አሸብር ኃይሉ
ሞኖፖሊ ካፒታሊዝም ወይም ኢምፔሪያሊዝም አምስት መለያ ገፅታዎች እንዳሉት ምሁራን ይናገራሉ። እነዚህም የምርት ካፒታል ክምችት መፍጠር፣ በባንክ እና በኢንዱስትሪ ካፒታል ጥምረት የፋይናንስን ካፒታልን መፍጠር፣ የሞኖፖሊስቶች ማህበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ማደራጀት፣ ካፒታልን በማንቀሳቀስ ወደ ውጭ በማውጣት (ኢንቨስትመንትን) መፍጠር እና የርካሽ የሰው ጉልበት መጠቀም፣ ሰፊ የማይነጥፍ ገበያ እና አጥጋቢ ትርፍ ለማግኘት የሚያስችል ሁኔታ እያንዳንዱ ሞኖፖሊስትና እና ድርጅቶች የሀገሩን ክልል ወይም ብሔራዊ ድንበር ጥሶ በመውጣት በዓለም አቀፍ ሞኖፖሊስቶች ማህበር አማካኝነት ዓለምን በወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ስር ማኖር ናቸው ።
ከላይ የተጠቀሱትን ሞኖፖሊ ካፒታሊዝም ወይም ኢምፔሪያሊዝም ዋና አላማዎች ለማስፈፀም የሞኖፖሊስቶች ቁንጮ ሀገረ አሜሪካ ጉድጓድ ገብታ፣ ተራራ ወጥታ እና ባህር አቆራርጣ በባሌም በቦሌም ብላ እጇን በማስረዘም ዴሞክራሲን፣ ነፃነትን፣ ፍትሕን ለማስፈን ነው በሚል እራሷ አሜሪካ ለይምሰል በምታደርጋቸው ማስመሰያ የፅንሰ ሃሳቦች ጥርቅም የሀገራትን ድንበር በመጣስ የፈለገችውን ስትሾም፤ የፈለገችውን እሷን ከመሰሉ ሞኖፖሊስቶች ጋር በመሆን ስትሽር ኖራለች ። አሁንም ይህንን እኩይ ተግባሯን ቀጥላበታለች ።አሜሪካ እና እሷን የመሰሉ ሞኖፖሊስቶች በሚያበድሩት እና በሚረዱት ገንዘብ የሀገራትን ሉዓላዊነት ሳይቀር ጨምድደው በመያዝ የሀገራትን የመኖር ህልውና ሲፈታተኑ ኖረዋል፤ አሁንም እያደረጉት ነው ።
የእነሱን ሃሳብ የማይከተል የትኛውም የዓለማችን ሀገር የተለያዩ የማዕቀብ ዓይነቶችን ይደረደሩበት እና ከማንኛውም ዓይነት የዓለም አቀፋዊ ኢኮኖሚዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ግንኙነቶች እንዲርቅ ይደረጋል ።እነዚህን ዓለም አቀፋዊ መገለሎች ደርሰውበትም የሞኖፖሊስቶችን የማሰሪያ ገመዶች የሚቋቋም ሀገር ካለ በወታደራዊ ዘመቻ ሊያፈራርሱት ይሞክራሉ ።ይህን የአሜሪካ እና ተከታዮቿ ወታደራዊ እርምጃ ገፈት የቀመሱት ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ነው ።ስለሆነም በኢምፔሪያሊስቶች ድብቅ ሴራ በዓለም ባሉ ሀገራት የደረሰውን ሰቆቃ ለመግለፅ አይደለም በወረቀት ላይ በድምጽም መከተብ እጅግ አስቸጋሪ ነው ።
የሚገርመው እነኝህ ሞኖፖሊስቶች በማይጨበጥ እና ራሳቸው እነኳን አንድ ቀን አክብረውት በማያውቁት ዴሞክራሲ በሚባል ፅንሰ ሃሳብ የዓለም ሀገራትን ከዳር እስከዳር ጠፍንገው ለማሰር የማፈነቅሉት ድንጋይ የለም ።እውነት ዴሞክራሲ የሚባለውን ፅንሰ ሃሳብ የሚያከብሩት ቢሆኑ እና ለሰብዓዊ መብት ቢጨነቁ ኖሮ እነሱ በዓለም ሕዝብ ላይ እንዲህ ባልቀለዱ ነበር ።
ይህን የካፒታል ሞኖፖሊስቶች ጫና ወደ ሀገራችን አምጥቶ ማየቱ ተገቢ ሆናል ።ከእራሳቸው ጥቅም ውጪ ለማንም የማይጨነቁት የካፒታል ሞኖፖሊስቶች በሀገራችን ላይ በተለያዩ ጊዜያት ትልቅ በደል ፈጽመውብናል ። ለምሳሌ ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ኢምፔሪያሊስት አሜሪካ ከጣሊያን እና ከተቀሩት የአውሮፓ የቅኝ ገዢ ኃይሎች ጋር በመተባበር ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችው ወረራ ይሳካ ዘንድ ለማገዝ ወረራ በተፈጸመባት ኢትዮጵያ ላይ የመሣሪያ ግዥ ማዕቀብ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ አጼ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ ወደ አሜሪካ ለመግባት ቢጠይቁም እስከ መጨረሻው ሳይፈቀድላቸው ቀርቷል። ነገር ግን ጣሊያንን ኢትዮጵያውያን በእራሳቸው ተፋልመው ከሀገራቸው ማስወጣት ሲችሉ ግን አሜሪካ በኢትዮጵያ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት የቀደማት አልነበረም ።ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን እና የአየር መንገድ፣ የአውራ ጎዳና ባለሥልጣን፣ የውሃ ልማት ባለሥልጣን እና ሌሎች ተቋማት በአሜሪካን የተፈጠሩ ናቸው ። እዚህ ላይ አንድ ነገር መገንዘብ ያስፈልጋል ።ይህም ሀገራት በሁሉ ነገራቸው በጠነከሩ ቁጥር የካፒታል ሞኖፖሊስቶች ጫና እየቀነሰ የሚሄድ መሆኑን ነው ።
