በአዝማቹ ክፍሌ
አዲስ አበባ ከተቀረቆረችበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስካለችበት ደረጃ እስክትደርስ የተለያዩ ለውጦችን አስተናግዳለች ።ከነዚህም ውስጥ የትራንስፖርት አሰጣጥና እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ነው ።ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ሁኔታው እንደ ህዝብ ብዛትና እንደዘመኑ ከጋሪ እስከ አውቶቡስ አገልግሎት የደረሰ ነበር ።በወቅቱ የነበረውም ህዝብ ትራንስፖርት እምብዛም የማይጠቀም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመንገድ ግንባታም ደካማ እንደነበር ይነገራል ።ይህ ሁኔታ ታድያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባለበት ቀጥሎ የትራፊክ መጨናነቅ እንደፈጠረም የሚታወቅ ነው።
ከሚሊኒየም መባቻ በኋላ የአዲስ አበባ መንገዶች ቀን ወጥቶላቸው በመጠነኛ ደረጃም ቢሆን መገንባት ጀመሩ ። ነዋሪውም መጠነኛ እፎይታ አግኝቶ መንቀሳቀስ ቢጀምርም የትራንስፖርት እጥረቱ ግን እያንገሸገሸው እስከዛሬ ዘልቋል ።በከተማው አስተዳደር በኩል የታክሲ፣ የአውቶቡስና ሌሎች አማራጮችን እየተጠቀምኩ ነው ቢልም ችግሩን የፈታ ነገር ግን እስካሁን አልታየም ።እስቲ በተወሰነ መልኩ የትራንስፖርት ችግሩንና ምክንያት ይሆናሉ ምንላቸውን እያነሳን እንመልከት ።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ችግር በምክንያትነት የሚነሳው ብዛት ያላቸው መንገዶች አለመኖርና የተሰሩትም መንገዶች የጥራት ችግር ነው ። አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ መንገዶች ታስቦባቸው ዲዛይን ወጥቶላቸው ቢጀመሩም ማለቂያቸው ግን የተገላቢጦች ሆኗል። ምክንያቱ ምንድነው ተብሎ ቢፈተሸ የፍሳሽ ማስወገጃ አለመኖር፣ የመንገዱ አሰራር ወጣ ገባ መሆን እንዲሁም በትክክለኛ ግብዓት አለመሰራት ሆኖ ይገኛል ። የሚያስገርመው ነገር ደግሞ መንገዶቹ ብዙ አመት ሳያገለግሉ መበላሸታቸው ነው… ።ዛሬ ተሰርተው ነገ የሚበላሹ ሽሮ ፈሰስ የሚሏቸው የመንገድ ስራዎችም የአዲስ አበባ መገለጫዎች ናቸው ።በሌላ በኩል ሳይታሰብባቸው ተሰርተው አገልግሎት የማይሰጡ መንገዶችን ማንሳትም ይቻላል ።
አዲሱ ገበያ አካባቢ የተሰራው የቀለበት መንገድ አንዱ ክፍል አገልግሎት አይሰጥም ። መንገዱ በአራት ማሳለጫ የተገነባ ቢሆንም የመኪና መቆሚያ፣ የኳስ መጫወቻ እና ለከብቶች መነገጃነት እያገለገለ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ በመንገድ አካፋይ ላይ የሚገኙት ቦታዎች፣ የመንገድ ማዞሪያዎችንና መታጠፊያዎችን እንደዚሁ በብረት አጥር እንዲዘጉ ተደርገው ነበር ።ይሁን እንጂ ብረቱ ብዙም ሳይቆይ ተነቃቅሎ ጠፍቶ በአሁኑ ወቅት የተተከለበት ኮንክሪት ብቻ ፈጦ ይታያል ።አሁንም እንደዚሁ እንደሚጠፋ እየታወቀ የመንገድ አካፋዮች ላይ የብረት አጥር እየተሰራ ይገኛል ።
