ዳግም ከበደ
በዛሬው የፋሽን ገፅ አምዳችን ላይ ስኬታማ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የፋሽን ባለሙያዎችን እናስተዋውቃችኋለን። እንደሚታወቀው ይህ አምድ ልዩ ትኩረቱን ፋሽን ላይ አድርጎ የአገራችን የፋሽን ኢንዱስትሪ እድገትን ለማበረታታት ይሰራል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ዝንቅ የሆነና በእጅጉ ማራኪነትን የተላበሰ የበርካታ ባህላዊ እሴት ባለቤቶች ነን። ይህን ቱባ ሃብት ለራሳችን ተጠቅመን ለቀሪ ዓለም የምናስተዋውቅባቸው ልዩ ልዩ መንገዶች አሉን።
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ባህላዊ ሃብቶቻችንን ለቀሪው ዓለም ከምናስተዋውቅበት መንገድ አንዱ የፋሽን ኢንዱስትሪው ነው።
ይህ ዘርፍ በአይነተ ብዙ መንገዶች እድገት አሳይቶ ስኬት ላይ የሚደርስ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባህላዊ እሴቶቻችንን ሳንበርዘ ለቀሪው ዓለም ማስተዋወቅ ያስችለናል። ከዚህ ባለፈም አገራችን ኢትዮጵያ የፋሽን ቱሪዝም ተደራሽ ሆና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲኖራት ያስችላል።
የፋሽን ኢንዱስትሪን ዓለም የደረሰበት ልቀት ጋር እንዲስተካከል ለማድረግ የአናብስቱን ሚና ከሚጫወቱ አካላት መካከል የሞዴሊንግ ባለሙያዎች ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው።
እነዚህ ብቁ የፋሽን ኢንዱስትሪው ድምቀቶችን ተንተርሶ የሚደረግ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ ስኬታማ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ታዲያ ብቁ የሞዴሊንግ ባለሙያ ለማፍራት ትምህርት፣ ፍላጎትና ቴክኖሎጂ የታገዘ ተቋማዊ አደረጃጀት ያስፈልጋል።
ዓለማችን ላይ እጅግ የላቀ የፋሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ካላቸው አገራት ውስጥ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ ይጠቀሳሉ። በነዚህ አገራት ደግሞ እውቀታቸው ጫፍ የነካ፣ ለሞዴሊንግ ሙያ ሁሉን መስፈርት ያሟሉ አያሌ ሞዴሎች ይገኛሉ። ከአገራቸው አልፈውም ዓለም አቀፍ ዝናን ማትረፍም ችለዋል።
ለመሆኑ እኛ የት ነን?
ኢትዮጵያ በፋሽን ኢንዱስትሪ እድገት ደረጃ በእጅጉ ወደኋላ የቀረች ብትሆንም በአነስተኛ ጥረት የተሻለ ስኬት ላይ መድረስ የሚያስችል በባህል፣ ተፈጥሮና መሰል ሃብት የታደለች ነች። ሆኖም አሁን ላይ ከቀሪው ዓለም ጋር ስትነጻጸር ያልደረጀ፣ ከመንግስትም ሆነ ከግሉ ዘርፍ ድጋፍ የማይደረግለት ሁኔታ ውስጥ ነው የምትገኘው።
ይህን እንበል እንጂ በግላቸው በፋሽን ዘርፍ ላይ ተሳትፎ አድርገው አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡና አሁንም እያስመዘገቡ ያሉ ግለሰቦችና ተቋማት የሉም ለማለት አይደለም።
በተለይ በሞዴሊንግ የፋሽን ኢንዱስትሪውን ዘርፍ የተቀላቀሉ ወጣት ባለሙያዎች በእጅጉ አነስተኛ ናቸው። ከውጤታማነታቸውም አንፃር መለካት ብንችል በጣት የሚቆጠሩ ካልሆኑ የሚፈለገው ደረጃ ላይ የደረሱ ብርቱዎችን ለማግኘት ልንቸገር እንችላለን።
የዛሬው የፋሽን አምድ በሞዴሊንግ ሙያ ላይ ተሰማርተው ዓለም አቀፍ እውቅናና ስኬት ላይ የደረሱ ባለሙያዎችን ማንሳትን ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህን ስናደርግ ደግሞ ልንደርስበት የምንፈልገው ግብ ሌሎች መሰል ተሰጥኦና እውቀት ያላቸው ወጣቶች ተበረታትተው ዘርፉን እንዲቀላቀሉና እንደ አገር የምንፈልገው የእድገት ደረጃ ላይ እንድንደርስ ነው።
