ኃይለማርያም ወንድሙ
ታኅሳስ አርሶ አደሩ እርሻውን ጨርሶ እረፍት የሚያገኝበት ወቅት ነው ይባላል። አርሶ አደሩ ከክረምት ጀምሮ ማሳውን በዘር ሸፍኖ፣ አርሞ፣ አጭዶ ከምሮ አበራይቶ እህሉን ወደ ጎተራው ከቶ ገናን ልፋቱን አስልቶ ተደስቶ የሚውልበት ነው ይሉታል።
በዓሉ ለእረኛ ልዩ ትርጉም እንዳለውም ይገለፃል። የገና ዳቦው፣ እርዱ ሁሉ በተለይ ለእረኞች ደስታን ይፈጥራሉ። በገጠር የገና ዕለት እረኛ እርድ እስኪጠናቀቅ ከአቅራቢያው እንዳይርቅ አልያም ከብቶቹ ከበረት እንዳይወጡ ይደረጋል፤ ገና ጨዋታውን ተጫውቶ ቤት ያፈራውን የበዓል ምግብ በልቶ ከቃዬው ሳይርቅ ከብቶቹን እንዲያሰማራ ይደረጋል።
እረፍቱ ለአርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ለእረኞችም ጭምር ይተርፋል ማለት ነው። እረኞች የደረሰው ሰብል በብዛት ታጭዶ ተወቅቶ ወደ ጎተራ የሚከተትበት ወቅት ስለሆነ ከብቶቻቸውን የሚያሰማሩት በነፃነት ስለሆነ ፋታ ያገኛሉ። ከብቶቼ የደረሰ የሰው ሰብል ይበሉብኛል ብሎ አይሰጋም፤ ስለዚህ ዘና ይላል፤ ይዝናናል።
የገና በአል ሲደርስ በትርና ሩር ይዘው በቡድን ተመዳድበው የገና ጨዋታ ለመጫወትና የማይችሉትም እረኞች ቀደም ብለው የሚለማመዱበት ጊዜ ነው። ለዚህ ነው መሰለኝ እረኞች ‹‹በታኅሳስ ልቤ ይላል ፈሰስ›› የሚል ተረትም የሚነገርባቸው። እረኞቹ ሃሳብ አይገባኝም፤ ልቤ ፋታና እርካታ ያገኛል ሲሉ ነው። በርግጥም ከላይ እንደጠቀስነው ልባቸው ፈሰስ ይላል።
ልደተ እግዚእ ዘንድሮ በታኅሣሥ 29 (January 7) የሚከበር ሲሆን፤ በበዓሉ ዋዜማ ታኅሣሥ 28 ኦርቶዶክሳውያን ሌሊቱን በማኅሌትና በቅዳሴ ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑበታል። የቤተመቅደሱ ማኅሌት ቅዳሴ እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት የሚዘልቅ ሲሆን፤ ቅዳሴው ሲጠናቀቅ ምዕመናን ወደ የቤታቸው ይሄዳሉ ።
በማግስቱ ታኅሳስ ለበዓሉ የሚሆኑ ምግቦች ይዘጋጃሉ፤ በግና ዶሮ የሚያርዱ በሬ ገዝተው ቅርጫ የሚከፋፈሉ እንዳቅማቸው ኪሎ ስጋ ገዝተውም የሚያከብሩ በከተሞች ይታያሉ። ምግብ ማዘጋጀት የማይችሉም በጎረቤት ግብዣ የሚታደሙበት እድሉ ሠፊ ነው።
አሁን ደግሞ በአላትን አብሮ ለማሳለፍ በሚል የሚካሄዱ የተለያዩ ሰፋፊ ዝግጅቶች ኪሳቸው ለተራቆተባቸው߹ እርጅና ለተጫጫናቸውና ጤና ላጠራቸው ወገኖችን በበዓል ወቅት ከተፍ እያሉ ናቸው። እነዚህን ዝግጅቶች በአዘቦትም ቀን ልናስባቸው ይገባል። ለእነዚህ ወገኖች በአልን ተንተርሰን ብቻ ሳይሆን በአዘቦት ቀናትም ማሰብ ይገባል።
በከተሞች ምግብ ከደረሰ በኋላ ቡናው ተፈልቶ ጎረቤት ተጠርቶ ጎረቤቱ ሁሉ ይገባበዛል። በቤቱ የሚጎዘጎዘው ቄጠማ፣ የሚቆላው ቡና መአዛ፣ የዕጣን ጢሱ ሁሉ የበዓሉን ድባብ የሚያደምቁ ናቸው። የገና በአል ዳቦ ተቆርሶ ስጋ ቁርጡ߹ ክትፎው߹ ጮማው߹ ዶሮ ወጡን እየበሉ ጥብሱን እየነጩ ጠላ አረቄ ውስኪና ቢራውን እየተጎነጩ ደስታውን በጋራ ይታደሙታል።
ይህን የበዓል ድባብ ሳስብ ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ በ1950ዎቹ ከጻፈው ሀገሬ ከሚለው ግጥም አንዱ ታወሰኝ። ከግጥሙ የተወሰነውን ስንኝ እንድታነቡ ስጋብዛችሁ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ እያልኩ ነው።
…ጮማው፣ ክትፎው፣
ሥጋ ቁርጡ ጥብሱ ዶሮ ወጡ
ጎመኑ ስብ ጮማው ቆሎው ፍትፍት ሥጋ
ድርቆሹ ፍትፍት ነው ቃሪያው ሙክት ሥጋ
ጠጁ ነው ወለላ
ከኮኛክ ያስንቃል የመንደሩ ጠላ።…
በከተሞች ለህፃናቱና ታዳጊዎች በወላጆች የሚገዛላቸው ልብስና ጫማ የሚፈጥርላቸው እርካታ ልዩ ነው። ለገና በአል ሰሞን ሙክት በግ የተገዛበት ቤት ህፃን ወደ ሙክቱ እያሳየኝ እኛኮ ሰንጋ በሬ ተገዛልን ያለኝ አይረሳኝም። ልጆች እርስ በርስ በሚኮላተፍ አንደበታቸው የኛ በግ እኮ ትልቅ ነው ..የኛኮ ግብዳ ነው እያሉ በደስታ ማውራታቸው የተለመደ ነው።
አንዳንዶቹ ቀንድ ያለው በግ እና ቀንድ የሌለው በግ ሲገዛላቸው ህፃናቱ የኛ በግ እኮ ቀንድ አለው ግብዳ ነው ያሸንፋል ብለው ቀንድ የሌለው በግ ለተገዛላቸው አቻዎቻቸው ያወራሉ። በተለይ ቂርቆስ߹ አራዳ ጉለሌን በመሳሰሉት አካባቢዎች ነዋሪዎች ህፃናት ዘንድ። የራሳቸው ሠፊ ግቢ ያላቸው ወላጆች ህፃናት ከጎረቤቱ እኩዮቻቸው ጋር ለመጫወት ብዙም እድሉ የላቸውም።
የቤት እንስሳትን በስዕልና በምስለ ድምፅ (ፊልም) ብቻ የሚያውቁት ህፃናት በጉን በአካል ማየታቸው ድምፁን መስማታቸው በራሱ የሚፈጥርላቸው ደስታ ልዩ ነው።
የበአሉ ድባብ በእለቱ ከሰዓት በኋላ ወደ መጠጥ ቤቶች ይሸጋገራል። ጎረምሶችና አባወራዎች የበአሉን እለት ከመኖሪያ ቤት ወደ መጠጥ ቤት በመትመም ያጣብቡታል። ድራፍቱ ቢራው እንደ ጉድ ይጠጣል፤ ጭፈራው ይቀልጣል። በመጠጡም ጭንቅላቱ የዞረ ኪሱ ይራቆታል፤ ከስካሬ አገግማለሁ ያለው ሰውዬ አልወጣም ብሎ ሊገግም ሁላ ይችላል።
በበአሉ ማግስት በአራዳ በቂርቆስ በኮልፌ በአዲሱ ገበያ በሽሮሜዳና መርካቶ በመሳለሚያ እህል በረንዳ በመሳሰሉ የገበያ ቦታዎች ነጋዴዎች በረንዳቸውን አይከፍቱም። ገበያተኛም ለመግዛት አይሄድም። አንዳንድ እንግዳ ሰው የሥራ ማቆም አድማ መቱ ወይ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። የመጀመሪያውን ቀን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያከበሩ ሰዎች በማግስቱ ዘመድ በመጠየቅ አረፍ በማለት ያሳልፉታል።
በአሉን ተንተርሰው ወጪያቸውን በአግባቡ የሚያወጡ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል አንዳንዶች ገንዘባቸውን በረባ ባልረባው ጨርሰው (በተለይ በመጠጥ በጭፈራና ዳንኪራ) ኪሳቸውን አራግፈው ድብርታቸውን ተከናንበው ገንዘብ የሚገኙበት ጊዜ እንደ ራስ ዳሸን ተራራ ረዝሞ የመከራ ወቅት የሚሆንባቸው አሉ። በተለይ በአሉን ለማክበር ብለው ተበድረው ለመክፈል የሚቸገሩ አሉ። አንዳንዶቹም በቂቤ የረሰረሰው ክትፎ፣ ቁርጡ ጮማው ጥብሱ የተወሰኑ ቀናት አንጀታቸው ከየት መጣ ብሎ እየጠየቀ ያውካቸዋል።
በአሉን በማኅሌት በጸሎት በዝማሬ በደስታ በሆታና በእልልታ የሚያከብሩ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል በመብላት በመጠጣት እንዲሁም በጭፈራና በከበርቻቻ ብቻ የሚያከብሩ ጥቂት አይደሉም። በአሉን ማክበር ይገባል፤ የአከባበር ሥርዓታችን ግን ልከኛ (መጠጥ የማያበዛ በአግባቡ የሚኖር) መሆን አለበት። መጻፉም እኮ ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን ነው የሚለው። በአሉ የሐሴት እንዲሆንላችሁ ተመኘሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2013