አብርሃም ተወልደ
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩት አበይት በዓላት መካከል የገና (የልደት) በዓል አንዱ ነው። ይህ በዓል ሰማይ እና መሬት የታረቁባት፣ ሰው እና መላእክት በአንድነት የዘመሩበት ፣ ከሁሉም በላይ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲጠበቅ የነበረው የአዳም ተስፋ የተፈፀመበት፣ ተስፋውም ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ታላቅ የደስታ ቀን ነው።
በዓሉ ከሃይማታዊ ማለት የኢየሱስ ክስቶስ ልደትን ከማሰብ ባሻገር ትውፊታዊ ባህላዊ የአከባበር ስርዓቶችም አሉት። ባህላዊ እና ማህበራዊ አከባበሩ እንደየአካባቢው ቢለያይም የጋራ የሚያደርጋቸው የአከባበር አይቶች ግን አሉ። ከእነዚህም መካከል የገና ጨዋታ እና ቤት ያፈራውን ህብረት መመገብ ፣መረዳዳት በአገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ሊባል በሚችል መልኩ የሚከወን ተግባር ነው።
የቀደመው የገና በዓል አከባበር መልክ
አቶ ጌታቸው እርቅይሁን ይባላሉ ፤የ80 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋው ናቸው። አቶ ጌታቸው አዲስ አበባ ኑሮአቸውን ከአደረጉ 53 ዓመታትን አስቆጥረዋል። የመጀመሪያ የገና (የልደት) በዓል አከባበርን የሚያውቁት ገጠር ባሉበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳሉ። አቶ ጌታቸው አከባበሩንም ሲያስረዱ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የገና በዓሉ አከባበር ክዋኔ ሃይማኖታዊውንና ትውፊታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ እንደሆነ ይናገራሉ።
በልደት በዓሉ ከሚደረጉ ተግባራት መካከል የገና ጨዋታ አንዱ ነው የሚሉት አቶ ጌታቸው ጨዋታውን ለመጫወት ወጣቶች እና ጎልማሶች ከያሉበት ይሰበሰባሉ፤ ጨዋታው የሚሆኑ ቁሶቹን ተጨዋቾቹ በመያዝ ይመጣሉ። አዛውንቶች ጨዋታውን መርቀው ይከፍታሉ። ከአዛውንቶችም መካከል አቅም ያለው እና ሸነጥ ያደረገው ካለ ከወጣቶች እና ከጎልምሶች ጋር በመሆን ይጫወታሉ።
እንደ የአካባቢው ልማድ የገና ጨዋታ የታህሳስ ወር እንደገባ የሚጀመሩ ሲኖሩ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ከወሩ አጋማሽ በሌላው ደግሞ በዋዜማው እንደሚከናወን አቶ ጌታቸው ይገልጻሉ።በጨዋታው ወቅት ጎራ ለይተው በሚጫወቱ መካከልም በሆታ እና በእልልታ የሚያዜሟቸው የተለያዩ ዜማዎችም አሉ፤ይህም በጨዋታው ተቃራኒ ቡድን ላይ ነጥብ ሲያስቆጥሩ እንዲህ እያሉ ያዜማሉ ፡-
«አሲና በል አሲና ገናዬ።
ኢዮሃ! አሲና በል
ኢዮሃ! አሲና ገናዬ።
ጨዋታው የፈጀው ጊዜ ፈጅቶ ሲጠናቀቅ ደግሞ ድል ያደረገው ቡድን
“. . .ማታ ነው ድሌ
ይሄ ነው አመሌ።”
በማለት እየዞሩ ሲጨፍሩ ያመሻሉ፤ ሽልማቶችን ይሰበስባል። ታዲያ ከዚህ በህላዊ የገና ጨዋታ በኋላ ሁሉም ቤት እንደ አቅሙ ድግስ ስለሚኖር ደግሞም ሁሉም የደገሰው እንዲበላላት ስለሚፈልግ በተራ ያለአንዳች ልዩነት አንተ ከዚያኛው ዘር ነህ፤ አንተ ከዚህ ነህ ሳይባል በህብረት ሁሉም በአንድነት ይመገባል። ተረኛው ደግሞ በሚቀጥለው ቀን እንዲሁ ያደርጋል። እንዲህ እንዲህ እያለ በዓሉ ያልፋል።