በመሆኑም መሄጃችንን እዚህ ጋር ገታ እናደርግና በግል ጥረታቸው ወደ ስኬት የመጡ የፋሽን ዓለም ኢትዮጵያዊ ፈርጦችን እንጠቃቅሳለን።
ትዝታ አብርሃም
ኢንተርናሽናል ሞዴል ትዘታ አብርሃም ትባላለች። ትውልደ ኢትዮጵያዊ የፋሽን ኢንዱስትሪ ፈርጥ ስትሆን የተወለደችው ጅቡቲ ነው። ቤተሰቦቿ በስራ አጋጣሚ እዚያ በመሄዳቸው ውልደቷ በዚያው እንዲሆን ምክንያት ነበር። በጎረቤት አገር ጅቡቲ ጥቂት ብትቆይም አሁንም በመሰል ምክንያት ወላጆቿ ወደ ጣሊያን አገር በማቅናታቸው እድገቷንና ኑሮዋን እዚያው ለማድረግ ተገዳለች።
ትዝታ በጣሊያን አገር ትምህርቷን በምትከታተልበት ግዜ እንደሌሎቹ ዜጎች ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላት አልነበረም።
ይልቁንም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ነው ያለፈችው። ከዚህ መካከል ደግሞ ዋንኛው በቆዳዋ ቀለም ይደርስባት የነበረው ትችትና ዘረኝነት ነበር።
ትዝታ ከላይ ባነሳውና ሌሎች መሰል ትዕግስትና ብልህነት ከእውቀት ጋር የሚጠይቁ ፈተናዎች ብትጋፈጥም ይህን ሁሉ ግን በድል ተወጥታ የምትወደው የፋሽን ሙያን ተቀላቅላለች። በዚህም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2002 “የጣሊያን የአፍሪካ ሚስ ውድድር” አሸናፊ ሆነ የስኬት ጉዞዋን አሃዱ ብላለች። ይህ አጋጣሚ የፈጠረላትን እድል ሳታባክን በመጠቀሟም ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፉ ተወዳጅ የፋሽን ብራንድ እቃዎች አምራች ላይ በአስተዋዋቂነት ሰርታለች።
ለምሳሌ ያህል ለማንሳት ብንሞክርም “ፌሪ፣ ሪፕለይ ፣ፌንዲ፣ ሞቺኖ፣ ጓውልተር” የተባሉ ተወዳጅ የፋሽን ብራንዶች ይጠቀሳሉ። ከዚህ ውጪ በ2010 “የሚስ ኢጣሊ” ተወዳዳሪ ከመሆኗ በላይ በቱሪዝም ኮንሰልታንቲ የዲፕሎማ ባለቤትና በርካታ ፊልሞች ላይ መተወን የቻለች ተወዳጅ ሞዴሊስት ነች።
ሃያት አህመድ
ኢንተርናሽናል ሞዴል ሃያት አህመድን አብዛኛዎቻችን የፋሽን ተከታይ እና የዘርፉ ወዳጅ ባንሆንም እንኳን እናውቃታለን። በዓለም የሞዴሊንግ “የሚስ ወርልድ” ውድድር ላይ የመጀመሪያዋ ተሳታፊ በመሆን የፋሽን ኢንዱስትሪውን በእጅጉ ያነቃቃች ተወዳጅ ሞዴሊስት ነች። በጊዜው እዚህ ውድድር ላይ ስትሳተፍ የሶስተኛ ዓመት የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ተማሪም ነበረች።
በውድድሩስ ላይ እስከ ግማሽ ፍፃሜ በመድረስም ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ላይ ከማስጠራት ባለፈ እዚህ ተወዳጅ ውድድር ላይ ሌሎች መሰል ወጣት ባለተሰጥኦዎች “ይቻላል” በሚል መንፈስ እንዲነቃቁ በር ከፍታለች።
የተለያዩ ምርቶችን የማስተዋወቅ ስራ በሞዴሊስትና የፋሽን ባለሙያዎች እንዲሆን ፈር ከቀደዱት ውስጥ ትጠቀሳለች። ሃያት አሁን ላይ የግል ፍላጎቷን ለማሟላት የተለያዩ ትምህርቶች የተማረች ሲሆን። በዋናነት ግን ሴት የኢትዮጵያ አብራሪ ለመሆን ባደረገችው ከፍተኛ ጥረት ስኬታማ ሆና በቅርቡ ፓይለት ትሆናለች።
እንደ መውጫ
ዛሬ የኢትዮጵያ የፋሽን ኢንዱስትሪ እድገት ፈተናዎችና ስኬታማ ሞዴሊስቶችን በቁንጽልም ቢሆን አንስተን ቆይታ አድርገናል። ገፃችን ስለሚገድበን እንጂ በዛሬው እትማችን ያነሳናቸው እውቅ ኢንተርናሽናል ሞዴሊስቶች እኚህ ብቻ ሆነው አይደለም።
በመሆኑም በቀጣይ እትማችን ላይ ሌሎች መሰል ስኬታማ ሰዎችንና ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሄዱትን ርቀት እንደምንዳስስ ቃል እየገባን ለዛሬ ግን ሃሳባችንን እዚሁ ላይ ለመቋጨት እንገደዳለን። ቸር እንሰንብት::
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 2013