ለምለም መንግሥቱ
ማዘጋጃ ቤት የተቋቋመበት፣ የሕዝብ ቁጥሩ ሁለት ሺህ እና ከዚያ በላይ የሆነ፣ ከዚህ የሕዝብ ቁጥር ውስጥ ደግሞ ቢያንስ 50 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ ከግብርና ውጪ በሆነ የሥራ መስክ የተሰማራ ሆኖ ሲገኝ ከተማ የሚለውን ስያሜ ያገኛል።
አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተያዘውን ግብ ለማሳካት በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ከተሞች ተመጣጣኝ የዕድገት ደረጃ፣ ፖለቲካዊና ልማታዊ ሚና እንዲኖራቸው ፍረጃና እርከን መወሰኛ መሥፈርት አስፈላጊ እንደሆነም በ2009 ዓ.ም የከተማ ልማት እና ቤቶች ሚኒስቴር የከተሞች ፈረጃና የአስተዳደር እርከን መወሰኛ መሥፈርት በሚለው ሰነዱ ላይ ማስፈሩ ይታወሳል።
በዚህ መሥፈርት የተመሰረቱ ከተሞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው እያደገ ሲሄድ በከተሞች የመኖር ፍላጎት ይጨምራል። የነዋሪ ቁጥር ሲጨምር ደግሞ በዚያው ልክ መኖሪያ ቤቶች፣ የጤና፣ የትምህርት ቤቶችና የተለያዩ አገልግሎቶችን ማሟላት ይጠበቃል። ይህን ለማሟላት ደግሞ በቂ የሆነ የግንባታ ቦታ ሊኖር ይገባል። በአሁኑ ጊዜም መሠረተ ልማቶችና የመኖሪያቤቶችን ፍላጎት ለማጣጣም እንደሀገር የተያዘው አቅጣጫ ከተሞችን ወደ ጎን መለጠጥ ወይንም እንዲሰፉ ማድረግ ሳይሆን፣ ዕድገቱ ወደላይ እንዲሆን ነው።
ለዚህም ነው በከተሞች በስፋት የሕንፃ ግንባታዎች በመከናወን ላይ የሚገኙት። መንግሥት የከተማ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን ለማሟላትም የጋራ መኖሪያቤት በመገንባት እየወሰደ ባለው አማራጭ በመጠኑም ቢሆን ችግሮችን ማቃለል ችሏል። በአሁኑ ጊዜም እስከ አራተኛ ወለል ባለው በአንድ ሕንፃ እስከ 30 አባወራ ይኖራል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አነስተኛው ባለ ሦስት ወለል ሲሆን፣ ከፍተኛው ደግሞ ከ12 ወለል በላይ ደርሷል። በቤት ልማት የተሰማሩት ቤት አልሚዎችም እንዲሁ ከፍተኛ ፎቅ የመኖሪያቤት በመገንባት ላይ ይገኛሉ። ለንግድና ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉትም በተመሳሳይ ወደላይ በመገንባት ላይ ይገኛሉ።
እንዲህ ያሉ አማራጮች ከመሬት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት አበረታች ቢሆኑም ግንባታዎቹ ፍላጎትን ማሟላት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ እንደሆነ ይተቻል። ከግንባታ የጥራት መጓደል ጋር የተለያዩ አስተያየቶች ይቀርባሉ። ከሚነሱት ሀሳቦች አንዱ ከመጸዳጃና ከምግብ ማብሰያ ቤቶች የሚወጣ ፍሳሽን የተመለከተ ነው። ውጫዊ ውበታቸው የሚማርኩ ሕንፃዎች ሳይቀሩ ወደ ውስጥ ሲገቡ ጣሪያቸው በፍሳሽ ጠቁሮ፣ አንዳንዱም በእርጥበቱ ሽታ ፈጥሮ እንታዘባለን።
በሐንፃው ውስጥ ለውስጥ ሰርጎ የሚገባው ፍሳሽ ከአንዱ ወደሌላው ክፍል በመተላለፍ የቤቱን ውበት ከማበላሸቱ በላይ በሕንፃው ላይ ጉዳት ማስከተሉ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል። አንዳንዶች በፍሳሹ ከመቸገራቸው የተነሳ ዕቃ እስከመደቀን ይደርሳሉ። ከእርሱ በላይ ካለው ሕንፃ በሚወርደው ፍሳሽ ከመቸገሩ የተነሳ በመጸዳጃቤት ውስጥ ጃንጥላ ይዞ ለመቀመጥ እንደተገደደ ሲናገር የሰማሁበትን ማንሳት ጥሩ ማሳያ ይሆናል።
