ዳግም ከበደ
በመንግስት ተቋም ብልሹ አሰራር አይቻለሁ፤ዛሬ ነቀፋዬን መንግስት ላይ እወረውራለሁ። እንዳልኩት ብልሹ አሰራር በግልጽ አይቻለሁ።ብልሹ አሰራሩን በዚህ እንወራወር አምድ ላይ የማሰፍረው ደግሞ አንድም እንደ ዜጋ ሁለትም የታዘበውን ተመልክቶ እዚህ ላይ ችግር አለ ማለት እንደሚገባው ጋዜጠኛ ሆኜ ነው።
ባሳፈርኩት ሃሳብ ላይ ተቃውሞ ያለው ማንኛውም አካል አስተያየትህ አሊያም ትዝብትህ ራሱ ለተጨማሪ ትዝብት የሚዳርግ ነው” በማለት ምላሽ የማስቀመጥ መብቱ የተጠበቀ ነው።
ነገሩ እንዲህ ነው። ጉዳዩም የሚጀምረው ከዛሬ አራት ወር በፊት ነው። ከመደበኛ ስራዬ ውጪ አንድ ጉዳይ (የቤተሰብ ቤት ስም ማዘዋወር) ገጥሞኝ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ቅርንጫፍ ተገኝቻለሁ።
ግቢ ውስጥ እጅግ በጣም በርካታ ሰዎች በጠዋት ተሰብስበዋል። ከዚህ ቀደም ወደ ቢሮዬ ስገባ የማልፈው በአካባቢው አጥር ጥግ ስለነበር ተመሳሳይ የሰው ብዛት እመለከት ነበር። ሰዎቹ በጠዋት መሰብሰባቸው አንዳች ብርቱ ጉዳይ ገጥሟቸው ስለመሆኑ ግልፅ ነው። ይሄው አንድ ጓደኛዬ “ከክፍለ ከተማና ከሞት ማንም አይቀርም” እያለ የሚያሾፈው አባባል ደርሶብኝ እኔም በዚሁ ስፍራ በጠዋቱ ተገኝቻለሁ።
ከበራፉ ስደርስ የተገልጋዩ መብዛትና የአካባቢው መጨናነቅ እዚያው ባድርም እንደማልጨርስ ያመላክታል። ለማንኛውም ብዬ ወደ አንዱ ሰው ጠጋ ብዬ “ስም ላዘዋውር ነበር፤ዛሬ ያልቅልኝ ይሆን” ስል ጥያቄዬን አስከተልኩለት። ሰውየው ካለማወቄ በላይ የዋህነቴ ገርሞታል መሰለኝ ፈገግ እያለ የኔን ጥያቄ ወደጎን ትቶ “ ይሄው እኔም ተመሳሳይ ጉዳይ ይዤ እዚህ የተረገመ ቢሮ ስመላለስ ከሶስት ወራት በላይ ሊያልፈኝ ነው” በማለት ችግሩን አማሮ ገለጸልኝ።
“የተረገመ” የሚለውን ቃል ከአፉ ሲያወጣ በሁኔታው ምን ያህል እየተጉላላ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም። እኔም የኔን ጉዳይ “ይሄ ሰው ሶስት ወር እንዴት ሊጉላላ ቻለ? ስም ማዘዋወር ምን ያህል አስቸጋሪ ቢሆን ነው? እርሱ ይሄን ያህል ከቆየ የኔስ ምን ያህል ሊወስድ ይችላል በማለት” ከራሴው ጋር እሟገት ገባሁ።
የቡድን መሪው
ህጋዊ ሰነዶቼን ይዤ ይመለከተዋል ወደተባለው የስም ዝውውር የቡድን መሪ ቀረብኩ። ፊቱን ከስክሶ በተሰላቸ መልኩ ሰነዴን ተቀብሎ በመፈረም “ውጪ ጠብቅ” የሚል ቀጭን ትእዛዝ ሰጠኝ። እኔም ከአጠገቡ ፈጠን ብዬ ወደተባልኩት ቦታ አመራሁ።ሰነዴ ከመዝገብ ቤት ተፈልጎ እስኪመጣ ከሁለት ሰዓት በላይ ወሰደ።
ጠብቅሁ፡፡በትእግስት ጠበቅሁ፡፡ አዳዲስ ሰነዶች በፍጥነት ሲወጡ የኔና የጥቂት ሰዎች ግን ሊወጣ አልቻለም። ምክንያቱን ማጣራት ያዝኩ፡፡ “ፋይል ለማውጣት ጉርሻ ካልሰጠህ ፋይልህም ግዜህም እዚሁ ይበሰብሳሉ እንጂ” ንክች አያደርጉትም ሲል ተመሳሳይ ሁኔታ የገጠመው ባለጉዳይ ነገረኝ። የኔና የጥቂቶች ፋይል እዛው መቅረት ሁኔታውን ይበልጥ እንዳምን አስገደደኝ።
ቡድን መሪው ሲመለከተኝ እየሰለቸሁትም ቢሆን ሄጄ ተጨቃጭቄ በስንት አተካራ ፋይሌን ከመዝገብ ቤት አስወጣሁ። እንደ መጣም ሰነዶችን ወደሚያጣራው ባለሙያ ላከኝ።
ባለሙያው
“እከሌ የሚባለው ፋይል ያንተ ነው” ሲል እየገላመጠ ፊቱን ከስክሶ ጠየቀኝ። “አዎ” ስል ምላሼን ሰጠሁት። ፋይሉን ወደ አንድ ጥግ እየወረወረው “ሳምንት ተመልሰህ ና” ሲል ፊቱን አዙሮ ሌላ ጉዳይ ይመለከት ጀመር።
