. የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ሐውልት የካቲት 3 ይመረቃል
አዲስ አበባ፡- 15ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለዜጎች መብትና ደህንነት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መምከሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ከጥር 21 እስከ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በጅቡቲ የተካሄደው 15ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በጅቡቲ የሚኖሩ እንዲሁም ለሥራ ጉዳይ ወደ ጅቡቲ የሚመላለሱ ኢትዮጵያውያን ደህንነትና መብት ላይ በሰፊው መምከሩን ገልጸዋል፡፡
እንደቃል አቀባዩ ገለፃ፤ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የጅቡቲ መንግሥት በአገሪቱ የሚኖሩ የውጭ አገራት ዜጎች የመኖሪያና የሥራ ፈቃድን በተመለከተ በቅርቡ ያወጣው ሕግ ለኢትዮጵያውያን አስቸጋሪ እንደሚሆን በመግለፃቸው የኢትዮጵያውያን ጉዳይ በልዩ ሁኔታ እንደሚታይ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኡመር ጊሌ ቃል ገብተዋል፡፡
በወጪና ገቢ ንግድ መስመር የሚታየውን እንግልት ለመቀነስ በጅቡቲ በኩል ብልሽት የደረሰበት መንገድ እንዲጠገን ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ኢትዮጵያውያን በጅቡቲ በኩል ሲሻገሩ የሚያጋጥማቸውን አደጋ ለማስቀረት ከጅቡቲ ጋር በቅንጅት ለመሥራትና ክትትል ለማድረግ የሚያስችል ውይይትም ተደርጓል፡፡
ከውጭ ጉዳይ፣ ከትራንስፖርት፣ ከገቢዎች እንዲሁም ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሮች በተጨማሪ የሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት በመሆኑ፤ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የቴክኒክ ኮሚቴዎች በመቋቋማቸው በበርካታ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረግ ተችሏል። በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት መፈጠሩንም ቃል አቀባዩ አስረድተዋል፡፡
32ኛው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ከጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ የጠቆሙት አቶ ነቢያት፤ በኅብረቱ ተቋማዊ ሪፎርም፣ በአህጉራዊ ነፃ ንግድና በሌሎች የአፍሪካ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክርም ጠቁመዋል፡፡ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለአፍሪካ ነፃነትና አንድነት ላበረከቱት አስተዋፅኦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ፈለገ ሰላም የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ባለሙያዎች የተሠራው የመታሰቢያ ሐውልት የኅብረቱ የመሪዎች ስብሰባ በሚጀመርበት ቀን፣ የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚመረቅም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይና የጸጥታ ፖሊሲ ከፍተኛ ኃላፊ ፌደሪካ ሞጌሬኒ የካቲት 2 ቀን 2011 ዓ.ም፤የኢስቶኒያ ፕሬዚዳንት ክሪስቲ ካልጁሌይድ ደግሞ የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡም አቶ ነቢያት ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2011
አንተነህ ቸሬ