ዳንኤል ዘነበ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችን የሰላም ጉዳይ አሳሳቢነቱ ጣሪያ ከነካ ውሎ አድሯል። በተለይ ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዩኒቨርሲቲዎች የጸጥታ ስጋት ያረበበባቸው ሆነዋል። በ2012 ዓ.ም በሀገሪቱ ከሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች 22ቱ ግጭት ያስተናገዱ መሆኑን ልብ ይሏል። በዩኒቨርሲቲዎቻችን አካባቢ እየተፈጸሙ ያሉት ተግባራት ደግሞ አንገት የሚያስደፉ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲዎቹ በፖለቲካ እና በዘር ቆጠራ ተጽዕኖ በመውደቅ፤ ምክንያት አልባ በሆነ መልኩ ከፀብ አልፈው ወደ ሞት መናኸሪያነት እስከመለወጥ መድረሳቸው በእርግጥም አንገት ያስደፋል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከትውልድ አካባቢያቸው ርቀው ለመማር ፍላጎት እንዳይኖራቸው እስከማድረግ የደረሰ ነበር። ይህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችን ከምርምር ማዕከልነት ወደ ፀብ ማእከልነት ከመውረዳቸው ይመነጫል።
በሀገሪቱ በሚገኙ አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ሲከሰቱ በነበሩ ግጭቶችና ብጥብጦች የትምህርት ዘመን ቆይታቸውን አስፈሪና በስጋት የታጨቀ እንዲሆን ያደረገው መሆኑን ይናገራል። ታህሳስ 17 ቀን 2013 ዓ.ም አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባስመረቀበት ወቅት ካነጋገርናቸው ተማሪዎች መካከል በሜካኒካል ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ የተመረቀው ሰለሞን ዘሪሁን እንደሚለው፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ወቅት አስቸጋሪ የሚባሉ ጊዜያት እንዳሳለፈ ይናገራል።
በየዩኒቨርሲቲዎቹ ብሔርን፣ ሀይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች፣ ብጥብጦች በሚነሱበት ወቅት ይሰማው የነበረው ስጋት ዛሬም ድርስ የሚረብሹት መሆኑን ይገልጻል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግጭቶች ባይነሱም፤ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በሚቀሰቀሱበት ወቅት ስጋት ይፈጠር ነበር። በየዩኒቨርሲቲዎቹ ሲነሱ የነበሩት ግጭቶችና ብጥብጦች ደግሞ ብሄርን፣ ሀይማኖት፣ ከጎሳ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ናቸው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቹ የጸጥታ ስጋት ወደመሆን ያሸጋገሯቸው ምክንያቶች ሲፈተሹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶችን ቁመናን የማይመጥኑ እንደሆኑ ይሰማኛል ይላል።
ዩኒቨርሲቲዎች የአእምሮ ማዳበሪያ፣ ማበልጸጊያ፣ የምርምርና የእውቀት መፍለቂያ ቢሆኑም፤ በሀገራችን ግን እነዚህ እውነታዎች እየከሰሙ መምጣታቸውን አመላካች መሆኑን የሚያነሳው ተመራቂ ተማሪ ሰለሞን፤ በዩኒቨርሲቲዎቻችን አካባቢ እየተፈጠሩ ካሉት ግጭቶችና ብጥብጦች ‹ዩኒቨርሲቲ› የሚለው ስያሜ ዩኒቨርሳል ከሚለው ትርጓሜ የመጣ እንደመሆኑ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች አለም ዓቀፍ እሳቤዎች ማንፀባረቂያ እንደሆኑ ይታሰባል። በዩኒቨርሲቲዎቻችን ከሰላም ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ስንገመግማቸው አሳማኝ እንዳልሆኑ ያብራራል።
«በየዩኒቨርሲቲዎቻችን አካባቢ ብሄርን፣ ሀይማኖትን፣ የፖለቲካ አመለካከትን መሰረት አድርገው ግጭቶች ሲነሱ ታዝበናል። እነዚህ ሁኔታዎች የከፍተኛ ተቋማቶቻችንን ደረጃ እንድንጠራጠር የሚያደርግ ነው። በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሊደርሱበት የሚገባው የአስተሳሰብ ደረጃ አንድነትንና አብሮነትን ይዞ እየተጓዘ እንዳልሆነ እንድናስብ አድርጓል» ይላል ሰሎሞን።
በኢኮኖሚክስ ትምህርት ዘርፍ የተመረቀችው ወይንሸት አስፋው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ግጭቶችን ለመቀስቀስ ሙከራዎች እንደነበሩ ታስታውሳለች። በተለይ በ2012 ዓ.ም በአብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭትና ብጥብጥ በሚያስተናግዱበት ወቅት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመሳሳይ ብጥብጥ በብሔር፣ በሀይማኖት ግጭቶች እንዲነሱ አንዳንድ ተማሪዎች ሙከራዎችን ሲያደርጉ ነበር። ነገር ግን በተማሪዎች አርቆ አሳቢነት ለመክሸፍ መቻሉን ነው ያስረዳችው። በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ብጥብጦች በተማሪዎች መካከል የእርስ በእርስ ጥርጣሬ፤ አለመተማመን ይፈጠር እንደነበር ትገልጻለች። በሀገራችን በአብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ ግጭቶችና ብጥብጦች፤ የስጋት ተጽእኖው በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለሚማሩ ተማሪዎች ስጋት የሚፈጥርና ትልቅ የስነልቦና ጫናን የሚፈጠር በመሆኑ፤ እኛም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተዘዋዋሪ የጉዳቱ ሰላባ ነበርን ስትል አስታውሳለች።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፀጥታ ችግር ባይከሰትም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ግጭትና ብጥብጥ በሚከሰትበት ወቅት ስጋቱ አይቀሬ ነበር የምትለው በኢኮኖሚክስ የተመረቀቸው ወይንሸት፤ በተማሪዎች መካከል አለመተማመን እስከመፍጠር የሚደርስ መሆኑን ትናገራለች። በየዩኒቨርሲቲዎቹ ሲነሱ በነበሩ ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች የተነሳ በወላጆቻችን ላይ ትልቅ የስነልቦና ቀውስ ያደረሰ መሆኑን ታስረዳለች። «በአብዛኛው ወላጅ ዘንድ የነበረው ስሜት ተመሳሳይነት ነበረው። በዩኒቨርሲቲዎች ሲፈጠሩ ከነበሩ አስከፊ ክስተቶች የተነሳ ወላጅ ልጆቹን በኩራት ሳይሆን በሥጋት እስከመላክ ያደረሰው ሲሆን፤ አንዳንድ ወላጆች ሥጋቱ አይሎባቸው ልጆቻቸውን በመጨረሻው ሰዓት ከትምህርት ገበታ ያስቀሩም እንደነበሩ በቅርበት እናውቃለን» ትላለች።
