ታምራት ተስፋዬ
ቆሻሻን ማስተላለፍ (የቆሻሻ ቅብብሎሽ) /Waste Transfer/ቆሻሻ መቀባበል ከአነስተኛ ቆሻሻ ማጓጓዣ ተሸከርካሪ/ከጋሪ ጀምሮ ተሳቢ ወዳለው ትልቅ ተሸከርካሪ ድረስ ያለውን የማስተላለፍ ወይም የመቀባበል ሂደት ያጠቃልላል።
ይህ ሁኔታ ትናንሽ ቆሻሻ የሚያጓጉዙ ተሸከርካሪዎች ቆሻሻውን በፍጥነትና በብዙ ምልልስ አድርሰው ወዲያውኑ ወደ መስመራቸው እንዲመለሱ ስለሚያደርጋቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻ በከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ማከሚያ ጣቢያ ወይም ማስወገጃ ቦታ ሲያጓጉዙ ፍጥነትና ቅልጥፍናን ይጨምራል።
የቅብብሎሽ ጣቢያ ቦታ አመራረጥና የቅብብሎሽ ጣቢያው አይነት የሚወሰነው በቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ወይም የቆሻሻ ማከሚያ ቦታ አቀማመጥና መገኛ ሁኔታ እንዲሁም ቆሻሻው ከሚመነጭበትና አጠቃላይ የቆሻሻ አሰባሰብ ተግባራዊ ስርዓት መሰረት የሚወሰን ይሆናል።
በኢትዮጵያ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከየቤቱ የሚመነጨው ቆሻሻ የአወጋገድ ችግር ያለበት መሆኑና በአካባቢ ላይም በሚያሥከትለው የንፅህና ጉድለትና ለጤናም ጠንቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የበርካቶች የቅሬታ ምንጭ ሲሆን ቆይቷል።ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ የጊዜያዊ ደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በማስገንባት ላይ ይገኛል።
የደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያዎቹ ግንባታ ቆሻሻን በስርዓትና በየፈርጁ በመለየት መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ታልመው የሚገነባ ሲሆኑ፣በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ 39 የሚሆኑ የደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያዎች ተገንብተዋል።ከነዚህ ውስጥም በሳምንቱ መጨረሻ በቦሌ ክፍለ ከተማ የተገነቡ ሁለት ጊዜያዊ ጣቢያዎች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።
በመድረኩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ እንደተናገሩት ጊዜያዊ የደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያዎች ቆሻሻን መልሶ ለመጠቀም የሚያስችሉና የአካባቢን ንጽህና ለመጠበቅ የጎላ ጠቀሜታ አላቸው።
በዚህ ዓመት ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ከመጠቀምና ወደ ልማት በመቀየር ጋር ተያይዞ ከ3600 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተከናወነ ባለው ተግባር በርካቶችን ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል።በአሁን ወቅት በከተማዋ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ውጤታማ በሆነ መልኩ እውን ለማድረግ እንዲቻል ህብረተሰቡ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገዱን ማሻሻል ይጠበቅበታል።ህብረተሰቡ ተባባሪ ካልሆነ ግን ፕሮጀክቶቹ የታለመላቸውን ግብ ሳያሳኩ ይቀራሉ።በመሆኑም በመተባበር ተፈጻሚ መሆን መቻል አለበት።
የአዲስ አበባ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ለማም ጣቢያዎቹ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሃብት ለመለወጥና የአካባቢ ንፅህናን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አቅም የሚፈጥሩ ስለመሆናቸው በመጠቆም፣መሰል ግንባታዎችም በተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት ላይ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መኮንን አምባዬ በበኩላቸው፣መሰል ዘመናዊ የቆሻሻ ቅብብል ጣቢያዎችን በቀሪዎቹ የክፍለ ከተማው ወረዳዎችን ይገነባሉ ብለዋል።የደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያዎች በጽዳት ስራ ተደራጅተው ለሚሰሩ ማህበራት አባሎች ግልጋሎት እንዲውል ይደረጋል።ጣቢያው በውስጡም ዘመናዊ የእቃ ማስቀመጫ፣ ንፅህና መጠበቂያና መፀዳጃን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን ያካትታል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013