በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
እለቱ እሁድ እረፋድ ነው። ሦስት ወጣቶች በአካባቢያቸው ካለው ዛፍ ስር ተሰብስበዋል። ከሦስቱ አንዱ በቅርቡ ከዩኒቨርስቲ የተመረቀ ሲሆን፤ ሌላኛው ከቴክኒክና ሙያ የተመረቀ እንዲሁም ሦስተኛው አስረኛ ክፍል ላይ ትምህርቱን አቋርጦ በአካባቢው ካለ ፋብሪካ ውስጥ በመጫንና ማውረድ ስራ ላይ የተሰማራ። ዘወትር እሁድ እረፋድ ላይ በአካባቢያቸው በሚገኘው ሜዳ ጥግ ላይ ተቀምጠው ስል ተለያዩ ጉዳዮች ማውራት ልምድ ካደረጉ ሰነባብተዋል። አንዳንዴ ሌሎች የአካባቢውን ልጆች ጨምረው ኳስ ይጋጠማሉ። አንዳንዴ ስለ እግር ኳስ ሲከራከሩ ይውላሉ። አንዳንዴ ስለ ኃይማኖት ሞቅ ያለ ክርክር ያደርጋሉ። ሦስቱም የተለያየ እምነት የሚከተሉ እንዲሁም የተለያየ አፍ መፍቻ ቋንቋ ካላቸው ቤተሰብ የወጡም ናቸው።
ሦስቱም አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ በወጣትነት እድሜ ላይ መገኘታቸውና ቀጣዩ የህይወታቸው አቅጣጫ ግልጽ ሆኖ የማይታያቸው መሆኑ ነው። በአንድ አካባቢ መገኘታቸው ሦስቱንም እሁድ ቀን ከያሉበት ተሰባስበው ሰፈር ውስጥ ስለምታስቀራቸው በውስጣቸው ያለውን እርስበርስ የሚተነፍሱበት ጊዜያቸው ነች።
ሦስቱም ወጣቶች በተገናኙ ቁጥር ዘወትር የሚነሳ አንድ የማይቀር ጉዳይ አለ። እርሱም ከሀገር የመውጣት ህልም። በሦስቱም ልብ ውስጥ ከሀገር መውጫ መንገዱ ላይ ሁሌም ውይይት አለ። አንዳንዴ ሀገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ ፈጽሞውኑ አይታሰብም ብለው ያምኑና በየትኛውም መንገድ ከሀገር መሰደድ አማራጭ እንደሌለው ያወራሉ። አንዳንዴ ደግሞ ህይወትን አስይዞ የሚደረግ ስደት ተገቢ አለመሆኑን ለቤተሰብ የእድሜ ልክ ሃዘን ምንጭ መሆን ነው ብለው ከስደት አቅጣጫ ፊታቸውን የመለሱ ይመስላሉ።
በተለይም በአካባቢው በትጋቱ የተለወጠን ሰው አንስተው በሚያወሩበት ጊዜ በስደት ላይ በጋራ ይዘምቱበታል። በሚቀጥለው ሳምንት ግን ተረስቶ በስደት ውስጥ ያለው ብልጽግና ወለል ብሎ እየታያቸው ሲጎመጁ ቆይተው ይለያያሉ ። በቤተሰባቸውም ሆነ በሰፈራቸው ውስጥ የሚገኙ በስራቸው የተደላደሉ የሚመስሉ ሰዎች የእነርሱን ጉዳይ እንደ ጉዳይ የሚመለከቱ ሳይሆኑ ጸሐይ ብቅ ስትል በጠዋት ወጥተው ጸሐይ ስታዘቀዝቅ የእነርሱን መዳከም ጠብቀው ሰፈር የሚደርሱም ይመስላቸዋል። ዛሬም በእሁድ እረፋድ ላይ ከተለመደው ርዕሰ ጉዳይ ተነስተው ግራና ቀኙን ይዘው እየተጨቃጨቁ ነው።
እኒህ ሦስት ወጣቶችን በምናባችን ይዘን በወጣቶች ዙሪያ በሀገራችን የሆነውን አንድ ሁለት ብለን እንቁጠር። አንድ የወጣቶች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ለእኒህ ወጣቶች አስር ቢሊዮን ብር መድባ ለወጣቶች ተስፋን ለመጫር መሞከሯ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
