ፍሬህይወት አወቀ
የግል ባለሃብቶች በሀገሪቱ የልማት ሥራዎች ላይ የጎላ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ አዋጭነቱ አያጠያይቅም። ይሁንና የግሉ ዘርፍ ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት የሚችለው በሚሳተፍባቸው የንግድና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ህጋዊነት ባለው መንገድ ማስተናገድ ሲቻል ብቻ ነው።
ያ ካልሆነና ግልጽ የሆነ የመጫወቻ ሜዳ ለሁሉም ባለሀብቶች በእኩል ደረጃ ካልተዘጋጀ ከሚሰጡት ጥቅም የበለጠ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ የከፋ ይሆናል።
ከግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ውጭ የሀገር እድገት አይታሰብምና ጥቂት የማይባሉ በሀገሪቱ ያሉ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፎች ተሰማርተው ይታያሉ። እነዚህ የግል ባለሃብቶች ከሚሳተፉባቸው ዘርፎች መካከልም የመኖሪያ ቤት(ሪልስቴት) ግንባታ ይጠቀሳል።
መንግስት በሀገሪቱ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ሲያቀርባቸው ከነበሩ አማራጮች ጎን ለጎን የግል ባለሀብቱ ተሳታፊ የሆነባቸው ሪልስቴቶችም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በሀገሪቷ ባሉ የክልል ከተሞች ሲንቀሳቀሱ ይታያል።
እነዚህ በግል ባለሀብቱ እየተገነቡ ያሉት የሪልስቴት መኖሪያ ቤቶች በሀገሪቱ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ምን ያህል ማቃለል ችለዋል? ተደራሽነታቸውስ ለየትኛው የማህበረሰብ ክፍል ነው? ከመንግስት ጋር በጋራ በመሆን አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል ማዕከል ያደረገ ግንባታ ማከናወን ለምን አልተቻለም? አጠቃላይ እየሰጡ ባለው አገልግሎት ደንበኞቻቸውን ምን ያህል ማርካት ችለዋል? የሚሉ ጥያቄዎችን ያቀረብንላቸው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ታደሰ ከበበ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።
በሀገሪቱ ያለው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና የአቅርቦት እጥረት መኖሩ ግልጽ ነው። ይህን ተቃርኖ ለማስታረቅም በርካታ ተዋናዮች በዘርፉ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ቤቶችን ገንብቶ ለነዋሪዎች ለማቅረብ ተሳታፊ ከሆኑት ተዋናዮች መካከል አንደኛው መንግስት ነው።
ሁለተኛው የግሉ ዘርፍ ነው። ሶስተኛው ደግሞ መንግስትና የግሉ ዘርፍ በጋራ ሆነው በሚያደርጉት ጥረት ነው።
ከእነዚህ ዋና ዋና ተዋናዮች መካከል በግለሰቦች ሀብት የሚገነባው የሪልስቴት መኖሪያ ቤት ነው። ይህ በቤት ልማት አልሚ ባለሀብቶች የሚገነባው መኖሪያ ቤት ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ከሚያደርጉ አማራጮች አንዱ ነው።
ይሁንና በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ምን ያህል ቀርፈዋል? ተደራሽነታቸውስ ለማነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እስካሁን ያላቸው ሚና መጠነኛ ነው።
የሪልስቴት የቤቶች ልማት በሀገሪቱ ከተጀመረ ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ አይደለም። ከዚህ ጋር ተያይዞ በቂ አቅም የሌላቸው በመሆኑ ባለሀብቶች አጠቃላይ የመኖሪያ ቤት ችግር መቅረፍ የሚያስችል አቅም ላይ አይደሉም።
