አዲስ አበባ፡- የሬስ ኢንጂነሪንግ ሠራተኞች በተቋሙ ብልሹ አሰራር መንገሱንና የኅብረት ስምምነት ጥሰት እየተፈጸመ መሆኑን ገለጹ፡፡ የሬስ ኢንጂነሪንግ ሠራተኞች በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በተቋሙ አምባገነንነትና ማናለብኝነት ነግሷል፡፡ የኅብረት ስምምነት ጥሰቶች እየደረሱ ናቸው፡፡ በኅብረት ስምምነቱ የተቀመጡ ጥቅማ ጥቅሞች እየተሻሩ ይገኛሉ፡፡ ሠራተኞችን በማናደድና በማበሳጨት ስራውን ጥለው እንዲወጡ ግፊት እየተደረገ እንደሚገኝ በመጠቆምም፤ ከሥራ የተሰናበቱ ሠራተኞችን እንደማስፈራሪያነት በመጠቀም ሌሎችን እያሸማቀቋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለአገርም ለወገንም የሚጠቅም ድርጅት እየወደቀ እንደሚገኝ ያመለከቱት ሠራተኞቹ፤የመልካም አስተዳደር ችግሩ ሊቀረፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ህዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም በተለጠፈ ማስታወቂያ በኅብረት ስምምነት መሰረት እስከ 95 በመቶ ፕሮፊደንት ፈንድ መስሪያ ቤቱና ሠራተኛው ያስቀመጠውን ብድር መውሰድ ይቻል የነበረው ተቀይሮ ድርጅቱ ያዋጣውን መበደር እንደማይችል በማስቀመጥ ግልጽ የኅብረት ስምምነት ጥሰት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ ሰራተኛው ለዓመት ዕረፍት ሲወጣ የትራንስፖርት አበል ለአንድ ዓመት አንድ ጊዜ ይከፈል የነበረው 500 ብር የትራንስፖርት አበል በማቋረጥ በግልጽ የኅብረት ስምምነት ጥሰት መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ማዋከብና የተለያዩ ጫናዎች እንደሚደርስባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ከሥራ የተሰናበቱ የሬስ ኢንጂነሪንግ ሠራተኞችና የሠራተኞች ማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባላትም ከአንድ ዓመት በፊት ከሥራ ተሰናብተው ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝ ጠቁመው ‹‹መለዋወጫ እቃዎችን ከተቋሙ ሽያጭ ማዕከል ገብተን መግዛት ተከልክለናል፣ የተረከብነውን ንብረት ማስረከብም ሆነ ንብረቱ ስላለበት ሁኔታ ማወቅ አልቻልንም›› ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
ከሥራ የተሰናበቱ ቅሬታ አቅራቢዎች አቶ አንድነት ሃይሉ፣ አቶ ተስፋዬ አለማየሁ፣ አቶ ሃይሉ ምትኩ፣ አቶ ቴዎድሮስ ክንዴና አቶ ስዮም ወርቅነህ፤ ከሥራ ከተሰናበትን በኋላ ድርጅቱ ያለብንን ንብረት በ10 ቀን እንድናስረክብ ጠይቆን ልናስረክብ ስንቀርብ በወቅቱ ንብረቱን የሚረከበው ኃላፊ እረፍት እንዲወጣ በመደረጉ ንብረቱን ለማስረከብ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ ግለሰቡ በፍቃዱ እረፍቱን ትቶ በሚያመቸው መልኩ ቀን መድቦ መረከብ ቢጀምርም ሁለት ሰዎች ንብረታቸውን ካስረከቡ በኋላ የአንድ ሰው ንብረት በሙሉ በመጥፋቱ ወደ ተቋሙ እንዳንገባ በመታገዳችን ማስረከብ አልቻልንም ብለዋል፡፡
ከሥራ የተሰናበተ ይቅርና ሥራ ላይ የሚገኝ ሠራተኛም ቢሆን ንብረቱን ማንቀሳቀስ የሚችለው በድርጅቱ ኃላፊዎች ፊርማ ብቻ ሆኖ ሳለ ጠፋ መባሉ ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ የአንድ ሰው ንብረት የጠፋውም ሆን ተብሎ እነርሱን ለማጉላላትና ጫና ለማሳደር እንደሆነ አመልክተው፤ በዚህ ምክንያትም ንብረት ያላስረከብን ሠራተኞች ስጋት ላይ ወድቀናል፣ ስለሆነም ድርጅቱ ንብረቱን ለመረከብ ሁኔታዎችን ያመቻችልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ወደ ተቋሙ ሽያጭ ማዕከል እንዳንገባ መታገዳችን ሌላም ችግር ፈጥሮብናል ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ድርጅቱ የተለያዩ የመለዋወጫ ዕቃዎችን በብቸኝነት ስለሚያስገባ ወደ ሽያጭ ማዕከሉ ገብተው ዕቃዎችን ለመግዛት መታገዳቸው አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ ንግድ ፍቃድ እስካወጣና አገልግሎት እስካቀረበ ድረስ ሊከለከሉ እንደማይገባ አመልክተዋል፡፡
በአካልም በመሄድ ስልክ በመደወልም ከድርጅቱ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2011
ዘላለም ግዛው