ሁለት በጥቃቅንና አነስተኛ አደረጃጀት ተስፋን ለመስጠት የተሄደበት እርቀትም እንዲሁ ተጠቃሽ ነው። ሦስት በአዲስ አበባ የታክሲ ስርዓት አስከባሪዎች ሆነው ወጣቶች አገልግሎት መስጠት ከመጀመራቸው በፊት የነበረውን የሰልፍ ላይ ግርግር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡።አራት የፓርኪንግ አገልግሎት ላይም ወጣቶችን አደራጅቶ ወደ ስራ በማስገባት የመንገድ ዳር መንገዶች የገንዘብ ማግኛ ምክንያት ከሆኑ እንዲሁ ሰነባበቱ አምስት ብዙ ያነጋግር የነበረው የኮብልስቶን ንጣፍን በዩኒቨርስቲ ምሩቃን ማሰራቱንም እንጨምረው።
ስድስት፣ሰባት…ወዘተ እያልን ልንቆጥር እንችላለን። ግን ሀገራችን ለወጣቶች ተስፋን ለመስጠት የሄደችበትን እርቀት ይህንንም ያንንም መሞከር አይነት ቢመስልም ዘለቄታዊ መፍትሄው አሁንም ውሉ የተገኘለት አይመስልም። በእዚህ መካከል ተስፋ በማጣት በብዙ ውጣውረድ ውስጥ የሚያልፉ ወጣቶቻችንን ቤት ይቁጠራቸው፤ ገመድን በአንገታቸው የሚያጠልቁትን ሳንዘነጋ። ውጫዊው እንቅስቃሴ ስለ ወጣቶች እያደረገ ያለውን እዚህ ጋር ገታ አድርገን ወጣቶች በውስጣቸው ሊያደርጉት ስለሚገባው ያልተነገረውን ጎልቶ ይታያልና እርሱን ዛሬ እንመልከት። በደጅ ካለው በእጅ ያለውም እንበል።
ፈላስፋና ደራሲ ፍራንሲስ ባኮን “ጥበበኛ ሰው ከገጠሙት እድሎች በላይ እድሎችን ይፈጥራል” ብለዋል። ከእዚህ ቀደም “በልብህ ያለው ምንድን ነው?” የሚል መጣጥፍ ማስነበባችን ይታወሳል። በልብ የሞላው እግርን ያንቀሳቅሳል ስንል በልብ የሞላው ያለውን የገዢነት አቅምም ዳስሰናል። ዛሬ ደግሞ “በደጅ ካለው በእጅ ያለው” በማለት በውስጡ የተነሳሳውን በእጁ ላለው እንዴት ዋጋ መስጠት እንደሚችል እንመለከታለን። በእጃችን ያለ ወርቅ እንደ መዳብ የምንቆጥር እንዳንሆን በእጃችን ያለውን በማወቅ ውስጥ የህይወታችን ጉዞ ውስጥ እንድንበረታ እንመክራለን።
በእጅህ ያለው ምንድን ነው?
በእጅህ ያለው ማለት ብዙ እርቀት ሳትሄድ አሁን ባለህበት ሁኔታ ውስጥ የእኔ ብለህ ልትቆጥረው የምትችለው በአንተ ዘንድ ያለው ችሎታ፣ እውቀት፣ ክህሎት፣ ሰው፣ ገንዘብ፣ ቁሳቁስ፣ ወዳጅ፣ ወዘተ ማለት ነው። ወዘተ ብለን ቁጥሩን ያበዛነውን ዝርዝር ወደ አራት እንክፈለው።
1. የራስ አቅም (ችሎታ፣ እውቀት እና ክህሎት) – አንድን ሥራ ለመስራት የሚያስችል ግብዓትህ መካከል ዋናው ስለምትሰራው ስራ ሊኖርህ የተገባው ችሎታ፣ እውቀት እና ክህሎት ይገኝበታል። የራስህ አቅም! በአንተ ውስጥ የሚገኝ አቅም። ሁሌም እያደገ ሊሄድ የሚገባው፤ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቅድሚያ ልትሰጠው የተገባህ አቅም። አሁን ባለህበት ሁኔታ ውስጥ ሆነህ በራስህ አቅም ልትሰራው የምትችለው ምንድን ነው? መልስህ “ምንም”ሊሆን እንደማይችል እሙን ነው።