ተመራቂ ተማሪዋ ወይንሸት በየዩኒቨርሲቲዎቹ ከፀጥታ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች በእኛ ላይና ከእኛ በፊት በነበሩት ተማሪዎች እንደተፈጠረው ሁሉ በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሊደገሙ እንደማይገባቸው ታመላክታለች። በተለይ ባለፈው የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲዎቻችን ሲስተናገዱ የነበሩት አሰቃቂ የሞት ዜናዎች በፍጹም መደገም የለባቸውም። «ስለዚህ የዩኒቨርሲቲ ነባር ተማሪዎች ሆነ ወደ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የሚገቡት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት ለመማር እንደሆነ መረዳት አለባቸው። በዩኒቨርሲቲ ቆይታ ሲያደርጉ ትኩረታቸውን ወደ ትምህርት ማድረግ ይኖርባቸዋል» ስትል ምክሯን ለግሳለች።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ አመት ካስመረቃቸው ተማሪዎች አንዱ የሆነው ኤፍሬም ተፈራ፤ ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ምክንያት አልባ በሆነ መልኩ የፀብ መናሃሪያ እንዲሆኑ፤ ብሎም ወደ ፀብ ሜዳነት እንዲቀየሩ ያደረገ መሆኑን በመግለጽ ንግግሩን ይጀምራል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቹ በአብዛኛው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ዥዋዥዌው እና የዘር ቆጠራ ተጽዕኖው ስር እንደወደቁ መገንዘብ ይቻላል። በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ በሚገኙት አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደታቸውን መከወን እንዲቸገሩ ያደረጋቸው ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ከክልላቸው ውጪ ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አንሄድም እስከማለት መድረሳቸውን ያስታውሳል።
የ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን በማሳያነት የሚጠቅሰው ተማሪ ኤፍሬም፤ በዚህ አመት በርካታዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች በብጥብጥና በረብሻ ሲናጡ ነበር። ዩኒቨርሲቲዎቹ በብጥብጥ የሚናጠውን ግቢያቸውን መልክ ማስያዝ ተስኗቸው ሊዘጉ ቋፍ ላይ በደረሱበት ወቅት ኮሮና እንዳስተነፈሳቸው ይናገራል። ጥቂት ዩኒቨርሲቲዎችም ቀድመው ተዘግተውም እንደነበር ያስታውሳል። በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ለሚነሱ ብጥብጥ፣ ግጭቶቹ መንስዔአቸው በአብዛኛው ተመሳሳይ የነበሩ ሲሆን፤ የሀገርን ሰላም የማይሹ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ሆን ተብሎ የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎችን በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለመሰብሰብ በተሰሩ ሴራዎች ጥፋቶቹ ሊደረሱ እንደቻሉ መረዳቱን ይናገራል።
የዩኒቨርሲቲዎችን ቁመና ከምርምር ማዕከልነት ወደ ግጭት ማዕከልነት የለወጡ እነዚህና መሰል ችግሮችን በ2013 ዓ.ም መፍትሄ ማግኘት ይኖርባቸዋል ያለው ተማሪ ኤፍሬም፤ ለዚህ ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢው ያለውን ማህበረሰብ፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ የአካባቢው ፖሊስና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላትን በማካተት ሰላም ላይ የሚሠራ አደረጃጀት መፍጠር የሚገባ መሆኑን ያመላክታል።
ሰላምን በተመለከተ ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ እንዲሁም ለጥበቃ ሠራተኞች ግንዛቤ መፍጠር መቻሉ ሌላው የመፍትሄ መንገድ እንደሆነ ያመላክታል። በዩኒቨርሲቲዎች ከአስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚታዩ ድክመቶችን መቅረፍ የሚገባ መሆኑንም ጠቅሶ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ተማሪዎችን ደህንነታቸውን ተጠብቆ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲከውን ማድረግ መቻላቸውን ያነሳል። «ስለዚህ እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ፤ የሌሎች ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ራሳቸውን በሚገባ በመፈተሽ መስራት ከቻሉ መጪው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር እንጂ የፀብ ማዕከል አለመሆናቸውን ማረጋገጥ ይቻላል» ሲል መፍትሄ ያለውን ሀሳብ አመላክቷል።
በአጠቃላይ ሰሞኑን በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን በመጥራት ላይ የሚገኙ ሲሆን ተማሪዎችም ሰላምን ሰንቀው ወደ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ለማቅናት ዝግጅት ለማድረግ ደፋ ቀና ሲሉም ይታያል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎች በ2013 የትምህርት ዘመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን በማስጠበቅ ተማሪዎች ያለ ስጋት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ ትልቁና ዋነኛው የቤት ስራቸው መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን ጥር 03/2013