ዳንኤል ዘነበ
በዓለም ኮቪድ-19 ከተከሰተ ዓመት ሞልቶታል። በእነዚህ ጊዜያት ከ81.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 45.5 ሚሊዮን ያህሉ ሲያገግሙ፣ 1 ነጥብ 77 ሚሊዮን ደግሞ ሞተዋል።
የወርልድ ሜትሪክስ የታኅሣሥ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዕለቱ በቫይረሱ ታመው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 22 ሚሊዮን 081 ሺህ 847 ደርሷል። በኢትዮጵያ በተመሳሳይ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ የሚገኝ ቢሆንም፤ በኅብረተሰቡ በኩል የሚታየው መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል የሚሉ ስጋቶች እየተሰሙ ይገኛሉ።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት ጤና ጣቢያ ኮቪድ ሴንተር እያገለገለ የሚገኘው የጤና ባለሙያው ወንድወሰን ሀብቴ በሀገራችን የኮቪድ ስርጭት ያለበትን ደረጃ፣ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበሩት የገና እና ጥምቀት በዓላት ወቅት ስርጭቱ እንዳይጨምር መደረግ ስለሚገባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች በተመለከተ አስረድቷል። መልካም ንባብ።
በሀገራችን የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ በማሻቀብ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያሳየው፣ እስከ ታኅሣሥ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ለ1 ሚሊዮን 785 ሺህ 132 ሰዎች በተደረገው የላቦራቶሪ ምርመራ 125 ሺህ 049 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ነው። በቫይረሱ 1 ሺህ 944 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ 239 ሰዎች በጽኑ ህክምና ክፍል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙ መሆኑን ያመላክታል።
የአንድ ሰሞን ርብርብ
በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የሚያዙና ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ ታካሚዎች ቁጥር እየጨመረና ወረርሽኙም ከፍተኛ የሆነ የጤና ሥጋት እየሆነ መጥቷል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በሽታውን የመከላከያ መንገዶች እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዘና እየቀነሰ የመጣ ሲሆን፤ በአንጻሩ ደግሞ የበሽታው ስርጭትና የሚያስከትለው ጉዳት እየጨመረ ይገኛል። በኅብረተሰቡ ዘንድ ቫይረሱን አቃሎ የማየት አዝማሚያ ይታያል። በከፍተኛ ሁኔታ መዘናጋት እየተፈጠረ በመሆኑ ስርጭቱ ዕለት ከዕለት እየጨመረ መጥቷል። ቫይረሱ ወደ ሀገራችን በገባ ሰሞን ኅብረተሰቡ ባለው የግንዛቤ ደረጃ ከፍተኛ ጥንቃቄዎችን ሲያደርግ ነበር።
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የቫይረሱን ጉዳት ለመቀነስ በሚያስችል ደረጃ የመከላከል ሥራዎች ተሰርተዋል። በመንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የጤና ባለሙያዎች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ባለሀብቶችና ልዩ ልዩ ተቋማት በኩል በተመሳሳይ ሥርጭቱን ለመግታትና በቫይረሱ የተያዙትን ለመርዳት ርብርብ ሲደረግ ታዝበናል። አቅም የሌላቸውን ለመደገፍ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ወገንን የማዳን ሥራም ተሰርቷል።
በዚህ መልኩ ሲደረጉ የነበሩ ርብርቦች ደግሞ በእኛ በህክምና ባለሙያዎች በኩል ይፈጠሩ የነበሩ መጨናነቆችን ቀንሶልናል። የሰው ሕይወት እንደሌሎቹ ሀገራት በከፍተኛ ሁኔታ እንዳያልፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው። የቫይረሱ ስርጭት አሁንም ያልጠፋና ቀደም ሲል የነበሩ ጥንቃቄዎች ሳይጓደሉ መቀጠል ቢኖርባቸውም፤ እነዚህ ሁሉ ተግባራት በመቀዛቀዛቸው ችግሩ እያገረሸ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ቫይረሱን ለመከላከል መሠረታዊ የሚባሉ ጥንቃቄዎች እየተዘነጉ ናቸው። የቫይረሱን ሥርጭት ይከላከላል የተባለው ማስክም በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም። በአዲስ አበባ ያለው ሁኔታ ሲታይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ የማድረግ ደረጃው 70 በመቶ ደርሶ የነበር ሲሆን፤ አሁን ግን ወደ 50 በመቶ ዝቅ እንዳለ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ። በሀገራችን የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሆነ ቁጥሮች ይነግሩናል።
የቫይረሱ ሥርጭት ማሻቀብና መጪው ስጋት
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መልኩን ቀይሮ እንደ አዲስ መምጣቱ ተሰምቷል። በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የቫይረሱ ስርጭት ዳግም እያገረሸ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል። በሀገራችን በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ እንደመሆኑ፤ ወረርሽኙ በተለየ መልክ ከተከሰተ ዋጋ እንዳንከፍል ያሳስባል።
በተጨማሪም ዛሬና በቀጣይ ሳምንት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩት የገና እና ጥምቀት በዓላት ጋር ተያይዞ የቫይረሱ ስርጭት አስጊ ወደሆነ ደረጃ እንዳይሄድ እሰጋለሁ። ኅብረተሰቡ እነዚህን በአላትን ሲያከብር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት በጭራሽ መዘንጋት የለበትም።
የኮሮና ሥርጭት እንዳይባባስ ሁሉም የበዓሉ አክባሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል። የክርስትና እምነት ተከታዮች የገና እና ጥምቀት በዓላትን ሲያከብሩ የበሽታውን ሥርጭት በመከላከል ከሆነ ትልቅ ዋጋ እንዳለው ማመን ይገባል። ምእመኑ የአፍንና የአፍንጫ መሸፈኛ (የፊት ማስክ) በማድረግ፣ በአካል ንክኪ የሚደረግ ሰላምታን በመተውና አካላዊ መራራቅን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እየጨመረ እንደመምጣቱ ተግባራቱ ከበዓል ሰሞን ውጪም መቀጠል እንደሚገባቸው ሊታወቅ ይገባል። ኅብረተሰቡ ከዕለት ዕለት በሚያደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በበሽታው መያዝን የሚወሰን እንደሆነ ማስታወስ ይኖርበታል። የኮሮና ቫይረስ መከላከያ አራቱን የ«መ» ሕጎች በመተግበር የበሽታውን ሥርጭት ሁሉም መከላከል እንደሚችል በማመን፤ ሕጎቹን ተግባራዊ በማድረግ ራሱንም ወገኑንም ማዳን ይችላል ማለት ነው።
የባለድርሻ አካላት ሚና
የኅብረተሰቡ ኃላፊነት እንዳለ ሆኖ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት በኩል የሚጠበቅ የቤት ሥራ ያለ ሲሆን፤ በመጀመሪያ ከመንግሥት በኩል የሚጠበቀውን እንጥቀስ። በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ የሚገኘውን የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር እንዲቻል ኅብረተሰቡ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርግ ክትትል ማድረግ ይገባዋል። በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ በሚገኘው የገና በዓል እንዲሁም፤ በቀጣይ ሳምንት በሚከበረው የጥምቀት በዓል አከባበር የሰዎችን መሰባሰብ የሚፈልግ እንደሆነ ይታወቃል።
የቫይረሱን ስርጭት ከሚጨምሩ ምክንያቶች መካከል ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት፣ የአደባባይ በዓላት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ። ስለዚህ ችግሩ «በእንቅርት ላይ …» እንዳይሆን መንግሥት ከቤተ እምነቶች ጋር የተቀናጀ ሥራን መስራት አለበት። ሕዝበ ክርስቲያኑ የቫይረሱን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እንዲያከብሩ ማድረግ ይኖርበታል። በተለይ ደግሞ በጥምቀት በዓል ወቅት ከፍተኛ የሰው ቁጥር የሚገኝበትና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱም ሲፈፀም ሕዝቡን እርስ በእርስ የመነካካት ሁኔታ ይፈጠራል።
መንግሥት ከቤተ እምነቶቹ ጋር በመቀናጀት የሰውን ቁጥር በመቀነስ፤ ርቀትን በጠበቀ እና ከንክኪ በራቀ መልኩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እንዲፈፀም ማድረግ አለበት። በሌላ በኩል የበዓልን መምጣት ተከትሎ የሚደሩት ገበያዎች፣ ባዛሮች፣ መዝናኛ ቤቶች ላይ ለኮቪድ-19 ዳግም ትኩረት እንዲሰጡ ከማድረግ ባሻገር፤ ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚረዱ መሠረታዊ የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊነታቸውን መከታተል እንዲሁም ተፈጻሚ ማድረግ ይኖርበታል።
በተመሳሳይ በቤተ እምነቶች በኩል ደግሞ ምእመኑ ወደ ቤተ እምነቶች የሚመጡ ምዕመናን ሁሉም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ማድረግ አስገዳጅ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀው መመሪያ ተግባራዊ እንዲደረጉ መስራት ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ የየቤተ እምነቱ መሪዎችና አስተዳዳሪዎችም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ አለባቸው።
አማኞችና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ሥፍራ ሲገኙ በተለይም ለአምልኮና ለፀሎት ወደ ቤተ እምነታቸው ሲሄዱና በዚያ ቦታ ሲሆኑ፣ አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው በመንቀሳቀስ ራሳቸውንም ሌላውንም ማዳን ይችላሉ። በዚህ ረገድ በክርስትናም ሆነ በሌሎች የእምነት ተቋማቶች ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ኃላፊነታቸውን መወጣት ከቻሉ ከስጋት መውጣት ይቻላል።
የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ በጤና ሚኒስቴር በኩል የሚወጡ ሕጎችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ መቻሉ አንዱ መንገድ ነው። ስለዚህ ከሰሞኑ የጤና ሚኒስቴር ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያወጣውን ጥብቅ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይገባቸዋል። ይህ መመሪያ፤ ማንኛውም አገልግሎት የሚሰጥ መንግሥታዊም ሆነ የግል ተቋም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተገልጋዮች ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን የማቅረብ ኃላፊነት አለበት።
በተጨማሪም ተቋማቱ የተገልጋዮችን ሁለት የአዋቂ ዕርምጃ ተራርቀው የሚቆሙበትን ቦታ ምልክት የማድረግ እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን መተግበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው። ተቋማቱም የወጣውን መመሪያ መተግበርና ማስተግበር ይኖርባቸዋል ሲል አብራርቷል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2013