ምክንያቱም “ምንም” አቅም የሌለው ሰው ማለት የሞተ ሰው ስለሆነ። “ምንም” የሚል መልስ ሊመልስ የሚችለው በህይወት የሌለ ሰው በመሆኑ መልስህ “ምንም” የሚል ሊሆን አይችልም። በህይወት ያለ ሰው ዛሬ ላይ ተነስቼ ልስራ ቢል ሊሰራቸው የሚችላቸው ሥራዎች አሉ፤ በተለይም አንድ ሥራ አለ። በትኩረት ቢሰራው፤ ቀልቡን ሰብስቦ ቢሰራው፤ ተነቃቅቶ ቢሰራው ወደ ውጤት ሊቀይረው የሚችልበት አንድ ሥራ አለ። ይህን ሥራ ፈልጎ ማግኘትና ይህን ሥራ ለይቶ ይበልጥ በእዚህ ሥራ ላይ ተዘጋጅቶ መሰማራት ሲታሰብ ስራው የሚሰራበትን የራስን አቅም ማወቅ ያስፈልጋል። ባለንበት ዘመን በተለይም በሀገራችን ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው የሚወጡ በእውቀታቸው የሚሰሩበትን የማያውቁ ነገርግን የመመረቃቸውን የእውቅና ሰርተፍኬት የሚያቀርቡልን ብዙ ናቸው። ጉዳዩ ዲግሪና ዲፕሎማ የያዝክበት የሚል ሲሆን ልትሰራ የምታስበውን ሊያሰራህ የሚችል እውቀት፣ ክህሎት ወይንም ችሎታ የሆነን የራስ አቅም ማለት ነውና።
2. ገንዘብ – የገንዘብን አቅም ለመረዳት ብዙ እርቀት መሄድ አይጠይበቅም። ገንዘብ ያስፈልጋል፤ ነገርግን በጤናማ መንገድ መምጣትና በጤናማ መንገድ መተዳደር አለበት። በእጃችን ያለው የገንዘብ መጠን እንዲያድግና ፍሬ እንዲያፈራ ገንዘብ አያያዝን ማወቅ አለብን።
ገንዘብን እንዴት ማግኘት ደግሞም መጠቀም እንዳለብን ለማወቅ የግድ ብዙ ገንዘብ ኖሮን አጥፍተን ወይንም ገንዘቡ አጥፍቶን መሆን የለበትም። በገንዘብ ማጣት የምንቸገረውን ያህል በገንዘብ ብዛት መጥፋት ለምን እንደሚሆን እዚህ ጋር ማሰብ አለብን። ብዙ ገንዘብ ብዙ ሥኬት እንደሚያሳይ መታሰቡ ስህተት ነው። በእጅህ ላለው ገንዘብ የሚኖርህ ትርጉም እንዴት አሳድገዋለሁ፤ እንዴትስ የእኔ የሆነውን አቅም ወደ ሥራ ለመቀየር እገለገልበታለሁ በሚለው ትርጉም ነው።
3. ቁሳቁስ – ያሰብነውን ሥራ ለመስራት ሥራውን ለመሥራት ከሚያስፈልግህ ችሎታ፣ ገንዘብ በተጨማሪ ቁሳቁስ ያስፈልግሃል። በመርከብ ተጭኖ የሚመጣ ትልልቅ ማሽኖችን ለጊዜው አታስባቸው። ነገር ግን “በደጅ ካለው በእጅ ያለው” እሳቤ መሰረት በዙሪያችን ያለውን ቁሳቁስ ተመልክተን የምንሰራውን ልንተልም እንችላለን። በተቋማት ውስጥ ከሚቀረጹ ፖሊሲዎች መካከል አንዱ የንብረት አወጋገድ ፖሊሲ ነው። ንብረትን ማስተዳደር ንብረት መወገድ ባለበት ጊዜና ሁኔታ እንዲወገድ በማድረግም ነው። ባሉበት አካባቢ ያሉ ሊወገዱ የሚገባቸውን ቁሳቁስ ተመልክተው ቁሳቁሱን ያሰቡትን ወደ ሥራ መቀየሪያነት ተጠቅመው ውጤታማ ሥራን የሰሩ ወጣቶች በልዩ ልዩ የሚዲያ ዘገባዎች ተመልክተናል። በብዙ ብር ተገዝተው ከሚመጡ ቁሳቁስ በአካባቢያችን ያሉ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ ቁሳቁሶችን ለማየት አይናችንን መግለጥ ይገባናል? ምንስ ልሰራባቸው እችላለሁ? ወዘተ ብሎ በመጠየቅ መመላለስ አስፈላጊ ነው።
4. ወዳጅ – በሀገራችን ጠንካራ የማህበራዊ ህይወት/social capital አለ። ይህም ማህበራዊ ህይወት በእለት ተእለት ኑሯችን ውስጥ የራሱ የሆነ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖን ሊያሳድር ይችላል። በዙሪያችን ካሉ ሰዎች መካከል ማለትም ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት፣ ጓደኞች፣ ወዘተ መካከል በጣም የምንቀርባቸው የጠነከረ ወዳጅነት ሊኖረን የቻልን ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ወዳጅነት አንዱ ወረታችን ነው። ወዳጅነት ውስጥ ምክርን መቀያየር ይቻላል፤ ለመደጋገፍ በርንም ይከፍታል።
