ምህረት ሞገስ
ምስጋና ለፖለቲከኞቻችን! ይክበሩ! ይመስገኑ! የብሔር ማንነትን እያገነኑ የሳሉበት መንገድ፤ ጉዳዩን እያጦዙ አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ ለመድረስ አብቅቶናል:: የብሔር ነፃ አውጪዎች ማንን ከማን ነፃ እንደሚያወጡ በውል ሳያስረዱን ( አንዳንዴ እነርሱም ይህንን በደንብ የተረዱ አይመስለኝም)፤ ነፃ አውጪነትን እያቀነቀኑ ግራ በመጋባት እና ግራ በማጋባት ዘመናቸውን አሳልፈው አንዳንዶቹ የህይወታቸውን ብዙ ዘመን ከመፍጀት አልፈው እስከማለፍ ደርሰዋል::
ነፃ እናወጣለን ባዮች የብሔር ነፃ አውጪነት ጉዳይ ይዘው ኢትዮጵያን ማመስ ከጀመሩ ግማሽ ምዕተ ዓመት እየተቆጠረ ነው፤ ይከፉብኝ ይሁን! ያው መቼም ይህማ እውነት ነው:: ብቀጥል ይሻላል::
ቀጠልኩ! እንደሚታወቀው ብሔርን ነፃ እናወጣለን ተብሎ ጫካ መግባት ከተጀመረ ከ1960ዎቹ አካባቢ ጀምሮ ዘመኑ ሲሳላ ወደ አምስት አስርት ዓመታት ልንቆጥር ጥቂት ቀረን:: እናላችሁ የደንቆሮ ለቅሶ መልሶ መላልሶ እንደሚባለው ሁሉ በጥናት ላይ ያልተመሰረተው የነፃ አውጪነት ጉዳይ ዳብሮ ብዙዎችን አስከትሎ ስልጣን ለማስገኘት አብቅቷል::
ነገር ግን ቅሉ በጣም የሚያስገርመው ራሳቸው ነፃ አውጪ ነን ባዮቹ በስልጣን ላይ ወጥተው፤ ከስማቸው ጀምረው ተቀይረው ለህዝባቸው ነፃነትን ከማወጅ ይልቅ፤ በስልጣን ላይ ሆነውም ‹‹ነጻ አውጪ ነን›› ከማለት ወደ ኋላ አላሉም::
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ የቆየ ፓርቲ ነፃ አውጪነኝ ባይነቱን ሲቀጥልና ሲያስቀጥል ማየትም ሆነ መስማት ፈገግ ከማሰኘቱም ነጻ አውጪዎች የሃሳብ ድርቀት እንዳለባቸውና ገና እራሳቸውም ነጻ መውጣት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው ::
እነዚሁ ነፃ አውጪ ነን ባዮች ስልጣናቸውን ተቆናጠው ነፃ እናወጣዋለን ያሉትን ህዝብ ‹‹ነፃ ወጥተሃል፤ ከአሁን በኋላ ማንም አይጭንህም ›› ብለውት ይሆን ? እውነት ለመናገር ይህን ማለታቸውን አልሰማሁም::
እናላችሁ ስልጣን ላይ ወጥተው ሲመሩ የነበሩትም ሆኑ እስከ አሁን በብሔር ስም የመዘዙት ሰበዝ ስላላዋጣቸው ስልጣን ያልተቆናጠጡት የብሔር ነፃ አውጪነን ባዮች አሁንም እዛው ነፃ አውጪነት ላይ ተተክለው ቆመዋል:: እና አሁንም በእነርሱ እምነት ብሔርን እየተጫነ ያለ መንግስት ወይም የሆነ ማህበረሰብ አለ ማለት ነው::