“በአዲስ አበባ የበዓሉ አከባበር ህብረቱ ፣መተጋገዙ፣ መደጋገፉ …ከገጠሩ ኢትዮጵያ የተለየ አይደለም” የሚሉት አቶ ጌታቸው አዲስ አበባ ገራገር ደግ ህዝብ ያለበት ከተማ መሆኗን፤ ለዚህም በከተማዋ ባሳለፉት 53 ዓመታት ይህንኑ ማየታቸውን ይገልፃሉ።
በመሐል አንድነትን የሚንዱ ሰው ሁሉ ወደ ጎጡ ወደ ብሔሩ እንዲሄድ የሚያደርጉ ስራዎች ተሰርተው ለዘመናት በቆየው የህብረተሰቡ አንድነት እና መደጋገፍ ላይ ጥላ እንዲያጠላበት ሆኖ ነበር። አሁን ግን ወደ ተነሳንበት ወደ ቀድሞ በጎነታችን እየተመለስን ነው ይላሉ አቶ ጌታቸው።
ሌላኛው ግለስብ በጡረታ እስከተገለሉበት ጊዜ ለ41 ዓመታት አገራቸውን በሙያቸው አገልግለዋል፤ እኚህ የ84 ዓመትም የእድሜ ባለጸጋ ናቸው፤ ኢንጂነር አወቀ ወልደ ሚካኤል። በእሳቸው ዘመን የገና በዓል አከባባሩ ምን እንደሚመስል ላነሳንላቸው ጥያቄ ኢትዮጵያ አያሌ ባህል እና ሀይማኖታዊ ክብረ ባዕሎች ያሏት አገር እንደሆነች ጠቅሰው እሳቸው ባሳለፉት ዘመን የገና በዓል አከባበር “ልዩ ነበር!” በሚል የአድናቆት ቃል ጀመሩት።
አቶ አወቀ ከሁሉ የሚቀድመው ገና ጨዋታ ሲሆን ለዚህም ለጨዋታው የሚሆን ቦታ ፣ጨዋታውንየሚመራ ዳኛ በመምረጥ ዝግጅት የሚደረግ ሲሆን ከጨዋታው በፊት በሰፈሩ በታወቁ ሽማግሌዎች ምርቃት ይከናወናል፤ከዚያም ጨዋታ ይደረጋል። የገና በህላዊ ጨዋታ ከተከናወነ በኋላ አሸናፊም ተሸናፊም ሁሉም በህብረት በመሆን ይመገባሉ፤ የተለያዩ ግጥሞችን እና ስነ ቃሎችን በመጠቀም የተሸነፈውን ሸንቆጥ እያደረጉ ያሸነፈውን እያበረታቱ የተለያዩ ጨዋታዎች ይጫወታሉ።
ኢንጂነር አወቀ “ባሳለፍኩት ዘመን በበዓልም ሆነ ከበዓል ውጭ ‘እኔ’ የሚባል የለም ፤ህብረተሰቡ የሚሰራውን ሁሉ የሚሰራው፤ የትኛውም እንቅስቀሴው የገናን በዓልንም ጨምሮ ሌሎች በዓላትንም የሚያከብረው በህብረት ‘በእኛነት’ ሰሜት ነበር” ይላሉ።
መረዳዳት ያልተጻፈ ህብረሰቡ ልብ የተጻፈ እና ህብረተሰቡ ያለማንም ቅስቀሳ ሲያደርገው የኖረ ህግ እንደሆነ የሚናገት ኢንጂነሩ ያለህብረት አይደለም በዓል እና ደስታ ለቅሶም አይደምቅም የሚል አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
ኢትዮጵያ ግን በቀደመው ዘመን ላይፈቱ የተጋመዱ በዘር ያልሆነ እንዲሁ ፍቅር የተጋመደው ህዝብ የሚኖርባት ምድር እንደሆነች ይገልፃሉ። ይህች እድለኛ እና ከአምላክ የተሰጠች ምድርን አባቶች የተረከቡትን ከነበጎነቷ እንዳስረከቡን እኛም እንዲሁ እናድርግ የሚል መልክት ለትውልዱ ያስተላልፋሉ።
ኢንጂነሩ የሚከተለውን ምሳሌ በማንሳትም የህብረተሰቡ ችግሮች ምን እንደሆኑ ይጠቅሳሉ። በመንጋው ውስጥ አንዳንድ ኃይለኛ እንስሳት ቢኖሩ መንጋን ከወንዝ ውኃ በመጣበት ጊዜ ወንዙ ከሚመጣበት አቅጣጫ ጫፍ ላይ ይጠጣሉ፤እንደዚህ ያሉ እንስሶች የሚገርመው ነገር ለራሳቸው የሚበቃቸውን ያህል ከጠጡ በኋላ ሌሎች ንጽሁ ውሃ እንዳይጠጡ ያደፈርሱባቸዋል። ለራሳቸው የሚሆንላቸውን አግኝተው ለሌሎች ግን ምንም ባለማሰባቸው ክፉ አድርገውባቸው ምቾት ያሳጧቸዋል።
በመከራ እና በችግር ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ተገቢውን ድጋፍና እርዳታ የማናደርገው አቅም ስለማይኖረን ብቻ እንዳልሆነ ፤ በእኔነት መንፈስ ተሞልተን ከራሳችን ምቾች ወጥተን እነርሱን ለመርዳት ፍላጎት በማጣታችን ነው ይላሉ።
ከእንደዚህ ዓይነት እኩይ ተግባር ወጥተን ከግለኝነት እና ከራስ ወዳድነት ተላቀን በገና በዓል ፤ በዓሉ ራሱ አምላኩ ራሱን ኣሰልፎ ለዓለም የሠጠበት በመሆኑ ለጎረቤት እኛም ካለን በመቁረስ ከ “እኔ” ወጥተን “እኛ” ወደሚለው ማደግ ያስፈልገናል።