አጠቃላይ ከቤት ልማት ስርዓቱ ጋር በተያያዘም ውስንነቶች አሉ። ያም ሆኖ ግን አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች በርካታ የሪል ስቴት አልሚ ባለሀብቶች ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።
እነዚህ የቤት አልሚ ባለሀብቶች ለማነው ቤት እያቀረቡ ያሉት ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ መልሱ ከፍተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚል ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት ባለሀብቱ እንደ ንግድ ሥራ የሚያየውና ለትርፍ የሚሰራው በመሆኑ ነው። ይህም ሪልስቴቶች አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ማድረግ ያልቻሉበት አንዱ ችግር ነው።
በመሆኑም በቂ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ብቻ ተደራሽ በማድረግ ዋና ዓላማቸው ትርፍ ማግኘትና እንደ አንድ የገቢ ምንጭ አድርገው ማሰብ ነው። የቤት ግንባታውን የሚያከናውኑትም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ዜጎች ውጭ የሆኑ ዜጎችን ብቻ ታሳቢ በማድረግ ነው።
ይሁንና እነዚህ ሪልስቴቶች በቂ የሆነ የገቢ ምንጭ እና ከዛ በላይ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሰጡት አገልግሎትም በርካታ ቅሬታዎች እንደሚነሳበት አቶ ታደሰ አንስተዋል።
ይህንንም አቶ ታደሰ ሲያስረዱ ሪልስቴቶች እስካሁን የሚመሩበት የአሰራር ስርዓት የሌላቸው በመሆናቸው ግልጽነት ያልተፈጠረበት፤ ማን ይከታተላል፤ ማን ፈቃድ ይሰጣል፤ መሬት ከወሰዱ በኋላ ተከታትሎ ማን ያስፈጽማል የሚሉ በርካታ ጥያቄዎችን የሚያስነሱ የአሰራር ክፍተቶች አሉበት። ክፍተቶቹ ከአደረጃጀትም ሆነ ከህግ አንጻር የሚነሱ ናቸው።
አብዛኛው በሀገሪቱ የሚገኙ የሪልስቴት አልሚዎች ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በርካታ ቤቶችን ከገነቡ በኋላ መሬት በነጻ አልያም በመነሻ ዋጋ ይወስዱ ነበር። ነገር ግን መሬት ከወሰዱ በኋላ ቤቶቹን የሚገነቡ እንዳሉ ሁሉ፤ ጥቂት የማይባሉ ባለሃብቶች ደግሞ መሰረት አውጥተው መተው፤ ለሶስተኛ ወገን የማስተላለፍ እንዲሁም የግለሰቦችን ገንዘብ ሰብስበው የሚጠፋበት አጋጣሚ እና ሌሎች በርካታ ችግሮችም ተስተውለዋል።
ለእነዚህ ችግሮች በዋናነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል አንደኛው ሪልስቴቶች የሚመሩበት የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው በአደረጃጀት ሪልስቴቶችን ብቻ የሚቆ ጣጠር የሚመራው፤ በየጊዜው የግንባታ ሂደቱን የሚከታተል፤ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ፤ ለግንባታ ወጪ የሚሆነውን በሙሉ ለመከታተል የሚያስችል አሰራርም ሆነ አቅም የለም።
እነዚህ የዘርፉ ትልቅ ማነቆዎች በመሆናቸው አንዳንድ የሪልስቴት አልሚዎች ይህን ክፍተት ተጠቅመው ተገልጋዮችን ከማንገላታት አንስቶ ገንዘባቸውን እስከማሳጣት የሚደርሱበት ሁኔታዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ።
እነዚህን የተገልጋዮች ቅሬታ መፍታት የሚቻለውም ሪልስቴትን ብቻ የሚመለከት የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት በመሆኑ እስካሁን ያልነበረ በቀጣይ ተግባራዊ የሚሆን የሪልስቴት ልማትና ግብይት አዋጅ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተዘጋጅቷል።