እውነት አሁን የብሔር ማንነትን እየተጫነ ነፃነትን እየነፈገ ያለው ማን ነው? እነዚህ ፓርቲዎችስ ብሔራችን ነው ያሉት ነፃ እናወጣዋለን የሚሉትን ማህበረሰብ ነፃ የሚያወጡት ከማን ነው? በእውነት ለግማሽ ምዕተ ዓመት ነፃ አውጪ ነን ብለው የቆዩ ፓርቲዎች አሁንም ድረስ መገኘታቸው ወደ ፊትም መቀጠላቸው እንቆቅልሹ አልገባሽ ብሎኛል::
የድሮ ሰው ባላባት ሳይቀር ትግሬው ልጁን ለአማራ፤ አማራው ለትግሬ፤ አማራው ለኦሮሞ፣ ኦሮሞ ለጉራጌ፣ ጉራጌው ለሱማሌ፣ ሱማሌው ለአፋር፣ አፋሩ ለትግሬ፣ ብቻ ያገኘው ላገኘው ልጁን ይድር ነበር:: የጎንደር ሰው የሽሬን ሰው ማግባት መቼም አግራሞትን ፈጥሮ አያውቅም::
ጥንቃቄው ዘመድ ዘመድን እንዳያገባ ነበር:: አሁን ላይ ግን እየታየ ያለው ከቀጠለ ምስጋና ለብሔር ነፃ አውጪዎች፤ አንድ ብሔር ከሌላ ብሔር ጋር በጋብቻ የሚተሳሰርበት ሁኔታ የተመናመነ ይመስላል::
በእርግጥ የእኛ ነገር የሰራን ከማክበር ይልቅ፤ መናቅ እና ማንቋሸሽን እንደጥሩ በመውሰድ ሥራቸውን በማድነቅ የአገር ኩራት ሆነው ለዓለም አደባባይ መቅረብ ያለባቸውን ሰዎች፤ ፋቂ፣ ሞረቴ፣ ሸክላ ሰሪ በሚል በማሳነስ ‹‹ልጄን ለዚህ ሰው አልድርም›› የሚባልበት ሁኔታ እንደነበር መካድ አይቻልም::
ነገር ግን ያም ቢሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል:: ደግሞም ነፃ አውጪነን ባይ ፖለቲከኞች ህዝባችንን ነፃ ልናወጣ ተነስተናል ሲሉ ስለእነዚህ ሰዎች ሳይሆን በጥቅል ስለአንድ ብሔር ነፃ ማውጣትን በሚመለከት ብቻ የሚገልፁ መሆኑ ይታወቃል::
ሌላው ምናልባት ነፃ አለመውጣት ሲነሳ ሊጠቀስ የሚችለው ግዛት በማስፋፋት ወቅት የነበረውን በማንሳት ነው:: ወደ ኋላ ይታይ ከተባለ መታየት ያለበት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮች ተሞክሮም ሊሆን ይገባል:: የትኛውም አገር የተስፋፋው እና ትልቅ ሆኖ የተመሰረተው በጦርነት ነው::
ያለ ጦርነት የተመሰረተ አገር በዓለም ደረጃ ይጠቀስ ከተባለ አንድም ቢሆን ማግኘት አይቻልም:: ይህንን ከጭቆና ጋር በማስተሳሰር መነገጃ መደረጉ አሁንም ከዛ ግዛት በማስፋፋት ዘመን ከነበረው አስተሳሰብ በታች መሆኑን የሚያመለክት ይመስለኛል::
በዛ ዘመን ባላባትም ሆነ አስገባሪ መኖሩ የሚገርም ባይሆንም አሁንም ከዚያ አስተሳሰብ ጋር የሙጥኝ ብሎ በጨቋንና ተጨቋኝ ትርክት ስልጣን ለመቆናጠጥ ማሰብ ግርምትን የሚፈጥር ነው::
ሰዎች በቋንቋቸው መማር እና መዳኘት መቻል አለባቸው ከተባለም፤ ያው ነፃ አውጪዎቹ ሰው ራሱን በራሱ ማስተዳደር ላይ ጣልቃ ይገቡ እንደነበር የተነገረ ቢሆንም፤ ትምህርትም ሆነ ዳኝነት በራስ ቋንቋ እንዲሆን አመቻችተዋል የሚል እምነት አለኝ:: በእርግጥ ይህ ምን ያህል ሙሉ ለሙሉ ተተግብሯል የሚለው ቢያጠያይቅም የተሰራውን ወይም የሆነውን እንዳልሆነ መቁጠር ተገቢ አይደለም እና ለውጥ እንደነበር አልክድም::