ከግንባታው ጉድለት በተጨማሪ የአጠቃቀም ችግር ሲታከልበት ጉዳቱ ምን ያህል እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ለመሆኑ የሕንፃ የውስጥ ለውስጥ የፍሳሽ ችግር የክህሎት ወይንስ የግብአት አጠቃቀም? ችግሩ ከምን የመነጨ ይሆን? የዘርፉ ባለሙያዎች በዚህ ላይ ምን ይላሉ? ትዝብታቸውን ጨምረው ችግሩንና መፍትሄውን እንዲህ አካፍለውናል።
በሙያው ላይ ሰፋ ያለ ሀሳብ በማንሳት ችግሩንና መፍትሄውን የነገሩን የቀድሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንትና የአመሐ ስሜ ሕንፃ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ባለቤት ኢንጂነር አመሐ ስሜ ናቸው። የተነሳውን ሀሳብ በመጋራት በቅድሚያ መሆን ስላለበት ተግባር እንዲህ ብለዋል።
‹‹ወደ ግንባታ ከመገባቱ በፊት የግንባታ ዲዛይን ሥራ ይቀድማል። ለሚገነባው ሕንፃ የሚያስፈልገውን የፍሳሽ ማስወገጃ መሥመርም ሆነ አስፈላጊ ቁሳቁሶች የማሟላትና ስለአገልግሎት ዘመኑ በዲዛይን ሥራ ወቅት የሚታዩ ተግባራት ናቸው። የፍሳሽ፣ የኤሌክትሪክ፣ የአርክቴክ በአጠቃላይ የሕንፃውን ውበት፣ ይዘትና የሕንፃውን ጥንካሬ የሚሰሩ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ። እነዚህን ሁሉ አሟልቶ የተሰራው ዲዛይን መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ ነው የግንባታ ጨረታ ያሸነፈው ተቋራጭ ወደ ግንባታ ሥራ የሚገባው›› ይላሉ።
እንደ ኢንጂነር አመሐ ማብራሪያ የግንባታ ሥራ ከዲዛይን ዝግጅት ጀምሮ እስከ ቁጥጥር ሥራ ባሉ ሂደቶች ውስጥ የሚያልፍ ሲሆን፤ ሦስት ባለድርሻ አካላት በግንባታ ሥራው ላይ ይሳተፋሉ። እነርሱም ባለቤት፣ አማካሪ፣ ሥራ ተቋራጭ ናቸው። የሥራ ተቋራጩ ድርሻ በዲዛይኑ መሠረት በተጠየቀው ጥራት፣ የጊዜ ሰሌዳና በተቀመጠለት በጀት ግንባታውን መፈጸም ነው። ግንባታው በዚህ መልኩ ከተከናወነ የሕንፃ ፍሳሽ ችግር ሊነሳ አይችልም። ችግር ከተፈጠረም ከመነሻው ከዲዛይኑ ይሆናል።
ዲዛይን ሲሰራ የውሃ ሥርገት እንዳይኖር የሚያስችሉ ጥራት ያላቸው እንደ ውሃ መውረጃ ቱቦዎች ያሉ ግብአቶች መኖራቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በግንባታ ወቅት ደግሞ ግብአቶቹ ሕንፃውን ሊጎዳ የሚችል ውሃ ማስተላለፍና አለማስተላለፋቸውን መፈተሽ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ግን በክትትልና ቁጥጥር በታገዘ ክፍተቱን እያዩ በጥራት መሰራቱን እያረጋገጡ መሄድ ያስፈልጋል። የፍሳሽ ችግር ሊያጋጥም የሚችለው ከፍተኛ የውሃ ግፊት ሲያጋጥም ውሃው ውስጥ ለውስጥ የሚሄድበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። ሌላው በሕንፃው ውስጥ ከሚኖረው አጠቃቀም ችግር ጋር ይያያዛል።
የችግሮቹ መንሴዎች ከታወቁና የሙያ ሥነምግባሩ የሚያዘውን ተከትሎ ከተሰራ በብዙ ሕንፃዎች ላይ የሚታየው የፍሳሽ ችግር ከምን የመነጨ ነው የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው። ኢንጂነር አመሐ ሁሉም ሙያዊ ሥነምግባሩ የሚያዘውን ተከትሎ ሙያዊ ኃላፊነቱን ይወጣል ለማለት አያስደፍርም ይላሉ። የሙያ ሥነምግባር መጓደል በተቆጣጣሪ፣ በተቋራጩ እንዲሁም ዲዛይን በሚያደርገው አካል ሊፈጠር ይችላል። ይሄ ደግሞ ለጥራት መውረድ ከምክንያቶቹ መካከል ሆኖ ይጠቀሳል።
ግንባታው የሦስት አካላት ድርሻ ሆኖ ነገር ግን አልፎ ተጠቃሚው ጋር ደርሶ ችግር የመሆኑ ጉዳይ ያነጋግራል። እንደው እንዳጋጣሚ ከተደረሰበት ማዳን የሚቻልበት ዕድል ይኖር ይሆን? ኢንጂነር አመሐ በምላሻቸው፤ ተቋራጩ ሥራውን በሁለት ዙር ነው ለሚያስገነባው አካል የሚያስረክበው።
