(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ) gechoseni@gmail.com
«ግርምተ ሳይቴክ»
ርዕሱ የተውሶ ነው ።በግርምት የተገለፀው ሳይቴክም ሳይንስና ቴክኖሎጂን ያጣመረ ቃል ነው ።ለባለ ርዕሱ አዋሼ ምሥጋናዬ ይድረስልኝ ።ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከለገሱን አስደናቂ “በረከተ መርገምቶች” (Blessing in disguise እንዲሉ) መካከል የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስጦታዎች በእጅጉ ይማርኩኛል ።በአየር ሞገድ አቆራርጦ በየቤታችን ስለሚደርሰው የሬዲዮ ድምጽም ሆነ በድምጽና በምስል ተቀናብሮ ከጓዳችን ሰተት ብሎ ስለሚገባው የቴሌቪዥን ጥበብ ሁሌም እንደተደነቅሁ ነው ።
እ.ኤ.አ በ1901 ዓ.ም ሬዲዮን ለፈጠረው ለጉልዬም ማርኮኒ (1874 – 1971) እና በ1927 ዓ.ም የቴሌቪዥን ምሥጢር ይፋ እንዲሆን የምሥራቹን ላበሰረልን ለፊሎ ቴይለር (1906 – 1971) ስማቸውም ሆነ ግብራቸው ከመቃብር በላይ አውሏቸዋልና ለድካማቸውና ለጥበብ ግኝቶቻቸው ክብርን እንሰጣለን፡፡
የዓለማችንን ህዋ ከአድማስ እስከ አድማስ ጥቅጥቅ አድርገው ከሞሉት እልፍ አእላፋት (ቁጥሩ ይገልጸው ከሆነ) ድምጾች መካከል የምንፈልገው የሬዲዮ ጣቢያና ፕሮግራም እንዴት ነጥሮ ከቤታችንና ከጆሯችን እንደሚደርስ ባሰብኩ ቁጥር በግሌ በእጅጉ እገረማለሁ። መገረም አልኩ እንጂ አድናቆቴም ታክሎበት መሆኑ ልብ እንዲባልልኝ እወዳለሁ ።የቴሌቪዥን ባህርይውም እንዲዚያው ነው ።
መገረሜን የሚያንረው ዋናው ምክንያት ለፊዚክስ የሳይንስ ዘርፍ ባዕድ ስለሆንኩ ብቻም አይደለም ።የባዕድነት ጉዳይ ቢሆንማ ኖሮ የሬዲዮ ፈጣሪው ማርኮኒ ራሱ ለዚህ ታላቅ አበርክቶቱ ከካርል ፈርዲናንድ ብራውን ጋር እ.አ.አ በ1909 በፊዚክስ የኖቤል ሽልማትን በጋር ከተቀበለ በኋላ ስለ ረቀቀው ሳይንሳዊ ግኝቱ ሲናገር “እኔም ራሴ ብሆን በግኝቱ መደነቄ አልቀረም” ማለቱ ይዘከርለታል ።
የዓለማችንን አየር አጨናንቀው ጢም ስላሉት የድምጽ ሞገዶች እጅግ ብዙ ጥናቶች ተደርገዋል፤ ወደፊትም ምርምሩ የሚቆም አይመስልም ።በደምጽ ባህርይ ላይ የሚመራመሩ ብዙ የዘርፉ ሳይንቲስቶች እንዳረጋገጡት “ሰውን ጨምሮ ማንኛውም ፍጥረት የሚያወጣቸው ድምጾች በሙሉ ተንነው የሚጠፉ ሳይሆን በአየር ላይ እየተንሳፈፉ መኖራቸው እውነት ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱ ይመስላል ።በአዘቦት የመግባቢያ ቋንቋችን እንግለጸው ካልን ከአፋችን የምናወጣቸው ድምጾች በሙሉ እንደ ጢስ ብን ብለው የሚጠፉ ሳይሆን በአየሩ ላይ እየተንሳፈፉ ይኖራሉ እንደ ማለት ነው፡፡