ነገር ግን መዘንጋት የሌለበት ይህ ጉዳይ በተለይ ከትምህርት ጋር ተያይዞ በነፃነት ስም የተሰጠው መብት በራስ ቋንቋ ከመማር ጋር ተያይዞ የራሱን ጣጣ ይዞ መምጣቱ መረሳት የለበትም::
በተጨማሪ ‹‹መድሎ እና ጭቆና የሰፈነው መቼ ነው? ሰው በቋንቋው ለመጠቀም ዳር ዳር ያለው ከመቼ ጀምሮ ነው?›› የሚሉ ጥያቄዎች ከተነሱ ግን ፤ በተቃራኒው ደግሞ ሰፋፊ ጥፋቶች ስለነበሩ ያንንም መጠቃቀስ ያስፈልጋል:: አፍን በእጅ ላይ የሚያስጭን መገረም እስከሚፈጥር ድረስ ነፃ አውጪነን ባዮቹ የብዙዎችን ነፃነት ደፍጥጠው በብሔር ስም እየነገዱ ጥቅማቸውን እያሳደዱ በተደላደለ ሁኔታ በቅንጦት መኖራቸው ሊገለፅ ይገባል::
ያም ሆኖ ‹‹የበላችው ያገሳታል በላይ በላይ ያጎርሳታል›› እንደሚባለው በተለይ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላም ከማን ነፃ እንደሚያወጡ ባይታወቅም ለሁለት አስርት ዓመታት ብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ ነፃ አውጪ ነን እያሉ በብሔር ስም መነገዳቸውን ቀጥለዋል::
ጠለቅ ብሎ ለማየት ቢሞከር በብዙ መልኩ ከብሔር ጋር የተሳሰሩ ፓርቲዎች ፅንፈኛ ብሔርተኛነት ይስተዋልባቸዋል:: ጥያቄያቸው ይታይ ሲባልም ግልፅነት ይጎድለዋል:: በየጊዜውም ይቀያየራል:: በቅድሚያ በነፃነት መነጋር እና መዳኘት ቢጠየቅም፤ ከመናገር አልፎ ማስተዳደር ታክሎበት ራስን በራስ ላስተዳደር የሚል ጥያቄ ተነስቶ ምላሽ ለመስጠት ተሞክሯል::
አሁን ደግሞ አንዳንድ ፅንፈኛ ብሔርተኞች ‹‹ክልሌ የራሴ እና የራሴ ብቻ በመሆኑ እኔ ብቻ ልኑር›› ወደሚለው ጽንፈኛና ሞገደኛ አስተሳሰብ ያደገ ይመስላል:: እነዚህ ፅንፈኞች ዲሞክራሲ ፣ የጋራ ማንነት ብሎ ነገር አይታያቸውም:: መነጣጠል የሚያመጣው ጣጣ አይታሰባቸውም::
አሁን ብሔር ገኖ ከእኔ ብሔር ውጪ ማንንም ማየት አልፈልግም የሚል ትውልድ እንዲበራከት አድርጓል:: ክበሩ ተመስገኑ አገር ለመበተን ጫፍ ላይ የሚያደርስ ሃሳብ በማፍለቅ ሃሳቡን አጠንክሮ በማስረፅ ሊነቀል የማይችል ነቀርሳ መትከል ለቻላችሁ ነፃ አውጪነን ባዮች ምስጋና ይገባል::
የኛዎቹ ምርጦቹ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች መቼም ሞኝ የተከለውን ብልህ አይነቅለውም ይባል አይደል:: እናንተ የተከላችሁትን መንቀል የትውልዱ ከባድ ፈተና ነው:: ትውልዱ ደግሞ የተከሉትን ነቀርሳ ከመንቀል ይልቅ ተጋብቶበት ማስፋፋቱን ተያይዞታል::
የፖለቲከኞቻችን ዋነኛ መሰብሰቢያ የሆነው የብሔር ፅንፈኝነት የሁሉንም ነገር ቦታ ይዞታል:: የብሔር ጉዳይ አገሪቱን እንዳይሰነጣጥቃት እስከ መስጋት የተደረሰው ለዚሁ ነው:: ስለኢኮኖሚ ዕድገት እና ስለዴሞክራሲ በማሰብ ፓርቲ አዋቅሮ ፖሊሲ ቀርፆ ስልጣን መያዝን ከማሰብ ይልቅ፤ ስለ ነፃ ማውጣት በማጠንጠን ህዝብን ወደማያባራ እልቂት የመውሰድ አባዜ መላ ሊበጅለት ይገባል::
ህዝቡም መንቃት አለበት:: እንደምሳሌ የሚጠቀሰው ትህነግም ብሔርን መሰረት ያደረገ መድሎ እና ጭቆና ነበር ቢልም ራሱ ያንኑ ተግባር ሲፈፅም ብቻ ሳይሆን ሲያስፈፅም ታይቷል:: ምስጋና ለእነርሱ እና ለፅንፈኛ ብሔርተኞች የመንግስት ሰራተኛ እንኳ ብሔር እና ቋንቋ እየመረጠ ሲያገለግል አይተን ታዝበን አልፈናል::
በማስረጃ የተደገፈ የተፈፀመ ታሪካዊ በደል ለማሳያነት ማቅረብ ሳይቻሉ፤ ለክርክር የሚበቃ እና ሚዛን የሚደፋ መረጃ መጥቀስ እና በማስረጃ ማረጋገጥ የማይሆንላቸው ነፃ አውጪ ነን ባዮዎች ነጻ ሳይወጡ ነጻ ለማውጣት ደፋ ቀና ሲሉ ኖረዋል፤ አሁንም አይታጡም:: እውነት ላይ ያልተመሰረተ አስተሳሰብ ስጋት እና ፍርሃት ከማምጣቱም በላይ፤ ጨቁኛለሁ የሚል አካል አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን፤ ተጨቁኛለሁ የሚለው አካልም ያለማረጋገጫ በዚህ ላይ ከልቡ ማመኑም ያስተቸዋልና ልብ ማለት አለበት::
ፖለቲከኞቻችን ተቀባይነት እናገኛለን ብለው የሚያስቡት በታታሪነታቸው፣ ለአገር አሳቢ በመሆናቸው፣ ለአገር ተቆርሪ በመሆናቸው፤ የተሻለ አማራጭ በማምጣታቸው ሳይሆን ምንም ባይሰሩም በብሔራቸው እናሸንፋለን ብለው በማመናቸው መሆኑን መገንዘብ ይገባል::
ለፖለቲካ ግባቸው መሟላት የተጠቀሙት መንገድ ብሔርን መነሻ ማድረግ መሆኑ በስህተት ሊወሰድ ይችላል:: ይህ የራስ ጉድለትን ለመሸፈን ብሔር መሸሸጊያ መሆኑ ግን ያመጣው መዘዝ ከባድ በመሆኑ፤ ጥፋተኛነታቸውን አምነው ይቅርታ መጠየቅ የሚኖርባቸው ፅንፈኞቹ ብሔርተኞች እና ነፃ አውጪነን ባዮች ሊሆኑ ይገባል የሚል እምነት አለኝ::
ፖለቲከኞች ብሔርን የሚያነሱት ጥቅማቸውን መሰረት አድርገው የስልጣን ምኞታቸውን ለማሳካት እንጂ የትኛውንም ሰው ወይም ማህበረሰብ እና መደብ ነፃ ለማውጣት አይመስለኝም:: ያው መቼም እንደው ባልገባን ጉዳይ ላይ በስሜት እየተናጡ ተራራ ማከሉን ተለማደነዋል::
በትክክል የነበረውን ብቻ ሳይሆን ያለውንም ሳንረዳ ተጨቁነናል የምንል እንዳለን ሁሉ በተቃራኒው በኩራት ጨቁኜያለሁ ብለን የምንመፃደቅ አንጠፋምና ሰከን ማለት ሳይሻል አይቀርም::
የፖለቲካ ነጋዴዎቹ የሚመቻቸውን ሰበዝ ይመዛሉ:: ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሰርገኛ ጤፍ የተቀላቀልን ነን:: ብዙዎች ቀልድ ቢመስላቸውም እውነታውን ለማየት ከሞከሩ የራሳቸውን የዘር ሐረግ በማጣራት ማረጋገጥ የሚችሉት ሰርገኛ መሆናቸውን ብቻ ነው:: እናም እንቶኔ ነው አሉ:: የሆነ ነፃ አውጪ ግንባር ውስጥ ቀንደኛ ፖለቲከኛ ሆኖ በነፃ አውጪነት ተመዝግቧል::
ሰውየው በአሁኑ አጠራር የአንድ ክልል ተወላጅ ነው:: ነገር ግን በቅድሚያ ህውሓት ሆነ እና የትግራይ ነፃ አውጪ ሆነ፤ ቀጠለ እና የአባቴ አባት ትግሬ ቢሆንም እናቱ ኦሮሞ ናት የእነ እንቶኔ ዘር ብሎ ወደ ኦሮሞ ፓርቲ አመራ::
ቀጠለ እና የደቡብ የሥልጣን ኮታ አለመሟላቱን ሲሰማ ተወልጄ ያደግኩት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ደሜ የተሳሰረው ከደቡብ ከአንዱ ብሔር ነው አለ:: የዚህ ሰው ነፃ አውጪነት ለየትኛው ብሔር ይሆን:: ይህ በግልፅ ባይነገርም በተግባር ታይቷል::
በእኔ በኩል እነዚህ ነፃ አውጪነን ባይ ፖለቲከኞቻችን ስለማህበረሰብም ሆነ ስለአገር አያስቡም:: ስግብግቦች ናቸው:: የሚማገደው የሰው ህይወት፤ የምትፈርሰው አገር አታሳዝናቸውም:: እነርሱ ዛሬን ጠግበው ካደሩ ኢትዮጵያ ሃያም ቦታ ሆነ ሰላሳ ቦታ ብትሰነጣጠቅ ብቻ እነርሱ ከሞቱ በኋላ ብትፈርስ ምንም አይመስላቸውም::
ከነተረቱስ ‹‹እኔ ከሞት ሰርዶ አይበቀል›› አለች አህያ ይባል አይደል:: ማንነት ሲባል ሁሉም የሚያስበው የብሔር ማንነትን ነው:: ነገር ግን ሰው የተለያየ ማንነት አለው:: ከዚህ ውስጥ ዋነኛ የሚባለው ብሔር ነው ለማለት ያጠራጥራል:: የሃይማኖት ማንነት አለ:: የሞያ ማንነት አለ:: ሌሎችም የአስተሳሰብ ማነትን የመሳሰሉ ውስብስብ ማንነቶች አሉ::
አሁን ኢትዮጵያውያን የምንፈልገው ነፃ አውጪ ነን እያሉ የሚነግዱትን አይደለም:: ሁሉንም እኩል የሚያስተናግድ ነፃ ተቋም የሚመሰርቱትን እና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመጡ ፖለቲከኞችን ብቻ ነው::
ወደ ፊትም ለልጆቻችን ማስተላለፍ የምንፈልገው ያደገች አገርን እንጂ በድህነት የምትማቅቅ በስጋት ውስጥ የምትገኝ አገርን ማስረከብ አንሻም:: ስለዚህ እባካችሁ የብሔር ነፃ አውጪነን ባዮች ምክንያታዊ ለመሆን ብትሞክሩ ደስ ይለናል:: ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2013