‹‹የዘንድሮ የገና በዓል ከሌላ ጊዜ አንፃር ሲታይ በተወሰነ መልኩ ቀዝቀዝ ያለ ይመስላል፡፡›› በማለት ሃሳባቸውን የሚጀምሩት ሸማች ወይዘሮ አልማዝ ወርቁ፤ ምክንያቱን በውል ለመረዳት ቢያዳግትም በበዓላት ጊዜ ህብረተሰቡ ገበያ ላይ ያሳይ የነበረው ሽሚያ እና መገፋፋት አሁን ላይ አለማስተዋላቸውን እና ተረጋግቶ መሸመት መቻሉ ገበያውንም አረጋግቶታል የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡
ሙሉ ለሙሉ ጭማሪ የለማ ማለት አይቻልም፡፡ በተወሰነ መልኩ የዋጋ ጭማሪ ቢታይም ያን ያህል ተጋኖ የሚነገር እንዳልሆነ አመልክተው፤ ፒያሳ የመገናኛ ብዙሃን ማሰልጠኛ አካባቢ ቀይ ሽንኩርት በ16 ብር፤ ነጭ ሽንኩርት ደግሞ በ90 ብር መግዛታቸውን ጠቅሰው፤ ገበያው ከበዓል ሰሞን በፊትም ተመሳሳይ እንደነበር እና በሽንኩርት ላይ ከበዓል ጋር ተያይዞ ጭማሪ አለማየታቸውን ይናገራሉ፡፡
በተወሰነ መልኩ ከቁም እንስሳት ጋር ተያይዞ ካለፈው ጊዜ የተለየ ጭማሪ መኖሩን እንዳስተዋሉ እና ካለፈው ማለትም ለዘመን መለወጫ ከገዙት ፍየል ብዙም ያልተለየ ፍየል በ5ሺህ ብር፤ ባለፈው ከገዙት ፍየል በ500 ብር ጭማሪ መግዛታቸውን ይገልፃሉ፡፡
ሌላኛው ሸማች አቶ ፍፁም ካሳም በተወሰነ መልኩ ጭማሪ ቢኖርም ብዙም የተጋነነ ጭማሪ አለማየታቸውን ገልፀው፤ ነገር ግን ባለቤታቸው እንደነገሯቸው ሎሚ እና እንቁላል እጅግ መወደዳቸውን ከዚያ ውጪ በተለይ በቅቤ፣ በዶሮ እና በበግ ገበያ ላይ ግን የዋጋ ጭማሪ አለመኖሩን እንዳረጋገጡ ይገልፃሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ እና የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ሚኤሳ እንደሚናገሩት፤ ቢሮ በአጠቃላይ የቁጥጥር እና የድጋፍ መደበኛ ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በዓል ሲሆን ደግሞ ከመደበኛ ሥራው በተጨማሪ የተለየ ሥራ የሚሰራ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በከተማዋ ባሉ ወረዳዎች እና ክፍለ ከተሞች ገበያው እንዳይረበሽ እና የዋጋ ንረት እንዳይኖር ልዩ ግብረ ኃይል አቋቁሟል፡፡
ግብረ ኃይሉ በአጠቃላይ የበዓል ገበያው ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲከወን እና ሥርዓት እንዲኖረው የህግ ጥሰት እንዳይፈፀም ቁጥጥር እና ክትትል ያደርጋል፡፡ ይህን ሲሰራ እያንዳንዱን የንግድ ተቋም በር ለበር የማረጋገጥ ሥራ ይሰራል፡፡ የዋጋ ንረት መኖር አለመኖሩ ይረጋገጣል፡፡
ዋጋ የሚያንሩ እና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት ላይ ደግሞ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተጨማሪ የአየር በአየር ሽያጮችን እና ያለንግድ ፈቃድ እና ደረሰኝ መቆረጥ እያለበት ያለደረሰኝ እንዳይነግዱ ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡
በተጨማሪ እንደአቶ ዳንኤል ገለፃ፤ ጥራቱ የተጓደለ ምርትን ይዞ ወደ ገበያ የመምጣት ሁኔታ አለ፡፡ በተለይ ከበዓላት ጋር ተያይዞ እነዚህ ሁኔታዎች በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ በመሆናቸው ግብረ ኃይሉ በእነዚህ ላይም ይሰራል፡፡ በተለይ ጊዜ ያለፈባቸው እና የተበላሹ ምርቶች ለገበያ የሚቀርቡበት ሁኔታ ሊፈጠር ስለሚችል በዛ ላይ ክትትል ይደረጋል ይላሉ፡፡
አቶ ዳንኤል፤ በበዓል ሰሞን ከተበላሹ ምርቶች ባሻገር የሚዛን ጉድለት የሚታይበት ሁኔታ መኖሩን፤ አንዳንዴ ከአንድ ኪሎ ላይ ሩብ ኪሎ እስከ መቀነስ የደረሰ ተግባር እንደሚፈፀም በማስታወስ፤ ይህንን ችግር ለመከላከል የተቋቋሙት ግብረኃይሎች የሚሰሩ መሆኑንም ነው የሚያመለክቱት፡፡
እስከ አሁን በተሰራው ሥራም በየክፍለ ከተማው አየር በአየር ሲሸጡ የተያዙ እና ሌሎችም ከላይ የተጠቀሱ ተግባራትን ሲያከናውኑ የነበሩ ነጋዴዎች የተያዙ መሆናቸውን እና ሱቆችም መታሸጋቸውን በተጨማሪ ማስጠንቀቂያ እና የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡
በሌላ በኩል በዋነኛነት ለዋጋ ንረት ምክንያት የሚሆነውን የምርት እጥረት ችግር ማለትም የበዓል ምርት ፍላጎት እና አቅርቦትን ለማጣጣም በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል የኢንዱስትሪ ምርትም ሆነ የግብርና ምርቶች ወደ ገበያው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ዳንኤል ያመለክታሉ፡፡
በተለይ የግብርና ምርቶችን፣ ዶሮ እንቁላል እና የመሳሰሉ የቁም እንስሳትን ሳይቀር ከክልሎች ጋር በማስተሳሰር ወደ ከተማው እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በንግድ ሥርዓቱም ጭምር ያለውን ምርት ቁጥጥር በማድረግ ችግር ሲኖርም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በተለይ በቁም እንስሳት በኩል በከተማዋ በተገነቡ ስድስት የቁም እንስሳ የገበያ ማዕከላትም ግብረ ኃይሎቹ እየሰሩ መሆናቸውን በመጠቆም፤ ህብረተሰቡ በእነዚህ ማዕከላት ገብቶ ግብይቱን እንዲፈፅም የተመቻቸ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ትልቁ መረሳት የሌለበት ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ማንኛውም ሸማች ወደ ግብይት ማዕከላት ሲገባ ራሱን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን አስታውሰው፤ ራሱን የመጠበቅ ማክስ የማድረግ ብቻ ሳይሆን ሳኒታይዘር የመጠቀም እና ርቀቱን የመጠቀም ጉዳይ ለማስታወስ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁንም ሸማቹም ሆነ ነጋዴው ኮቪድን እየተከላከለ ግብይቱን መፈፀም እንዳለበት ሊረሱ አይገባም ብለዋል፡፡
ከዚያ ውጪ በየትኛውም አካባቢ የሚያጋጥሙ ህገወጥ እንቅስቃሴዎች እና ከንግድ ጋር ተያይዘው የሚያጋጥሙ ጥሰቶች ካሉ በነፃ የስልክ መስመር ‹‹ 8588›› ጥቆማ ከተሰጠ ጉዳዩ በተጠቆመበት አካባቢ ባለው መዋቅር አማካኝነት ተገቢውን የእርምት እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2013