“ከአፍ የወጣ አፋፍ” የሚለው ሀገራዊ ብሂላችን ምናልባት የተፈጠረው ከዚህ እውነታ ተነስቶ ይሆንን? እርግጠኛ አይደለሁም። ለማንኛውም ከአንደበታችን አፈትልከው የሚወጡት የበረከትም ይሁን የእርግማን ቃላት፣ የሰላምም ይሁኑ የጦርነትና የሽብር ቀረርቶዎች፣ የሠርግ ማድመቂያ የሙሽራዬ ዜማም ይሁን የለቅሶ ሙሾ አገልግሎታቸውን እንዳጠናቀቁ በንነው የሚጠፉ ሳይሆን አየሩን ተቆጣጥረው ዝንተ ዓለም ከደመና ጋር እየተጋፉ ይኖራሉ እንጂ እንደ እንፋሎት ተንነው አይጠፉም፡፡
የሬዲዮና የቴሌቪዥን ሳይንሳዊ ምሥጢር ለግርምት መዳረጉ ብቻም ሳይሆን እንቆቅልሽ ሊሆንብን የሚችለው ከዚህ ምሥጢር ጋር መጋፈጥ ስንጀምርና ልብ ብለን ስናጤነው ነው ።
ቁጥሩ ካላነሰ በስተቀር ትሪሊዮን ጊዜ ትሪሊዮን ወይንም በእኛው የቁጥር ስሌት ምእልፊታት (10,000,000,000) ጊዜ ምእልፊታት ከሚቆጠሩ የድምጽ ሞገዶች መካከል እንዴት የምንፈልገው ድምጽ ሹልክ ብሎ በመውጣት በሬዲዮና በቴሌቪዥን አማካይነት ከጆሯችንና ከዓይናችን ሊደርስ ቻለ? ዝቅ እናድርገው ካልንም የሞባይል ስልካችን ጉዳይስ አይግርምም? ለዘርፉ ሳይንስ ባዕዳን ለሆንነው እኔን መሰል ዜጎች ከዚህም በተሻለ ገለጻ ጠቢባኑ እንዲያብራሩልን ማስታወሻ አኑሬ ወደ ዋናው ርዕሴ አቀናለሁ፡፡
የሀገሬን አየር እየበከሉ ያሉ ሞገዳዊ ድምጾች፤በረጅም ዘመናት ታሪኳ ውስጥ ሀገሬ ከትካዜ ነፃ ሆና የኖረችባቸውን ጊዜ ለይቶ ለማመልከት ብዙ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል ።እንደ ሀገሬ ቆዛሚ፣ እንደ ዜጎቿ ብሶተኛ፣ እንደ ፖለቲካዋ ህመምተኛ የሆነ ሌላ ሀገር ይኖር ከሆነ እየጠቋቆምን ብንጽናና አይከፋም ባይ ነኝ ።“በሺህ ዘመናት ታሪካችን” መካከል ሺ ህ ህፀፆችን በመምዘዝ የራሳችንን ክብር በመቶ ዕድሜ ካልከረከምን እያልን የምንፋለምበት፣ የምንጋደልበት፣ የምናፈናቅልበትና የምንፈናቀልበት የድምጽ ጩኸትና ኡኡታ አየሩ ላይ መታተሙን እንረዳው ይሆን ።ሉዓላዊነታችንን የተዳፈሩ የውጭ ጠላቶችን እያቅራራንና እየፎከርን ድል ያደረግንባቸው ዜማቻችን ብቻም ሳይሆኑ በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች መግባባት ተስኖን የተጯጯኽንባቸውና የተጠዛጠዝንባቸው “ቃላቶቻችን” በሙሉ ከአናታችን
ከፍ ባለው ህዋ ላይ እየተንሳፈፉ እንደሚታዘቡንስ ተረድነት ይሆን?
