሉንና የክልሉን የማዕድን ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ጠይቋል፡፡ ባለሀብቶች ወደዞኑ መጥው ሥራ እንዲጀምሩ የተለያዩ የማስተዋወቅ ሥራዎችንም እያከነናወነ ይገኛል፡፡ እስካሁንም በዞኑ ያለውን የማዕድን ሀብት አውጥቶ ጥቅም ላይ ማዋል ያልተቻለው ዞኑ ያለውን ሀብት በስፋት ባለማስተዋወቁ ነው፡፡
የማዕድን ሀብቱ ክምችትና የምርት መጠን ታውቆ ባለሀብቶች በዘርፉ ገብተው መሥራት ለሚፈልጉ በሚገባ አልተዋወቀም፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የዞኑን ማዕድን ሀብት የሚያስተዳደር ባለቤትና አደረጃጀት አለመኖሩ የማዕድን ሀብቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል እክል ፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት በዘርፉ ሥራ የጀመሩ ባለሀብቶች እስካሁን የሉም፡፡ እነዚህን ችግሮች ቀርፎ የማዕድን ሀብቱን ጥቅም ላይ እንዲውል ከማድረግ አንፃር የዞኑ የማዕድን ሥራዎች ፍቃድ አስተዳደር ችግሮቹ እንዲፈቱ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ከማቅረብ በዘለለ የሠራው ሥራ የለም፡፡ እስካሁን ለተጠየቀው ጥያቄ ምንም ዓይነት ምላሽ አላገኘም፡፡
የደላንታ ወረዳ የማዕድን ሀብት ልማት ፈቃድ መስጠትና ማስተዳደር ቡድን መሪ አቶ በርይሁን አበረ እንደሚሉት በወረዳው በዋናነት የኮንስትራክሽን ማዕድናት አሸዋ እና የጥርብ ድንጋይ ይገኛል፡፡ የኦፓል ማዕድንም በወረዳው ባሉ 27 ቀበሌዎች ውስጥ በስፋት ይገኛል፡፡
የኮንስትራክሽንም ሆነ የጌጣጌጥ ማዕድን ሀብቱ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ባህላዊ የማዕድን አምራቾችን በማደራጀት ሲሆን በተለይ ደግሞ በጌጣጌጥ ማዕድን ዘርፍ 27 ማህበራት ተደራጅተው በማምረት የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸው ለማዕከላዊ እና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
ቡድን መሪው እንደሚሉት የማዕድን ሚኒስቴር በፌዴራል ደረጃ ቢቋቋም አደረጃጀቱ ታች ድረስ ባለመውረዱና በቂ የሰው ኃይል ያለው ባለመሆኑ የማዕድን ሀብት በአግባቡ እየተመራ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን ሕጋዊ አምራቾችን ማደራጀት ቢቻልም ሕገወጥ የማዕድን አመራረት በሚፈለገው ልክ መቆጣጠር አልተቻለም፡፡
የመዋቅር ችግር፣ የሰው ኃይል እጥረትና ቋሚ የሆነ መሥሪያ ቤት አለመኖርም የማዕድን ክትትልና የቁጥጥር ሥራውን ለመሥራትና የወረዳውን የማዕድን ሀብት ለመመራት አላስቻለም፡፡ በሰው ኃይል እጥረት ምክንያትም የማዕድን ሀብቱን በእውቀት ላይ ተመስርቶና ጥናት አድርጎ ለመለየት አልተቻለም፡፡ አምራቹም ምርቱን አምርቶና ሕጋዊ ደረሰኝ ቆርጦ በመሸጥ ለወረዳው ግብርና ሮያሊቲ በማስገባት በኩልም ክፍተት ይታያል፡፡
እንደ ቡድን መሪው ገለፃ እነዚህን ችግሮች በጊዜያዊነት ለመፍታት በተለይ የዞኑ የማዕድን ዘርፍ መዋቅሩን ለማስተካከል እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ይሁንና አሁንም ድረስ ውጤት ማምጣት አልተቻለም፡፡ በቀጣይም በወረዳው ያለውን የማዕድን ሀብት በአግባቡ በመምራት የሚፈለገውን ጥቅም እንዲሰጥ ለማድረግ የፌዴራል ተቋሙ እገዛ አድርጎ መዋቅሩ ታች ድረስ እንዲወርድና በሰው ኃይል እንዲሟላ ለክልሉ ጥያቄ ቀርቧል፡፡
የወልድያ ከተማ አስተዳደር የማዕድን ሥራዎች ፍቃድ አስተዳደር ቡድን መሪው አቶ ደጀኔ ይርሳው በበኩላቸው እንደሚሉት በከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ የማዕድን ሀብቶች ያሉ ሲሆን በብዛት ግን ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ አሸዋ፣ ጥቁር ድንጋይና ገረጋንቲ የመሳሰሉ ሀብቶች ይገኛሉ፡፡ በነዚሁ የኮንስትራክሽን ማዕድናት ውስጥም የተለያዩ ወጣቶች ተደራጅተው በማምረት ላይ ናቸው፡፡
እንደ ቡድን መሪው ገለፃ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የሚገኘው ማዕድን በጂኦሎጂካል ሰርቬይ በዝርዝር የተጠና አይደለም፡፡ ሆኖም ይህን ችግር ለመፍታት ከከተማው የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበርና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂካል ትምህርት ክፍል ጥናት እንዲያካሂድ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
በከተማው በቂ የሆነ የኮንስትራክሽን ማዕድን ሀብት በተለይም የካባ ድንጋይ ካለመኖሩ ጋር በተያያዘም በሚፈለገው ልክ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር አልተቻለም፡፡ የመንግሥትንም ሆነ የግል ሥራ ተቋጮችን የኮንስትራክሽን ማዕድናት ፍላጎት በሚፈለገው ልክ ማርካትም አልተቻለም፡፡ እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት በከተማው ያለውን የማዕድን ሀብት የመለየትና የማጥናት ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የካሳ ግመታ ኮሚቴ በማቋቋም የማዕድን ማውጫ ቦታ ተለይቶ ሥራ ላይ እንዲውል እንቅስቃሴም ተደርጓል፡፡ በይበልጥ ደግሞ የከተማው ማስተር ፕላን ሲከለስ የገጠር ቀበሌዎች በከተማው ሥር ስለሚካለሉ ከሥራ ዕድል ፈጠራና፣ ከሥራ ተቋራጮች በኩል ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል፡፡
በዋናነት ደግሞ የማዕድን ዘርፉ ትልቅ የአደረጃጀትና የመዋቅር ክፍተት ያለበት ከመሆኑ አኳያ የሚታየው የአደረጃጀት ክፍተት የክልሉ መንግሥት በአፋጣኝ መሙላት የሚችል ከሆነ በከተማው ያለው የማዕድን ሀብት በሚፈለገው ልክ ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ በዘርፉ የሚታየው ሰው ኃይል እጥረት በቀጣይ ሊፈታ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 03/2013