ሌላው የትራንስፖርት ችግር ተደርጎ የሚወሰደው አማራጭ የትራንስፖርት ሁኔታዎች አለመመቻቸት ነው። አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲባል የሳይክል፣ አነስተኛ ታክሲዎች እንዲሁም ሌሎች መንገዶችን ያካትታል። የሳክይክል ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ብዙ ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም ውጤታቸው ግን ምንም ሆኗል ።ለሳይክል ትራንስፖርት ይሆናሉ ተብለው የተገዙት ሳይክሎች አቧራ ጠጥተው አንድ መጋዘን ውስጥ መከማቸታቸው የአንድ ወቅት ዜና ሆኖ ያለፈ ጉዳይ ነው ።
በሌላም በኩል ጀሞ አካባቢ ለሳይክል መንቀሳቀሻ ተብሎ የተገነባው መንገድ ምን አይነት አገልግሎት እየሰጠ እንዳለ ቦታው ድረስ ሆዶ ማየት በቂ ነው ።እነዚህ ሁኔታዎች ሲታዩ ከአራት ኪሎ እስከ ፒያሳ የሚወስደውን መንገድ ለሳይክል መንቀሳቀሻ ይደረጋል የተባለው እቅድ ተፈፃሚነት ጥርጣሬ ውስጥ ይከተዋል ።ከዚህም በዘለለ አሁን ያሉት የከተማዋ መንገዶች እንኳን ለሳይክል ለመኪና በቂ አለመሆናቸው የሚታወቅ ነው ።በቅርቡ ይጠናቀቃሉ ተብለው የሚጠበቁት መንገዶች ሲያልቁ ደግሞ የመኪና እጥረት አለ የሚል ዜና ልንሰማ እንችል ይሆናል::
ሁለተኛው የትራንስፖርት እጥረቱን ካባባሱት ውስጥ የአንበሳ አውቶቡስ የተቆራረጠ አገልግሎት አሰጣጥ ነው ።የአንበሳ አውቶቡስ ሲመሰረት ጀምሮ ለህዝቡ በቅናሽ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ ነበር ።ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ለህዝቡ ከሚሰጠው አገልግሎት ይበልጥ ሰርቪስ የሚሰጥባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው ።ለዚህ ደግሞ በየምክንያቱ የሚዘጋጁ ጉብኝቶችና ፕሮግራሞች ተጠቃሽ ናቸው ።
የአንበሳ አውቶቡስ እንደ ቀድሞ በቁጥር ሳይሆን ፊት ለፊቱ ላይ ወይም በጎን በኩል በሚፅፋቸው የመሄጃ መስመሮች ተገልጋዩ በቀላሉ እንዲጠቀም ቢያስችለውም፤ ሁሉም አንድ ቦታ የሚሄዱ በመሆናቸው አብዛኛው ተጓዥ ለእንግልት ተዳርጓል ።ይህን ሁኔታ ለማየት መገናኛ አካባቢ የተወሰኑ ደቂቃዎችን ማሳለፍ በቂ ነው ።መገናኛ አካባቢ ጠዋትም ሆነ ማታ ረጅም ሰዓት የሚቆይ ሰልፍ ማየት ከመለመድ አልፎ እንደ ምልክት መቆጠር ተጀምሯል ።ሰልፉን ያቃልላሉ የተባሉት የትራንስፖርት አማራጮች ሰልፍ ፈጣሪ ሆነው የሚታዩት በመገናኛ አካባቢ ነው ማለት ይቻላል ።
ሌላው ደግሞ የሸገር አውቶቡሶች ለትራንስፖርቱ ችግር መቃለል ታስበው የገቡ ቢሆንም የተፈለገውን ለውጥ ያመጡ አይመስልም ። አውቶቡሶቹ የትራንስፖርት እጥረት በሚታይባቸው አካባቢዎች ቢሰማሩም የህዝቡን ሰልፍ ማቃለል አልቻሉም ። ልክ እንደ አንበሳ አውቶቡስ ሸገር አውቶቡስም በተለያዩ ምክንያቶች ሰርቪስ እየሰጠ ይገኛል። ይህን እውነታ ለመመልከት ዘወትር ቅዳሜ አውቶቡሶቹ ‹‹ሰርቪስ›› የሚል ምልክት እያበሩ ሲያልፉ መመልከት በቂ ነው ።
የታክሲውን ሁኔታ ማንሳት አያስፈልግም ምክንያቱም ሰበብ እየፈጠሩ ከመቆምና ከመበላሸት ባለፈ ሰልፍ ሲያዩ መኪና ማቆም ልማድ አድርገውታል ።የታክሲ ሰልፍ አስከባሪዎችም ገንዘባቸውን ከተቀበሉ በኋላ ስለተሰለፈው ህዝብ ደንታም አይሰጣቸው ።መንግስት ያሰማራቸው ተቆጣጣሪዎችም ትራንስፖርቱን ከማሳለጥ ይልቅ የግልና የመንግስት መኪናዎችን በመቁጠር ተጠምደዋል ።የትራንስፖርት ስምሪት ባለሙያዎቹ ከህዝቡ እኩል ተሰልፈው ከመዋል በዘለለ ምንም አይነት አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ። ኪሳራ ብቻ::