ይህ አዋጅ በርካታ ጉዳዮችን የሚዳስስ ሲሆን ለአብነትም አንድ ሪልስቴት ሪልስቴት ለመባል ማሟላት የሚገባውን ዝርዝር መስፈርት ጨምሮ አልሚውና ገዥው እንዴት መገበያየት እንዳለባቸው እና ቤቶቹም እንዴትና በምን ሁኔታ መተላለፍ እንዳለባቸው አዋጁ በግልጽ ያስቀምጣል።
አጠቃላይ ማን ምን ማድረግ እንዳለበትና እንዴት መገበያየት እንዳለባቸው በአዋጁ የተካተተ በመሆኑ ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችንና የተገልጋይ ቅሬታዎችን መቅረፍ ይቻላል።
በተለይም የውጭ ሀገር ባለሃብት ሲሆን፤ ምን ያህል ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ማድረግ እንደሚችል በግልጽ የተቀመጡ ዝርዝር ነገሮች አሉ። እነዚህን ዝርዝርና ግልጽ የአሰራር ስርዓቶች በመንግስት ሲጸድቁ በዘርፉ ያለውን ችግር መቅረፍ ይቻላል ሲሉም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በተያያዘም የሪልስቴት አልሚ ባለሀብቶች ጋር የተለያዩ ችግሮች የሚስተዋሉ ቢሆንም በቅድሚያ በመንግስት በኩል ያለውን ክፍተት መድፈን ይገባል ያሉት አቶ ታደሰ፤ የሪልስቴት ግንባት በሀገሪቱ ከሁለት አስርት ዓመታት ያልበለጠ እድሜን ያስቆጠሩ ይሁን እንጂ አሁን ባለው መረጃ በትክክል ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው የሪልስቴት አልሚ ባለሃብቶች በሀገሪቱ አሉ ለማለት የማይቻል መሆኑን ተናግረዋል። ይህም የዘርፉ ዋነኛ ችግር እንደሆነ አመላክተዋል።
በሀገሪቱ የሪልስቴት ግንባታ የሚገነባው በሪልስቴትነት ተመዝግበውና ፈቃድ አግኝተው አይደለም። ማንኛውም ባለሃብት መሬትና ገንዘብ ካለው የንግድ ፈቃድ ማረጋገጫ ሳይጠየቅ የሪልስቴት ግንባታን ማከናወን ይቻላል።
ባለሃብቶቹ በራሳቸው ይዞታም ይሁን ነባር ይዞታዎችን በግዥ አግኝተውም ቢሆን ቦታ አለኝ ‹‹እገሌ ሪልስቴት ነኝ›› ብሎ ሪልስቴት ሊገነባ የሚችልበት አሰራር ነው ያለው። ይህን ተከትሎም ማስታወቂያ ይነገራል፤ ገንዘብ ይሰበሰባል ከዛ ቀጥሎም በትክክል ይሰራ አይሰራ የሚከታተል የለም። ቦታው ለተባለለት ዓላማ ውሏል አልዋለም የሚታወቅ ነገር የለም።
ስለዚህ በሀገሪቱ ያሉት ሪልስቴቶች ምን ያህል ተገልጋዮችን በቃላቸው መሰረት እያገለገሉ እንደሆነ ማወቅ አይቻልም። ከዚህ በተጨማሪም ምን ያህል የሪልስቴት አልሚዎች በሀገሪቱ እንደሚገኙ እንኳን በተባራሪ ከሚሰማው በስተቀር በትክክል ቁጥራቸው አይታወቅም።
ለዚህም ፈቃድ እንዲያገኙ የሚያደርግ አስገዳጅ ህግ ባለመኖሩ ነው። አሁን በአልሚውና በገዥው መካከል ያለው ግንኙነት በመተማመን ላይ የተመሰረተ ነው። ነገር ግን በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው መሰረታዊ መፍትሔ መሆን የሚችለው ዘርፉ የህግ ማዕቀፍ ሲበጅለት ብቻ ነው።
ቤት በመገንባቱ የመኖሪያ ቤት እጥረት የሚቃለል መሆኑን የሚያምነው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ ማንም ይሁን ማን በህጋዊ መንገድ መሬት ካገኘና በህጋዊ መንገድ ፕላኑን ጠብቆ ከገነባ ችግር የለበትም፤ ይፈቅዳል። ነገር ግን የሪልስቴት አልሚ ባለሀብቶች እነማን እንደሆኑ፤ መቼ ገንብተው እንደሚጨርሱ፤ ፋይናንሱ በራሳቸው ነው ወይስ ከተገልጋዮች ሰብስበው ነው የሚሉትን ጥያቄዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አያውቅም። ማወቅ የሚችልበት የህግ አግባብም የለውም።
በሀገሪቱ ያለው የመኖሪያ ቤት እጥረት በቀላሉ በሪልስቴት አልሚዎች ብቻ የሚፈታ አይደለም። ይሁንና እነዚህ ሪልስቴቶች በቤት ልማቱ ላይ ያላቸው ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