የመጀመሪያ ዙር ርክክብ ፍሳሽ መኖሩን ለማረጋገጥ የተዘረጋ የውሃ መሥመር ካለ በዚያ አማካኝነት ይፈተሻል። ከሌለ ደግሞ ከፍተኛ የውሃ ግፊት በሚለቅ መሣሪያ በመጠቀም ይታያል። ችግር ካለ ተቋራጩ እንዲያስተካክል ይደረጋል። የመጨረሻውና ሁለተኛው ርክክብ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ እንዲፈጸም የሚደረግ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ርክክብ ላይ እንዲያስተካክል የተነገረውን መፈጸሙ ይረጋገጣል።
የሕንፃ ግንባታዎች በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መከናወናቸው ለፍሳሽ ችግር እንደምክንያት ሲጠቀስም ይሰማል። ይሄ ምን ያህል ትክክል እንደሆነና ተጽዕኖውን በተመለከተ ኢንጂነር አመሐ እንዲህ አብራርተዋል። የቤት ልማት ሥራው ይለያያል።
መንግሥት ለዜጎች የሚያስገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአብዛኛው የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የሙያ ሽግግር ለማድረግ በትሥሥር ነው የሚከናወኑት። በፍሳሽ፣ በኤሌክትሪክና በሌሎችም ሙያዎች የተደራጁ ማህበራትን ከተቋራጭ ጋር በማያያዝ ተቆጣጣሪው እየተከታተላቸው እንዲሰሩ ይደረጋል።
እንዲህ ባለው አሠራር ሁሉም ኃላፊነቱን ይወስዳሉ። በመሆኑም በፍሳሽ በኩል ለሚፈጠረው ችግር በፍሳሽ ሥራ ላይ የተሰማራው ማህበር ተጠያቂ ይሆናል። የተቀናጀ አሰራር ከአላማው አንጻር የሚደገፍ ቢሆንም በተጠያቂነት ላይ ክፍተት ይፈጥራል። ተቋራጩ ሙሉ ሥራዎችን ተረክቦ ከሆነ ግን ኃላፊነቱ የእርሱ ስለሚሆን ችግሩ የማን እንደሆነ በቀላሉ መለየት ይቻላል።
አሁን ግን መንግሥት እንዲህ ያለውን አሰራር በማስቀረትና ግብአትም ከማቅረብ ሥራ ወጥቶ ተቋራጩ ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ ቤቱን ገንብቶ የሚያስረክብበት አሰራር በመዘርጋቱ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት መኖሩን ኢንጂነር አመሐ ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንዳሉት ችግሩ መንግሥት በሚያሰ- ራቸው የጋራ መኖሪያቤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በግለሰቦች በሚገነቡ ሕንፃዎች ላይም በተመሳሳይ ክፍተቱ ይስተዋላል። ኢንጂነር አመሐ ችግሩን ከግብአት ጥራት ጋር ያያይዙታል። ጉዳዩም በአሰሪው አካል ላይ ይወድቃል። በግልም ሆነ በመንግሥት የሚከናወነው የሕንፃ ግንባታ የሀገር ሀብት በመሆኑ ጉድለቱ የአንድ አካል ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።
ለተፈጠረው ክፍተት ተጠያቂ ሳይኖር ተገልጋዩ ችግሩን ተቀብሎ እንዲኖር እየተደረገ ነው። ለመሆኑ ተገልጋዩ መብቱ እስከምን ድረስ ነው? ኢንጂነር አመሐ በምላሻቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን ለአብነት ያነሳሉ። በቅድመ ግንባታ ወቅት ተቋራጩ የተለያዩ ውሎችን ይገባል። ከውሉ ውስጥ አንዱ በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ከቤቱ መሠረት ጋር የተያያዘ ችግር ካጋጠመ ተጠያቂ ይሆናል።
