ውብሸት ሰንደቁ
የአንድን ኢኮኖሚ በመንግሥት ትከሻ ብቻ ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር አይቻልምና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ይህንን አስመልክቶ ኢትዮጵያ በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ትላልቅ ሪፎርሞችን እያካሄደች ትገኛለች። በተለይ በግሉ ዘርፍ አሳሪና አላንቀሳቅስ ያሉ አሠራሮች መፈተሽ የሪፎርሙ አንዱ ዓላማ ነው።
የሲዳማ ክልልም ሪፎርሙን መነሻ አድርጎ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በክልሉ የባለሀብቶች የማልማት ፍላጎት ኖሮ በቢሮክራሲ፣ በፋይናንስ አቅርቦት እጥረት፣ በመሬት አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማት እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶች እንዳይስተጓጎል በኢንቨስትመንት ቢሮው በኩል ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ወደኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ባለሀብቶችና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ሲፈልጉ ሲዳማ ክልልን ቅድሚያ ሰጥተው እንዲያዩ ለማድረግ እንሠራለን ያሉት የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ሜሳ ናቸው።
ከከተማና ገጠር መሬት አቅርቦት፤ ለኢንዱስትሪዎች ከሚያስፈልገው ፀጥታና ደህንነት እንዲሁም ከመሠረተ ልማት አንፃር ያሉ ችግሮችን ወደምቹ ሁኔታ በመቀየር ለረጅም ጊዜ የመብት ጥያቄ ሲያነሳ የነበረው ሕዝብ እንዲከወንለት በሚጠብቀው ልክ ሥራዎችን ለመሥራት የክልሉ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ እየተጋ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ክልል የመሆን የሕዝብ ጥያቄ ከረጅም ጊዜ የፖለቲካ ጥያቄ በኋላ መልስ ያገኘ ነው። ከለውጡ በኋላ የመጣው አመራር ጥያቄውን ተቀብሎ ሲዳማ ክልል እንደክልል ተቋቁሞ መዋቅራዊ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሆነ ነግረውናል።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በመንግሥታዊ መዋቅር አደረጃጀቶች እየሠራና እያጠናከረ እንደሆነ በክልሉ ውስጥ በየዘርፉ ያሉ አቅሞችን በትክክል እንዲለይ የሚያደርግ ዕድል አግኝቷል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
አቶ ደሳለኝ እንደሚሉት የሲዳማ ክልል ለኢንቨስትመንት ያሉት ምቹ ሁኔታዎች በርካታ ሲሆኑ የክልሉ አቀማመጥ፣ በተፈጥሮው ለግብርና የተመቸ፣ ለመዝናኛ ቱሪዝም ትልቅ አቅም ያለው መሆኑና በከርሰ ምድርና በገፀ ምድሩ ላይም የተለያዩ ማዕድናት ክምችቶች ያሉበት በመሆኑ ከዚህ ቀደም በጥንቃቄና በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ የመመራቱ ነገር ውስንነት ነበረው። ይሄ በኢኮኖሚው ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ስለሆነ በእዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
ሲዳማ ክልል በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ሁኔታዎች ለኢንቨስትመንት ያሏትን ምቹ ሁኔታ አሟጣ ለመጠቀም የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገች ነው። ኢንቨስትመንት ከሚጠይቃቸው ነገሮች አንዱ የአካባቢ ሰላም ነው። በዚህ ረገድ የሲዳማ ክልል ጥሩ እና አንፃራዊ ሰላም የሰፈነበት ክልል ነው።
በተያዘው ዓመት በርካታ ኢንቨስትመንቶችን ወደክልሉ መሳብ ተችሏል። ምንም እንኳን በክልሉ የተለያዩ አደረጃጀቶች ገና በመጠናቀቅ ላይ ቢሆኑም የተለያዩ ሰፊ ሥራዎች የሚጠይቁ ተግባራት ከፊት ተደቅነዋል። የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ተችሏል ብለዋል ኮሚሽነሩ።
የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ የተቻለው ከአደረጃጀት ሥራው ጎን ለጎን በክልሉ ያሉት አቅሞች በሳይንሳዊ ዘዴ ተለይተው ወደማስተዋወቁ እና የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን የመሳቡ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ ነው።
በክልሉ በግንባታ ሥራዎች፣ በአገልግሎት ዘርፉና በኢንዱስትሪዎች የግብርና ልማትን ጨምሮ ያሉትን ዕድሎች ለመጠቀም በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ ነው ያሉት። ይህን ለመጠቀም የሚመጡ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶች ያለምንም ሥጋት ወደ ክልሉ ገብተው እንዲሠሩ ለማስቻል ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።
አቶ ደሳለኝ እንዳሉት በርካታ ባለሀብቶች በሲዳማ ክልል ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ማሳወቃቸውን ገልጸው ሰሞኑን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አፍስሶ የገባው አንጋፋ አማ የተባለ የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካ እና ሌሎችም ተመሳሳይ ድርጅቶች ወደ ክልሉ ገብተዋል።
ቀደም ብለው የገቡ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ በክልሉ የሚታየው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ደረጃ ላይ ነው። ክልሉ በተፈጥሮ የተመቸ በመሆኑ ምክንያት ሌሎች በግብርና ልማት ሥራዎች የተሰማሩ ባለሀብቶች አሉ።
በሲዳማ ክልል በይርጋለም ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ የተለያዩ ባለሀብቶች የገቡ ሲሆን በፓርኩ ውስጥ የተለያዩ ኢንዱስትሪያል ቅባቶችን የሚያመርቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ይገኛሉ። ለምሳሌ ከቻይና የመጣ ወተት ላይ የሚሠራ አግሮ ኢንዱስትሪ እና የመሳሰሉትን በዚህ ውስጥ መጥቀስ ይቻላል። በክልሉ ውስጥ ለመሥራት እየታየ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው።
ይህንን ተከትሎ ሥራ ላይ ያለው ይህ ፍላጎት እንዲቀጥልና እኛም እንደክልል ፍላጎቱን የማስተናገድ አቅም ፈጥረን እንድንቀጥል ነው። ክልሉን መርጠው የሚመጡ ባለሀብቶችም ቢሮክራሲው ተቀንሶ፣ ሳይንገላቱ በአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል የጠየቁትን አስተናግዶ ወደሥራ ማሰማራት እንዲቻል ታላቅ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው ብለዋል ።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደ ሲዳማ ክልል ምቹ የለም ያሉት ኮሚሽነር ደሳለኝ ክልሉ ለሁሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተመራጭ ነው። በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ በሆቴልና ቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች ለሚሠራ ባለሀብት የተመቻቸ ክልል ነው። ክልሉ እንደሚታወቀው ቡና በብዛት የሚመረትበት አካባቢ ነው።
ቡናን ከሲዳማ አምርቶ ለዓለም ገበያ ማቅረብ የቀረውን ደግሞ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ማዋል ላይ ለሚሠሩ በተለይ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ዕሴት ጨምሮ አምርቶ ለሚሠሩ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ።
በቆላማው አካባቢ የተለያዩ የቅባት ሰብሎች በብዛት ይመረታሉ፤ በደጋው አካባቢ ደግሞ ገብስ፣ ስንዴና የመሳሰሉት ምርቶች እንደልብ የሚመረቱበት ክልል ነው፤ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርትም የታደለች ክልል በመሆኗ እነዚህን ምርቶች አምርተው አልያም አስመርተው ለፋብሪካ ግብዓት አድርገው ሌላ በማምረት ኤክስፖርት ለማድረግ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ይህ ዓይነት ምቹ ሁኔታ እንዳለ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ከማርና ከእንስሳት የሥጋ ምርት ጋር የተገናኙ ነገሮች ጋር የሚሠሩ ባለሀብቶች ዕሴት ጨምሮ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የሚችሉበት ምቹ ተፈጥሯዊና ከባቢያዊ ሁኔታ አለ ብለዋል።
በክልሉ ከግብርና ዘርፉ ባሻገር ቱሪዝም ላይም በርካታ ለባለሀብቶች ምቹ የሆኑ ሁኔታዎች አሉ። ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻዎችንም በመለየት ላይ ነው የምንገኘው። የሲዳማ ክልል በባህሉ ረገድም ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ያለበት አካባቢ ነው። በተፈጥሮ አቀማመጥ የሀዋሳ ከተማ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በሪል ስቴት በግንባታና በተለያዩ ዘርፎች እና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ መሠማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ የሆነች ከተማ ናት።
በክልሉ ሀዋሳ ብቻ ሳትሆን ይርጋ ዓለም፣ አለታ ወንዶ እና ሌሎች ከተሞች ለእንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ምቹ የሆኑ ከተሞች ናቸው። የሀዋሳ ከተማን ብቻ ነጥለን ብናይ እንኳን በሀዋሳ ከተማ ዙሪያ ብቻ ያሉ ለሆቴልና ቱሪዝም ምቹ የሆኑ ሥፍራዎች ሐይቁን ጨምሮ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችና መዝናኛዎችን ለመሥራት የተመቻቸች ናት። በዚህች ክረምትም በጋም በማትሰለች ሀዋሳ ከተማ እንዲህ ዓይነት ለማልማት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ማግኘት ለባለሀብቱም ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል ኮሚሽነር።
በክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ ሰዎች ሲዳማ ክልል በሁሉም ረገድ ጥሩ መዳረሻ መሆኗን ማወቅ ይኖርባቸዋል። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በደንብ አነቃቅተን በቴክኖሎጂ ሽግግር የሀገር ውስጥን ፍጆታ መተካት እንዲችልና የውጭ ምንዛሬን ሊያድን በሚችል ደረጃ እንዲደርስ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራ ይሆናል።
ከቴክኖሎጂ ሽግግር ጎን ለጎን የሥራ ዕድል ፈጠራውም ዋና የትኩረት አቅጣጫችን ነው። በክልሉ ያሉ ከባድ ኢንዱስትሪዎች በመጠቀም አቀናጅተን እንሠራለን። በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ የተሻለ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ጠንካራ ኢንዱስትሪዎችን ለመሳብና ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን ይላሉ።
በክልሉ ኢንቨስተሮች ሲመጡ ከምንለካባቸው አንዱ መሥፈርታችን የአካባቢውን ምርት እንደ ግብዓት የመጠቀሙን ነገር ነው ያሉት ኮሚሽነር ደሳለኝ ኢንዱስትሪዎች ሲመጡ የሰው ኃይል ቀጥረው የሥራ ዕድል ከፈጠሩና የአካባቢውን ምርት እንደግብዓት ተጠቅመው በማምረት ኤክስፖር ካደረጉ እግረ መንገዳቸውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ይፈጥራሉ።
ይህም ለክልሉ ኢኮኖሚ ማደግና ለሕዝቡ ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። ለአብነት ያህል ከሰሞኑ የተቀበልነው የብረት ምርትን የሚያመርት ኢንዱስትሪ ለሚያመርተው ምርት እንደ ግብዓት የሚጠቀመው ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ግብዓቱ ከዚሁ ከክልሉ ነው የሚገኘው።
በሚቀጥሉት ጊዜያት የተለያዩ ነገሮች ሲመቻቹ ደግሞ ከሀገር ውስጥ 100 በመቶ ግብዓቱን ተጠቅሞ በማምረት ኤክስፖር እንዲያደርግ 400 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገበ የሕንድ ድርጅት በመቀበል ሂደት ላይ እንገኛለን ብለዋል ኮሚሽነሩ።
በይርጋለም ኢንዱስትሪ ፓርክ ፈቃድ የወሰደው የአቦካዶ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪም በዚሁ አግባብ ግብዓቱን በሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲጠቀም ስምምነቶች ተደርገዋል። በዚህ መሠረትም ለምርቱ የሚረዱትን ምርጥ የአቦካዶና የማንጎ ዝርያዎችን እያመጣ ወደ አርሶ አደሩ በማሰራጨት፤ አርሶ አደሮች ደግሞ ምርቱን የማንጎና የአቦካዶ ምርቱን በማምረት ለፋብሪካው እያቀረቡ በግብዓት አቅርቦት እንዲተሳሰሩ እየተደረገ ነው።
ምርቱ በጥንቃቄ ተመርቶ ወደ ፋብሪካ ገብቶ አስፈላጊው የኢንዱስትሪ ውጤት ይገኝ ዘንድ ለገበሬዎቹ የአመራረት ሂደቱን እንዲያውቁት ተደርጓል፤ በምርት ስብሰባ ጊዜ ሳይቀር ፍራፍሬዎቹ ጉዳት ሳይደርስባቸው ጥራታቸውን ጠብቀው ለፋብሪካው ግብዓትነት እንዲቀርቡ ዘመናዊ የፍራፍሬ መሰብሰቢያ ማሣሪያ ለገበሬዎቹ ተሰራጭቷል። ከዚህ በተጨማሪ የፍራፍሬዎቹ መሰብሰቢያ አራት ማዕከሎች ተገንብተዋል።
ፍራፍሬዎቹ በአጭር ጊዜ የሚደርሱና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚደርጉ ናቸው። በክልሉ የወተት ምርት እንዲያመርት የገባው የቻይና ሀገሩ ኢንቨስትመንትም በዚህ መንገድ እንዲሆን ታስቦ እየተሠራ ነው። ጥሩ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞች ወደ አርሶ አደሮቹ እንዲሰራጩና አርሶ አደሮቹ ከነዚህ ላሞች የሚያገኙትን ወተት ለኢንዱስትሪው ግብዓት እንዲያቀርቡ ለማድረግ የተጀማመሩ ሥራዎች አሉ።
የወተት አምራች ኢንዱስትሪው በሙሉ አቅሙ ወደሥራ ሲገባ ከ60 ሺህ በላይ ሊትር በቀን በግብዓትነት የሚጠቀም በመሆኑ ብዙ አርሶ አደሮችን መጥቀም የሚችል ነው። ሌሎች ፋብሪካዎችም በተመሳሳይ ይህን አካሄድ ተከትለው እንዲሠሩ ጥረት ይደረጋል። የትኛውም ኢንቨስትመንት ዘላቂነትና ጠቀሜታ የሚኖረው ከአካባቢው እና ከማህበረሰቡ ጋር ሲተሳሰር በመሆኑ ለዚህ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
ኮሚሽነሩ በማጠቃለያቸው እንዳሉት የትኩረት አቅጣጫቸው ባለሀብቶችን የሚስብ ምህዳር መፍጠር፤ ባለሀብቶች ሲመጡ ደግሞ ሳይጉላሉና ምቾት ተሰምቷቸው ወደሥራ እንዲሰማሩ ማድረግ ነው። በሲዳማ አካባቢ ሲወራ የነበረው ገፅታን የሚያጠለሽ አሉታዊ ሥራ አሁን የተገላቢጦሽ ሆኖ ሁሉም ነገር እንደተቀየረ በተለይ የሀገር ውስጥና የገር ውጭ ባለሀብቶች ሊገነዘቡ ይገባል።
አሁን በሲዳማ ክልል ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። እንዲያውም አንዳንድ ባለሀብቶች በጥርጣሬ መጥተው ካዩ በኋላ ነገሩ የተገላቢጦሽ እንደነበር ይረዳሉ። የሆነ ሰዓት ላይ ተጋኖ የተወራው የሆነና ያልሆነ ወሬ የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጎድቶታል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ቀደም ብሎ በተሠራጩ መልዕክቶችን እየተጠራጠሩ አንድ እርምጃ ወደሲዳማ ሁለት እርምጃ ወደኋላ የሚሉ ካሉ ክልሉን መጥተው ቢያዩ፤ የተሠሩ ሥራዎች ክልሉ በቅርቡ የተቋቋመ ክልል ስለማይመስል ብዙ ነገሮችን ይረዳሉ። ሚዲዎችም ሲዳማ ክልል በአሁኑ ሰዓት በሰላምና ደህንነትም ይሁን በሌሎች መለኪያዎች የኢንቨስተሮች መዳረሻ እንደሆነ እንዲያሳውቁልን እንፈልጋለን ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2013