ወጣቱ ትውልድ ከሁሉ አስቀድሞ ታሪኩን በአግባቡ ማወቅ አለበት ሲሉም ይመክራሉ። ለዚህም የቀድሞ አባቶች በዓልን እንዴት እንዳሳለፉት፣ እንዴት ወገኖቻቸውን ይረዱ እንደነበር መለስ ብሎ ማየት ይጠቅማል። ወጣቶች ከሚለያያቸው ጥቂት ምክንያቶች ይልቅ /ለዚያውም እውነት ያልሆኑ/ የሚያቀራርቧቸው አያሌ ምክንያቶች እንዳሉ በማሰብ መገፋፋትን በመተው ለአገር አንድነት፣ ሰላም እና ብልጽግና መስራት ይኖርባቸዋል።
ከምንም ነገር በፊት መቅደም ያለበት የሀገር ሰላም ሲሉም ያስገነዝባሉ። እኛ አረጋውያን የምንጦረው፤ ብንታመም አስታማሚ አግኝተን መኖር የምንችለው፣ ስናርፍም በክብር የምንቀበረው የሀገር ሰላም ሲኖር ነው። ህጻናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች ተምረው ለቁም ነገር የሚበቁት ሀገር ሰላም ሲሆን እንደሆነ የጠቀሱት ኢንጂነር አወቀ ችግሮቻቸንን ተመካክረን በመፍታት የህዝቦችን አብሮ መኖር እሴት ማጠናከር አስፈላጊ ነው ይላሉ።
ይህንን ችግር ፈተን በመላው ሀገራችን ሰላም እንዲጎለብት የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅብናል ብለዋል።ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በመነጋገር መፍታት ይገባናል ነው የሚሉት ።
ለአገር አንድነት ችግሮችን በመፍታት የህዝቦች አንድነትና አብሮነት ትስስር ማጠናከር ይገባናል፤ተሳስበንና ተደጋግፈን መኖር አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ዛሬ የሚከበረው የገና በዓልም ከዚህ አንፃር በደስታ፣ በመተሳሰብና በመደጋገፍ ተከብሮ ማለፍ እንዳለበት የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው አባቶች የገለፁት።
መሰናበቻ
ኢትዮጵያ ባህል የበረከተባት የተዋበ ማንንት ያነፃት ውድ ምድር ናት። ኢትጵያዊነት የባህል ድርብርብነት የመከባበር ተምሳሌት የውህደት የአብሮ መኖር ውጤት ነው። ማህበረሰባዊ እሴቶቻችንን የእርስ በእርስ መከባበራችንን የሚያጎሉ የአብሮ መኖር ትስስራችንን የሚያደምቁ ትልቅ ሀብቶቻችን ናቸው።
አገሪቱ በተፈጥሮ ውበቷ በታሪክ ቅርስ በበርካታ ብሔር ብሄረሰቦች መገኛ በቱሪዝም አብቶቿ የምትታወቅ አገር እንደሆነች ሳይታለም የተፈታ ነው።ስለዚህም አገሪቱ ያላትን የበለጸገ ባህል የደረጀ ባህላዊ እውቀት በመጠቀም የአገር አንድነት ማስጠበቅ ተገቢ ነው።
እኛም አባቶቹ እንዳነሱት ሀገራችን በእያንዳንዱ ክልል እና ብሄር ብሔረሰብ ዘንድ የሚገኙ ባህላዊ ዕወቀት የደረጀ ድንቅ የመረዳዳት የመቻቻል የሰላም እና የፍቅር እሴቶች አሉን፤ እነዚህ እሴቶች የመጣብንንና የሚመጣብንን ሰይጣናዊ የጥፋት ውሃ ለመከላከል ለመግታት ከመርዳት አልፈው ለአገሪቱ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ግለሰብ እድገትና ብልጽግና ወሳኝ ናቸው።
ስለዚህም ልክ እንደ ቀደመችው ኢትዮጵያ ያሏትን ድንቅ ትውፊቶች ከአገር አልፎ ለዓለም ምሳሌ እንዲሆኑ ማበልጸግ እና ለአገራዊ መግባባት እና አንድነት መጠቀም ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የፍቅር የመቻቻል አገርነቷ ይቀጥላል። መልካም በዓል!!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2013