የጋራ መኖሪያቤቶቹ ባቋቋሙት ማህበር በኩል ክትትል በማድረግ ያጋጠሙ ችግሮች እንዲስተካከሉ ይደረጋል። ኢንጂነሩ ይሄን ይበሉ እንጂ በቤቱ ውስጥ የሚኖረው ነዋሪ አሰራሩን በግልጽ ያውቃል ለማለት እርግጠኛ መሆን አይቻልም። አፈጻጸሙም ቀላል እንደማይሆን መገመት አያዳግትም።
ኢንጂነር አመሐ በሰጡት የመፍትሄ ሀሳብ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ባይቀረፍም መቀነስ ግን ይቻላል። ለግብአት ግዥ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር በመንግሥት በኩል መፍትሄ ማግኘት አለበት። የግንባታው የቆይታ ጊዜ ለረጅም ጊዜ ታቅዶ በግብአት ጥራት መጓደል ከዕቅዱ በታች መውረድ የለበትም። በባለሙያው በኩል ደግሞ የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይጠበቃል። ሙያዊ ሥነምግባርን የተከተለ አሰራር ሲጎለብትና የግንባታ ክህሎቱ ሲያድግ ክፍተቶቹ ይታረማሉ።
ኢንጂነር አመሐ እንደ አንድ ባለሙያ ተሞክሮአቸውን እንዲህ አካፍለውናል። ‹‹እኔ እንደተቋራጭ ሥራ ስወስድ በዲዛይንም ሆነ በሌላ ችግር መኖሩ ከተሰማኝ ኮንትራቱን ከሚያስተዳድረው አካል ጋር በመነጋገር በጥራት ገንብቼ ለማስረከብ ጥረት አደርጋለሁ። ለእኔ የአንድ ሕንፃ ግንባታ ሥራ አንድ ልጅ ተወልዶ ቁምነገር ደረጃ እስከማድረስ ነው። ለትውልድ የሚሸጋገር ሥራ መሥራት የአንድ ባለሙያ ኃላፊነት ነው ብዬ እወስዳለሁ።
ለራስ መታመንን ብንለማመደው ለሁላችንም ጠቃሚ ነው።›› የዲዛይን ባለሙያው ተመሳሳይ የሆነ ሥራ መሥራት ሳይሆን፣ ወቅታዊውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበና ከሚፈለገው አገልግሎት ጋር የሚጣጣም ነገር ጊዜ ወስዶ እንዲሰራ፣ ተቆጣጣሪው አካልም ተገቢ ባለሙያ በሥራው ላይ ስለመኖሩና ግብአቶቹ ጥራት ያላቸው መሆናቸውን በመፈተሽ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የተማረችው ኤሌክትሪክል ኢንጂነሪንግ ቢሆንም፣ ለአጭር ጊዜ የጥራት ቁጥጥር ባለሙያ ሆና በመሥራቷ ከሙያው ብዙም አለመራቋን የምትናገረው ወጣት ቤሉል በረከት፤ በተደጋጋሚ የተጠቀመችበት 22 ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሚገኝ አንድ ሆቴል ቤት ውጫዊ ውበቱና መጸዳጃ ቤቱ ውስጥ ያለው ፍሳሽ የቤቱን ገጽታ ማበላሸቱን አንስታ የፍሳሽ መኖር ምን ያህል ጉዳት እንደሚያስከትል ለአብነት ትጠቅሳለች።
የጥራት ቁጥጥር ባለሙያዋ እንዳለችው፣ በሕንፃው ውስጥ ፍሳሽ መኖር የሌሎችንም ሥራዎች በማበላሸት እጀሰባራ እንደሚያደርግ ትናገራለች። በእርጥበቱ ምክንያት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሊቋረጥ ይችላል። ስለዚህ ሁሉም ባለሙያ ለሙያው መጨነቅ እና ሙያውን ማዕከል ባደረገ መልኩ ሙያዊ ግዴታውን መወጣት አለበት። ወጪ ለመቆጠብ ወይንም ላልተገባ ጥቅም ሲባል ከሥነምግባር ውጪ በሆነ መንገድ መሥራት ዋጋ ያስከፍላል።
ጥራት በሌለው ግብአት የተሰራ የፍሳሽ መውረጃ በተደጋጋሚ የጥገና ወጪ ያስከትላል። ይህ ሲሆን ደግሞ ባለሙያውን ያስወቅሳል። ተጠቃሚውንም ይጎዳል። ባለሙያዎች ተናንበው ቢሰሩ ችግሩን ቀድሞ መከላከል እንደሚቻል ትገልጻለች። ተናብቦ አለመሥራት በመሠረተ ልማት ዝጋታ ላይ ተደጋግሞ ይነሳል።
አንዱ የገነባውን ሌላው ያፈርሳል። ሁሉም የራሱን መወጣቱን እንጂ አንዱ ያስከተለው ጉድለት የሁሉንም ልፋት ከንቱ እንደሚያስቀረው ግንዛቤ አይያዝም። ችግሩ ተወግዶ የጋራ ኃላፊነት እስኪፈጠር ድረስ ጉዳዩን ደጋግሞ ማንሳት ተገቢ ነው ብለን እናምናለን። አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013