በዛሬው የአዲስ ዘመን ዱሮ አምዳችን በይዘታቸውና አዘጋገባቸው ወጣ ያሉና አሁንም ተነባቢ ይሆናሉ ብለን ያስብናቸውንና አዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1950ዎቹ ያስነበባቸውን ዘገባዎች ይዘን ቀርበናል ፡፡
ሰዎችና አራዊቶች ተካፋይ የሚሆኑበት ተአምራዊ ትርኢት በአዲስ አበባ ሊታይ ነው እንስሶች እንዲሁም ሰዎች በአንድነት ልዩ ልዩ ተአምራታዊ ትርኢት የሚያሳዩበት ዘ ግሬት ሮያል ሰርከስ የተባለ የሕንድ ድርጅት አባሎች በጥቅምት ወር መጀመሪያ አዲስ አበባ መጥተው ልዩ ልዩ ትርዒቶች የሚያሳዩ መሆናቸውን ሚስተር ኤች ኤፍ አቦት የድርጅቱ ወኪል ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ከተቋቋመ ከ፵ ዓመት በላይ ሲሆነው፤ ይህ ድርጅት ወደውጭ አገር ሔዶ ትርኢት ሲያሳይ የመጀመሪያ ጊዜው ነው፡፡ቡድኑ ፪፻፶፩ ሰዎችና ፹ እንስሶች ይገኙበታል፡፡
ከዱር አራዊቶቹ መካከልም ዝሆኖች፣ ነብሮች፣ አንበሶች፣ ከአንበሳና ከነብር የተዳቀሉ ̎ላይገር̎ የተባሉ አራዊቶች ድቦች እንዲሁም የሚደንሱ ፈረሶች ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በቀር ልዩ ልዩ አክሮባት የሚያሳዩ ሕፃናት አሉ፡፡
̎ የሞት ክልል ̎ በሚባል አንድ ክብ ነገር ውስጥ በሞተር ብስክሌት ተቀምጠው የመሽከርከር ትርኢት የሚያሳዩ አሉ፡፡ ይህ ትርኢት በተለይ አሠቃቂና የሚያስደነግጥ መሆኑን ሚስተር አቦት ገልፀዋል፡፡
ከዚህም ሌላ የፈረስና የድብ ግልቢያ፤ የሞተር ብስክሌት ሩጫ የአየር አክሮባትና የመብረር (ትራፓፕ)ትርኢት ይታያል፡፡በዚሁ አስደናቂ ትርኢት ውስጥ ፳፱ እንስሳት ላንድ ሰው ሲታዘዙና ሲሽቆጠቆጡ ይታያሉ፡፡
የሰርከሱ ቡድን አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ድሬዳዋን መቀሌን ጅማን መስዋንና አሥመራን እንዲሁም ደሴን የሚጎበኝ መሆኑ ታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቆየውም ለ፳፬ ሳምንት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህ የስር ካስ ድርጅት አንድ የግል ድርጅት ነው፡፡
ይሁን እንጂ አሁን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውና ሌሎችንም አገሮች የሚጎበኘው፤ በሕንድ መንግሥት ፈቃድ የካልቸር መልእክተኛ ሆኖ እንደሆነ ሚስተር አቦት ገልጸዋል፡፡
ቡድኑ ተግባሩን ለማከናወን የሚስችለው ልዩ ልዩ ዝግጅትና መገልገያዎች ይዞ የሚጓዝ እንደመሆኑ መጠን ሰው የሚይዝ ድንኳን ከነወንበሩ እንዳለው ተገልጿል፡፡
ቡድኑ አዲስ አበባ ከቆየ በኋላ ወደ ሱዳን፤ ከዚያም ወደ ደቡብ ሰሜናዊ አሜሪካና ወደ ምዕራብ እስያ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ የስርካሱ ቡድን አዲስ አበባ በሚቆይበት ጊዜ በዚህ ዓይነት ሙያ ለመሠልጠን ዝንባሌ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለማሠልጠን ፈቃደኛ መሆናቸውን ሚስተር ኤች አቦት ገልጸዋል፡፡
መስከረም 28 1955 የወጣው አዲስ ዘመን በፊት ገጹ ያሠፈረው
በግፍ የታረደ እንስሳ ስጋ ተፋረደ ሀገረ ሕይወት በጅባትና ሜጫ አውራጃ በደንዲ ወረዳ ግዛት ሰኔ 20 ቀን 1950 ዓ.ም
1.ፉላስ ዱለሜ
2.አባ ጠጅቱ
3.ከበደ ብሩ
4.በዳዲ ያደታ
5.ካብትህ ይመር ዋሊና የተባሉ ሰዎች ፈይሳ ደበሌ ከተባለው ሰው ቤት ሌሊት ሔደው ሁለት የቀንድ ከብት ሠርቀው ወስደው ከዱር አርደው ሲበሉ ከነዚህ መካከል በ5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰውን ሰው በግፍ የታረደው እንስሳ ስጋ ስላነቀው ፉላስ ዱላሜ የተባለው ጓደኛው ከአነቀው ስጋ ለማስጣል ሲል ማዠራቱ ላይ በጡጫ ቢመታውና ወዲያውኑ ተመቺው ቢሞት አጥፊዎቹ ሬሳውን በመተባበር ደብቀው እቀብር ጉድጓድ ጥለውት የኤጀርሳ ለፎ ም/ወረዳ ገዥና የዚሁ ክፍል ፖሊስ አዛዥ ወሬው ከህዝብ አንደበት ስለተሰማቸው ጉዳዩን በምርመራ ተከታትለው ሬሳውን ከጣሉበት አግኝተው አስነስተው ወንጀለኞቹንም ይዘው ሀገረሕይወት አስቻለው ከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርበዋቸው የመጨረሻ ፍርዳቸውን ለመቀበል በቀጠሮ ላይ ናቸው፡፡
የአውራጃው ግዛት አዣንስ በቀለ ወልደ ገብርኤል፡፡(ሐምሌ 27 19 50)
ሊሠርቅ ገብቶ ሲያንኮራፋ ተያዘ
ከሳዮፓሎ(ብራዚል)፤ በጣም የሚያንኮራፋ ሰው ድምጽ የቤቱ ባለቤት አልጋው ሥር በመስማቱ ቢመለከት ቤት ሰባሪ ሌባ እንቅልፍ እንደያዘው ማግኘቱን የሳዮፓሎ የፖሊስ ጓድ አስታወቀ፡፡
የአሥራ ስምንት ዓመት ዕድሜ ያለው ሎፋስ ካስቶዶ ደሳሳ ቤቱን ሰብሮ ሲገባ በጨለማ ውስጥ ሰው ሲራመድ በመስማቱ አልጋ ውስጥ ገብቶ ተደበቀ፡፡
ነገር ግን ደክሞት ስለነበር ከዚያው እንቅልፍ ይዞት ሄደ፡፡ ከእንቅልፍም ሲነቃ የሽጉጥ አፈሙዝ ተደቅኖበት ፖሊስ ከቦት አገኘ፡፡(ሮይተር)
ሐምሌ 6/1958 አዲስ ዘመን
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 2013