አሁን ላይ ደግሞ ከራሳቸው ማደግ እና ማበብ ውጭ የሌሎች መሞት እና መጎሳቆል ቅንጣትም ያህል የማይደንቃቸው አሜሪካ እና በእሷ መስመር የተኮለኮሉ ሞኖፖሊስት ሀገራት ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ስትጀመር ኢትዮጵያ በየትኛውም መልኩ ለግንባታ የሚሆን ምንም ዓይነት እርዳታ እና ብድር ከየትኛውም ሀገር እንዳታገኝ ከለከሉ፤ አስከለከሉ ።እልህ ሚስማር ያስውጣል እንዲሉ ይህን ክልከላ የሰሙት ኢትዮጵያውያንን ለፕሮጀክቱ መጀር በእልህ እንዲነሱ አደረጋቸው ።የግድቡንም ሥራ በአንድነት እና በወኔ ጀመሩት ። የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት ማድረግም ቻሉ።ይህ የኢትዮጵያውያን ጥንካሬ ጉሮሮ ላይ የተሰነቀረ የዓሣ አጥንት የሆነባቸው ሁሌም ከራሳቸው እድገት ውጪ ለማንም ማደግ የማይጨነቁት እነ አሜሪካ እና አጋሮቻቸው አሁን የኢትዮጵያን ፖለቲካል ኢኮኖሚ በፈለጉት ቅኝት ለመቃኘት ይመቻቸው ዘንድ ከወር በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት የሕግ ማስከበር ሥራ ሲሰራ በሚዲያዎቻቸው የኢትዮጵያን ክፉ ተመኙ፤ የቻሉትንም ያህል ያልተደረገን ተደረገ እያሉ የዓለምን ሕዝብ በማደናገር የቻሉትን ጮሁ ። በየሚዲያዎቻቸው ለፈፉ፡፡
ነገር ግን የመከላከያ ሰራዊት በኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር እስከ ዳር ተደግፎ የሞኖፖሊስቶችን ምኞት ውሃ ውስጥ ጨምሮታል ።ይህ የሚገርም መደጋገፍ ደግሞ የየትኛውንም የሞኖፖሊስቶች ሀገር የማፍረስ ተልዕኮን የማኮላሸት አቅም አለው ።
ሁሌም የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ደህንነትና እድገት የጎን ውጋት የሆነባቸው ጥቅማቸው የተነካበቸው ኢምፔሪያሊስቶች አሁን ላይ ደግሞ ሱዳንን ያልሆነ ጉም በማስጨበጥ ኢትዮጵያን እስከማስወረር ደረሱ። በኦሮሚያም ግጭት፣ በሶማሊያም ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በጎንደር በአፋር በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ጥፋት ደግሰው ላይ ታች ቢሉም የጥፋት ታዳሚዎች ግብዣውን ባለመቀበላቸው የኢምፔሪያሊስቶች ህልም ከህልም ሊያልፍ አልቻለም።
በመጨረሻም እጅ የሚያስገባ ቀዳዳ ባለበት ጆንያ ጤፍን ተሸክሞ ለመሸጥ መሞከር ጤፉ ገበያ ሳይደር በመንገድ ተድፍቶ እንደሚያቅ ለማንም የተሰወረ አይደለም ። ስለዚህ መጀመሪያ ለመሸጥ ከመሸከምህ በፊት የጆንያህን ቀዳዳ መስፋት እና መድፈን ያስፈልጋል ።ካልሆነ በቀዳዳው የፈሰሰው ጤፍ ጆንውን ባዶ ያስቀረውና ለኪሳራ ይዳርጋል ።እዚህ ላይ አንድ ነገር መገንዘብ ያስፈልጋል፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በሆነ ባልሆነ ግጭት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ከመቼውም በላይ ደፍነን እና ተደጋግፈን መቆም ያለብን ሰዓት አሁን ይመስለኛል ።ካልሆነ ግን ሞኖፖሊስቶች ትንሽ ክፍተት ካገኙልን ትንሿን ክፍተት እያሰፉ ያለ ገላጋይ እንዲጫወቱብን አጨብጭበን እንደፈቀድንላቸው ይቆጠራል ።ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ልክ ግድቡ ሲጀመር እና የመጀመሪያው የውሃ ሙሊት ሲደረግ ከነበረው አንድነታችን በላይ ጠንክረን መገኘት የውዴታ ግዴታችን ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም