
”ሁለት ልጆቼ ክፍል ውስጥ እየተማሩ ሳሉ በአቅራቢያቸው በሰሙት ተኩስ በመረበሻቸው እስካሁን ክፍል ውስጥ ሆነው ሲማሩ ይባትታሉ” የሚሉት የአማራ ክልል የማዕከላዊ ጎንደር ደምቢያ ወረዳ አይምባ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ በተሃ አቻምየለህ ናቸው። በትምህር ቤት አካባቢ እንዲህ ዓይነት የሚረብሹ እና የሚያውኩ ተግባራት መፈፀም በሕፃናት ስነ ልቦና ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ብርቱ ስለመሆኑም ይናገራሉ።
የእሳቸው ልጆች በግጭቱ የደረሰባቸውን ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ተቋቁመው እየተማሩ ቢሆንም በግጭቱ የተነሳ ሌሎች ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ተማሪዎች በአካባቢያቸው ተፈጥሮ በነበረው ሁኔታ ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ስላሳደረባቸው ትምህርት ለማቋረጥ የተገደዱበት ሁኔታ ስለመኖሩም ያነሳሉ። ወላጆችም እንዲሁ በግጭቱ ተማርረው «ልጆቻችን ተምረው እውቀት ይቀስማሉ ማለት ዘበት ነው ብለው ከእንግዲህ ወዲህ ትምህርት ቤት አንልክም » እስከማለት የደረሰበት ስለመኖሩም ነው የነገሩን። በአጠቃላይ በአማራ ክልል ያለው ግጭቱ ሴት ተማሪዎች ወደ ትዳር፤ ወንድ ተማሪዎች ወደ እርሻ እንዲሰማሩ የሆነበትን የጨለማ ዘመን በመፍጠር አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረም ነው ብለዋል ወይዘሮ በተሃ።
”ልጄ ትልቅ ሕልም ነበራት። አንደኛ የምትወጣ የደረጃ ተማሪም ነበረች ” የሚሉት ደግሞ በምስራቅ ጎጃም ዞን ጎንቻ ሱስነሴ ወረዳ ነዋሪው አባት በላይ በለው ናቸው። እኝህ አባት እንደሚሉት ልጃቸው ትማርበት የነበረው ትምህርት ቤት በግጭቱ ጉዳት ደርሶበታል። አካባቢያቸውም በግጭቱ በእጅጉ በመጎዳቱ እሳቸው እና ቤተሰባቸው አካባቢያቸውን ለቅቀው ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ ተገድደዋል። እዚህ አሁን ባሉበት አካባቢ ደግሞ ትምህርት ቤት የለም። ራቅ ብሎ ቢኖርም የተረጋጋ ሰላም ባለመኖሩ ትምህርት በወቅቱ አልተጀመረም። በመሆኑም ልጃቸውም እስከ አሁን ድረስ መመዝገብ አልቻለችም። በቀጣይ ዓመት ግጭት ወደ ሌለበት ከተማ በመላክ ቤት ተከራይታ ወይም ዘመድ ጋር ተቀምጣ እንድትማር ስለማሰባቸውም አቶ በላይ ነግረውናል። በግጭቱ ምክንያትም ሆነ ግጭት በሌለበት ሁኔታ ሴት ተማሪዎች ላይ በአካባቢው ሊፈፀም የሚችል ጠለፋ እና ሌላ በርካታ ጾታዊ ጥቃት ሊኖር ስለሚችል እስከዛው ልጃቸውን እየጠበቁ እንደሚቆዩም ነው የተናገሩት። ”ልጄ ትልቅ ደረጃ የመድረስ ሕልም ያላትና ጎበዝ ተማሪ ነች። ትዳር ባትጠላም ትምህርቷን እስከመጨረሻው ሳታጠናቅቅ ትዳር ውስጥ መግባት እንደማትፈልግም ነግራኛለች። ስለዚህ ሕልሟን እንድታሳካ እስከመጨረሻው ከሚያሰናክሉ ተግዳሮቶች፤ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች የግጭት ሳይሆን እንደ ድሮው ተመልሰው የእውቀት አውድማ እስኪሆኑ እንጠብቃለን ” ብለዋል።
በኢትዮጵያ እዚህም እዛም በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የነዚህ ወላጆች ልጆች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች በርካታ ሕፃናት ዛሬም ከትምህርት ገበታቸው ለመራቅ ተገድደዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ (ፕ/ር) ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ በአማራ ክልል የትምህርት ንቅናቄ መድረክ ላይ ተገኝተው ነበር። በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ግጭት ብሎም ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ በተከሰተባቸው ክልሎች በርካታ ሕጻናት እና ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል። የሚኒስቴሩ መረጃዎች የሚያሳዩትን ዋቢ አድርገው በቁጭት እንዳነሱትም በ 2017 ዓ.ም ትምህርት ዘመን እንደ ሀገር ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ከነበረባቸው ውስጥ ከሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም ብለዋል።
በአማራ ክልል ብቻም አሁን ባለው ግጭት ምክንያት ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ለመሆን ስለመገደዳቸውም ገልፀዋል። ከ 3 ሺህ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸው በመስተጓጎሉ ተማሪዎቻቸውን ሊመዘግቡ እና ሊያስተምሩ አለመቻላቸውንም አውስተዋል። በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ በተዘጋጀው የትምህርት ንቅናቄ መድረክ ላይ ”ትምህርት የረጅም ጊዜ ሥራ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ ትምህርት በአንድ ዓመት እና በሁለት ዓመት ሲቋረጥ የሚፈጠረው የሥነ ልቦና ጫና እጅግ ከባድ ስለመሆኑም ደጋግመው ለታዳሚው አስገንዝበዋል።
በተለይ ከትጥቅ ግጭቱ ጋር ተያይዞ እነዚህ ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎች ተመልሰው በመግባት ትምህርታቸውን ቢከታተሉ እንኳን የደረሰባቸው የሥነ ልቦና ቀውስ ትምህርት የመቀበል አቅማቸውን በብርቱ እንደሚጎዳው ነው በአጽንዖት የተናገሩት። በግጭት ጊዜ ያለፈውን ትምህርት ለማካካስ ለትምህርት ተቋማትም ሆነ በተለይ ለተማሪዎቹ በእጅጉ አስቸጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ እንዳለም ነው ያመለከቱት።
(ፕ/ር) ብርሃኑ እንዳከሉት እንደምንም አካክሰው እንኳን ትምህርታቸውን ቢቀጥሉ በዕድሜ ከእነሱ ካነሱ እና ከታናናሾቻቸው ጋር መማራቸው ጫናውን በብርቱ የጎላ እንደሚያደርግባቸውም አንስተዋል።
ግጭት የልጆቻችንን የወደፊት ዕድል ክፉኛ እንዳያበላሽ መጠንቀቅ፤ በግጭቶች አካባቢ ያሉ ትምህርት ቤቶች ዓለም አቀፍ ሕግጋት እንደሚያዙት ከማንኛውም ወገን ጥቃት እንዳይደርስባቸው እና ልጆች ትምህርታቸው እንዳይሰናከልባቸው ማድረግ ይገባልም ብለዋል። ይሄን ለማድረግ የወላጆች እና የአካባቢው ማሕበረሰብ ሚና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባውም ያሳስባሉ። በተለይ ከሴቶች ትምህርት ጋር ተያይዞ ግጭት ባለባቸው አካባቢ ያሉ ወላጆች፤ ትምህርት ተቋማት ብርቱ የቤት ሥራ የሚጠብቃቸው መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ሳያሳስቡ አላለፉም።
‹‹በኢትዮጵያ ሴቶች ለመማር ብዙ ዋጋ የሚከፍሉበት ሁኔታ አለ›› ያሉት (ፕ/ር) ብርሃኑ ከማሕበረሰቡ ጀምሮ ለሴቶች ትምህርት ያለው ቅበላ አናሳ መሆኑን በማሳያነት ይጠቅሳሉ። ይሄን አመለካከት በመለወጥ የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ ማሳደግ ግድ እንደሚልም አንስተዋል። ፖሊሲዎች እና መመሪያዎች ሲረቀቁ ትጥቅና ግጭት በነበረባቸው እና ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ሴት ተማሪዎችን ታሳቢ እንዲያደርጉ እየተሰራ ስለመሆኑ ይናገራሉ። ሥራው በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍልም ሆነ በየክልሉ ተደራራቢ ጉዳት ያስተናገዱ ሴት ተማሪዎችን ትኩረት ያደረገ መሆኑን አውስተዋል።
በአጠቃላይ ሴቶች በትምህርት ገበታ ከሚገጥማቸው ተግዳሮት ጋር ተያይዞ ችግራቸውን ለመፍታት የሚሰሩ ሥራዎች ስለመኖራቸው ይናገራሉ።
ሚኒስትሩ (ፕ/ር) ብርሃኑ የትጥቅ ግጭት ሴት ተማሪዎችን ከምንም በላይ ተጎጂ ያደርጋል፤ ለስነ ልቦና ስብራት ይዳርጋል። ሴቶች እንኳን በትጥቅ ግጭት ወቅት በመደበኛው የትምህርት ጊዜም ቢሆን ከትምህርት ገበታቸው የሚያስተጓጉላቸው በርካታ ተግዳሮቶች አሉባቸው። ይሄንኑ በመፍታት ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ሁሉም አካላት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
‹‹ትምህርት ቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ነው›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሕጻናት የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን የሚገነቡበት፣ ችሎታቸውን የሚከፍቱበት ቁልፍ መሣሪያ እና ድልድይ ስለመሆኑም ያስረዳሉ። ነገር ግን በብዙ የዓለም ክፍሎች የሚካሄድ ግጭት እና ጦርነት ይህን መብት እየጣሰ ስለመገኘቱም አብራርተዋል። ግጭት በተለይም የትጥቅ ግጭት የሚያስከትለው መዘዝ ዘርፈ ብዙ፤ ተፅዕኖውም ከፍተኛ ነው።
