ውቤ ከልደታ
ሰላም እንዴት ናችሁ ውድ የአዲስ ዘመን ቤተሰቦች፤ መቼም ሰሞኑን የበዓል ሰሞን ነውና በያለንበት አካባቢ ገበያው እየደራ መሆኑን ሳናስተውል አልቀረንም፤ በተለይ ወትሮም ቢሆን ኮሮና እንኳ ያልበገረው የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ግርግር በዚህ ሰሞን ይበልጥ ደምቆ መንገዶቻችን እየጠበቡ ይገኛሉ። የእግረኛው፣ የጎዳና ላይ ነጋዴው፣ የአሽከርካሪው፣ የደንብ እከባሪው፣ ወዘተ ኧረ ምኑ ቅጡ ሁሉም ጎዳናውን የሚጨናንቅ ነው። ለዛሬም ትዝብቴ መነሻ የሆነኝ ይኸው የጎዳና ላይ ምልከታዬ ነው።
ከላይ በመግቢያዬ እንደጠቆምኩት ሰሞኑን የገና በዓል ተቃርቧልና መንገዶቻችን ሁሉ እየተጨናነቁ ነው። በተለይ እግር ጥሎት መርካቶ አካባቢ የሄደ ሰው ካለ ይህንን ትርምስ እስከሚጠግብ ድረስ ጠግቦ ይመለሳል። የሰሞኑን የመርካቶን ሁኔታ ያየ የሥነጽሑፍ ወዳጅ በዚህ አጋጣሚ ታላቁን ባለቅኔ ፀጋዬ ገብረመድህንን ግጥም በአእምሮው እያሰላሰለ ሥነጽሑፍ ምን ያህል የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ እንደሆነ ይገነዘባል ብዬ አስባለሁ።
አይ መርካቶ፤
አገር ከየጐራው ወጥቶ
አንችን ብሎ ነቅሎ መጥቶ
ግሳንግሱን ጓዙን ሞልቶ
ኀልቁ መሳፍርትሽ ፈልቶ
ባንች ባዝኖ ተንከራቶ—አይ መርካቶ
በገና ሰሞን መንገዱን ከሚያጨናንቁት አካላት መካከል ደግሞ የገና በዓል ባዛሮች ተጠቃሽ ናቸው። ሰሞኑን በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ተከፍተው እናያለን። እነዚህ ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች ታዲያ በመጀመሪያ ሲታቀዱ ዓላማቸው መልካም እንደሆነ እንገነዘባለን።
ምክንያቱም በአንድ በኩል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደምቹ አጋጣሚ ይጠቀሙበታልና። ይህ ደግሞ እነዚህ ዘርፎች እንዲጎለብቱና ሌሎች ተተኪዎችም በዚህ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው አዲስ የሥራ ዕድሎችን እንዲፈጠሩ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል።
ነገር ግን እነዚህ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች በሚታሰበው ልክ ወይም በመጀመሪያ እንደተቀረጹበት ዓላማ ተግባራዊ የማይሆኑበት በርካታ አጋጣሚ ይስተዋላል። ለምሳሌ በነዚህ ኤግዚቢሽኖች ላይ የሚቀርቡ ምርቶች በአንድ በኩል በትክክል በነዚህ የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች የሚቀርቡ አለመሆናቸው አንዱ ሲሆን በሌላ በኩል የሚቀርቡትም በየጊዜው አዳዲስ ምርቶችን ይዘው ለመቅረብና ገበያ ለመሳብ የሚያደርጉት ጥረት ሲታይ እምብዛም ስኬታማ ናቸው ለማለት አያስደፍሩም።
ከዚህ ይልቅ እነዚህ ባዛሮች በበዓል ሰሞን የሚዘረጉበት ቦታ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የተኩ እስከሚመስል ለእግረኛና ለተሽከርካሪ መንገዶችን በመዝጋት ተጨማሪ የትራፊክ መጨናነቅ ሲያስከትሉ ስናይ ከስኬታቸው ይልቅ ጥፋታቸው ጎልቶ የሚመጣበትን ሁኔታ እንመለከታለን።
«ግርግር ለሌባ ይመቻል» እንደሚባለው በበዓል ሰሞን እንዲህ በየጎዳናውና በየመንገዱ ያለው መጨናነቅ ታዲያ በአንድ በኩል ለሌቦች ትልቅ ድግስ ነው። ከዚህም ባሻገር ይህ ግርግር በተለይ በአሁኑ ወቅት እየተባባሰ ለመጣው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ይበልጥ የሚያጋልጥ ነው።
ሌላው የሰሞኑ ትዕይንት ደግሞ የጎዳና ላይ ንግድ ነው። የጎዳና ንግድ የብዙ ዜጎችን የዕለት ጉርስ ለማሟላት የመጥቀሙን ያህል የሚያስከትላቸው በርካታ ጉዳቶችም እንዳሉት ይታወቃል። ምክንያቱም እነዚህ ነጋዴዎች ሕጋዊ ባለመሆናቸው ለመንግሥት ግብር አይከፍሉም። በዚህ የተነሳ ግብር ከሚከፍለው ሕጋዊ ነጋዴ ጋር ተወዳድረው በሚሸጡበት ወቅት ምርታቸውን በአነስተኛ ዋጋ የማቅረብ ዕድላቸው ሰፊ ስለሚሆን ሕጋዊ ነጋዴዎች ገበያቸው ይቀንሳል። ይህ ደግሞ በገበያ ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ጫና ይፈጥራል።
በሌላ በኩል እነዚህ ነጋዴዎች ሕጋዊ ሆነው የሚሰሩበት ዕድል ተመቻቷል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ በሕገወጥ መንገድ መስራት በመለማዳቸውና የሚያገኙት ትርፍም የተሻለ በመሆኑ የጎዳና ንግድን ሲመርጡ ይስተዋላል።