በደጅ ካለው በእጅ ያለው እሳቤ መሰረት የወዳጅነትን ትርጉም በሚገባ በማስቀመጥ በዙሪያችን ያሉ ወዳጆችን ዋጋ በሚገባ ማየት ተገቢ ነው። ወዳጅነት ውስጥ ከሌሎች ውድቀት መማር ይቻላል። ወዳጅነት ውስጥ ከሌሎች ሥኬት መማር ይቻላል። ወዳጅነት ውስጥ ያላየነውን ነገር እንድናይ ይሆናል። ወዳጅነት ውስጥ በአስቸጋሪ ጊዜዎች ደጀንነትም ይኖራል።
ከእዚህ በላይ የተገለጹት አራቱ በዙሪያችን ያለ ሀብት ማሳያዎች ማለትም የራስ አቅም (ችሎታ፣እውቀትና ክህሎት)፣ ገንዘብ፣ ቁሳቁስ እና ወዳጅ የተሰኙት ግብዓቶች አንድን ሥራ ከውስጣችን አውጥተን ወደ መሆን ለማምጣት በብዙ የሚረዱን ናቸው።
እራሳችንን በሆነ ነገር ውስጥ ቆልፈን ያለንበትን ከባቢ ሁኔታ ለመቀየር ከማሰብ በእጃችን ያለውን መመልከት አለብን። በእጃችን ያለውን በሚገባ ተመልክተን ለራሳችን የማከናወን አቅም አለኝ የሚለውን እምነት በመያዝ ለተግባር ስንነሳ በደጅ እናልም ከነበረው በእጃችን ያለውን ወደ ውጤት መቀየር ቻልን ማለት ነው።
በእጅ ያለውን እንዴት ወደ ውጤት እንቀይር?
ሮበርት ስቲቨን ካፕላን የተሰኙ ጸሐፊ በሥራ አጋጣሚ ስለሚገጥሟቸው በሥራቸው እርካታን ስላጡ ሰዎች ሲጽፉ “እምቅ አቅምህ ላይ መድረስ ማለት ወደ መዋቅር አናት ላይ መውጣት አይደለም” ይላሉ። ሠራተኞች ደሞዛቸው እንዲያድግ ተጽእኖ የማሳደር እድላቸውም እንዲሰፋ ወደ ላይ መውጣትን እንደ ሥኬት ይቆጥሩታል። በእርግጥ ከአንድ የሥራ ደረጃ ወደሌላው እያደጉ መሄድ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው።
ምክንያቱም በተቋም ውስጥ በታችኛው መዋቅር ውስጥ ያለን ሰራተኛ እድሜ ልኩን ከታች መቀመጡን እንደ ጥንካሬ ልንወስደው አንችልም። እድገትን መፈለግ በሁሉም ሰው ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ። በተጨባጭ ግን ችግሩ ወደ ላይ በወጡ ቁጥር የሥራ እርካታ የማይገኝበት ሁኔታ ሲኖር ነው። አንዳንዱ ወደ ላይ በወጣ ቁጥር የሥራ እርካታው እየጨመረለት ሲሄድ ሌሎች ደግሞ ይበልጥ የስራ እርካታቸው እየቀነሰ ይሄዳል። ይህ ለምን እንደሚሆን በጻፉት ጽሁፍ ሮበር ስቲቨን የሚመክሩት የራስን አቅም አውቆ በራስ አቅም ላይ የሥራን አካሄድ መተለም የሚል ነው።
ራስን ማወቅ በእጃችን ያለውን ከማወቅ ይለያል። በእጃችን ያለውን የራስ አቅም፣ ገንዘብ፣ ቁሳቁስና ወዳጆችን ማወቅ በቀጥታ ወደ ውጤት አያደርስም። ወደ ውጤት የሚያደርሰው በእጃችን ያለውን እንዳወቅን እንዲሁ ራስን ማወቅ ሲቻል ነው።
ቤተሰብ፣ ጓደኞች እና የሥራ ባልደረቦች በታያቸው መሰረት የሥኬትን ትርጉም በውስጣችን ያኖሩ ይሆናል። በተጨባጭ የሥኬት ትርጉም ግን እንዲያ አይደለም። የሥራ ስኬት መነሻ ሊያደርግ የሚገባው የውስጥ ፍላጎትን ሲሆን ተግባራዊነቱም በእኛ የሚወሰን ነው። በራሳችን ጠንካራና ደካማ ጎን።