“ዛሬ ለምን አትመለከትና አታስተናግደኝም” የሚል ጥያቄ ሳነሳለት “ያንተ ብዙ የሚታይ ጉዳይ አለው” ሲል አሁንም አድበስብሶ ዝም አለ። ፋይሉን አጣርቶ ለሚመለከተው አካል ማስተላለፍ ሲችል ህጋዊ ሰነድ ይዤ ያለምክንያት በቀጠሮ ያመላልሰኝ ያዘ። ሳምንት ስመጣ ሌላ ሳምንት፤ እርሱንም ሳከብር ነገ ከነገወዲያ እያለ በአንድ ቀን የሚሰራ ስራ ከአስራምስት ቀን በላይ ፈጀ።
እርሱ ብቻ ሳይሆን ሰነዱን የሚመለከቱ ባለሙያዎች ሁሉ ስነምግባር ከጎደለው ምላሻቸው ውጪ አላግባብ በርካታ ደንበኞችን በቀጠሮ ሲያመላልሱ በዚህ ባለጉዳይነቴ ታዘብኩ። በጥሩ ፊት ባያስተናግዱ በህጉ መሰረት ባለጉዳይን ቢያስተናግዱ ምን ይጎልባቸው ይሆን።
ነገሩ ግን ወዲህ ነው። ደንበኛው በቀጠሮ ሲሰላች እና ጉዳዩ በእንጥልጥል ሲቀር የግዴታ በዚያ ቦታ ባሉ ስነ ምግባር የጎደላቸው ባለሙያዎች ወጥመድ ውስጥ ይገባል። ያን ጊዜ የፋይሉ ክብደት ተመዝኖ አላግባብ ለነሱ በግል ክፍያ እንዲፈፅም ይደረጋል። ከእያንዳንዷ ሰነድ ከህግ አግባብ ውጪ ባለሙያው ለራሱ ዳረጎት አስቆርጦ ካልሆነ ንክች አያደርገውም።
ይሄን በአካል እቦታው ድረስ ሄዶ የሚመለከት ሰው ከእያንዳንዱ ተስተናጋጅ ጠጋ ብሎ ሊሰማ ይችላል። “ህጋዊ ጥያቄ ጠይቀህ ለምን ገንዘብህን አላግባብ ለሌባ ትሰጣለህ” የሚል ጥያቄ ብታነሱለት ያመላልሰኛል ፋይሌን ይጥልብኛል የሚል ስጋት እንዳለው ሊነግራችሁ ይችላል።
የችግሩ ጥልቀት
በመሬት ልማት ማኔጅመንት የካ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የታዘብኩት ችግር ዘርፈ ብዙ ነው። በቀጠሮ አሰላችቶ ተገልጋይን አላግባብ ሙስና ውስጥ ከመክተት አንስቶ፣ የቢሮ አደረጃጀት፣ የሲስተም መጥፋት፣ የመረጃ አሰጣጥ ክፍተትና እጅግ ብዙ እንከኖችን አስተውያለሁ። አቅም ያለው ሰው በጥቅሻ፤ ሊያውም የተዛባ መረጃ ሰጥቶ ጉዳዩን አጠናቆ ሲሄድ እናቶች፣ አካልጉዳተኞች፣ አቅመ ደካማ አዛውንቶች እና ሌሎችም በርካታ ተገልጋዮች እንደ እንጀራ እናት ስነምግባር በጎደለው ባለሙያና ኃላፊ ተመናጭቀው ግራ ሲጋቡ መመልከት ይቻላል።
የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊዎች የከተማዋን የመሬት ወረራ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ለወራት ያህል ምርመራ ማድረጋቸው ይታወቃል። ሆኖም ግን አሁንም ድረስ እንደ አዲስ የተጀመረው አገልግሎት አሰጣጥ እንከኖቹ ብዙ ናቸው። በዚህ ትዝብቴ የሚመለከተው የመንግስት አካል እንዲያውቀው የወረወርኩትን ትዝብት ጨምሮ በርካታ ችግሮች በክፍለ ከተሞችና በሌሎች መሰል ቢሮዎች ውስጥ ስላሉ ጆሯችሁን ወደዚህ አካባቢ መልሳችሁ መላልሳችሁ ብታዘነብሉ የሚል መልክት አለኝ።
ሌላው ግምት ውስጥ እንዲገባ የምፈልገው ጉዳይ በርካታ ስነ ምግባር የጎደላቸው ባለሙያዎች በዚህ ስፍራ ቢኖሩ፣ በቆይታዬ መልካምና ቅን ባለሙያዎች አጋጥመውኛል፡፡እነዚህን መሰል ሰዎች በዚህ ቢሮ ውስጥ እንዲበዙ ጠንክሮ መስራት ላይም ታሳቢ ይደረግ እላለሁ።
ይህ ብቻ ሳይሆን የክፍያ ስርዓት፣ የኔትወርክና ሲስተም ጉዳይ ከቢሮ አደረጃጀትና ንፅህና ጋር ደምሮ ማመቻቸት የመንግስት ኃላፊነት መሆኑን ልጠቁም እወዳለሁ። እዚህ ላይ ከተሰራ ተገልጋይም ይረካል፣ መንግስትም የተቀላጠፈ ግልጋሎት ለህብረተሰቡ ይሰጣል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013