ከአንድ ሀገር ማህፀን ተፈጥረን እንደ ኤሳውና ያዕቆብ የቀዳሚነት ብኩርናን ለመቀማማት የምንፋለመው እኛው ራሳችን ነን ።ድምጹም የራሳችን እንጂ የባዕዳን ቀረርቶ አይደለም ።ለቀጣዩ ትውልድ የከበረውን “የታሪክ ብራና” ከማውረስ ይልቅ የራሳቸውን “ተረት ተረት” እየጮኹ በመናገር ለተተኪያቸው መልሰው እንዲያወርሱና ንፁሑን አየራቸውን በእነርሱም ዘመን እንዲበክሉ የቆሻሻ ወረቀት የምናመላክታቸው እኛው “ምንጅላቶች፣ አያቶችና አባቶች ነን፡፡”
ሁላችንም በምንግባባበት ቋንቋ ለመግለጽ ካስፈለገም የሀገራችን ሕዋ በቆሸሹ ድምጾችና በተበከሉ ንግግሮች እንዲያድፍ በቀዳሚነት ምክንያት እየሆኑ ያሉት ርዕዮተ ዓለማቸው የሸተተው የኅሊና ሕሙማን ፖለቲከኞች ናቸው/ነበሩም ብለን ፍርጥ አድርገን መናገር እንችላለን፡፡
እንደ አንድ ሀገር ዜጎች ከምንስማማባቸውና ከምንግባባቸው ድምጾች ይልቅ ልዩነታችንን አየሩ ላይ መበተን ይቀናናል ።ከሕብረ ብሔራዊነት ይልቅ “የነጠላ ማንነታችንን ዜማ” በማቀንቀን መራርነትን የመዝራትን ምርጫ እናስቀድማለን። ተነጋግሮ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ አደነጋግሮና ተደነጋግሮ መለያየትን እንደ ጀብድ በመቁጠር ብሶታችን እንደ ገደል ማሚቶ እንዲያስተጋባ እንተጋለን ።ከእኛነታችን ይልቅ የእኔነት፣ ከይሆናል ይልቅ አይሆንም፣ ከብዙህነት ይልቅ ነጠላነት መለያችን ሆኖ ይህንኑ ክፉ ደዌ ታቅፈን ዘመናትን አሸብተናል፡፡
የታሪካችን አየር በጥይት ባሩድ ሲታጠን መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ከአንደበታችን የሚወነጨፉት የቃላት ሚሳኤሎች ምን ያህል ጥፋትና ውድመት ሲያስከትሉ እንደኖሩ በምስክር ይረጋገጥ የማይባልለት ያፈጠጠ ሐቅ ነው ።በተለይም ዛሬ የኢትዮጵያን አየር እየበከሉ ያሉት ድምጾች ለታሪክ የሚሸጋገር ቁስል እያኖሩ ብቻም ሳይሆን እኛን የዛሬዎቹንም ዜጎች በእህህታ ህመም ላይ ጥለው ለደዌ እንደዳረጉን ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡
የሬዲዮ ፈጣሪው ማርኮኒ ወይንም የቴሌቪዥኑ የፈጠራ ባለቤት ቴይለር በሕይወት ቢኖሩና በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ያረበቡትን ድምጾችና ምስሎች አንጥረው ለጆሯችንና ለዓይናችን አድርሱልን ብንላቸው ምን ሊያቀርቡልን እንደሚችሉ መገመት አይከብድም ።የቀዳሚ ግምት እንስጥ ከተባለ ግን በግፍ የተገደሉ የንጹሐን ዜጎች የደም ጩኸት፣ ልጆቻቸውን በግፈኞች የተነጠቁ እናቶች እዬዬና ሙሾ፣ ፈጣሪን ከመንበሩ የሚቀሰቅስ የግፍ ዲስኩር፣ ምክንያት አልባ ትቸት፣ “እኔ እበልጥ” የማንነት ጉሰማ፣ የሥልጣን ጥማት ሀራራ፣ የትዕቢት ቀረርቶ፣ የማን አለብኝ ጀብድና ፉከራ፣ ለተረኝነት መራወጥና ፊት ቀደምትነት፣ ሀሜት እና የውድመትና የተፈናቃዮች ሰቆቃ የመሳሰሉትኑ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል ።ለመሆኑ ከመሰሪነት የቃላት ስንጠቃ ይልቅ የቅንነት ጥያቄዎችን እየተጠያየቅን እንዳንግባባና እንዳንወያይ አዚም ያደረገብን ማን ይሆን?