ምንም እንኳን መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ ባይችሉም በቂ ወይም ከፍተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች አማራጭ ሆኖ በመቅረቡ የጥቂቶችን ጥያቄ በመመለስ ረገድ የማይናቅ ድርሻ አላቸው።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የሚቻልበት ዋነኛው መንገድ የረጅም ጊዜ ክፍያን በማመቻቸት ነው። ለዚህ ደግሞ በሀገሪቱ የሚገኙ የሪልስቴት አልሚዎች የአቅም ውስንነት አለባቸው። ምክንያቱም በራሳቸው ገንዘብ ቤት ገንብተው ለተገልጋዮች በረጅም ጊዜ ክፍያ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ያላቸው ባለሃብቶች የሉንም።
በዚህ ምክንያት ሪልስቴቶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተደራሽ ማድረግ አልቻሉም።
ታድያ እነዚህን ሪልስቴት አልሚዎች ከመንግስት ጋር ተቀናጅተው መኖሪያ ቤት እንዲገነቡና የሚገነቧቸውን ቤቶችም ቢያንስ መካከለኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ተደራሽ ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ለምን አልተቻለም ስንል ላነሳነው ጥያቄ፤ አብዛኛውን ማህበረሰብ ተደራሽ ያደርጋል ተብሎ ተስፋ የሚጣለው በዋናነት መንግስት ላይ ነው።
እርግጥ ነው መንግስት ለእያንዳንዱ ግለሰብ ቤት ገንብቶ ማዳረስ አይችልም። ስለዚህ አቅም ያላቸው ግለሰቦች በራሳቸው ከሚገነቡት በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ በቤት ልማት ግንባታ ላይ በስፋት እንዲሳተፍ በመንግስት አቅጣጫ ተቀምጧል።
ስለዚህ በቀጣይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያዘጋጀው የሪልስቴት ልማትና ግብይት አዋጅ ጸድቆ ስራ ላይ ሲውል ለአልሚዎቹ አስፈላጊውን ድጋፍና ክተትትል በማድረግ የተለያዩ አቅርቦቶችን ማሟላት ይቻላል። አልሚዎቹ እነዚህን እና መሰል ድጋፎችን ከመንግስት ማግኘት ሲችሉ የሚገነቧቸውን ቤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ አብዛኛውን ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ ባይቻልም መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተደራሽ ማድረግ ይቻላል።
በዚህ መልኩ የግሉን ዘርፍ ተሳታፊ ማድረግ ከተቻለ በቤት ልማቱ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን አቶ ታደሰ ያስረዳሉ።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሪልስቴት አልሚ ባለሀብቶች ተመዝግበው በህግ አግባብ ማረጋገጫ የወሰዱ ባለመሆናቸው እዚህ መሀል ገብቶ ማስተካከል አይቻልም። ነገር ግን በቀጣይ እያንዳንዱ የሪልስቴት አልሚ ተመዝግበው ማረጋገጫ ወስደው ይህን ያህል ቤት በዚህ ጊዜ እንገነባለን ብለው በህግ አግባብ እንዲቀርቡ ይደረጋል።
ያኔ መንግስት መሬት በማቅረብም ይሁን ሌሎች ድጋፎችን በአማራጭ ሊያቀርብ ይችላል። ምክንያቱም የተዘጋጀው አዋጅ ባለሀብቱ ማሟላት የሚገባውን እና መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል በግልጽ የሚያስቀምጥ በመሆኑ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል።
በአጠቃላይ ባለሃብቱ ከመንግስት የተሻለ አቅም ያላቸው በመሆናቸው በህግ ማዕቀፍ ውስጥ መመራት እንዲችሉና በደንብ ከተያዙና አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ከተቻለ የቤት ግንባታውን ማፋጠን ይቻላል። አሁን ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችም ምላሽ የሚያገኙና ቤቶችን በፍጥነት የማቅረቡ ነገር ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 01/2013