ያም ሆኖ ግን የጎዳና ንግድን ለመቆጣጠር ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው የሚሰሩት የደንብ ማስከበር አካላት ይህ ሥራ እንዲቆም የሚፈልጉ አይመስልም። ምክንያቱም ብዙዎቹ ከነዚህ የጎዳና ነጋዴዎች ጋር አብረው የሚሰሩ እስከሚመስ ድረስ የሌባና ፖሊስ ጨዋታ ዓይነት ቀልድ ሲቀላለዱ እንጂ በትክከል ሥራውን ለማስቆም ፍላጎት አያሳዩም።
የሰሞኑ የጎዳና ነጋዴዎችና የደንብ አስከባሪዎች ትዕይንት የራሱ ድራማዊ መልክ ያለው ነው። ከነሱ ውጪ ሆኖ ቆም ብሎ ለተመለከተ ምን እየሰሩ እንደሆነም ሊገባው አይችልም። እነዚህ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች የሚሸጡትን ዕቃ በየመንገዱ ላይ ዘርግተው ሲሸጡ በላስቲክ ጠቅልለው ነው።
ከዚያ ከሩቅ የደንብ አስከባሪዎች ሲመጡ ሲመለከቱ የሚሸጡትን ዕቃ ጠቅልለው አስፋልቱን ተሻግረው ቆመው ይመለከቷቸዋል። እነዚህ የደንብ አስከባሪዎችም መንገዳቸውን ይዘው ቀጥ ብለው ያልፋሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ግን አንዱን ዘንጥለው ይሄዳሉ፤ ልክ እንደተናካሽ ጅብ። ከዚያ ሌላው ነጋዴ ወደቀደመው ሥራው ይመለሳል። የተወሰደበት ደግሞ ተከትሏቸው ይሄዳል፣(ምናልባት ትንሽ አጉርሶ ዕቃውን ሊቀበል)።
በነዚህ ጎዳናዎች ላይ ደግሞ የጎዳና ነጋዴዎችም የየራሳቸው ደረጃ ያላቸው ይመስላሉ፤። ምክንያቱም አንዳንዶቹ የጎዳና ነጋዴዎች እና ሱቅ በደረቴዎች አይነኬዎች ናቸው። ማንም ቢመጣ እነሱ ከዚያ ፈቀቅ አይሉም። የደንብ አስከባሪዎችም አልፈው ከመሄድ ውጪ ከነዚህ ጉዳይ ያላቸው አይመስሉም።
ሌላው የሰሞኑ ትዕይንት ደግሞ በትራንስፖርት ዘርፍ ዙሪያ የሚታይ ነው። በተለይ የታክሲ አሽርካሪዎችና የትራፊክ ፖሊሶች የሰሞኑ እሰጣ አገባና ግርግርም ልክ እንደ ጎዳና ላይ ነጋዴዎችና ደንብ አስከባሪዎች የራሱ የተለየ ገጽ አለው። አንዳንድ የታክሲ አሽከርካሪዎች በበዓል ሰሞን የታክሲ ሥራ ከመስራት ማቆም ይመረጣል ይላሉ። ምክንያቱም በበዓል ሰሞን ያለምንም ጥፋት መከሰስ የተለመደ ነውና።
አንድ የታክሲ ሹፌር ጓደኛዬ ሰሞኑን እንዳጫወተኝ አሁን አሁን በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ያለው ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሷል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትራፊክ ስምሪትን ለማስተካከል በየቦታው በተሰማሩ የመንገድ ትራንስፖርት ስምሪት ባለሙያዎች የሚደረገው ጫና አስደንጋጭም አሳፋሪም እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።
እዚህ ላይ ግን መታየት ያለበት የአሽከርካሪዎችም ጥፋት መኖሩን ልብ ልንል ይገባል። አብዛኞቹ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎችና አውቶቡሶች ቢያንስ አንድ እንከን የሚያጣቸው አይደሉም። ይህ ደግሞ እነሱን ለሚከታተል የትራፊክ ባለሙያም ሆነ የመንገድ ትራንስፖርት ሠራተኛ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
አንድ ሰው መብቱን ለመጠየቅ በቅድሚያ ራሱ ግዴታውን መወጣት አለበት። የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ አሽከርካሪም በቅድሚያ የሚያሽረክረው ተሽከርካሪ ከጉድለቶች የፀዳ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አለበት። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ አገልግሎት መስጠቱ አንድም ለቅጣት ይዳርገዋል፤ አልያም ለአደጋ ያጋልጠዋል።
እንግዲህ የበዓል ሰሞን ሰርግና ምላሽ ከሚሆንላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ነጋዴዎችም ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ በበዓላት ሰሞን ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን ማካሄድ የተለመደ ነው። ነገር ግን በዓልን እየጠበቁ ኅብረተሰቡን ለተለያዩ ጉዳቶች መዳረግ ከሞራልም ሆነ ከሕግ አንጻር ተጠያቂነትን የሚያስከትል በመሆኑ ሊታሰበብት ይገባል፤ መልካም በዓል።
አዲስ መን ታህሳስ 28/2013