አንድ ቤተ እስራኤላዊ ወዳጄ ያጫወተኝ ታሪክ ሁሌም ትዝ እያለ ያስገርመኛል ።ታሪኩን ካጫወተኝ ዓመታት ስለተቆጠሩ ዛሬም መሰል ድርጊቶች እየተፈጸሙ ይሁን ወይንም አይሁን እርግጠኛ አይደለሁም ።
ቀደም ባሉት ዓመታት ማንኛውም እስራኤላዊ በኢየሩሳሌም መንገዶች ወይንም በአሃይፋና በመሰል ዋና ዋና ከተሞች አውራ ጎዳናዎች ላይ የሚጓዘው ቀልቡን አረጋግቶ ሳይሆን ግራና ቀኙን እየቃኘና እተገላመጠ ነበር ።ምክንያቱ ደግሞ በጽዮናዊነት ጥላቻ የወፈፈና የሰከረ አንድ አጥፍቶ ጠፊ በወገቡ ላይ በታጠቀው ፈንጂ ራሱን ሰውቶ ንጹሐንን የመፍጀት ጥላቻ ሥር ሰዶ ስለነበረ ነው ።በዚህ ምክንያትም የዚህች ምስኪን ሀገር ንጸሕ አየር ሁሌም የሚበክለው ጣጣ አያጣም ነበር ።
ይህንን የወዳጅ ሀገር ገመና ዘክዝኮ ያጫወተኝ ቤተኛ ወዳጄ ታሪኩን ሲያወጋኝ ልቡ በሀዘን እየቆሰለ እንደነበር ትዝ ይለኛል ።ፈጥኖ ወደ አእምሮዬ የመጣው የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገር ጉዳይ ሆኖ እንጂ የአንዳንድ ቅርብ ጎረቤት ሀገራት ታሪክም ከዚህ የሚለይ አይደለም፡፡
በዛሬይቱ ኢትዮጵያም ልብ ተቀልብ ሆነን የምንወያይባቸውና የምንቆዝምባቸው በርካታ ሀገራዊ ገመናዎቻችን ለእኛ እንደ አዘቦት ቀን መርዶ ቢቆጠሩም ለባዕዳን ሰሚዎች ግን ጆሮን ጭው የማድረግ አቅም ያላቸው ናቸው ።ቀደም ባሉት ዘመናት የጦርነት ታሪክ ስንተርክ የኖርነው ድንበር ተሻግረው የመጡ ወራሪዎችን እንዴት ቀጥተን እንደመለስን በኩራት በመተረክ ነበር ።የዘንድሮው ጦርነታችን ግን ከአንድ ማኅፀን ወይንም አብራክ እንደተፈጠሩት አቤልና ቃየን፣ ዔሳውና ያዕቆብ፣ ይስሐቅና እስማኤል ብጤ መሆኑ በእጅጉ ማሳፈር ብቻም ሳይሆን ለክፉ ትችት የሚያጋልጥ ሀገራዊ ማፈሪያችን ጭምር ነው፡፡
በሀገራችን ሕዋ ላይ የታመቁት ጥቋቁር ድምጾች ምን መልዕክት ተሸክመው ዙሪያችንን እንደ ደመና እንደከበቡን ለሁላችንም ግልጽ ነው ።“የንጹሐን ጭፍጨፋ፣ መርዶ፣ የታሪክ ቁስሎች ሲጎረጎሩ የሚደመጡ ድምጾች፣ ከክልሌ ነቅለህ ውጣ ዛቻ፣ ለተጠቃሚነት እፍታ ግብግብ፣ ለመሬት ወረራ መስገብገብ፣ በሥልጣን ኮርቻ ላይ ለመንፈላሰስ መፋተግ፣ ዝርዝሩ ብዙ፣ ገመናውም የትዬለሌ ነው፡፡
እናስ ምን እርምጃ ይወሰድ?
ግብሩ እንደ አስተያየቱ ባይቀልም መተግበሩ ግድ፣ ያለመተግበሩም ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል መጠርጠሩ ጨለምተኛ አያሰኝም ።አሃዱ፤ ወደ ብሔራዊ ቀልባችን እንመለስ ።ክልዔቱ፤ በርግማን የተበከለውን አየራችንን በመግባባትና በሰላም ቋንቋ ለመፈወስና ለመፈዋወስ ሁላችንም የየድርሻችንን እንወጣ ።ሠልስቱ፤ ከታሪካችን ገጾች ውስጥ አመዱን ሳይሆን ፍሙን እየገላለጥን ከበቀልና ቂም ቆፈናችን እንላቀቅ ።
አርባዕቱ፤ ከመገፋፋት መተቃቀፍ፣ ከሆድ አደርነት ይልቅ ለአፍቅሮ ኅሊና ቅድሚያ እንስጥ ።እድፋሙን የፖለቲካችንን ባህል በመነጋገር እናጽዳው ።የግላችንን ማዕድ በግፍ በሚጋገር ዳቦ ከመሙላት ይልቅ ነጋችንን ለማበልጸግ እንትጋ ።መንግሥት ሆይ! ዜጎች ሆይ! ሕዘበ አዳም ሆይ! ቆም ብለን እናስብ ።ረጋ ብለን እንምከር ።ኢትዮጵያ ዘላለማዊት፣ እኛ ዜጎቿም ጊዜያዊ ነዋሪዎች እንጂ እንደ ማቱሳላ ዘጠኝ መቶ ዓመታት የመኖር ፀጋ አልታደልንም ።
የተበከለው የሀገራችን አየር “ሊፈወስ” የሚችለው ቂምና ጥላቻን፣ መገፋፋትና መቆራቆዝን፣ እብሪትና ትምክህትን አስወግደን እኔነትን ለሚያሸንፍ እኛነት ስንገብርና የተባበረ የሰላም ድምጽ ወደ አየሩ ስንልክ ብቻ ነው። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ጥር 01/2013