በቅርቡ የከተማ አስተዳደሩ ያስገባቸው ደጋፊ አውቶቡሶች ችግሩን ያቃልላሉ ተብሎ ቢታሰብም ምን ሰዓት ላይ አገልግሎት እንደሚሰጡ አይታወቅም ።ጠዋትና ማታ ላይ የተወሰኑ ደጋፊ አውቶቡሶች ሲንቀሳቀሱ ቢታይም በተፈለገው ደረጃ ግን አገልግሎት እየሰጡ አይደለም። ለምን እና እንዴት መስራት እንዳለባቸው ባለማወቃቸው የትራፊክ ጭንቅንቅ ለመፍጠር የገቡ እስኪመስል ድረስ ተገትረው ይውላሉ::
ሌላው አነስተኛ የታክሲ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራው ነው ።በቅርቡ በቴክኖሎጂ የታገዙ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ወደ ገበያው ገብተዋል ።እነዚህ በቴክኖሎጂ የታገዙ የታክሲ ሰጪ ድርጅቶች ከነችግራቸውም ቢሆን ጥሩ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው አያጠራጥርም ።ነገር ግን የዋጋቸው ሁኔታ ሁሉንም ህብረተሰብ ያማከለ ባለመሆኑ ጠዋትና ማታ የሚሰለፈውን ህዝብ ችግር ማቃለል አልተቻለም::
በቴክኖሎጂ የታገዘ የታክሲ አገልግሎት አሰጣጡ እንደተጀመረ አካባቢ በርካታ ችግሮች ገጥመውት እንደ ነበር አይዘነጋም ።ከዚህም ውስጥ ቀደም ብለው አነስተኛ ታክሲ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ሰዎች ስራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሯል በሚል ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ነበር ።ችግሩን ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ ጣልቃ ገብቶ ቀደም ብለው በአነስተኛ ታክሲ ስራ የተሰማሩ ሰዎች በመደራጀት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እንዲሰጡ እገዛ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ ነበር ።የገባው ቃል ይፈጸም አይፈጸም የሚታወቅ ነገር የለም::
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ትራንስፖርትን በተመለከተ ብዛት ያላቸው ቢሮዎች ተቋቁመዋል። አንዳቸውም ግን የከተማውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት መፍትሄ አላመጡም ።ለምን ተብሎ ቢታይ ቢሮና ሰራተኛ ሰብስበው ከመዋልና ገንዘብ ከማውጣት ውጪ ችግሩን ተረድተው መፍትሄ ማምጣት እንደማይችሉ መረዳት ይቻላል ።ቢሮዎቹ ከኪሳራ በስተቀር መፍትሄ አያመጡምና የሚዘጉበትና የሚቀነሱበት ሁኔታ መፈጠር አለበት::
እዚህ ጋር ሳላነሳ የማላልፈው ጉዳይ በትራንስፖርት ዙሪያ የተቋቋሙት ቢሮዎች አንዳቸውም ይመለከተናል ሲሉ አይደመጡም ።ሁሉም የእንትና ስራ ነው…..እሱ ነው ኃላፊነት የተሰጠው በሚል ስራውን ሲወራወሩ ይውላሉ ። ሪፖርታቸው ላይ ግን ምን ይፅፉ ይሆን ። የሚቆጣጠራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትስ ምን አይነት ግብረ መልስ እየሰጠ እዚህ አደረሳቸው ።ያገባኛል ባዩስ ማን ይሆን?
አዲስ ዘመን ጥር 03/2013