በምሳሌነት እንደጠቀሱትም ትምህርት ቤቶች ያወድማል፤ መምህራንን ያፈናቅላል፣ ቤተሰቦች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ወደ ሌላ ወደ ማያውቁት ቀዬ እንዲሰደዱ ያደርጋል። በብዙ ዘመን እና ድካም የተገነባውን የሕብረተሰቡን መዋቅር ያፈርሳል፤ የሕጻናት እና ወጣቶችን ብሩህ የወደፊት ተስፋ በብርቱ ይሸረሽራል። በኢትዮጵያም በተለያዩ ክልሎች የተነሱ ግጭቶች አሁን ላይ በትምህርት ዘርፉ እየተደረገ ያለውን የለውጥ ሂደት ክፉኛ እየተፈታተኑት ስለመሆናቸውም አልሸሸጉም። ከትጥቅ ግጭት ጋር የተያያዘ እና በሴት ተማሪዎች ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ጾታዊ ትንኮሳ እና ጾታዊ ጥቃቶች በተለይ የሴት ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማረጋገጥ ትልቅ እንቅፋት እየሆኑ ስለመሆናቸውም አንስተዋል።
ግጭቶቹ በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች ያሉትንም ሕጻናት እና ወጣቶች በትምህርት ሊያገኙት የሚችለውን የወደፊት ዕድል ክፉኛ ሲያጨናግፉት ስለመታየቱም ሳያነሱ አላለፉም። እንደ እርሳቸው ሀሳብ ”በደምሳሳው የትጥቅ ግጭት የሚያስከትለው ክፉ ተግባር ውጤት ምንነት ከዛሬ በላይ ገና ወደፊትም ይገለጣል” ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በትምህርቱ ዘርፍ አንድም የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት፤ ሁለትም የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል የለውጥ ሂደት ስታካሂድ ቆይታለች። ለውጡ እንደ ሀገር በሁሉም መስክ ሀገሪቱ የምትፈልገውን ያህል የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት እና የትምህርት ጥራትን ያረጋግጣል ተብሎ የተገባበት ነው።
ትምህርት ሚኒስቴር ይህን ዓይነቱን ሂደት ድርቅ፤ መሬት መንሸራተት፤ ግጭት ብሎም ጦርነትና ሌሎች ሂደቱን የሚገዳደሩ ተግዳሮቶች በተለያዩ ክልሎች በሚነሱበት እና በብርቱ እየተበራከቱ በመጡበት የትጥቅ ግጭት ውስጥ ሆኖም እንኳን ለስኬት እንዲበቃ ሲል ብዙ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል፤ አሁንም እየሰራ ይገኛል። በግጭት ውስጥም ሆኖ በአማራ ክልል ብቻ የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ የተሰራው አንድ ማሳያ ነው። በዚህ ንቅናቄ ለሥራው ከ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ማሰባሰብ ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የአዳዲስ የትምህርት ቤቶች ግንባታ እንደዚሁም የነባር ትምህርት ቤቶች ጥገና ማከናወን ተችሏል። በአጠቃላይ እንደ ሀገር “ትምህርት ለትውልድ ” በሚል የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ በርካታ ከትጥቅ ግጭት ጨምሮ በሌሎች ተግባራት የወደሙና ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ እንዲሁም ግንባታቸው ያልተሟላ የትምህርት ተቋማትን ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ባለፉት ጊዜያት ሕዝቡ በራሱ ከ39 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ስለማሰባሰቡ የትምህርት ሚኒስትሩ (ፕ/ር) ብርሃኑ አንስተዋል። በዚህም 5 ሺህ 957 ቅድመ አንደኛ፣ አንድ ሺህ 738 የአንደኛ እና መካከለኛ፣ 268 የሁለተኛ ደረጃ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋልም ብለዋል። 31 ሺህ 252 ትምህርት ቤቶች ጥገና እና እድሳት ተደርጎላቸው የመማር ማስተማር ሥራውን እንዲያከናውኑ መደረጉንም የትምህርት ሚኒስትሩ (ፕ/ር) ብርሃኑ ይናገራሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም