ዳግም ከበደ
ዛሬ በመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ስፍራ በሚሰጠው የገና (የክርስቶስ ልደት) ክብረ በዓል ላይ እንገኛለን። በድምቀት የሚከበረው ይህ በዓል በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቷቸው ደምቀው ከሚታሰቡ ተመሳሳይ ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ይዘት ካላቸው መካከል ይጠቀሳል።
በዓሉ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የእየሱስ ክርስቶስ ውልደትን አስመልክቶ በፆም፣በፀሎት እንዲሁም በተለያዩ ስነስርዓቶችን በማድረግ ታስቦ የሚውል ነው። ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያውያን ይህ በበዓል በመጣ ቁጥር ከሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቱ ባሻገር ባህላዊ ይዘቶችንም በማላበስ በዓሉን ይበልጥ ደማቅ ያደርጉታል።
ገና በመላው ዓለም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበር ከመሆኑ አኳያ የየአገራቱ ምዕመናንና የበዓሉ ታዳሚዎች ስነ ስርዓቱን ሲፈፅሙ አንድ የሚያደርጓቸው በርካታ ጉዳዮች አሏቸው። ከዚህ ውጪ ትውፊትን መሰረት የሚያደርጉና ከልደት በዓል ጎን ለጎን ለማድመቂያነት የሚካሄዱ ስነ ስርዓቶች እንደየአገራቱ፣ ባህል ወግና ልማድ ይለያያሉ።
የገና በዓል በመላው ዓለም በሚከበርበት ወቅት እለቱን በድምቀት ለማክበር የሚያስችሉ ስርዓቶች ይከወናሉ። ለምሳሌ ያህል ምዕራባዊያን የገና አባት በሚል ስጦታ የመሰጣጠት፣ ቤታቸውን በተለያዩ አንፀባራቂ ቁሳቁስ በማስዋብ፣ የፅድ ዛፍ በቤታቸው ውስጥ በማቆምና በመብራት በማስጌጥ እንዲሁም በተለያዩ የጎዳናና የቤት ውስጥ ስነ ስርዓቶች ያከብሩታል። ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ደግሞ እለቱን በአብያተ ክርስቲያናት በመገኘትና በርከት ያሉ ስርዓቶችን በመፈፀም ያሳልፉታል።
አሁን አሁን በአገራችን የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል/ገና/የሚከበርበት ስርዓት ከዚህ ቀደም የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ይከውኑት ከነበረው የተለየ እየሆነ እንደመጣ በርካቶች ሲናገሩ ይደመጣሉ። በተለይ ሃይማኖታዊና ኢትዮጵያዊ መሰረት የሌላቸው ትውፊቶችን የሚፃረሩ እንደሆኑ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ይጠቅሳሉ።
ኢትዮጵያዊም ሃይማኖታዊም ይዘት የላቸውም የሚሏቸውን ምሳሌዎችንም ይጠቅሳሉ። አስተያየት ሰጪዎቹ በገና ወቅት በቤት ውስጥ የሚሰቀሉ ጌጣጌጦች፣ የፅድ ዛፍ፣ ጭንቅላት ላይ የሚደረጉ ቆቦች በምዕራባዊያን የኢኮኖሚና የስልጣኔ የበላይነት ምክንያት ሰርገው የገቡ መሆናቸውን ነው የሚያነሱት።
የዝግጅት ክፍላችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት (ገና) ክብረ በዓል በሀገራችን ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ይዘቱን ሳይለቅ እየተከበረ ይገኛል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት ወደን ከላይ እንዳነሳነው ነባራዊ ሁኔታዎችን በመዳሰስ ጀምረናል።
ይህን በዓል በልዩ ድምቀት ከሚያከብሩት የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መምህር የሆኑ መምህር አነጋግረናል። እርሳቸውም ከሃይማኖታዊ ዘውጉ ባሻገር በኢትዮጵያ ውስጥ ትውፊትን መሰረት አድርጎ “የገና በዓል” እንዴት መከበር እንደሚኖርበት ያስገነዝባሉ። እኒህ መምህር በተለይ አሁን አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በተሳሳተ መልኩ የገና በዓልን መሰረት አድርገው የሚከወኑ ስርዓቶችን ተችተዋል።
እኚህ መምህር በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር ምክትል ዲን መምህር ቃለፅድቅ አሰፋ ናቸው። በኢትዮጵያ የገና በዓል አከባበር እና የተሳሳቱ የምዕራባዊያን ስርዓቶችን በተመለከተ ከመምህር ቃለጽድቅ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ አንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ከበዓሉ በፊት ፆም
የገና (የክርስቶስ ልደት) በዓል ታህሳስ 29 ከመከበሩ አስቀድሞ “ፆመ ነቢያት” በሚል የሚጠራውን ፆም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናንና የሃይማኖት አባቶች ለቀናት ይፈፅማሉ። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ነብያት ወልደ እግዚአብሄር የሚመጣበትን ቀን በፆም በፀሎት እያሰቡ ተስፋ አድርገው ይለምኑ የነበረውን ጊዜ ለማስታወስ ነው። በታላቁ መፅሃፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ነብያቱ ስለዚህ ጉዳይ በስፋት ተናግረዋል። በዓሉ ከሚከበርበት ቀን በፊት ባለው አንድ ወር ውስጥ ባሉትአራት ሰንበቶች እነዚህ ነቢያት ስለ እየሱስ ክርስቶስ መወለድና መሰል ጉዳዮች የሚተርኩት ትንቢቶች ይነገራሉ።
ቅዱስ ያሬድም እነዚህን አራት እሁዶች የራሳቸው ስያሜ እንዲኖራቸው አድርጓል። አንደኛውን እሁድ “ስብከት” በሚል ሲጠራው ይሄም ክርስቶስ ለማዳን በምድር ላይ መምጣቱን የሚወክል ነው። ቀጥሎ ያለው እሁድም “ብርሃን” ይባላል። ይሄም የጨለማው ዘመን ማብቃትና የብርሃን መምጣትን ለማሳየት ታስቦ ነው።
ሌላኛው ሰንበት ደግሞ “ኖላዊ” ወይም እውነተኛው ጠባቂ የሚል ትርጉም ያለው ስያሜ የያዘ ነው። ይህ ማለትም ሰውን ከሃጢያት የሚያወጣው ወልድ እግዚአብሄር የሚገለጥበትን ለማስታወስ ነው። ነብያትም ይሄንን በማሰብ ሱባኤ በመግባት ይፀልዩና ያመሰግኑ ነበር። ከዚህ የተነሳ ከገና በፊት ለአንድ ወር የሚሆን ቅድመ ፆምና ፀሎት ይኖራል።
በዓሉ እንዴት ይከበራል
የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዓበይት የጌታ በዓላት ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው። ይህ በዓል በቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ መንፈሳዊ ተግባር የሚከናወን ሲሆን ከዋዜማው ጀምሮ በሚደረጉ ስነስርዓቶች ተከብሮ ይውላል።
በዋዜማው በቀን ቅዱስ ያሬድ የሰራው ምስጋናን ይጀመራል። ምሽቱ ሲደርስ ደግሞ ስርዓተ ማህሌት ይከወናል። በዚህ ስርዓተ ማህሌት ላይ የሚካሄዱት ስብዓተ እግዚአብሄር (የሚነገረው ቃለ እግዚአብሄር) በታላቁ መፅሃፍ ቅዱስ የተፃፈው ሉቃስ ወንጌል ምእራፍ ሁለት ላይ ያለው ቃል በሙሉ ይነገራል።
በተለይ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ “ቅድስት ድንግል ማሪያም ጌታን እንደወለደች፣ አምላክ ከቅድስት ድንግል ማሪያም እንደተወለደ” እና ይህን የመሳሰሉ ስርዓቶች በምሽቱ ስርዓት ይነገራል።
የኦርቶዶክስ እምነት ካህናት በቤተ ክርስቲያን ሆነው ማህሌት ሲቆሙ ነጫጭ ልብስ ይለብሳሉ። ምክንያቱም የክርስቶስ ልደት ማለት ሰው ከሃጢያት ነፃ የወጣበት፣ አምላክ ሰው የሆነበት፣ የ5500 ዘመን የሃጢያት ኑሮ የተሻረበት እንዲሁም የሰው ስጋ ለብሶ ከቅድስት ድንግል ማሪያም የተወለደበት እለት በመሆኑ ትልቅ በዓል ነው።
ከዚህ የተነሳ ምእመናንም እምነቱ በሚፈቅደው አልባሳት ተውበው በቤተ እግዚአብሄር ይሰባሰባሉ። ማህሌት ቆመውም ከዚያ በመቀጠል ስርአተ ቅዳሴ ያከናውናሉ። በስርአተ ቅዳሴውም ምዕመናኑ ስጋዎ ደሙ (ቁርባን) ይቀበላሉ። ባእለ እግዚአብሄር ባለበት ቦታ ስርአተ ንግስ ሲያከናውኑ በሌላ ቦታ የሚገኙት ደግሞ እነዚህን ሃይማኖታዊ ተግባራት አከናውነው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።
የቤት ውስጥ ስርዓት
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በቤተ ክርስቲያን ካከናወኑ በኋላ በየቤታቸው ተጨማሪ ደማቅ ዝግጅት የሚያደርጉ ይሆናል።
ከዚህ ውስጥ ዋንኛው ኢትዮጵያዊ የሆነ ባህላዊ ምግብ የመቋደስ ክንውን ነው። ለዚህ እንዲረዳ ሁሉም እንደየ አቅሙ ዳቦ፣ጠላ እንዲሁም ሌሎች ባህላዊ ምግቦችን የሚያዘጋጅ ይሆናል።
በተለይ በዚህ ዝግጅት ላይ ከጎረቤት ጋር በመሆን መብላትና መጠጣት የተለመደ ነው። በገጠሩ አካባቢ በግ እና ዶሮ በማረድ ተደስተው ያሳልፋሉ። ይህ በዓልም ጌታ እየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን በመሆኑ የደስታ ቀን ተደርጎ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ስለሚቆጠር ያለምንም ሃሳብና ትካዜ በደስታ ሁሉም እንዲያሳልፈው ይፈልጋል።
ገናና ባህላዊ ስርዓት ትስስር
በትውፊት የሚገናኙና የገና በዓል በመጣ ቁጥር ጎን ለጎን የሚካሄዱ ባህላዊ ስርዓቶች አሉ። ከነዚህ ውስጥ “የገና ጨዋታ” የሚባለው ይጠቀሳል። ይሄም ቢሆን ሃይማኖታዊ ዳራ ያለው ሲሆን ሰብአ ሰገሎች በኮኮብ ተመርተው ወደ ቤተልሄም መሄዳቸውን፤ በሄሮድስ ቤትም ኮኮቡ በቆመ ጊዜ ሰብአ ሰገሎቹ “የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው” የሚል ጥያቄ አቅርበው እንደነበር፤ በዚህ ጊዜ ንጉስ ሄሮድርስ መደንገጡን መፅሃፍ ቅዱስ ይነግረናል።
ይህን በማስመልከትም ንጉሱ “ሩር” የሚባል ሰላይ በድብቅ እነሱን አስከትሎ መላኩን በትውፊት ይነገራል። ይህን ሰላይም መልአክ በሰይፍ እንደቀላው (እንደመታው) ይገለጸል። በዚህ መነሻ ምክንያት በእንጨት የሚሰራ የሰይፍ ቅርፅ ያለው ዱላና ክብ “ሩር” የሚመስል ኳስ ተሰርቶ ወጣቶች የገና ጨዋታ በሚል በሰፋፊ ሜዳዎች ላይ በእለቱ ይጫወታሉ።
አሁን አከባበሩ ምን ይመስላል
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያዊ የኦርቶዶክስ እምነት ስርዓትን የሚቃረን የገና በዓል አከባበር እየተስተዋለ ነው። ከእምነቱና ከትውፊቱ ውጪ በሆነ መንገድ የምእራባዊያን ባህልና ስልጣኔ በተጫነው መንገድ ወጣቶችና ማህበረሰቡ በአሉን እያከበሩት ይገኛል። ይሄ ትክክል አይደለም።
በአሉ በተሳሳተ መንገድ እንዲከበር አንዱ ችግር የግንዛቤ እጥረት ነው። መሰልጠን ማለት የሌላውን ባህል መሸከም ሳይሆን በአእምሮ ማደግ ነው። የራስን እምነት፣ ባህል እና ወግ አጉልቶ ማሳየት ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም በርካታና ጥቅም ያላቸው፣ ማስተማር የሚችሉ፣ ትውልዱ ቢጠቀምባቸው የሚለወጥባቸው ባህላዊ ጨዋታዎች አሉን። ይህን አለማድረግ ከስነ ምግባር መውደቅ እና የሌላውን መናፈቅ ነው።
በኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ እምነት ውስጥ የገና ዛፍ የሚባል፣ በራስ ላይ የሚደረግ ቀይና ነጭ እንዲሁም ሌሎች በዛፉም ሆነ በሰው ላይ የሚደረጉ ጌጣጌጦች የሉም እንዲሁም ተቀባይነት የላቸውም። ክርስቶስ የተወለደው በከብቶች ግርግም ውስጥ ነው። የከብቶች ግርግም ደግሞ ዛፍ የለውም።
ስለዚህ የክርስቶስ መወለድን ዛፍ እቤታችን ውስጥ በማቆም መወከል አንችልም። ከምዕራባዊያን ያመጣነው ይህ ባህል የምንፈልገውን ትክክለኛ መልእክት የሚያስተላልፍልን አይደለም። እንዲያውም ምዕራባውያኑ ኢ-መፅሃፋዊ ልምድ ስላላቸው ይህን ሊያደርጉ ችለዋል። በኢኮኖሚ ጎልተው መታየታቸውም በሌላው አነስተኛ ኢኮኖሚ ባለው አገር ላይ ጫና የማስከተሉ ውጤት ነው እንጂ ዛፍ ሰቅሎ የልደት በዓልን ማክበር የኢትዮጵያውያኑ ባህል አይደለም።
የኢትዮጵያውን ትክክለኛው ባህል፣ ዳቦ መድፋት፣ ጠላ መጥመቅ፣ ከጎረቤት ጋር ተጠራርቶ በጋራ በመመገብ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ የገና ጨዋታዎችን በመጫወት በአሉን ማሳለፍ ነው ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ማህበረሰቡ መልካሙን ነገር እንዲያዳብር ትልቁን ሚና እየተወጣች ናት። መልካሙን፣ ማህበረሰቡ የሚጠቅመውንና የአገር ገፅታ የሚገነባውን ባህል እንዲያዳብር ያንንም ይዞ እንዲያድግ ሰርታለች። ይሄ መገለጫም ከሃይማኖቱ ጎን ለጎን እንዳይጠፋና እንዳይበረዝ ጠብቃ የቆየችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ናት።
አሁንም የወንጌል መምህራን ይህ እንዲቀጥል በማስተማር ላይ ናቸው። የክርስቶስ ልደትም ከምዕራባዊያን ጫና ወጥቶ በትክክለኛው ኢትዮጵያዊ ስርዓት እንዲከበር ለማድረግ አሁንም ድረስ ቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2013