ታምራት ተስፋዬ
የሰው ልጅ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት በጨመረ ቁጥር የፀሐይ አስፈላጊነትና የምድር ላይ ህይወት ቁርኝት ይበልጡኑ ይፋ እየሆነ መጥቷል።በርካታ የስነ ፈለክ ሊቃውንት ስለፀሐይ ጠንቅቀው ለማወቅ እጅግ ብዙ ጥናት አድርገዋል።ሆኖም ኮከቢቱን በተመለከተ ብዙ ጥያቄዎች ገና አልተመለሱም።
በተለይም ከፀሐይ በላይ ኃይል መስጠት የሚያስችል የኒውክሌር ኃይል ለማፍለቅ ብዙ ደክመዋል። ይሁንና እስካሁን የተካሄዱ ምርምሮች ለዚህ የኃይል ጥያቄ ምላሽ መስጠት አልሆነላቸውም።
አንዳንድ አገራት በአንፃር ይቻላል የሚል እሳቤን የሚፈጥሩ ግኝቶችን ይፋ በማድረግ ላይ ናቸው። ደቡብ ኮሪያም ከእነዚህ አንዷ ናት።ከቀናት በፊትም National Research Council of Science & Technology፣ ኮርያ ሰው ሰራሽ ፀሐይን ስለመፍጠሯ አስነብቧል።
በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኝ Korea Superconducting Tokamak Advanced Research ወይንም (KSTAR),የተሰኘ የምርምር ተቋም የተሰራው ሰው ሰራሽ ፀሐይም በአንድ መቶ ሚሊየን ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍተኛ ሙቀት ለ20 ሰከንድ በመዝለቅ የአለምን ክብረ ወሰን መስበር ችላል።
የምርምር ተቋሙ ግኝቱን እውን ለማድረግ ከኮሪያ ፊውዥን ኢነርጂ ኢንስቲትዩት፣ከሴኡል ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲና ከአሜሪካው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ጋር መተባበሩም ታውቋል።ተመራማሪዎቹ አርቲፊሻል ፀሐይ ሲሉ የሰየሙት ከፍተኛ አስተላላፊ ቁስ የሀይድሮጅንአይሶቶፖችን የያዘ ሲሆን ይህ አዮኖችና ኤሌክትሮኖች የሚለያዩበትን የፕላዝማ ኩነት (state) እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው።
አዮኖቹ ከፍተኛ መጠን ባለው ሙቀት እንዲግሉ ይደረጋል።እኤአ በ2018 KSTAR በመቶ ሚሊየን ዲግሪ ሙቀት ሰው ሰራሽ ፀሐይን መፍጠር ቢቻልም መሰል ሕልውናዋ መቆየት የቻለው ግን ለ1ነጥብ 5 ሴከንድ ብቻ ነበር።በ2019 በተደረገ ሙከራ የቆይታ ጊዜው ለ8 ሴኮንዶች ያክል ብቻ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ የአሁኑ ሁለት እጥፍ ስኬትን ያስገኘ ነው። ይሕም በኒውክሌር ፊውዥን ዙሪያ ለሚሰሩት ጥናት ምቹ ሁኔታ እንደሆነ ተነግሮለታል።
ምንም እንኳን ከ100 ሚሊዮን በላይ ከፍ ያለ ሙቀትን መያዝ የሚችሉ ሌሎች የፊውዥን ቁሶች ቢኖሩም እስካሁን ከ10 ሴኮንዶች በላይ ሙቀቱን ተቋቁመው መቆየት የቻሉ ግን አልነበሩም። ይህኛው ሙከራ ሊሳካ የቻለውም የምርምር ተቋሙ የውስጣዊ ግድግዳውን አቅም በማሻሻሉ ሲሆን ለዚህ ያበቃውም ባለፈው አመት የተሰራው ከፍተኛ ሙቀትን መቋቋም የሚችል ቁስ (plasma operation mode) መጠቀሙ ነው።
የኮሪያ ፊውዥን ኢነርጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ሲ ሁ ዮዋን፣ ግኝቱን በኮከብ ላይ በሚደረጉ ቀጣይ ምርምሮች እጅግ ወሳኝ፣አይን ገላጭና የይቻላል መንፈስን የሚያጎናፅፍ ስለመሆኑ ሰፊ አስተያየታቸው አጋርተዋል።
በሴኡል ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የኒውክሌር ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር ያንግ ሱ ና ግኝቱ የኒዩክሌር ማበልጸጊያ መሳሪያ ለማግኘት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አስረድተዋል።ሌላኛው የምርምሩ ተሳታፊ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ያንግ ሲኦ ፓርክም፣የምርምር ተቋሙ ይፋ ባደረገው ወሳኝ ግኝት ላይ ተሳታፊ በመሆናቸው ክብር እንደሚሰማቸው ገልፀዋል።
የምርምር ተቋሙ በቀጣይ ግኝትና ውጤቱን በሚመለከት በአለም አቀፍ ደረጃ በፊውዝን የምርምር ላይ ለተሰማሩ ተቋማትና ባለሙያዎች የሚያጋራ ይሆናል።የመጨረሻ ግቡም እኤአ በ2025 ከመቶ ሚሊዮን ዲግሪ ሼልሲየስ ሙቀት በላይ ለሶስት መቶ ሰከንድ ቆይታ የምታደርግ ሰው ሰራሽ ፀሐይን መፍጠር ስለመሆኑ ታውቃል።
የአገሪቱ ብሄራዊ የፊውዥን ምርምር ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት ሱክ ጄይ ዩ፣መሰል ከባድና ፈታኝ ምርምሮችን በማስቀጠል የሰው ልጅ ጥያቄ ሁልጊዜ ለመመለስና የኒውክሌር ፊውዥን ኢነርጂን እውን ለማድረግ እንደሚተጉ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013