በእሁድ ማለዳ ተሰብስበው ሥራ በማጣት ውስጥ ስደትን ለሚተልሙት ወጣቶች እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ቅብጠት መስሎም ሊታያቸው ይችላል።
ሮበርት በጽሁፋቸው በምርምር ስራቸው እውቅና ያገኘ የኢንዱስትሪው ቀዳሚዎች ተርታ የሚሰለፍ አንድ ተመራማሪ በገንዘብም ሆነ በእውቅና የጎደለበት ነገር ሳይኖር በሥራው ደስተኛ እንዳልሆነ ሲሰሙ መገረማቸውን ለሃርቫርድ ቢዝነስ ሪቪው ላይ በጻፉት ጽሑፍ ላይ አመላክተዋል። በጥናታቸውም ይህ አይነቱ ገጠመኝ ደጋግሞ የሚገጥማቸው መሆኑን እና የሥራ ህይወት ትርጉም ሲታይ ራስን በማወቅ በእጃችን ያለውን በማሳደግ ውስጥ፤ በውስጥ ልንሠራው የወደድነው በመስራት ሊገለጥ እንደሚገባው ይመክራሉ።
በእጃችን ያለውን ወደ ውጤት ለመቀየር ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል ራስን ማወቅን ያስቀድማሉ። ራስን ማወቅ ማለት ያለንን ጠንካራ አቅም ማወቅ እንዲሁም ሊስተካከል የሚገባውን ደካማ ጎናችንንም መለየት መቻል ነው።
ሙያዊ ምክርን ፈልገው ወደ እኒህ ጸሐፊ የሚመጡ የተቋም መሪዎች ሆኑም የመሪነት ህልም ያላቸው ግለሰቦች የበረከተ ጠንካራ ጎናቸውን የመዘርዘር አቅም ያላቸው መሆኑን ተገንዝበዋል። ነገር ግን የደካማ ጎን መዝርዝርን ማስቀመጥ ቀላል አይሆንላቸውም። በእጃችን ያለውን ወደ ውጤት ለመቀየር ስናስብ ጠንካራ ጎናችንን መለየት ያስፈልጋል እንዲሁም ደካማ ጎናችንን። በእጃችን ያለውን ለመዘርዘር ስናስብ ችሎታ፣ ገንዘብ፣ ቁሳቁስ እና ወዳጆች ያልናቸው ልንሰራው ላሰብነው ነገር ወሳኝ ግብዓት ሲሆኑ ይህ ወሳኝ ግብዓት ሊያድግ የሚችለው በጠንካራ ጎናችን ላይ ካረፈና በደካማ ጎናችን እንዳይበላሽ ከተጠበቀ ብቻ ነው።
በአንድ ወቅት ከእጃችን የነበረ ነገር ግን ከእጃችን አሁን የሌለን ነገር እንዘርዝርና ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ እንሞክር? የነበረ ግን የጠፋ ወዳጅነት ቢሆን፣ ገንዘብም ሆነ ንብረት ቢሆን፣ ችሎታም ቢሆን የጠፋበት ምክንያቱ ምንድን ነው?ምክንያቶቹን ለመዘርዘር እንሞክር። የዘረዘርነው ምክንያቶች ውስጥ የእኛ ደካማ ጎን የፈጠረው ምን ያህሉን ነው? ሰዎችን በማማከር ሂደት ውስጥ የሚስተዋለው ከእጃቸው ያለው ነገር እንዲጠፋ ምክንያት ሆኖ የሚገኘው የራሳቸው ደካማ ጎን ነው።
ፍጹም የሆነ ሰው ስለሌላ ደካማ ጎንን በማወቅ፤ ደካማ ጎናችን አሁንም ከእጃችን የቀረውን እንዳያበላሽ እንዴት ለመያዝ ማወቅ አለብን። ራስህን እወቅ እርሱም ጠንካራ ጎንህን እና ደካማ ጎንህን በማወቅ ውስጥ ነው።
ሚስትር ኤካርትም በአስራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን በተጻፈ ጽሁፍ ውስጥ “በቅድሚያ ራሱን ማወቅ ያልቻለ ሰው እግዚአብሔርን ሊያውቅ አይችልም” ብለዋል።
ቅዱስ ቴሬሳ የፍጹምነት መንገድ/The way of Perfection በተባለ ጽሁፋቸው “ሁሉም የመንፈሳዊ ህይወት ችግር መነሻው ራስን አለማወቅ ነው።” ብለዋል። ጆን ካልቪን ደግሞ እንዲህ አሉ“የእኛ ጥበብ ሁለት ነገሮችን የያዘ ነው። የእግዚአብሔር እውቀትና ራስን ማወቅ። ሁለቱም አብረው ተጣምረው የሚሄዱ እንጂ የትኛው ከየትኛው እንደሚቀድም ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው።”
አብዛኛዎቻችን ማን መሆናችንን ሳናውቅ ወደ መቃብር እንወርዳለን። ሳናስበው የሌላን ሰው ህይወትን በመኖር ዘመናችንን እንፈጽማለን፤ ወይንም ሌላ ሰው የሚጠብቀውን ለማሟላት ስንዳክር። ይህ አይነቱ ህይወት ከራሳችን፣ ከሌሎች ሰዎች እንዲሁም ከፈጣሪ ጋር የሚያጋጨን ይሆናል።
በእጅ ያለችው ወፍ መርህ/The Bird in Hand Principle
ዶ/ር ሳራስ ዲ. ሳራስቫቲ የተሰኙ አጥኚ “በእጅ ያለችው ወፍ”የሚሉት መርሆችን አስተዋውቀዋል። አኚህ አጥኚ ነገ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን ከሚል ስጋት ወጥተው ዛሬ በእጃቸው ያለውን ነገር ወደ ውጤት ለመቀየር የሚሰሩ ሰዎች ውጤታማ መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ጽፈዋል።
ጥናታቸውን 27 ውጤታማ በሆኑ በተለያዩ ኢንዱስትሪ ውስጥ ባሉ ሥራ ፈጣሪዎች ላይ አድርገው ነበር የሰሩት። በእጅ ያለችው ወፍን ለመረዳት ሦስት ነጥቦችን አንስቶ ራስን መጠየቅ ይገባልም ይላሉ። እነርሱም አንተ ማን ነህ? ምንስ ታውቃለህ?ማንንስ ታውቃለህ? የሚሉ መሆናቸውን። ከእዚህ በላይ በእጃችን ያሉትን አራቱን በእጃችን ያሉትን መመልከቻ ነጥቦችን እና በእጃችን ያለውን ወደ ውጤት መቀየሪያውን በእኒህ ሦስቱ ውስጥ እናገኛቸዋለን።
• አንተ ማን ነህ?/Who you are? ይህ ጥያቄ ዋጋ የምንሰጠውን ነገር የምንፈትሽበት እንዲሁም ለመስራት የምናስበውን ነገር ለመስራት የሚያስፈልገንን አቅም የምንፈትሽበት ጥያቄ ነው። በውትድርና መሰማራት የውስጥ የውስጥ መሻቱ የሆነውን ወይንም ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው የሆነውን ግለሰብ በሌላ ቦታ ላይ ብናሰማራው ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ብዙ ነገሮች አሉ። መስራት የምንወደውን ሥራ በውስጣችን ማዳመጥ መቻል ለእዚህ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንድንሰጥ ያግዛል።
•የምታውቀውስ ምንድን ነው?/What you know? ከትምህርት ቤት ተምረን ከወጣነው ትምህርት ባሻገር በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚረዳ ምን እውቀት አለን። ጥራት ያለው ውሳኔ መወሰን መቻል ለውጤታማ ሥራ አስፈላጊ ነው። ለሌሎች ያለን ልብም እንዲሁ ስለራሳችን የምናውቀውን ያሳያል። ራሳችንን በማወቅ የምንረዳበት ጥያቄ ነው። በጠንካራና ደካማ ጎን ትንተናችን ራሳችን በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ያለውን አቅማችንን መፈተሸ ማለት ነው።
• ማንንስ ታውቃለህ ነው?
አዲስ ዘመን ጥር 01/2013